“ስምምነት ላይ ከደረስንባቸው ነገሮች መካከል የሶማሌ ክልል ሕዝብ ጉዳዩን ያለጣልቃገብነት በነፃነት እንዲያከናውንና ኦብነግም የራስን ዕድል በእራስ የመወሰን ጥያቄውን ጨምሮ ፖለቲካዊ ፍላጎቱን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲያካሂድ ማድረግን ይጨምራል” ሲሉ አቶ ያሲን ለቢቢሲ ተናግረዋል። BBC

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግስትና የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ)በአስመራ ከተማ ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል፡፡ የስምምነቱን ውል እስከአሁን መንግስት ለሕዝብ ይፋ አላደረገም፡፡ በመገናኛ ብዙሃን ስነገር የነበረው ኦብነግ የትጥቅ ትግሉን በመተው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መወሰኑን ነበር፡፡ ይህ ይበል ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው፡፡ ሆኖም BBC የኦብነግን የውጭ ጉዳይ ፀሀፊ የሆኑት አቶ አህድ ያስንን ጠቅሶ እንደዘገበው የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን ህዝበ-ውሳኔ እንዲካሄድና የሶማሊ ሕዝብ ከኢትዮጵያ መገንጠል ከፈለገ ያ መብት እንዲከበር፤ መቆየትም ከፈለገ ያ ውሳኔ እንዲከበርለት ውሳኔ ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡

ይህ ምላሻቸው ከመልስ ይልቅ ብዙ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡ ከሚነሱት ጥያቄዎች መካከል፡-

1. መንግስት ሕዝበ-ውሳኔ እንዲደረግ ተስማምቷል ወይ? ወይስ

2. በስምምነቱ ውስጥ ሕገ-መንግስቱን ተግባራዊ እናደርጋለን በመባሉ አንቀፅ 39 በዝሁ ውስጥ የተካተተ በመሆኑ ያው ፍላጎታቸውን መግለፃቸው ነው?

3. ኦብነግ ማን ሆኖ ነው በሶማሊ ክልል ጉዳይ ላይ እንድህ ያለ ውሳኔ እንዲደረግ የሚያደርገው? (በዝሁ ጉዳይ ላይ ወደታች የሚንለው አለን)

4. ሕዝበ-ውሳኔ የክልሉ ፓርላማ የሚያውጀው ጉዳይ ነው ወይስ መንግስት ከነፃነት ግንባር ጋር የሚያደርገው ስምምነት ነው?

የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለ ሶማሊ ሕዝብ የሚያውቀው በጣም ውስን ነው፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሶማሊ ክልልን የሚያውቀው ወይ በልቦለድ አሊያም በአብዲ ኢሌ ሳቢያ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ያለፉት መንግስታት ሁሉ ከሰዉ ይልቅ ለመሬቱ ትኩረት መስጠታቸው ነው፡፡ ስለዝህ ወደ ዋናው ጉዳይ ከመግባታችን በፊት የተወሰኑ እውነታዎችን ማስቀመጡ አመለካከታችን እንዲጠራ ያደርጋል፡፡

1. የሶማሊ ሕዝብ ከkኦሮሞና አማራ በመቀጠል በሕዝብ ብዛት 3ኛው ብሄር ነው፡፡ የሕዝብ ብዛቱም 8 ሚልዮን እንደሆነ ይገመታል፡፡

2. በመሬት ቆዳ ስፋት ከኦሮሚያ በመቀጠል 2ኛ ደረጃን ይዟል

3. ክልሉ ከልማት የራቀ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ያለበት ክልል ነው፡፡

4. ክልሉ ከ30 በላይ የሶማሊ ጎሳዎችን የያዘ ክልል ነው፡፡ ከነዝህም ጎሳዎች አንዱ የኦጋዴን ጎሳ ነው፡፡ ይህ ጎሳ ከክልሉ ሕዝብ በአማካይ 25-30 በመቶ የሚሆን ሕዝብ ይወክላል፡፡ የተቀረው 70-75 በመቶ ሌላው የሶማሊ ጎሳ አባሎች ናቸው፡፡

5. ኦብነግ የሚወክለው እንደስያሜው የኦጋዴንን ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ በአመራሩም ሆነ በአባሎቹ ሌሎች ጎሳዎች አልተካተቱም፡፡ በዝያ ላይ ሁሉም ኦጋዴን የሆነ ግለሰብ ኦብነግን ይደግፋል ማለትም አይደለም፡፡ ኦብነግን አጥብቀው የሚቃወሙ ብዙ የኦጋዴን ሰዎች መኖራቸውንም መዘንጋት የለብንም፡፡ በግምታችን ካሉት 25-30 በመቶ ከሆኑት ኦጋዴኖች ኦብነግን የሚደግፉ ከ5-10 በመቶ አይበልጡም፡፡ ይህንን ያልንበት ምክንያት የሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡

6. 70-75 በመቶ የሚሆኑት (sleeping giants) አንድም ቀን ስለመገንጠል ጥያቄ አቅርበው አያውቁም፡፡ መንግስት ሁሉግዜ ለኦጋዴን በሚሰጠው ሽፋን (ይህም የሆነበት ምክንያት የሶማሊን ክልል ከሶማሊያ ጋር እንዳይመሳሰል ከመፈለግ አኳያ መሆኑን ልብ ይሏል) ምክንያት የሌላው ብዙሃን ድምፅ እንዲመክን ተደርጓል፡፡

ስለዝህ አንድ የራሱን ጎሳ እንኳ በቅጡ መወከል ያልቻለ ነፃ አውጪ ጋር ስምምነት ለማድረግ በመፈለግ ብቻ የመገንጠል ጥያቄውን በስምምነቱ ውስጥ ሊካተት ይችላል፡፡ ለረጆ ይህ ይሆናል ብለን አስበን አናውቅም፡፡ የኦብነግ የውጭ ጉዳይ ፀሀፊ ያለው እውነት ከሆነ መንግስታችን ከስሯል፡፡የሶማሊ ሕዝብንም እንደሸጠው ይቆጠራል፡፡ ካልሆነ ግን ይህን የተሳሳተውን መግለጫ በማረም ግንባሩ መራር እውነታውን እንዲውጥ ሊደረግ ይገባል፡፡ እዝህ ጋር የሚታየን የክልሉ ፕሬዝደንት መጫወት የፈለገው ጨዋታ በእሳት እንደመቀለድ ይቆጠራል፡፡ ይህም የሆነበት ዋንኛ ምክንያት ፕሬዝደንቱ እነሱን ወደ አገር ቤት ካስገባ በኃላ አንዱን በስልጣን ሌላውን በኮንትራቶች ደልሎ ነገሩን ለማስቀረት ያለመ መሆኑን መረጃዎች እየደረሱን ስለሆነ ነው፡፡ ስልጣንም ሆነ በገንዘብ መደለል የማይቻል ቢኖርስ ?ይሄ እንደቀላል የተደረገ ጉዳይ ኅብረተሰቡ ውስጥ ሰርፆ ቢገባስ?

ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ባለፉት 10 ዓመታት የሶማሊ ሕዝብ በአብዲ ኢሌና በፌዴራል ባሉ አበሮቹ ተጎድቷል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥም በሀብትና በስልጣን ክፍፍሉ ተጠቃሚ አልሆነም፡፡ ለአብነትም አሁን ያገኘውን አንድ ፌዴራል ሚኒስቴር መጥቀስ ይቻላል፡፡ በቁስል ላይ እንጨት ስደድበት እንዲባል ለዝህ ቦታ የታጨው ሰው ከክልሉ ከግማሽ ቢልዮን ብር በላይ የዘረፈ ነው፡፡ በአሁኑም የአስመራ ስምምነት አብይ ሚና የተጫወተ ሰው ነው፡፡ ከዝህ ሁሉ በላይ ክልለ ላይ ነዳጅ አግኝቷል፡፡ በዝህም ግዜ ሕዝቡን የራስህም መብት ወስን ቢባል ከኦጋዴኑ ውጭ ያሉትም ጎሳዎች በስሜት በመገፋፋት የመደገፍ አዝማሚያ ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡ስለዝህ ይህን ስምምነት መቃወም የሁላችንም የዜግነት ግዴታ ነው፡፡

መንግስትም ሆነ ሌላው አገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሶማሊ ወንድሞችና እህቶች እንደ ሁለተኛና ሦስተኛ ዜጎች መቁጠር በማቆም በኢትዮጵያዊነቱ እንዲኮራ መደረግ አለበት፡፡ ለዝህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት በኬንያ የሚኖሩ ሶማሊዎች ጉዳይ ነው፡፡ መንግስት ከኬንያ መማር ይኖርበታል፡፡ የዝያን ግዜ መገንጠል የሚለው ጉዳይ በራሱ ግዜ ተኖ ይጠፋል፤አንድነቱንም ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በማበር ያበረታል!!

Rajo

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *