“Our true nationality is mankind.”H.G.

የኢትዮ-ኤሜሪካ ግንኙነትና የምሥራቅ አፍሪካ የበላይነት ጉዞ!!” የበሰለ ምግብ?”

ትንታኔ
በገልፍ ሀገራት መካከል የነበረው ቀዝቃዛው ጦርነት በምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካዊ ሥነ-ምኅዳር አዲስ ታሪክ እየጻፈ ነው፡፡ እንደተለመደው የአሜሪካ ፖሊሲ ደግሞ የድርሻውን እያበረከተ ነው፤ ከቀጠናው ኃያልና የረዥም ጊዜ ወዳጇ ኢትዮጵያ ጋር በመሆን፡፡

በ1983ዓ.ም አሁን ኢትዮጵያን እየመራ ያለው ሥርዓት ወደ ስልጣን ከመጣ አንስቶ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ገንብታለች፤ በተለይ ሽብርን በመዋጋት ረገድ፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ ቀጠና ሞጋች ኃይሎች መጥተውባት አሜሪካ ፊቷን ከጸረ-ሽብር ወደ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ጦርነቶች አዙራለች፡፡ ይህም አሜሪካ ቀጠናውን እንዲሁ በዋዛ እየተመለከተች አለመሆኑን አመላካች ነው፡፡

ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኢመሬቶች በአንድ ሆነው ከኳታርና ቱርክ ጋር ተካርረዋል፤ ሁለቱም ቡድኖች ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ ግንኙነት በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡

በእርግጥ እነዚህ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ስልት የተቀረጸው በድሮ ቀኝ ገዥዎች ብሪታንያ፣ ፈረንሳይና ጣልያን ነው፡፡ ዓላማውም የስዊዝ መተላለፊያ መስመርንና ዋነኛ የመርከቦች እንቅስቀሴ ማዕከሉን መቆጣጠር ነበር፡፡ ነገር ግን የአሁኑ ዘመን ግንኙነት የባላንጣነት አይደለም፡፡ ይልቁንም ቀጠናውን በምጣኔ ሀብትና ሰላም ዘርፎች የሚጠቅም ፉክክርና ትብብር የሚታይበት ሆኗል፡፡ በተለይ በሰላም ረገድ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት አስደማሚ ለውጥ እያሳዩ ነው፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ ከ20 ዓመታት መቃቃርና ጦርነት በኋላ ሰላም አውርደዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም መሆን በምሥራቅ አፍሪካ ሰላም መስፈን ላይ ትልቅ ድርሻ አለው›› ብለዋል የአማኒ አፍሪካ ፖሊሲ ጥናት አማካሪው ሃሌሉያ ሉሌ፡፡ 
ነገር ግን በተመሳሳይ የአሜሪካ የቀጠናው ፖሊሲም እየተቀየረ ነው፡፡ ምክንያቱም በቀጠናው አዲስ ኃይል እየተፈጠረ ነውና፡፡ በቀይ ባሕርና የመን አካባቢ የአሜሪካ ተቀናቃኞች እየተፈጠሩ ነው፤ በየመን ጀርባ ኢራንና ሳዑዲ አረቢያ እየተፋለሙ ነውና፡፡ ሳዑዲ አረቢያ ለአሜሪካ ወዳጅ ለኢራን ባላንጣ ነችና በአሜሪካና ኢራን መካከል ያለው የኑክሊዬርና ማዕቀብ ፍጥጫ በምሥራቅ አፍሪካ ሌላ የፍልሚያ ግንባር ሊሆንም ይችላል፡፡ ስለዚህም የአፍሪካ ቀንድንና መካለኛው ምሥራቅን በበላይነት ለመምራት የመን ውስብስብ የጦር ሜዳ ሆናለች፡፡

የአዲሱ ቀዝቃዛው ጦርነት መሠረቶች

የምሥራቅ አፍሪካን የበላይነት ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለው ሽኩቻ የቀጠናው ‹‹አዲስ ቀዝቃዛው ጦርነት›› ተብሏል፡፡ የገልፍ ሀገራት ቀዝቃዛው ጦርነት የተቀሰቀሰው በ2017 (እ.አ.አ) ሳዑዲ አረቢያ የአረብ ሀገራት ሁሉ ኳታርን እንዲገልሏት ማነሳሳት ስትጀምር ነው፡፡ ወዲያውኑ ራሷ ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ የተባበሩት አረብ ኢመሬቶች በአንድ ወገን ኳታርና ቱርክ በሌላ ወገን በአፍሪካ ቀንድ ወታደራዊ መሠረት (ቤዝ) እንዲኖራቸው ወታደራዊ ስምምነት ከቀጠናው ሀገራት ጋር በማድረግና የንግድ ወደቦችን

ለመቆጣጠር እሽቅድድም ጀመሩ፡፡

ኢትዮጵያ ደግሞ ምንም እንኳ ይህ የቀዝቃዛው ጦርነት ሲለኮስ በውስጣዊ አለመረጋጋት ውስጥ ብትሆንም ባለፉት ሁለት ምዕተ ዓመታት ከውጭ ኃይሎች ጋር ስትጋፈጥ ኖራለችና ራሷን አመቻችታ እንዴት ሁኔታውን ለመልካም ዕድል መጠቀም እንዳለባት ታብሰለስል ጀመረች፡፡

በዓፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ነበራት፤ ነገር ግን በደርግ ዘመን ፊቷን ወደ ሩሲያ አዞረች፡፡ እንደገና ደግሞ ከ1983ዓ.ም በኋላ ኢትዮጵያ ለአዲስ ግንኙነት ፊቷን ወደ አሜሪካ መለሰች፡፡ በተለይ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ አንስቶ የፀረ-ሽብር አጀንዳ ሲጧጧፍ የኢትዮጵያን ገናና ፕሮፌሽናል የመከላከያ ሠራዊት መመኪያ በማድረግ አሜሪካ ግንኙነቷን አድሳ ኢትዮጵያን የልብ ወዳጇ አደረገች፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የቻይናና ሩሲያ የምጣኔ ሀብት ግስጋሴ የአሜሪካን የሽብርተኝት ትኩረት አስቶ በአፍሪካና ሌሎች አካባቢዎች ያላትን ቅቡልነት እየፈተነ መጣ፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ‹‹የዚህ ዘመን የልዕለ ኃያላን ሽኩቻና ፉክክር ሽብርተኝነት ላይ ሳይሆን ብሔራዊ ደኅንነት ላይ ነው›› ነበር ያሉት የአሜሪካው የመከላከያ ኃላፊ ጀምስ ማቲች የ2018 (እ.አ.አ) የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክተው ሲናገሩ፡፡

ማቲች ንግግራቸውን ሲቀጥሉም ‹‹እያደገ የመጣውን እንደ ቻይናና ሩሲያ ያሉ ሀገራት የፖለቲካ ተቃርኖ መጋፈጥ ከፊት ለፊታችን ተደቅኗል›› ብለው ነበር፡፡ ጀምስ ማቲች ይህንን ሲሉና የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ ላይ ሀገራቸው ተጠምዳ ሳለ ኢትዮጵያ በሕዝብ ፖለቲካዊ የለውጥ ጥያቄና በመንግሥት ለውጡን የመመከት ሙከራ ተወጥራ ነበር፡፡ በሀገሪቱ በኦሮሞና አማራ ክልሎች የተቀጣጠለው የለውጥ ጥያቄ ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ውስጣዊ የግንባሩ ድርጅቶች የሐሳብ ፍትጊያ ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያ አጣብቂኝ ውስጥ ነበረች፡፡ በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ዕይታ መነጽር ልትሰወር ጫፍ ደርሳ ነበር፡፡

በነበረው የሀገሪቱ የፖለቲካ ቅርጽ ማጣት ኢሕአዴግ የውጩን ዓለም የመፍትሔ መንገዶች ሲፈትሽ በርካታ የቻይና የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት እና የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን መሳብ ጀመረች፤ ቻይናም የአሜሪካን የበላይነት በምጣኔ ሀብት ለመገዳደር በኢትዮጵያ በስፋት መሠማራት የአፍሪካ መግቢያ ቁልፍን በእጇ ማስገባት ሆነላት፡፡ በዚህ የተነሳም አሜሪካ ሳትፈልግ ትኩረቷን ከጸረ-ሽብር ወደ ምጣኔ ሀብት ጦርነት በማዞር ከቻይና ጋር ለመሽቀዳደም ተገደደች፡፡

አሜሪካ እንደ ቀደመው በቀውስ ውስጥ ለገባችው ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ አለማድረጓና በቀውስ ውስጥ ለነበረው ኢሕአዴግ ዝምታን መምረጧ ግንባሩ በራስ መተማመኑ እንዲከዳውና በውስጣዊ ጉዳዮች እንዲጠመድ አደረገው፡፡

በ2010ዓ.ም አጋማሽ ገደማ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የመፍትሔው አካል ለመሆንና ሀገሪቱን ለማረጋጋት በፈቃዳቸው ራሳቸውን ከኃላፊነት አነሱ፡፡ ይህንን ተከትሎም ዶ.ር ዐብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ብቅ አሉ፡፡
ዶ.ር ዐብይ ወደ ስልጣን በመጡ በሳምንት ውስጥ የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኤች አር-128 የተባለውንና በኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ ጥሰት እየተፈጸመ ነው የሚለውን ማዕቀፍ አጸደቀ፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለኤች አር-128 መጽደቅ የነበራቸው ሚናም ከፍተኛ ነበር፡፡ ‹‹ኤችአር-128 የኢትዮጵያ መንግሥት መሻሻል እንዳልቻለ የማንቂያ ደወል ነበር፤ ማሻሻያዎችን ካላደረገ ከአሜሪካ ጋር በወዳጅነት እንደማይቀጥልም አመላካች ነበር›› ብለዋል በሚኒሶታ ነዋሪ የሆኑት ምሁርና ፀሐፊ ሐሰን ሁሴን፡፡

ዶ.ር ዐብይ ወደ ስልጣን እንደመጡ ፈጣንና ቅጽበታዊ የሚባል ለውጥ ማምጣት ጀመሩ፤ እስረኞች ተፈቱ፣ በአንድ ወቅት ‹ሽብርተኛ› ተብለው ለተፈረጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ጥሪ አቀረቡ፣ በመገናኛ ብዙኃንና ሐሳብን በነፃነት በመግለጽ ላይ የነበሩ ገደቦችን አነሱ፡፡ ሌላውና አስደማሚው እርምጃ ደግሞ በኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል የነበረውን ለዓመታት የዘለቀ አለመግባባት የፈቱበት መንገድ ነው፡፡ ይህም አንዱ ውጫዊ ተፅዕኖ የፈጠረ እርምጃ ነበር፡፡
‹‹የቻይና እጅ በኢትዮጵያ ጎረቤት ጅቡቲ መርዘሙም ለአሜሪካ ሌላው የራስ ምታት ሆኖ ብቅ አለ፤ የአፍሪካ ወታደራዊ መሠረቷ ጂቡቲ ሆናለችና፡፡

ኤርትራም ሌላኛዋ የነገ የቻይና አማራጭ አፍሪካዊ መሠረት መሆኗ አይቀርም፡፡ ነገር ግን ከኢትዮጵያ ጋር በነበራት ግንኙነት ምክንያት የተጣለባትን ዓለማቀፋዊ ፖለቲካዊ መነጠል መቀልበስ አለባት›› ብለዋል ኢትዮጵያዊ ተንታኝ መሀሪ ታደለ ማሩ፡፡
ባለፈው ዓመት በጸጥታ የተደረጉ የዲፕሎማሲና የቤተ ክርስቲያናት ጥረቶች የኢትዮ-ኤርትራን ግንኙነት ለማደስ እንዳገለገሉም መሀሪ ታደለ ያምናሉ፡፡
በመካከል ደግሞ በየመን ጦርነት ላይ የምትገኘው ሳዑዲ አረቢያ በኤርትራ ወታደራዊ መሠረት ጥላለች፡፡ በኢራን የሚደገፉ የሁቲ አማጽያንን ለመዋጋት የመን የገባችው ሳዑዲ ከወታደራዊ መሠረትም አልፋ በኤርትራ ወደቦች ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ትፈልጋለች፡፡ ይህ ሁኔታ ምናልባትም ለኢትዮ-ኤርትራ መልሶ መወዳጀት አስተዋጽኦ ሳያበረክት እንዳልቀረ ሃሌሉያ ሉሌ ገምተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሳዐዲ-አረብ ኤመሬቶች ቡድን እየተዋጠች ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ.ር ዐብይ ከመጡ በኋላ የመጀመሪያ ከአፍሪካ ውጭ ጉብኝታቸውም በሳዑዲ ነበር፤ በዚያውም የተባበሩት አረብ ኤመሬቱን መሪ አግኝተው ነበር፡፡

በእንግሊዝ የሚኖሩትና በኢትዮጵያና ኤርትራ ጉዳይ በተደጋጋሚ የሚጽፉት አወል አሎ ደግሞ ‹‹እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የቀጠናውን ተለዋዋጭ አካባቢያዊ ፖለቲካ መቆጣጠርና የበላይነታቸውን ማስጠበቅ አለባቸው›› ብለዋል፡፡ 
‹‹በመካከለኛው ምሥራቃዊ ቀጠና ያለውን የአካባቢው ዘዋሪነት ውድድር አዲስ አበባ ገለልተኛ ሆና እየተመለከተችው ነው፤ ቢያንስ ቢያንስ ግን ያለችበት መልክአምድራዊና ስትራቴጂካዊ ሁኔታ ለቀጠናው የበላይነት ከተለያዩ አቅጣጫዎች መዋዕለ ንዋይ እንድትስብ ያግዛታል›› ብለዋል አወል አሎ፡፡

ከአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ እንደተገኘ መረጃ ‹‹አሜሪካ አሁንም ከኢትዮጵያ ጋር ከመቸውም በላይ ቁርጠኛ ሆና ትቀጥላለች፡፡››

‹‹ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከፍተኛ ወታደራዊ ድጋፍ በማድረግና ቀጠናውን ለማረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች ነው፡፡ በዓለም ላይ እጅግ ከፍተኛ ስደተኞችን የምትቀበል ሀገርም ነች›› ይላሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የአሜሪካው የአዲስ አበባ ዲፕሎማት፤ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለመሥራት ቁርጠኛ የሆኑበትን ምክንያት ሲያስረዱ፡፡

‹‹ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሆነና አዳጊ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ያልተነካ የሀብት ክምችትም አላት፡፡ በዶክተር ዐብይ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ደግሞ ለበለጠ አብሮነትና መሻሻል የሚበጅ ነው፡፡ ምክንያቱም ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ለፖለቲካዊ መረጋጋት እና ለምጣኔ ሀብት ማደግ መሠረቶች ናቸውና፡፡ ስለሆነም አሜሪካ ከኢትዮጵያ ከመነጠል ይልቅ የበለጠ መቅረብን ትፈልጋለች፡፡ ይህን ደግሞ በግልጽ እያየን ነው›› ብለዋል ዲፕሎማቱ፡፡

እንደ ዲፕሎማቱ በዚያው ልክ የአሜሪካ የፀረ-ሺብር ጥረቶች ከኢትዮጵያና አፍሪካ ጋር ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡ ‹‹ድንበር ዘለል ሽብርተኝነትና አክራሪነት በሳህለ ቀጠና፣ ሰሜን ናይጀሪያ፣ ሶማልያ፣ በቅርቡ ደግሞ በማዕከላዊ አፍሪካ፣ የቦከሀራም መነሳት፣ የአልቃይዳ በማግረብ አካባቢ የአልቃይዳ መኖር፣ በምዕራብ አፍሪካ የአይኤስ አይኤስ መኖርና አልሸባብ አዲስ ቀጠናዊ አቀራረብን ይጠይቃሉ›› ያሉት ደግሞ በአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ ቲቦር ናጌ ናቸው፡፡ እንደ ረዳት ኃላፊው አፍሪካዊ በደንብ የሰለጠነና ተከፋይ ሕግ አስከባሪ መኖሩ መፍትሔ ነው፡፡ ይህም አሜሪካ አሁንም የኢትዮጵያን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ልምድ ተጠቅማ በአፍሪካ ጸጥታና ደኅንነት ዙሪያ ቀኝ እጇ ሆና እንድትቀጥል ፍላጎት እንዳላት ማሳያ ነው፡፡

ምንም እንኳ ከላይ የተጠቀሱት ስጋትና ፈተናዎች ቢኖሩም የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት መታደስ ግን ለቀጠናው ፖለቲካዊ መሻሻል መሠረታዊ ነው፤ በውጫዊ ኃይሎች (እንደ አሜሪካ ባሉት) ቢታገዝ ደግሞ በቀውስና መከራ ውስጥ ለቆየው ምሥራቅ አፍሪካ የንጋት ወገግታ ነው፡፡

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ከተስማማች በኋላ ከጂቡቲና ሶማሊያ ጋርም የሰላምና ትብብር ስምምነት ተፈራማለች፡፡ ከበርካታ መቃቃር በኋላ ኢትዮጵያና ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዳይም መሠረታዊ የሚባሉ መግባባቶች ላይ ደርሰዋል፡፡ ሱዳንም ከግብጽ ጋር ያላትን ግንኙነት በማሻሻል በአሜሪካ ተጥሎባት ከነበረው ማዕቀብ እፎይታ እያገኘች ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ተደምረው ሲታዩ በምሥራቅ አፍሪካ አዲስ የስበትና የፖለቲካ ኃይል እየተፈጠረ ለመሆኑ ምልክቶች ናቸው፡፡ የምዕራቡና ምሥራቁ የምጣኔ ሀብት ጦርነት ፍልሚያም ለቀጠናው የበሰለ ምግብ ሆኖ የሚቀርብ እየመሰለ ነው፡፡

ምንጭ፡- ግሎባል ፖለቲክስ

በአብርሃም በዕውቀት – (አብመድ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ እያራመዱት ያለው አቋም የዴሞክራሲ መርህን የጣሰ ነው
0Shares
0