“Our true nationality is mankind.”H.G.

በሶማሌ ክልል የተጨፈጨፉና በጅምላ የተቀበሩ ዜጎች አስከሬን ወጣ – የአብዲ ኢሌ የፍርድ ሂደት ዝርዝር ዘገባ

በጅግጅጋ በጅምላ የተቀበሩ ሰዎች አስከሬን መውጣቱ ተገለጸ

ፍርድ ቤት ለአቶ አብዲ መሐመድ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

ቁጥራቸው በውል ባልታወቁ ሰዎች ግድያ፣ በከባድ የአካል ጉዳት፣ በሃይማኖት ተቋማት ቃጠሎ፣ በንብረቶች ውድመትና መፈናቀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ ሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት፣ ሁሉም በተደመረበት በዚህ ወቅት እነሱ መቀነስ እንደሌለባቸው ዓርብ ጥቅምት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡

ተጠርጣሪው አቶ አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ) ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት እንደተናገሩት፣ ቀደም ብሎ በነበረ ችሎት ፍርድ ቤት የእሳቸውን የማቆያ ቤት አያያዝ በሚመለከት ቤተሰብ፣ የሕግ ባለሙያና ሊጠይቋቸው የሚፈልጉ ሰዎች እንዲጠይቋቸው ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም ተግባራዊ አልሆነም፡፡ እንዲገናኙ የተፈቀደላቸው ከባለቤታቸው ጋር ብቻ መሆኑን፣ ጠበቃቸውንም ሆነ ሌሎች ዘመዶቻቸውን እንዳያገኙ እንደተከለከሉ ለፍርድ ቤቱ አሳውቀዋል፡፡

ቀደም ብሎ ከታሰሩበት ክፍል በመቀየር የአዕምሮ ሕመምተኛ ባለበት ክፍል ውስጥ በመታሰራቸው፣ ሕይወታቸው አደጋ ውስጥ መሆኑን አቶ አብዲ ለችሎቱ ተናግረዋል፡፡ አብሯቸው የታሰረ የአዕምሮ ሕመምተኛ ሁለት ጊዜ በር ነቅሎ በመወርወር አደጋ ሊያደርስባቸው እንደነበር ጠቁመው፣ ‹‹ይኼ የተለየ ጫና እየተፈጠረብኝ ያለው ሆነ ተብሎና የመንግሥትን ስም ለማጥፋት በሚያስቡ ግለሰቦች ነው፤›› ብለዋል፡፡ እሳቸው ኢትዮጵያን ለማጠናከር ብዙ የሠሩ በመሆናቸው ጫና ሊደረግባቸው እንደማይገባም ተናግረዋል፡፡ እየተደረገባቸው ያለው ጫና የመንግሥት ፍላጎት እንዳልሆነ ገልጸው፣ ‹‹ሁሉም በተደመረበት እኛ መቀነስ የለብንም፤›› በማለት መልዕክታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንዲደርስላቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በበኩሉ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ አቶ አብዲ የታሰሩት ብቻቸውን ነው ብሏል፡፡ ከእሳቸው ጋር የታሰረ የአዕምሮ ሕመምተኛ የለም፡፡ የተናገሩት ከእውነት የራቀ ነው፡፡ በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ወቅት እንደሚያማቸው በመግለጻቸው እንዲታሰሩ የተደረገው ቢሮ ውስጥ የነበረ ቢሆንም፣ ለጥበቃ የተመደበ ፖሊስ ጉሮሮ አንቀው ሊገድሉት ሲሉ በሌሎች ዕርዳታ መትረፉን በመጠቆም፣ ይኼንንም ያደረጉት መስተዋት ሰብረው ለማምለጥ መሆኑ በመታወቁ፣ ለእሳቸውም ሆነ ለጥበቃዎች ደኅንነት ሲባል ወደ ሌላ ማረፊያ ክፍል መቀየራቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ የታሰሩትም ለብቻቸው መሆኑንና ‹‹በር ተሰብሮ አደጋ ሊደርስብኝ ነበር›› ያሉትም ራሳቸው ሰብረው እንጂ፣ አንድም የአዕምሮ ሕመምተኛ አብሯቸው እንዳልታሰረ አስረድቷል፡፡

አቶ አብዲም ቢሆኑ በማረፊያ ቤት በየሳምንቱ ኃላፊዎች እስረኞችን ሲጎበኙ ምንም ዓይነት አቤቱታ አለማሰማታቸውን፣ እንዲያውም የፖሊስ አባሉ ላይ የፈጠሩትን ድርጊት በማንሳት፣ ‹‹እኔ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሆኜ ስመራ ኖሬ፣ ይኼንን ድርጊት መፈጸሜ ስህተት ነው፤›› በማለት ይቅርታ መጠየቃቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ከቤተሰብ ጥየቃ ጋር በተገናኘም ያቀረቡት አቤቱታ ትክክል አለመሆኑን የገለጸው መርማሪ ቡድኑ፣ ጠበቃና ቤተሰብ እንደማይከለከል ተናግሯል፡፡ ኃላፊዎቹ ሲጎበኟቸውም ምንም ዓይነት ተቃውሞ አለማቅረባቸውንም አክሏል፡፡ ከእሳቸው ጋር በተመሳሳይ ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩት የክልሉ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ራሂማ መሐመድ፣ የዳያስፖራ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱራዛቅ ሳኒና የፖሊስ ኮሚሽነሩ አቶ ፈርሃን ጣሂርም ለብቻቸው ከሌሎች እስረኞች ጋር ተቀላቅለው መታሰራቸውን የገለጹ ቢሆንም፣ ከእውነት የራቀና ፍርድ ቤቱ በማንኛውም መንገድ ቢያጣራ ለብቻቸው መታሰራቸውን ማረጋገጥ እንደሚችል መርማሪ ቡድኑ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡ የመርማሪ ቡድኑንና የአቶ አብዲን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹የታሰሩት ለብቻዎ ነው ወይስ ከሌላ እስረኛ ጋር?›› የሚል ጥያቄ ለአቶ አብዲ አንስቷል፡፡ ‹‹የታሰርኩት ለብቻዬ ቢሆንም፣ እግር ማዘርጋት በማትችል ጠባብ ቦታ ላይ በመሆኑ ከጎኔ የታሰረው የአዕምሮ እስረኛ ነው፤›› በማለት ከአዕምሮ እስረኛ ጋር በመታሰራቸው አደጋ ውስጥ እንደሆኑ የተናገሩትን የሚቃረን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹና መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ከላይ የተጠቀሰውን ክርክር ያሰሙት፣ መርማሪ ቡድኑ ከአሥር ቀናት በፊት በተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የሠራውን ምርመራ ካስረዳ በኋላ ነው፡፡ የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን በተሰጠው ተጨማሪ አሥር ቀናት ውስጥ፣ የተጠርጣሪዎቹን ግብረ አበሮች ለመያዝ ባወጣው የመያዣ ትዕዛዝ አንድ ተጠርጣሪ መያዙን፣ የ28 ምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በክልሉ በተፈጠረው ችግር ተገድለው በጅምላ የተቀበሩ በርካታ ሰዎችን አስከሬን በባለሙያ ታግዞ ማውጣቱንና ከካራማራ ሆስፒታል የ62 ሰዎችን ጉዳት የሚያስረዳ የምርመራ ሰነድ መሰብሰቡን ገልጿል፡፡ በክልሉ ለተደራጀው ‹‹ሄጎ›› ለሚባለው ቡድንና ለተጠርጣሪዎች ከክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ የተሰጠበት 105 ገጽ የሰነድ ማስረጃ መሰብሰቡን፣ የ14 ሞባይሎች፣ የአሥር ሲም ካርዶች፣ የሲዲዎችና የላፕቶፖች የቴክኒክ ምርመራ ውጤት ከመረጃና መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ መሰብሰቡን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡

በክልሉ የሚገኝ ሲቲ ክራውን የተባለ ሆቴል በሁከቱ መውደሙንና ከ68 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት እንደደረሰበት የሚያሳይ ሰነድ ከዳሸን ባንክና ከአንበሳ ባንክ መሰብሰቡን ገልጾ፣ በተሰጡት አሥር ቀናት ውስጥ የሠራውን የምርመራ ውጤት ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በቀጣይ የሚኖረውን የምርመራ ሒደት በሚመለከት እንዳስረዳው፣ ያልተያዙ ግብረ አበሮችን በተቋቋመው የክትትል ኃይል ተከታትሎ መያዝ ይቀረዋል፡፡ አካባቢው በረሃ ከመሆኑም በተጨማሪ ግብረ አበሮች የታጠቁና በቀላሉ ሊያዙ የማይችሉ በመሆኑ ጊዜ እንደፈጀበት አስረድቷል፡፡  

በመሆኑም በተቋቋመው የክትትል ቡድን እየሠራ መሆኑን አክሏል፡፡ ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ ሰዎችን የምስክርነት ቃል መቀበል፣ በጅምላ ከተቀበረበት የወጣውን አስከሬን ምርመራ ውጤት ከመለስ ዜናዊ መታሰቢያ ሆስፒታል መቀበል፣ ከክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የተሰበሰበ 105 ገጽ ሰነድ ወደ አማርኛ ማስተርጎም፣ ቀሪ የቴክኒክ ምርመራ ከመረጃና መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ መቀበል፣ ያልተያዘ በርካታ የጦር መሣሪያና ገንዘብ ፈልጎ መያዝ፣ የተደፈሩ ሴቶችን በማነጋገር የምስክርነት ቃል መቀበል፣ ሌሎች ከወንጀሉ ጋር የሚገናኙ ሰነዶችን መሰብሰብ እንደሚቀረው ለፍርድ ቤቱ  አስረድቶ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የመርማሪ ቡድኑን ተጨማሪ 14 ቀናት ጥያቄ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በጠበቆቻቸው አማካይነትና በራሳቸውም ጭምር ተቃውመዋል፡፡ የጠበቆቹ ተቃውሞ ምክንያት ተመሳሳይ ሲሆን፣ መርማሪ ቡድኑ ተጠርጣሪዎቹ ካሰራቸው 54 ቀናት የሆናቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ለስድስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሠራሁ የሚለው ተመሳሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አንድ ግብረ አበር መያዙንና ቀሪ ግብረ አበሮች እንዳሉ መርማሪ ቡድኑ መግለጹን በምሳሌነት ያነሱት ጠበቆቹ፣ ‹‹የተያዘው ግብረ አበር ከማን ጋር ነው የተባበረው? ቀሪ ግብረ አበሮች ስንት ናቸው? ከማን ጋር ተባበሩ? እስከ መቼ ድረስ ነው የሚይዛቸው?›› የሚል ጥያቄ አንስተው፣ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ በክልሉ ያለው ኃላፊነት የተለያየ በመሆኑ የምርመራ መዝገቡ ተለይቶ እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በተለያዩ ወረዳዎችና ዞኖች ምርመራዎች እንደቀሩት መናገሩን ጠበቆቹ አስታውሰው፣ ‹‹መቼም በሙሉ ሶማሌ ክልል ረብሻ አልነበረም፡፡ ተለይቶ እዚህ ዞንና ወረዳ ተብሎ መቅረብ አለበት፤›› ብለዋል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በሁለት ወራት ውስጥ ቃል መቀበልና የተደፈሩ ሴቶችን ቃል መቀበል፣ የሕክምና ማስረጃ መቀበል፣ ማስተርጎምና የቴክኒክ ምርመራ ውጤት መቀበል እንደሚቀረው በየቀጠሮው መርማሪ ቡድኑ እንደሚናገር አስታውሰው፣ ማስረጃዎቹን የሚቀበለው ከመንግሥት ተቋማትና ከመንግሥት ኃላፊዎች በመሆኑ፣ ይኼንን ያህል ጊዜ ሊወስድበት እንደማይችል በመግለጽ ተቃውመዋል፡፡ በደፈናው የቴክኒክ ምርመራ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ አለመሆኑንና የተደፈሩ ሴቶች ስንት እንደሆኑ ለፍርድ ቤቱ እንኳን ሳይገለጽ፣ የምርመራ ጊዜ መጠየቂያ በማቅረብ የተጠርጣሪዎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት መጋፋት ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

የወ/ሮ ረሂማ መሐመድ ጠበቃ አቶ ሞላልኝ መለሰ፣ ‹‹ፍርድ ቤቱ እንዲረዳልኝ የምንፈልገው›› በማለት፣ ‹‹ተጠርጣሪዎቹ ከመያዛቸው በፊት በክልሉ ተፈጸመ ስለተባለው ድርጊት በመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን ተሰጥቷል፡፡ በሁላችንም ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ በመሆኑም አሁን ብዙ ሰው ተገድሏል፣ ተጎድቷል፣ ተፈናቅሏል፣ . . .  በሚል የመርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ የሚያቀርበው አቤቱታ፣ ሁላችንንም በቴሌቪዥን ስናይ ወደነበረው ትውስታ ስለሚመልሰን ተፅዕኖው ቀላል አይደለም፤›› ካሉ በኋላ፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(4) ሊከበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ የያዛቸውን ተጠርጣሪዎች በጊዜው ገደብ ፍርድ ቤት አቅርቦ የተያዙበትን ምክንያት ማስረዳት ካልቻለ፣ ፍርድ ቤቱ የአካል ነፃነታቸውን ሊያስከብርላቸው እንደሚገባ አቶ ሞላልኝ አስረድተዋል፡፡ ጠበቆች የቆሙት በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ ባያስቀሩ እንኳ ለመቀነስ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሞላልኝ፣ ምርመራው ብዙ ጊዜ የሚወስድና ሰፊ ቢሆንም ተጠርጣሪዎቹ ግን ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተከብሮ መርማሪ ቡድኑ ሥራውን ሊቀጥል እንደሚችል አስረድተዋል፡፡        

መርማሪ ቡድኑ ቀረኝ የሚለው ሥራ ከተጠርጣሪዎቹ ጋር የሚያገናኘውን ነገር በግልጽ ማስቀመጥ እንዳለበት በፍርድ ቤት መነገሩን አስታውሰው፣ ቡድኑ በግልጽ ተጠርጣሪው በማረፊያ ቤት ሊያስቆየው የሚችለውን ነገር ለፍርድ ቤቱ ሊያስረዳ ባለመቻሉ፣ ጥያቄው ውድቅ ሊደረግ እንደሚገባ ተከራክረዋል፡፡ የእሳቸው ደንበኛ የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ ከመሆናቸው አንፃር፣ መርማሪ ቡድኑ ከሚለው ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለም አክለዋል፡፡ የዋስ መብታቸው እንዲከበርላቸውም ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ የጠበቆቹንና የተጠርጣሪዎቹን ሐሳብና የዋስትና ጥያቄ ተቃውሟል፡፡ ቡድኑ ለ24 ሰዓታት ያለ ዕረፍት እየሠራ መሆኑን፣ ያልተያዙ ግብረ አበሮች የታጠቁና ብዙ ገንዘብ ያላቸው፣ ወደ ውጭ አገር የመውጣት ዕድል ያላቸው በመሆኑ እነሱን ለመያዝ ጥንቃቄ ማድረግና ጊዜ የሚወስድ መሆኑን አስረድቷል፡፡ የሕክምና ማስረጃ የሚሰበሰበው ከተለያዩ ብዛት ካላቸው ሐኪሞች በመሆኑ ለማሰባሰብ ጊዜ እንደሚወስድ፣ ትርጉም ቤትም ወረፋ በመሆኑ እንደሚታሰበው በፍጥነት የሚደርስ አለመሆኑን፣ በአጠቃላይ ውስብስብና ሰፊ ሥራ ከመሆኑ አንፃር የጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

በሌላ በኩል ከእነ አቶ አብዲ መሐመድ ጋር ተጠርጥረው የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል ከተባሉት ተጠርጣሪዎች አንድ ተጠርጣሪ ይዞ ማቅረቡን መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ ተጠርጣሪው አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ) የሚባሉ ሲሆኑ፣ በዕለቱ ፍርድ ቤት ቀርበው የተጠረጠሩበትን የወንጀል ድርጊት መርማሪ ቡድኑ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪው ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን በሶማሌ ክልል ተፈጥሮ የነበረውን ግድያ፣ ቃጠሎና ዝርፊያ በፌስቡክ በማሠራጨት፣ ዘርና ሃይማኖት በመለየት በኮፍያና በቲሸርት በማተምና በማሠራጨት፣ በቪዲዮ በመቅረፅና በማዘጋጀት ችግሩ እንዲባባስ በማድረግ መጠርጠራቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉትም ሐሙስ ጥቅምት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በመሆኑ፣ ገና ቃላቸውን እንዳልተቀበለና ምርመራ አለማድረጉን በመግለጽ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪው አቶ ቴዎድሮስ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የኅትመት ባለሙያና 13 ማተሚያ ቤቶች እንዳሏቸው በመግለጽ፣ የተለያዩ የኅትመት አገልግሎቶች እንደሚሰጡ አረጋግጠዋል፡፡ የክልሉ ፖሊስ እንደሚፈልጋቸው መስከረም 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ሲነግራቸው ራሳቸው ከሄዱ በኋላ፣ መታሰራቸውንና ሲመረመሩ ቆይተው ጥቅምት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ምንም ነገር እንዳልተገኘባቸው በመግለጽ በነፃ እንዳሰናበታቸው አስረድተዋል፡፡ ከታሰሩበት ማረሚያ ቤት ሊወጡ ሲሉ ጥቅምት 8 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ ‹‹በፌዴራል ፖሊስ ትፈለጋለህ›› ተብለው ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው በስተቀር፣ ፌዴራል ፖሊስ እንደሚፈልጋቸው እንደማያውቁ አስረድተዋል፡፡ ንብረትና አድራሻ ያላቸው በመሆኑ ቢጠሩ ወይም ተፈልገውም ቢሆን ሊቀርቡ ይችሉ እንደነበርም አክለው የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የእነ አቶ አብዲንና የመርማሪ ቡድኑን ክርክር ከሰማ በኋላ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በሕግ ባለሙያና ቤተሰብ መጠየቅ ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን በመንገር፣ ፖሊስ ግዴታውን እንዲወጣና መብታቸውን እንዲያከብር አሳስቧል፡፡ አቶ አብዲ በማረፊያ ቤት ከጠባቂ ፖሊሶች ጋር መጋጨታቸውና የሚያሳዩት ባህሪ ተገቢ አለመሆኑን በመጠቆም፣ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በጥብቅ አሳስቧል፡፡ በፖሊስም በኩል ለሕይወታቸውና ለደኅንነታቸው አሥጊ በሆነ ቦታ እንዳይታሰሩ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ጊዜን በሚመለከት ፖሊስ ያቀረበውን የምርመራ መዝገብና በችሎት ያደረገውን ክርክር ሲመለከት አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘው፣ አሥር ቀናት በመፍቀድ ለጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ የአቶ ቴዎድሮስን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀናት ፈቅዶ ለጥቅምት 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ምስል  – ከፋይል

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0