ዛጎል ዜና – መገንጠል የኦሮሞን ህዝብ ቁመና እንደማይመጥን ዶክተር መረራ ጉዲና በድጋሚ አስታወቁ። መለስ ለተቃዋሚዎች ዓመታዊ በጀት እንደሚሰጡ ለጀርመን መንግስት ተወካይ በተናገሩት መሰረት በዓመት ለመድረክ ሃምሳ ዩሮ ብቻ እንደሚሰጥ ስናገር ተዋካይዋ ተደንቀው እንደነበር አስታወሱ። ተቀላቢ ፓርቲዎችን ዶክተር አብይ ቀለባቸውን እንዲቆርጡባቸው አሳሰቡ።

ከዋልታ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ዶከተር መረራ እንዳሉት በመልክዐምድር፣ በህዝብ ብዛት፣ በታሪክም ሆነ በማንኛውም መስፈርት የኦሮሞ ህዝብ ከኢትዮጵያ እንዲገነጠል ማሰብ አግባብ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ይህ የኦሮሞን ህዝብ አጠቃላይ ቁመና አይመጥንም። 

“አንድ ሰው አንድ ድምጽ” በሚል መርህ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከተመሰረተ የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ውስጥ የመሪነት ሚና ሊጫወት እንደሚችልና የሚያዋጣውም ይህ አካሄድ እንደሆነ አስምረውበታል። በሌላም በኩል በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲፈጠር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስትን ሳይሆን ተቃዋሚዎችን እንዲቃወሙና እንዲያከሽፍ ቀለብ የሚቆረጥላቸውን ” ተቀላቢ” ድርጅቶች በጀት እንዲያስቆሙ ጠይቀዋል።

ከጀርመን የመጡ አንዲት ሃላፊን ጠቅሰው ልምዳቸውን ሲናገሩ፣ መለስ ለለሴትየዋ “ለተቃዋሚዎች ዓመታዊ በጀት እሰጣለሁ። ከዚህ በላይ ምን አድርግ ነው የመትሉኝ” በማለት ቅጥፈት የተሞላው ምላሽ መሰጠቱን ገልጸዋል። ጠያቂው እንዲያብራሩ ሲያንደረድራቸው፤ ሴትየዋ ከሶስት ፓርቲ  መሪዎች ጋር ለመሰብሰብ ጥያቄ አቀረቡ። አንደኛው ሰው ከተቀላቢው ፓርቲ መሪ ጎን አልቀመጥም በሚል ቀሩ። መረራ ጥሪውን አክብረው ሄዱ። ዓመታዊ በጀት ከምንግስት እንደሚቆረጥላቸው መለስን ጠቅሰው ፈረንጇ ሴት ተናገሩ።

እንደተለመደው ፈገግ እያሉ መረራ ” በመድረክ ስር ላሉ ስድስት ፓርቲዎች ሃምሳ ዩሮ በዓመት ይሰጠናል” ሲሉ ” ተቀላቢ” የሚባሉት የፓርቲ መሪ በዓመት ሶስት መቶ ሺህ ብር እንደሚሰጣቸው ተናገሩ። የዚህን ጊዜ ሲትየዋ ” አንደኛው የፖለቲካ ፓርቲ ከአንተ ጎን አልቀመጥም ያለው እውነቱን ነዋ” ሲሉ በምጸት መናገራቸውን ገለጹ”  አያይዘውም ” ሃምሳ ዩሮ በአገራችን የአንድ ሰው ቀለብ እንኳን አይገዛም” ሲሉ ሴትየዋ ተገርመው መናገራቸውን ያወሱት መረራ ” ተቀላቢ ፓርቲዎች የአገሪቱ ፖለቲካ ታጥቦ ጭቃ አድርገውታል” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህንን ጉዳይ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ አመራር እንዲሰጡ ጠይቀዋል። በቃለ ምልልሳቸው ስም መጥራት እንደማይፈልጉ አመልክተዋል። በቅርቡ አየለ ጫሚሶ የሚሰጣቸው ገንዘብ ስላነሳቸው እንዲጨመርላቸው ለህወሃት የሚሰሩትን ውለታ በመዘርዘር የጻፉት ደብዳቤ ይፋ መሆኑ አይዘነጋም።

ብሄራዊ መግባባት የሚፈጠርብትን አግባብ መፈለግ ግድ እንደሆነ ያመለከቱት ዶክተር መረራ፣ አሁን በአገሪቱ እየታየ ያለው ለውጥ ተሳፋ ያሳደረባቸውን ያህል ስጋትም እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል። ድርጅታቸው በዚሁ ጉዳይና መንግስት ሊሰራቸው ይገባል ብለው የሚያምኑበትን በመዘርዘር ቢያቀርቡም፣ ከመንግስት ወገን ላለፉት ሶስት ወራት የውይይት እድል እንዳላገኙ አመልክተዋል። እሳቸው እንደሚሉት ከውጪ የገቡትም ሆነ አገር ቤት ያሉ ተቀናቃኝ ድርጅቶች አንድ ላይ የሚጫወቱበት ፍኖተ ካርታ ሊዘጋጅ ይገባል።

ሌላው አስገራሚ የመረራ ምላሽ የታሰሩት ስላታዊ በሆነ መንገድ ትግሉን ለማቀጣጠል እንደሆነ ተጠይቀው የመለሱት ነው ” እሱን ኢህአዴግን ሂድና ጠየቀው” አሉ። ጠያቂው ሊያውጣጣ ሞከረ ” ለደህንነቶቹ የሚናገረውን፣ የሚሰራውንና የሚተገብረውን የሚያውቅ ሰው ማሰር አይጠቅማችሁም ብያቸው ነበር” ሲሉ ኢህአዴግ እሳቸውንም ሆነ ሌሎችን ማሰሩ ዛሬን በመመልከት እንደሚረዳው ጠቁመዋል።

አዲስ አበባን አስመልክቶ ጠያቂውን ” አንተን ጨምሮ” አሉና ሚዲያዎች ህዝቡን ወዳልሆነ መንገድ እንዳይመሩት ስጋት እንዳላቸው አመልክተው አዲስ አበባ ላይ ሁሉም በሰላም የሚኖርበት ስርዓት መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል። የመረራ ፓርቲ ምክትል መሪ የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ግን አዲስ አበባ ላይ ያላቸው እየታ ደጽሞ የተለየ መሆኑ የሚታወስ ነው።  አንቀጽ ፫፱ በተመለከተ ፓርቲያቸው ተቃውሞም ሆነ ደግፎ ሰልፍ እንደማይወጣ ያመለክቱት መረራ፣ ወያኔ ለምን ይህንን አንቀጽ እንደደነቀረው ጠያቂው ከእነሱ ጠይቆ እንዲረዳ መክረዋል። 

እስር ቤት እያሉ ጡረታ ለመውጣት አስበው ከእስር ሲለቀቁ የተቀበላቸው ህዝብ፣ አምቦ ላይ ከሁለት ሚሊዮን ህዝብ በላይ ለአቀባበል መውጣቱ ህዝብ ገና ማገልገል እንዳልባቸው ይስተላለፈላቸው መልዕክት ሆኖ እንደተሰማቸው ዶክተር መረራ አመልክተዋል። አሁን ያለውን ለውጥ በተመለከት የአጠቃላይ ሕዝብ የትግል ውጤት እንደሆነ እንደ ሌሎች አክራሪ አመለካከት ያላቸው ሳይመሳደቁ ተናግረዋል።

ቄሮ የተሻለ፣ የጎንደር ህዝብ የተሻለ ታግሎ እንደነበር ግልጽ መሆኑንን ዶክተር መረራ ተናግረዋል። ዋናው ቁምነገሩ ይህንን ድል ዴሞክራሲያዊ፣ ሁሉም ህዝብ በእኩል የሚተዳደርበት ስርዓት መፈጠሩ እንደሆነ ከትንታኔ ጋር አስረድተዋል። 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *