በተለያዩ ክልሎች የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎች የሕዝብን ፍላጎት መሰረት አድርገው እንዲፈቱና ሕገመንግስቱ በሚፈቅደው አግባብ ተፈጻሚ እንዲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚመለከታቸው አካላት ባሉበት መመሪያ መስጥታቸው ተሰማ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መመሪያ ሲሰጡ ክፉኛ መተቸታቸውም ታውቋል።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ልዩ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ በማህበራዊ ገፃቸው ሳያብራሩ ባሰራጩት ዜና ጠቅላይ ሚንስትር አብይ  ከምክትላቸው አቶ ደመቅ መኮንን፣ ከኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች፣ ከአማራ እና ትግራይ ክልሎች የበላይ አመራሮች እና ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን በራያና አካባቢው የሰላም ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረጋቸው ተረጋግጧል።

የዛጎል የመረጃ ምንጮች እንዳሉት የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤዋ በማንነት ጉዳይ በሰጡት ሚዛን ያልጠበቀ ማብራሪያ ከአማራ ክልል አመራሮችና ከፌደራል ባለስልጥናት ዘንድ ክፉኛ ተተችተዋል። በትግራይ ክልል ታጣቂዎች የተወሰደው እርምጃና ግድያም ፍጹም ሊደገም እንደማይገባና ሕዝቡ ሃሳቡን በነጻነት እንዲገልጽ ሊፈቀድ እንደሚገባ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። ግድያውን የፈጸሙት ታጣቂዎችና መመሪያ የሰጡት ሃላፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ የማጥራት ስራ እንዲሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል። የሰላም ሚኒስትሯ ይህንን ጉዳይ በበላይነት እንዲመሩና ካሁን በሁዋላ እንዲህ ያለ ግድያ የሚፈጸም ከሆነ የመከላከያ ሰራዊት በቀጥታ ጣልቃ እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

አቶ ፍጹም በጥቅሉ ” በውይይቱ ማንኛውም አይነት ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲቀርብና እንዲስተናገድ ስምምነት ላይ ተደርሷል” ብለዋል። አያይዘውም ” ከዚህ ውጪ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑም በውይይቱ ተንስቷል” ብለዋል። 

በተለያዩ የዩቲዩብ አምዶችና በመንግስት ሚዲያዎች ሕዝብ እየገለጸ ያለው በደልና ምሬት ችግሩን ወደ ከፋ ቀውስ እንዳይከተው ስጋት የገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሁለቱም ወገኖች የሚተላለፉት ዜናዎች ጥንቃቄ እንደሚያሻቸው ትኩረት ሰጥተው አስገንዝበዋል። አቶ ፍጹም እንዳሉት ” በፌዴራልም ሆነ በክልል የሚገኙ የመንግስትም ሆነ የግል የመገናኛ ብዙሀንም በሁለቱ ክልሎች መካከል ይበልጥ መግባባትና መቀራረብ እንዲፈጠር በኃላፊነት መንፈስ መስራት እንዳለባቸው በውይይቱ ወቅት ተገልጿል” ብለዋል።

ለጥንቃቄ በሚመስል ጥቅል መረጃ የሰጡት አቶ ፍጹም ውይይቱ በስምምነት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *