“Our true nationality is mankind.”H.G.

«አማካሪ አያስፈልገኝም ብሎ የሚያስብ መሪ አልገባውም ማለት ነው» ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ እነሆ መንፈቅ አለፋቸው። ታድያ ጠቅላዩ መንበረ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ሃገሪቱን ያሳድጋሉና መሆን አለባቸው ብለው ከወሰዷቸው እርምጃዎች መካከል ምጣኔ ሃብታዊ ይዘት ያላቸው ይገኙበታል።

ቴሌንና አየር መንገድን የመሰሉ አሉ የሚባሉ የመንግሥት ድርጅቶችን ወደግሉ ዘርፍ ለማዘዋወር ከመወጠን አንስቶ ከጎረቤት ሃገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት እስከማጠናከር ድረስ።

የዳይስፖራ ትረስት ፈንድ (የአደራ ገንዘብ እንበለው) እና ለአፍሪካውያን እህት ወንድሞቻችን ቪዛ አየር መንገድ ሲደርሱ መስጠትን ጨምሮ ያሉ ከዚህ በፊት የማናውቃቸው ክንውኖች መታየት ጀምረዋል።

• ጫትን መቆጣጠር ወይስ ማገድ?

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማክሮና ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚክስ ምሁሩ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስካሁን ያከናወኗቸው ጉዳዮች መልካም ሆነው ሳለ በምጣኔ ሃብት ጉዳይ አማካሪ ያሻቸዋል ይላሉ።

እውን ጠቅላዩ ወደሥልጣን ከመጡ ወዲህ የምጣኔ ሃብት ፖሊስ ለውጥ አይተናል ወይ? ትልቁ ጥያቄ ነው።

«የምር የሆነ የፖሊሲ ለውጥ የለም ግን ሃሳብ አለ፤ የመለወጥ አዝማሚያ ታያለህ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጡ ወዲህ ይህ ነው ፖሊሲዬ በዚህ መልኩ ነው የምሄደው ያሉን ነገር የለም። ሃዋሳ በነበረው ጉባዔ (የኢህአዴግ) ላይም የተናገሩት ይሄንኑ ነው። በፊት የነበረው የኢኮኖሚ አስተሳሰብ እንዳለ እንደሚቀጥል ነው ፍንጭ የሰጡት።…»

« …በአንፃሩ ደግሞ ከዚያ ቀድም ብሎ አንዳንድ ትላልቅ የምንላቸውን የመንግሥት ኩባንያዎች በከፊል ለመሸጥ ሃሳብ እንዳላቸው አሳውቀዋል። ይህ የሚያሳይህ በፊት ከነበረው ለየት ባለ መልኩ ከፈት በማድረግ፤ የመንግሥት ሚና ብቻ ከጎላበት ኢኮኖሚ የግሉም ዘርፍ የሚሳተፍበት ኢኮኖሚ ለመመሥረት ቢያንስ ሃሳብ እንዳላቸው ያሳያል» ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

• ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መበራከት ምንን ያመለክታል?

የመንግሥት ድርጅቶችን የመሸጥ ጉዳይ ግን አከራካሪነቱ እንደቀጠለ ነው፤ ‘ሃገር መሸጥ ነው’ በሚሉና ‘እንዲህ ካልሆነ አናድግም’ የሚል ሃሳብ በሚያነሱ መካከል።

ለፕሮፌሰር አለማየሁ ግን ዋናው ጉዳይ ወዲህ ነው፤ መለየትና ማመቻቸት።

«ወደ ገበያ ተኮር ኢኮኖሚ የምንሄድበት ዋናው ምክንያት ውድድር ለማምጣት ነው፤ ውድድር ለማምጣት ደግሞ መወዳደሪያ ሜዳውን ማስተካከል አለብን። ውድድሩን የሚመራ፤ የሚቆጣጠር አካል ማደርጀት ያስፈልጋል። አለበለዚያ ዝም ብሎ ከመንግሥት ወደ ግል መሄድ፤ ‘ሞኖፖሊውን’ ከመንግሥት ወደግል መቀየር ነው። የግል ሞኖፖል ደግሞ ተጠያቂነት የለበትም፤ ብሩን የት ያጥፋው የት አይታወቅም፤ የሞራል ኃላፊነትም የለበትም።»

ምሁሩ «ምሳሌ ልስጥህ…» ይላሉ፤ «ምሳሌ ልስጥህ፤ ኢትዮ-ቴሌኮም በጣም ደካማ ነው፤ እናውቀዋለን። ሶማሊያ እንኳን ያለው የቴሌኮም አገልግሎት የተሻለ ነው። ኬንያማ አንደርስባቸውም። ስለዚህ እንደ ቴሌኮም ዓይነቱን ምን ማድረግ ነው? በከፊል መሸጥ። ችሎታው ላላቸው፤ ቢቻል ደግሞ አፍሪቃዊ ለሆኑ ድርጅቶች፤ በዚያውም ቀጣናዊ ግንኙነቱን ማጠናከር። እንደዚህ አድርጎ ተወዳዳሪነቱን ማጎልበት። ይህንን ውድድር የሚቆጣጠር ሥርዓት መዘርጋት፤ ከዚያ ለውድድር መክፈት። እንዲህ ነው መሆን ያለበት።»

ethiopian airlinesImage copyrightAFP

«አሁን በሌላ በኩል ደግሞ ስትመጣ አየር መንገድ አለ። አየር መንገድ በእኔ እምነት እንኳን ሊሸጥ፤ ለመሸጥ መታሰብ ራሱ የለበትም። ምክንያቱም በጣም ትርፋማ የሆነ ድርጅት ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ተወዳዳሪ የሆነ ድርጅት ነው፤ በጣም! ያለው ንብረት ወደ 80 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፤ ዕዳው 60 ቢሊዮን ገደማ ነው። ስለዚህ ንብረቱ በአያሌው ይበልጣል። በመንገደኛ የሚያገኘው ገቢ ‘ቶፕ’ ሰባት ከምትላቸው የአሜሪካ አየር መንገዶች ይበልጣል።»

«ይህ እንግዲህ ኢኮኖሚያዊ መከራከሪያ ነው፤ ወደ ባህላዊው ስትመጣ አየር መንገድ ቅርሳችን ነው፤ ዓለም ላይ ምንም ሳይሳካልን ሲቀር እንኳ አየር መንገዳችን ስኬታማ ነበር፤ ምልክታችን ነው። ‘ፕራይቬታይዜሽን ለውድድር ነው ካልን፤ በትንሽ ዋጋ ህዝቡን ለማገልገል ነው የምንል ከሆነ አየር መንገድን መሸጥ አዋጭ አይደለም። እኔ እንደ ኢኮኖሚስትም እንደ ዜጋም አልቀበለውም።»

ምክረ ሃሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ

በርካታ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦችን ያካተተ የህግ አማካሪ ያዋቀሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መሰል ውሳኔ በምጣኔ ሃብቱ በኩል እንዲያሳልፉ መወትወት ከተጀመረ ውሎ አድሯል።

እውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ያስፈልጋቸዋል ወይ? የሚል ጥያቄ የሚያነሱም አልጠፉም።

«ምንም ጥያቄ የለውም. . .» ይላሉ ፕሮፌሰር አለማየሁ። «ምንም ጥያቄ የለውም፤ አማካሪ ያስፈልጋቸዋል። ያደገ ሃገር ሆኖ ያለአማካሪ ያደገ እኔ አላውቅም። ከዚህም አንድ ደረጃ ፈቅ ማድረግ እችላለሁ። ያደገ ሃገር ሆኖ ያለቋንቋው ሳያስተምር ያደገ ሃገር እኔ አላውቅም። ቻይና ብትል ጃፓን፤ ጀርመን፣ አሜሪካ. . .እኔ አስተማሪ ስለሆንኩ ተማሪዎቼን ሳያቸው ከትምህርቱ እኩል ቋንቋ ችግር ነው። እንኳን የኢኮኖሚ አማካሪ ይቅርና ማለቴ ነው።»

«ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉን ነገር መሆን አይችሉም፤ ኢኮኖሚው ደግሞ የረቀቀ ነው። መዓት ፈርጆች አሉት። በእኔ ግምት ማንኛውም መሪ ያለኢኮኖሚ አማካሪ እሠራለሁ ካለ አልገባውም ማለት ነው።»

ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት. . .

ጠቅላዩ ከተመረጡ ወዲህ የመጀመሪያ ካሏቸው ሥራዎች መካከል ወደጎረቤት ሃገራት ብቅ ብሎ ወዳጅነትን ማጠንከር ነበር።

ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ. . . ታሪካዊ የሆነው ከኤርትራ ጋር የተደረገው እርቀ ሰላም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዘመን ከተከወኑ መካከል እንደስማቸው አብይ ሆኖ የሚጠቀስ ነው።

«የኛ ፖለቲካ እንደምታውቀው በጣም እየጠበበ፤ እየጠበበ እየሄደ ወደ ጎሳ፤ ከጎሳ ደግሞ ቀጥሎ ወደ መንደር፤ ከመንደር ደግሞ ወደ ቀበሌ መሄዱ አይቀርም በዚሁ ከቀጠለ። ሊህቃን ፍላጎታቸውን ለሟሟላት ሰዎችን የሚያደራጁበት መንገድ ነው የሚፈልጉት። ብትፈልግ ሶሻሊዝምና ካፒታሊዝም ይልሃል፤ ብትፈልግ ቀይ ሽብር፣ ነጭ ሽብር ይልሃል፤ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ቤኒሻንጉል ይልሃል፤ ማደራጃ ነው የሚፈልጉት በእኔ እምነት። ቀጣናዊ የሆነው የኢኮኖሚ አስተሳሰብ ከእንደዚህ ዓይነት አናሳ ከሆኑ አስተሳሰቦች አውጥቶ በሰፊው እንድናይ ስለሚያደርገን ከፖለቲካ አንፃር ጥሩ መነፅር ነው ብዬ ነው የምገምተው።»

• “በፍትህ ተቋማት ላይ የለውጥ እርምጃ ይፋ ይሆናል” ጠ/ሚ ዐብይ

«አሁን ወደ ኤርትራ እንምጣ. . . ነፃ የሆነ የህዝብ ፍሰት፤ ነፃ የሆነ የካፒታል ፍሰት፤ ነፃ የሆነ እንቅስቃሴ የመጨረሻው የዕድገት ደረጃ ነው። አውሮጳውያን ከ50 ዓመታት በላይ ነው ያ ጫፍ ለመድረስ የፈጀባቸው። በኢትዮጵያና በኤርትራ ጉዳይ ግን ባለፉት ጥቂት ወራት የሆነው የ50 ዓመቱን በአንድ ቀን እንደማድረግ ነው። የኔ ሪኮሜንዴሽን (ምክር) ምንድነው፤ ቆንጆ ነው ሃሳቡ፤ ህዝብን ከህዝብ ለማቀራረብ የሚደረገው፤ ነገር ግን ኤክስፐርቶች (ባለሙያዎች) ያስፈልጉናል። በዚህ መንገድ ነው የምንሄደው፤ በመርህ ደረጃ ሁላችንንም ተጠቃሚ የሚያደርግ፤ የሰላሙን ዘላቂነት የሚያረጋግጥ ሥርዓት ይህ ነው ብለው የሚመክሩ ‘ኤክስፐርቶች’ ማዘጋጀት ነበረባቸው የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ።»

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና አንግላ ሜርክልImage copyrightTOBIAS SCHWARZ

እነ ዓለም ባንክ ይታመናሉ?

የዓለም ባንክ፣ የዓለም የገንዘብ ተቋም እና መሰል አበዳሪ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ይህን ያህል የሻከረ የሚባል አይደለም።

በቅርቡ የዓለም የገንዘብ ተቋም ኢትዮጵያ በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት መልካም የሚባል ዕድገት ታስመዘግባለች የሚል ትንበያ ይዞ ብቅ ብሏል።

የዓለም ባንክም ለወዳጄ ኢትዮጵያ ያለሆነ ዶላር አፈር ይብላው በሚል 1.2 ቢሊዮን ዶላር ብድር ሰጥቷል።

«እኔ እነ ዓለም ባንክ ብድር ሲፈቅዱ ሃሳብ ነው የሚገባኝ። ለምን ብትለኝ፤ ከጀርባ የሆነ ነገር አለ ማለት ነው። እንጂ ዝም ብለው አይፈቅዱልህም። ወይ ፕራይቬታይዝ አድርግ ብለውሃል ወይ የሆነ ነገር ሽጥ ብለውሃል ማለት ነው። እነሱ የቆሙላቸው የምዕራብ ሃገር ድርጅቶች ከኋላ ሊገዙ ተሰልፈዋል ብዬ ነው የማስበው። ከአጠቃላይ የሃገር ውስጥ ምርታችን 60 በመቶ ዕዳ ነው። ይህ አሁን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ችግር አይደለም፤ የበፊቶቹ እንጂ፤ ቢሆንም ይህንን ዕዳ ወርሰውታል።»

ምሁሩ ሲቀጥሉ «አሁን እንዴት ይፍቱት ነው ዋናው ቁም ነገር» ይላሉ። «እኔ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ብሆን፤ እግዚአብሔር አያድርገኝና (ሳቅ. . .)፤ ምንድነው የማደርገው፤ ምዕራብም ምስራቅም አልልም። ከኢትዮጵያ ጥቅም አንፃር ነገሮችን አይቼ ጠቃሚው ላይ ትኩረቴን አድርጌ ፖሊሲዬን በዛ ነበር የምቀርፀው።»

ምጣኔ ሃብቱን ማሳደጉ ይቅርብንና ሰላሙ ይቅደም የሚሉ ድምፆች መሰማት ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ለፕሮፌሰር አለማየሁ እና መሰሎቻቸው ግን መፍትሄው ሁለቱን አንድ ላይ ማስኬድ ነው።

«ሁሉቱን አንድ ላይ ነው ማስኬድ ያለብን። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ያመጣው (ወደሥልጣን) ፖለቲካ ብቻ አይደለም፤ ኢኮኖሚውም እንጂ። ለምሳሌ ወጣት ሥራ አጦችን እንውሰዳቸው። ኦፊሻል ቁጥሩ 25 በመቶ ሥራ አጥ ወጣቶች እንዳሉ ነው የሚያሳየን። እኔ ያደረግኩት ጥናት እንደሚያሳው 40 በመቶ የሚሆኑ ወጣቶች ኢ-መደበኛ በሚባለው ዘርፍ ውስጥ ነው ያሉት፤ ሥራ አጥነት ማለት በሌላ ቋንቋ። ስለዚህ ለዚህ ሥራ አጥ ወጣት ሥራ ካልሰጡት ሊነሳባቸው ይችላል። ፋንዳሜንታል (መሠረታዊ) ችግሩ ምንድነው? ድህነት፣ ሥራ አጥነትና ፍትሃዊ ያልሆነ የገቢ ሥርጭት ነበር። ለኔ አብይን ካመጣው አብዮት ጀርባ ይሄ ጥያቄ አለ። ከላይ ያለው ‘አይድዮሎጂ’ ላዕላይ መዋቅሩ ነው። ውስጡ ግን ይሄ ነው። ስለዚህ ከፖለቲካው እኩል ኧረ እንደውም በበለጠ ይህንን ችግር ለመፍታት መንገድ ካልጀመሩ እሳቸውም ላይ ይመጣል።»

BBC Amharic

Related stories   ትህነግን በብሄራዊ ውይይት እንዲሳተፍ የሚደረግ ግፊት መኖሩን መንግስት ይፋ አደረገ፤ " ፍጹም ተቀባይነት የለውም" ብሏል

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0