ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በደቡብ ወሎ ዞን አልብኮ ወረዳ በ20 ሚሊየን ብር ለሚገነባው ትምህርት ቤት የመሠረት ድንጋይ አስቀመጡ።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በደቡብ ወሎ ዞን አልብኮ ወረዳ ለሚገነባው ጦሳ ፈላና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ነው በትናንትናው እለት መሰረተ ድንጋይ ያስቀመጡት።

በስነ ስርዓቱ ላይም የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፍያለው እና የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳዳሪ አቶ እጅጉ መላኬን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ወይዘሮ ዝናሽ በዚሁ ወቅት፥ የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በትናንትናው እለት መሰረተ ድንጋይ የተቀመጠለት ጦሳ ፈላና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱንም ገልጸዋል።

ለትምህርት ቤቱ ግንባታም ኅብረተሰቡ በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በእውቀቱ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፍአለ በበኩላቸው በክልሉ አሁን ያለውን ህዝብ ቁጥር የሚያስተናግዱ 900 ትምህርት ቤቶች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤትም ችግሩን በመረዳት ትምህርት ቤት ለመገንባት ለወሰዱት ተነሳሽነቱን አመስግነዋል።

ትምህርት ቤቱ 20 የሚሆኑ የመማሪያ ክፍሎች፣ የመምህራን ቢሮ፣ የአስተዳደር ህንጻ፣ ቤተ መጻህፍትና ቤተ ሙከራዎችን ያካተተ ሲሆን፥ 3 ሺህ 452 ተማሪዎች ተቀብሎ የማስተማር አቅም አለው።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የበልግ ዝናብ በአንዳንድ አካባቢዎች ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *