“Our true nationality is mankind.”H.G.

ሃይሌ ገ/ስላሴ ይህ ቀን ትዝ ይልሃል ?- አብይ አሕመድ አስታወሱኝ!!

በርካታ የግል ማስታወሻዎች አሉኝ። ስለ እራሴ የማወራ እየመሰለኝ ማፈሬ እንዳለ ሆኖ፣ በተለየ ምን እንደምጠብቅ በውል አይገባኝም። ግን የማትማቸው ይመስለኛል። ምክንያቱም በተለይም የቅርብ ጓደኞቼና የስራ ባልደረቦቼ እንዲያውቋቸው የምፈልጋቸው እውነቶች አሉና። ዳሩ ምን ያደርጋል የጾመና ቆሎ የቆረጠመ ሁሉ መልካም ተደርጎ በሚወሰድበት ሰፈር ውስጥ… 

ለዛሬ ትዝ ያለኝ አንድ ጉዳይ ነው። አማኑኤል ሆስፒታል ለስራ በሄድኩበት ወቅት ቋሚ ባልደረቦች አገኘሁ። ወቅቱ ዝናብ ክረምት ስለነበር አንድ ሊስትሮ የሚሰራ የአምኑኤል ቋሚ ነዋሪ አንዱን ከጎኔ የቆመ ሰውዬ ጠጋ አለውና፣ ” ጫማህን ልጥረግልህ” አለው። ሰውዬው እንደመድናበር ብሎ እንደማይፈልግ ተናገረ።

“አምኑኤል ሆስፒታል” የሚል ጽሁፍ ቁልቁል የተጻፈበትን ቢጃማ መሳይ አረንጓዴ ልብስ የለበሰው ሊስትሮ ” እግርህን እየው ጭቃ ነህ። ላሳምርልህ እንጂ ክፈል አላልኩህም” አለው። እንደገናም ” ቆሻሻ እኮ ሆነሃል። እየው…” ሊያስረዳው ሞከረ። ሰውየው እንደማይፈልግ ቦታ በመቀየር ገለጸ። የዛኔ ” ደንቆሮ” አለውና እብዱ ጥሎት ወደ እኔ ተጠጋና ፈገግ እያለ በርጋታ ይወራኝ ጀመር።

በዛው ጓደኛ ሆን። ይዞኝ ካፊቴሪያቸው ገባን። የፈለከውን ጋብዝ ብዬ ፈቀድኩለት። ሲጋራም እንዲገዛ ለጓደኞቹም እንዲያካፍል ነገርኩት። ከዛ በዙ አወጋኝ። የተማረ ሰው ነው። እጅግ ብዙ ልምድ ያለው። ከሃያ ዓመት ያላነሰ አማኑኤል ሆስፒታል ኖሯል። በሱ አማካይነት ሌሎችንም ድንቅ እብዶች ተዋወኩ። ወደድኳቸው። 

ጊዜ ሲኖረኝ እሄድ ነበር። ከበውኝ እናወራለን። እጅግ ግልጽና ቀጥተኛ ስለሆኑ ከህጻን ጋር የማወራ ያህል ነብሴ ይደሰት ነበር። እጅግ ያዝናኑኝ ነበር። አንዳንዴ ወሰድ ከሚያደርጋቸው በቀር “ጤነኛ” የምንባለውን ያስንቃሉ። ምንአልባትም በብዙ እብዶች መካከል ጤነኛ መሆናቸው እንደ እብድ አስቆጥሯቸው እንዳይሆን እሰጋለሁ።

የብሄር ፖለቲካ የታወጀብን ሰሞን አማኑኤል የገባች መሃንዲስ ” ኢትዮጵያን አትበጣጥሱ፣ ኢትዮጵያን ተዋት። እኛ አንድ ነን። ምን ትጠቀማላችሁ….” የምትል መልከ መለካም እህትም አጋጥማኛለች። ይህ ቅን አሳቢነትና አርቆ አስተዋይነት ካልሆነ በስተቀር ምንም ሊባል አይችልም። እኛ አገር የምንበጣጥሰው ጤነኛ ሆነን እስዋ በሽተኛ !!

እናም የአማኑኤል ጓደኞቼን አልፎ አልፎ ስለኑሯቸው እጠይቃቸው ነበር። በቀጥታ ሳይሆን እንዲሁ በወሬ በወሬ መካከል በሃሜት መልክ ሳይሆን በግልጽ ይነግሩኝ ነበር። ብዙ ሰምቻለሁ። በወቅቱም የቻልኩትን ሰርቻለሁ። እዛ ዝርዝር ውስጥ ባልገባም ለዛሬ ትዝ ያለኝን ላንሳ።

ትልቁ ችግራቸው ቱሃን ነበር። በቂ አንሶላም የላቸውም። መኝታ ክፍላቸው ሰለሚሞቅ ቱሃን እንደሚያስቸግራቸው የነገሩኝ ” ታንከኛ አደገኛ ነው” በሚል ነበር። በከፍተኛ ደረጃ የሚያስተኛ መድሃኒት ስለሚጠቀሙ እንጂ የቱሃንን ንክሻ መቁቋም ትልቅ መከራ ነው። ጋዜጣ ላይ መጽፍ ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ጥሩ ወዳጄ ሃይሌ ገብረስላሴ ስለነበር ችግሩን አስረዳሁት። እባክህን አንሶላ ግዛላቸው፤ መድሃኒትም አስረጭላቸው” ችግሩን አወራሁት። 

ሃይሌ አዋቂ፣ ማድረግ የፈለገውን የሚያደርግ፣ ላመነበት ጉዳይ ወደ ኋላ የማይል፣ በአመለካከት ደረጃም ቢሆን ሩቅ አሳቢ በመሆኑ ጥያቄዬን እንደ አንድ የግል ጉዳዩ ያየዋል የሚል እምነት ነበረኝ። የሃኪም ቤቱ የበላይ ጠባቂ ደግሞ ወ/ሮ አዜብ መስፍን በመሆናቸው ሃይሌ አንድ ነገር ቢያስብ እንደማይወሳሰብበት አስረዳሁት። ከሁሉም በላይ ግን ከትጥቅ አምራቾች ጋር ባለው የቀረበ ግንኙነት የጨርቅ ድጋፍ ለማድረግ ይሳነዋል የሚል ጥርጣሬም አልነበረኝም። 

በማስተዋል ሰምቶኝ፣ በፈገግታ ሸኘኝ። የግል ምክንያቱን ባላውቅም ውይይታቸን መከነ። የቀኝህ የምትሰጠውን የግራህ አትመልከት በሚለው ሰማያዊ መርህ ብቻውን ሄዶ ድጋፍ አድርጎም እንደሆነ አላውቅም።  ዛሬ ጠዋት ገን ኮምፒውተሬን ስከፍት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከባለቤታቸው ጋር መቄዶኒያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ወገኖቻቸውን ሲዳብሱና ሲያነቃቁ አየሁ። ወዲያው ሃይሌ ትዝ አለኝ። ሃይሌን የጋበዝኩት መቄዶኒያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከልን እንዲረዳ ባይሆንም ተገናኘብኝ። 

ይህንን ስል ሃይሌን ለማሳጣት አይደለም።ፍላጎቱም ባይኖረው መብቱ ነው። አንድ ወቅት አሰላ የከፈተውን መዋዕለ ህጻናትና ትምህርት ቤት እንዲሁም ህንጻ ለመምረቅ አብረን በሄድንበት ወቅት ምረቃው ላይ ዘፈን ያቀረቡ መጠነኛ ባንድ አባላት ነበሩ። ሰው እየተነሳ ብር ሲሰጥ ሃይሌ ከመቀመጫው ሳይነሳ ያያቸው ነበር። ሲጨርሱ ጠርቷቸው ” ሙሉ ባንድ ለመሆን የሚያስችላችሁን ማንኛውም ነገር በጽሁፍ ስጡኝና አሟላላችኋለሁ። ከዛ በሁዋላ ራሳችሁን ትችላላችሁ” ሲል በጆሮዬ ሰምቻለሁ። ለዚህ ምስክር ነኝ።

አብይ አህመድ የሚባሉት የኢትዮጵያ አዲስ መሪ ጉድ እያሳዩን ነው። እኚህ ሰው ስራቸው ሁሉ ይገርማል። ፍጹም ሩህሩህ ናቸው። የተረሱትን ማየት ይችላሉ። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ባለስልጣናትም ሰው ሰው እንዲሸቱ እያደረጉ ነው። አገር ተረጋግቶ፣ ይህ የሸፍጥና የሴረኛ ፖለትካ ሰክኖ ስራቸው ላይ አተኩረው መስራት የሚችሉበት እድል ቢኖራቸው ምን ሊሰሩ እንደሚችሉ ሳስብ ሃዘኔ ክፉኛ ይሆንብኛል። 

ዛሬ ከእሳቸው በተጨማሪም የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስና የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በመቄዶኒያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ተገኝተው ወገኖቻቸውን ዳሰዋል። አጽናንተዋል። ቀዳማዊ እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው 15 ዘመናዊ ዊልቸር ለማዕከሉ አበርክተዋል።

ፎቶ  – ፋና ብሮድካስቲንግ

0Shares
0