“Our true nationality is mankind.”H.G.

በዶ/ር አብይ አመራር ተቆልፏል !! – በኦጋዴን ጉዳይ

ዛጎል ዜና – የሶማሊ ክልል መሪ  አቶ ሙስጣፋ ጉዳዩን የተጀመረውን ለውጥ የማሳደፍ ተራ አሉባልታ እንደሆነ ቢገልጹም፣ አንድ ከፍተኛ የሶማሊ ክልል ባልስልጣን  ግን ለኦጋዴን ጉዳይ ” ተቆልፏል” የሚል አጭር ማጣፊያ አላቸው። 

አስመራ ስምምነት አድርገው በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ውል የገባው የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር አመራር  ለቢቢሲ በሰጡት መግለጫ አንቀጽ ፫፱ እንደሚጠቅሱ ቢናገሩም ጉዳዩ የአገላለጽ ግድፈት ነው ብለው እንደሚያምኑ በተለይ ለዛጎል አስተያየት የሰጡ ባለስልጣን ” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ እና ከሶማሌ ፕሬዚዳንት ጋር የጋርዮሽ ስምምነት ሲያደርጉ የኦጋዴን ጉዳይ ተቆልፎበታል” ሲሉ ያስረዳሉ። 

ኸማን ኮሆን ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን እንደመጡ ከፈጸሙት ታላቅ ተግባር ከኤርትራ ጋር ሰላም ማውረዳቸው መሆኑንን በአድናቆት መናገራቸውን የሚያወሱት እኚሁ ባለስልጣን ” አሁን በአገሪቱ ያለውን አካሄድና ስልታዊ የፖለቲካ ቀመር ባለመረዳት ሁሉም የማያውቀውንና ያልገባውን መፈትፈቱ ነው” ባይ ናቸው።

በኦጋዴን ምንም ዓይነት ችግር እንደማይፈጠር በእምነት ይገልጻሉ። ካሁን በሁዋላ ኦብነግ ቢያኮርፍ የት ሄዶ ብረት ያነሳል የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። ይህም ብቻ አይደለም በአጠቃላይ በምስራቅ አፍሪቃ ምን ዓይነት የፖለቲካ ሲስተም እንደሚተከል ለተረዱ እንዲህ ያለ ተራ ቧልት መስማት አሳዛኝም እንደሆነ ያመለክታሉ።

ትዕግስት ማጣት ትልቁ ችግር መሆኑን ያነሱት ባለስልጣን፣ ዛሬ ወደብ የሌላት ኢትዮጵያ የባህር ሃይል ለማቋቋም ስትሯሯጥ ነገሮች ወዴት እየሄዱ ነው በሚል አስፍቶ ከማየት ይልቅ፣ በተራ ወሬና በማይጠቅም አሉባልታ ማበድ እግባብ አልመሆኑን በመገረም ተናግረዋል። 

በቅርቡ ስለሚቀላቀሉ ፓርቲዎች፣ በክልል ስለሚኖሩ ጥምረቶችና የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ አዲሱ ስሌት ወጋገኑ ሲታይ ደግሞ ምን ሊባል እንደሚችል መገመት እንደማይችሉ ያወሱት የዛጎል መረጃ ምንጭ፣ ” ስጋት የገባቸው ክፍሎች በሚረጩት አሉባልታ በማራባት  አርቀው በማስብ የሚሰሩ መሪዎችን ለማንጓጠጥ መሞከር ከሚወራው በላይ ጣጣ እንዳያመጣ እፈራለሁ” ብለዋል። ሲያብራሩም ” እስከማውቀውና በቅርብ እንደምከታተለው  አሁን የተጀመረው ለውጥ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ መካከል እየተገመደ ያለው ሰንሰለት እንቅልፍ የነሳቸውን ክፍሎች በማዳመጥና አሉባልታቸውን በማሰራጨት ተባባሪ መሆን፣ ሁሉም ነገር ያለ ሕዝብ ድጋፍ ሊከናወን አይችልምና ለውጡን ለአጨናጋፊዎች አሳልፎ በመስጠት የሚመጣ ነው ጣጣው ” ብለዋል።

በስምምነቱ ላይ የተገኙት አዲሱ የሶማሌ ክልል መሪ ስምምነቱ እንደ ሌሎቹ ትጥቅ ጥለው በሰላማዊ መንገድ ወደ አገር ቤት ለመግባት እንደተስማሙት ዓይነት እንጂ ከኦብነግ ጋር የተለየ ስምምነት አለመደረጉን እምኝነታቸውን በራሳቸው የማህበራዊ ገጽ ጽፈዋል። በሌላም በኩል የሶማሊ ክልል ኦጋዴን ብቻ እንዳልሆነና ኦብነግም ብቻውን በዚህ ደረጃ ለመወሰን ማንዴት እንደሌለው፣ እጅግ አብላጫ የሆነው ሕዝብ ኢትዮጵያዊ መሆኑንን እንደሚያምን ከከልሉ የሚወጡ መረጃዎች ያረጋግጣሉ።

በጉዳዩ ዙሪያ መንግስትና ኦብነግ በይፋ ግልጽ መረጃ በቅርቡ እንደሚሰጡም ከምንጩ ለመረዳት ተችሏል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የመ/ሰራዊትን መለያ ለብሶ ከሱዳን ወደ ወልቃይት ሊገባ የነበረ የትህነግ የሽብር ሃይል ተደመሰሰ፤
0Shares
0