ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ጨለማ ቢመስልም አትጠራጠሩ ይነጋል እኛ ኢትዮጵያውያን የንጋት ጨለማ ላይ በመሆኑ መንጋቱ አይቀርም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ.ር ዐብይ አህመድ በጀርመን ፍራንክፈርት ከኢትዮጵያውን ለተነሳላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ

• አምባ ገነንነት ለህዝብም ለመንግስትም የማይጠቅም በመሆኑ በስራ ተለፍቶ የሚኖርበት ሀገር በመሆን ማሳየት ይኖርብናል፡፡ ሀረሬን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ መፍትሄ መስጠት ይኖርብናል፤
• በውጭ የሚገኙ ዜጎች በሀገር ውስጥ ለመስራት ካስፈለገ ይችላሉ፡፡ የማንነት ጥያቄ፣ የአንቀጽ 39 ጉዳይ እና የባንዲራ ጉዳይ በሂደት እየመከርንበት የሚሆኑ ጉዳዮች ናቸው፡፡
• ክልል ተወግዶ ክፍለሀገር ይምጣ ሳይሆን መሆን ያለበት አሁን የያዝነው ፌዴራሊዝም ምን ጎዳን ምንስ ጠቀመን የሚለው ተጠንቶ ምክረ ሀሳብ ቢቀርብ የተሸለች ሀገርን እንድንገነባ ያደርገናል፡፡
• ስደተኞችን ከአውሮፓ ለመመለስ ለተባለው እኔ አስካሁን የሰማውት ከእርሰዎ ነው የውጭ ዜጎችን በተመለከተ የመከርነው አስተምረን እያማለላችሁ የአፍሪካን ሀብት እየመጣችሁ በመሆኑ ቢያንስ ላስተማርንበት ክፍያ መፈጸም ለእነሱም የተመቸ ነገር እንፍጠር የሚለው ላይ ነው የመክርነው፤
• እኔ ኢትዮጵያ ስርቶ የሚበለጸግባት እንጅ ለስደት የምትዳርግ ሀገር ትሆናለች ብየ ስለማላስብ ይህን ምቹ ሁኔታ እንፈጥራለን፡፡ ብታምኑም ባታምኑም ኢትዮጵያ ለህዝቧ ምቹ መሆኛዋ ቅርብ ነው፡፡
• ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ጨለማ ቢመስልም አትጠራጠሩ ይነጋል እኛ ኢትዮጵያውያን የንጋት ጨለማ ላይ በመሆኑ መንጋቱ አይቀርም፡፡
• አዲስ አበባ ፓርክ የላትም ለተባለው ትክክል ነው፡፡ ይህም እንደጨለማው ችግር ይፈታል፡፡
• ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አንድ ዶላር ያልነው መደጋገፋችንነን መረዳዳታችንን ለማሳየት ነው፡፡ እናንተ የምታዋጡት አንድ ዶላር ላልተማሩ ወገናችሁ ማስተማሪያ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መረዳት የሚገባቸው ብዙ ናቸው እና እናንተ አንድ ዶላር ብታዋጡ የኢትዮጵያዊያን ትንሳኤ ሩቅ አይሆንም፡፡
• ትጥቅ የሚፈታው አካል ለምን አይፈታም ለሚለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ቁስል ስላለ በተገቢው ሁኔታ ማሳመን ይጠይቃል፡፡ታጥቆ የገባ ግን የለም፡፡
• ሀሳብ ያለው ኢትዮጵያዊ ችግር የሚፈታ ሰው ተደራጅቶ ችግሮቻችን መፍታት ሲገባ ጦርነት መጠፋፋት ይሆናል ትግስቱ በዛ እንደሚባል አውቃለው ነገር ግን ብዙ መታገስ አይሻልም ወይ ማንም የታጠቀ አካል ከነትጥቁ አልገባም፡፡ ይሁን እንጅ በቦቴ እየተጫነ የሚገባ መሳሪያ አለ፡፡ እኔ ግን መሳሪያ ከሚያቀብሉ ለምን ትራክተር ገዝተው አይሰጡም፡፡ የአማራ እና ትግራይ ክልልሎች ቢጋጩ ተጎጅው ምስኪኑ የአማራ እና የትግራይ አርሶ አደር ነው፡፡ በመሆኑም ተደብቀው የሚያጋጩ ሰዎች መስተካከል ቢችሉ ይሻላል፡፡
• ኦነግን በተመለከተ የተግባባነው ተወዳድረው ህዝባቸውን አሳምነው በእኩል መድረክ እንዲወዳደሩ ነው የተስማማ ነው፡፡ ይሁን እንጅ በአፈጻጸም ላይ የሚመጣ ችግር ነው እየተፈጠረ ያለው፡፡
• የፌዴራል ስርዓት ግጭቶችን የሚያስወግድ እንጅ ግጭት የሚፈጥር አይደለም፡፡ ክልልሎች የራሳቸው ሀይል ካላቸው በትናንሽ ችግሮች ይጋጫሉ፡፡ ይሁን እንጅ የጋራ መከላከያ ካላቸው ችግሮችን ያስወግዳሉ፡፡ የፌዴራል ጥቅሙም ይህ ነው፡፡
• የኢትዮጵያን ፍላጎት በፍጹም ለሌሎች ሀገሮች አሳልፈን አንሰጥም፡፡ ካረብ ሀገር ጋር የተባለው ከግብጽ ጋር ከሆነ በአባይ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ እኔ ሁሌም ለአል ሲሲ የምገልጽላቸው አባይን ገድቦ ማስቀረት ሳይሆን የጋራ መጠቃቀም መፍጠር እንደሆነ ነው የምንነጋገረው፡፡ ምን አልባት እንደ ሳኡዲ አረቢያ ያሉ ሀገሮችን በተመለከተ ከሆነ ከዚህ በፊት ከዋልንላቸው ውለታ ተነስተው የሰጡን እድል ነው፡፡ የትኛውም ሀገር ጋር በትብበር ለመስራት ካልሆነ ምንም ጥቅማችንን አሳልፈን አንሰጥም፡፡
• ትግራይን እና የአማራን ነገር እንዴት ያዩታል ለተባለው እንደ ህዝብ ከሆነ ችግር የለም፡፡ የኦሮሞ እና የአማራ ህዝብን መለየት አይቻልም ወደፊት የዲኤንኤ ምርመራው የሚለየው ሆኖ ጎጃምን ከወላጋ ፤ ከወሎ መለየት አይቻልም ፡፡ ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ መልኩን አያጣም እንደተባለው ነው፡፡
• የፍትህ ተቋማት ራሳቸውን የቻሉ እንዲሆኑ እየሰራን ነው፡፡ የውጭ ጉዳይን በተመለከተ ተሰርቶ ሲያልቅ የምናየው ነው በስደት ለሚኖሩ ሰዎች ስልጠና መስጠት እንፈልጋለን ለተባለው እኛም የምንፈልገው ነው፡፡ የምናደራጀውም ለዚህ ነው፡፡ ጸረ ለውጥ ላሉት ሁሌም ጸረ ሰላም ሀይሎች ይኖራሉ፡፡ ግን የለውጡ መስመር ማሸነፉ አይቀርም፡፡ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የቀረ ይኖር ይሆን እንጅ እየተሞከረ ነው፡፡ ተጠናክሮም ይቀጥላል፡፡
• አክሱም ላይ ላሉ ሙስሊሞች ችግርን በተመለከተ ከአሁን በፊትም አንስቸዋለው መሻሻሉን መረጃ የለኝም፡፡ ነገር ግን ችግሩን መፍታት ጥሩ ነው፡፡ ችግሩ ሲሰፋ ራሱ ችግር አለው ፡፡
• ካሚላት እንኳን ደህና መጣሽ፡፡ አንች ዋጋ ብትከፍይም ዛሬ ሀገርሽ ሴት ፕሬዝዳንት አላት፡፡የተለያዩ ሴቶችም ትልቅ ደረጃ ደርሰዋል፡፡አንች በከፈልሽው ዋጋ ግማሹ ካቢኔም ሴቶች ሆነዋል፡፡
• አዲስ አበባን አልተውኩትም፡፡ ለእኔ የተወረወረውን ቦንብ የቀለቡት እነሱ ናቸው፡፡ መቸም አልተለየዋቸውም፡፡ አልለያቸውም፡፡ አዲስ አበባን በማዘመን ልንክሳቸው እየሰራን እንጅ አልለያቸውም፡፡ የምንታማ አይደለም፡፡ ዜጎችን በቅንነት አለማገልገል የማታ ማታ አሳፋሪ ይሆናል ፡፡
• ማህበራዊ ሚዲያውን በተመለከተ ብዙ ውሸት ይናፈሳል፡፡ ከሰለጠነው በተለየ እኛ ሀገር የከፋ ነው፡፡ በመሆኑም እየሰለጠንን በሄድን ቁጥር ችግሩ ይቀረፋል ፡፡
• የህዳሴ ግድብ ከድለላ ከማስመሰል ወቶ እንዲሰራ ቁርጠኛ ውሳኔ በመወሰናችን አንጠራጠርም፡፡ ይሁን እንጅ ሜቴክ ሀገር ውስጥ ጥሩ ስራ የሰራ ቢሆንም የሰራውን ጥፋት በመሸፋፈን አንሄድም፡፡ ስለሆነም ወደሌሎች አቅም ወዳላቸው በማሸጋገር ስራውን ለመጨረስ ጥረት እንደምናደርግ ላረጋግጥላችሁ እወዳለው ፡፡
• የኦሮምኛ ቋንቋ ከአማረኛው መሳ ለመሳ ከአማረኛው ጋር እኩል የፌዴራል ቋንቋ ለምን አይሆንም የሚለው ለተነሳው ጣሊያን ያጠናው ጥናት እንደሚያሳየው አማርኛ ፣ኦሮምኛ ፣ትግርኛ ፣ሲዳምኛ እና አረብኛ የፌዴራል ቋንቋ እንዲሆን አጥንቷል፡፡ ምንም እንኳን ጣሊያን ሊወረን የመጣ ቢሆንም አሁን ካለነው ሰዎች የተሻለ አስተሳሰብ ነበረው፡፡ እኔ አማረኛም ፣አሮምኛም ስናገር ኩራት እንደሚሰማኝ ሁሉ ትግረኛም ስናገር ኩራት ይሰማኛል፡፡ይህ ከጥያቄዎች ሁሉ ትንሹ ነው፡፡ 
• ግጭት በዝቷል፤ መፈናቀል በዝቷል ለተባለው ግጭቶች ሲኖሩ መንገዶችን መዝጋት ተለምዷል፡፡ መቆም አለበት፤ ከግጭት መውጣት ይኖርብናል፡፡ 
• በአውሮፓ ባደረግነው መግባበት 1.2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ አግኝተናል፡፡ ይሁን እንጅ እንደሚያንሰን ገልጸን እንደሚጨመር መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ለዚህ ድጋፍ መገኘት ደግሞ በህዝቡ ነው፡፡ አንድ ከሆንን የማይከፈት በር የለም፡፡ የማንሻገረው ዥረትም የለም፡፡ ኢትዮጵያን ማገልገል ያኮራል፡፡ እናንተ ከጎናችን ከሆናችሁ ትናንሹን አጀንዳ በመተው ትላልቁን በመያዝ ወደፊት እንሻገራለን፡፡የተለያየ ባንዲራ ብንይዝም የተለያየ ሀሳብ ቢኖረንም በአንድነታችን እንኮራለን በሚል በመተቃቀፍ አንድነታችን እናጠናክር ብለዋል፡፡

በምስጋናው ብርሀኔ – (አብመድ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *