“Our true nationality is mankind.”H.G.

አገር ባለ ውለታነቷን የምታረጋገጥበት ሥርዓታችንን እንፈትሽ!

በገነት ዓለሙ

በአገራችን የተጀመረው ለውጥ ገና ከሴራና ከአሻጥር አደጋ ውስጥ ባይወጣም፣ ለውጡ በአገር ውስጥም በውጭ አገርም ቁርሾና ኩርፊያን፣ የጠላትነት ፖለቲካን እያፈረሰ፣ ዕርቅንና የፖለቲካ ድጋፍን እያበራከተ መቀጠሉ ዋናው አዝማሚያና አቅጣጫ፣ እንዲሁም ባህርይው ነው፡፡ የዴሞክራሲ ለውጡን የተጋፈጠው አደጋ ግን ቀላልና ለአፍታም ቸል የሚባል አይደለም፡፡ የለውጡ ተቀናቃኞች ጉዳይ የታወቀ ነው፣ የታወቀ ነው የምለው በድሮው፣ ‹‹ጠላትማ ምን ጊዜም ጠላት ነው . . ›› ይል በነበረው ቋንቋ ስሜትና ትርጉም ዓይነት ማለቴ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ሲበዛ አስቸጋሪ የሆነውና ለለውጥ ተቀናቃኙ፣ ድጋፍ ሆኖ የሚያገለግለው ለውጡንም ለአሻጥረኛ ቅስቀሳዎች የሚያጋልጠው በለውጥ ኃይሉ መካከል ያለው ልዩነት፣ ልዩነቱ የሚከሰትበትና የሚስተናገድበት አላዋቂነት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ፈላጊው ኅብረተሰብና ማኅበረሰብ ውስጥ በራሱ ኢዴሞክራሲያዊና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ፍላጎቶች፣ ፀባዮችና ተግባራት መኖራቸው ችግሩንና ሥጋቱን ማባባሱ አልቀረም፡፡

ከጥርነፋና ከግፍ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር በሚደረገው በዚህ አስቸጋሪና ውስብስብ ጥረት ውስጥ ሆነን፣ በኅብረተሰቡና በመንግሥት እንቅስቃሴና ዕርምጃዎች ውስጥ ከዴሞክራሲያዊነትና ከሕገ መንግሥታዊነት ውጪ የሆኑ ከእነሱ ያፈነገጡ ተግባራትን ደጋግመን እንመለከታለን፡፡ ገና አስቸጋሪና ያልለየለት ሽግግር ላይ በመሆናችን በዴሞክራሲያዊነት ሚዛን ቢመዘኑ ፈተናውን የማያልፉ ብዙ የወደቅንባቸው ነገሮች አሉብን፡፡

ዛሬም እንደ ትናንትናው የተወሰነ የሥልጣን መደብን እንደ ርስት ከየብሔረሰቡ ጋር አያይዞ የመመደብና የመዘርዘር ልማድ ገና በዴሞክራሲ አልተተካም፡፡ የአገርን ፀጥታና ሰላም የማስከበር ወቅታዊ ፈተና የለውጡ ዋነኛና ቅድሚያ ተግባር ከሆነው የፀጥታ ኃይሎችን ከፖለቲካዊ ወገናዊነት ከማፅዳት ሥራ ጋር ደርቦ የማካሄድ ተግባር ውስጥ ወድቀናል፡፡ እንዲህ ያለ ችግር ባለበት አገር ውስጥ ግን ዛሬ ወጣ ብዬ መነጋገርያ እንዲሆን የፈለግሁት ከዚህ ያነሰ ጉዳይ አለኝ፡፡ እሱም የሜዳይና የኒሻን ጉዳይ ነው፡፡

ይህን በመሰለ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ የብዙ ዘመን ታሪክ ያለውን፣ ዛሬ ግን ጎዶሏችን የሆነውን ያለ ብልኃትና ያለ ዕውቀት ደግሞ ዝም ብለን የቀጠልንበትን፣ የአገራችንን የ‹‹ክብር የማዕረግ›› ሥርዓት (Honour System) ጉዳይ እንመልከት፡፡ ስመ ጥሩው ባላምባራስ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል እስከ 1928 ዓ.ም. ድረስ ያሉትን የመንግሥት ሰነዶች አደራጅተውና አብራርተው ባቀረቡበት ‹‹ዝክረ ነገር›› መጽሐፋቸው እንደሚነግሩን ወግ ማዕረግ ያለው የክብር ምሥጋና መስጠት፣ ይህንንም በሽልማት፣ በማዕረግ፣ በኒሻንና በሜዳልያ መግለጽ ረዥም ታሪክ ያለው አሠራር ነው፡፡

በተለይም፣ ‹‹የኢትዮጵያ . . . መንግሥት በዓለም ላይ ያሉ የሠለጠኑ መንግሥታት እንደሚያደርጉት ሁሉ . . . ›› በታማኝነትና በቅንነት ብዙ ዘመን ላገለገሉ፣ በጦርነት፣ በሚያኮራ ሁኔታ ለተዋጉ፣ ጥበብ በማውጣት ድርሰት በመድረስ ለአገራቸው ዕድገትና ክብር ለደከሙ፣ ወዘተ የሚሰጡ ሜዳሊያዎችን ማዘጋጀት ከመንግሥት ሥራዎች ውስጥ አንዱ ሆኖ ኖራል፡፡ የእነዚህንም ኒሻኖችና ሜዳልያዎች ዝርዝር ‹‹ሙሉ ሀተታና የአሸላለሙን ዝርዝር ደንብ›› ይዘታቸውንና መልካቸውን ይነግሩናል፡፡

ከጣሊያን ወረራ በኋላም ይህ አሠራርና ሥርዓት ተጠናክሮ ቀጥሎ፣ በዘመናዊ የሕግ አወጣጥ ሥርዓት ታግዞ የኢትዮጵያ ሕግ አካል ሆኖ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከአገር ውጭም ጭምር የሚታወቅ ‹‹Honour System›› ሆኖ ኖሯል፡፡ በዚህም መሠረት አገራችን የማይናቅ ረዥም ዝርዝር ያላቸው የማዕረግ ደረጃም የወጣላቸው ሜዳልያዎችና ኒሻኖች ነበራት፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ የጦር ሜዳይ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጦር ሜዳይ፣ የዳግማዊ ምኒልክ የውትደርና አገልግሎት ሜዳይ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የብሔራዊ አገልግሎት ሜዳይ፣ የውስጥ አርበኞችና የስደተኞች ሜዳይ፣ የድል ኮከብ ሜዳይ፣ የመምህራን ሜዳይና የኮርያ ጦርነት ሜዳይ የሚባሉ ነበሩ፡፡  

የኒሻኖች ደንብ ደግሞ በየጊዜውና በየዘመኑ የተቋቋሙትንና የተወሰነላቸውን ደንብ በማሻሻልና በማጠቃለል የማኅተመ ሰሎሞን ማዕረግ፣ የንግሥተ ሳባ ማዕረግ፣ የሥላሴ ኒሻን ማዕረግ፣ የዳግማዊ ምኒልክ ኒሻን ማዕረግ፣ የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ ኒሻን ማዕረግ የሚባሉ እያንዳንዳቸው አምስት፣ አምስት ደረጃ ያላቸው የኒሻን ዓይነቶችን አቋቁሟል፡፡

ዝርዝሩን በተለይም አሁን ላይ ሆኖ ለሚያየው በጣም ይደንቃል፣ ይገርማል፡፡ መንግሥትና ሕግ በእንዲህ ያለ ጉዳይ እንዲህ ‹‹ሥራ ይፈታሉ?›› ጉልበትና ገንዘብ ያባክናሉ? ያሰኛል፡፡ ለምሳሌ የማኅተመ ሰሎሞን ማዕረግ የሚባለው ኒሻን የመጀመርያው ዓይነት ባዝግና (ኮለር) በተለይ ለማን እንደተወሰነ (ለንጉሠ ነገሥቱና ለእቴጌዪቱ የተመደበ መሆኑን)፣ ንጉሠ ነገሥቱ በልዩ አስተያየታቸው ለንጉሣዊ ቤተ ዘመዳቸውና ለውጭ አገር ነገሥታት፣ እንዲሁም ደግሞ እጅግ ከፍ ያለ አገልግሎት ላላቸው ሰዎች የሚሰጥ እግጅ በጣም የከበረ ሽልማት መሆኑ ተደንግጓል፡፡ የእያንዳንዱ ምሥልና ቅርፅ ከተጓዳኝ ዝርዝሮች ጋር በሕግ ተወስኗል፡፡ የእያንዳንዱ የኒሻን ዓይነትና ማዕረግ በተለይም የማኅተመ ሰሎሞን፣ የንግሥተ ሳባ ማዕረግ ኒሻኖች ተሸላሚዎች ቁጥር ከተወሰነ ቁጥር እንዳይበልጥ በሕግ ተደንግጓል፡፡ ከሦስት፣ ከአሥር፣ ከ20 . . . ፣ ከ45፣ ከ55 አይበልጥም ተብሎ በሕግ ተከልክሏል (በነገራችን ላይ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ታኅሳስ 2 ቀን 1940 ዓ.ም. ለፊልድ ማርሻል ሞንትጎመሪ የሸለሟቸው ታላቁን የሰሎሞን ኒሻንን ነው)፡፡

ይህ የክብርና የማዕረግ የሽልማት ሥርዓት በመላው የንጉሠ ነገሥቱ የሥልጣን ዘመን ዘለቀ፡፡ ከመስከረም 1967 ዓ.ም. ጀምሮ ሥልጣን የያዘው ወታደራዊ መንግሥት በ1971 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ (ስለቀድሞዎቹ ሜዳይዎችና ኒሻኖች በሕግ በግልጽ ሳይነገር) የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥትን የሜዳይና የኒሻን አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 169/71) አወጀ፡፡ በአዋጁም በሕጉ በዝርዝር በተወሰኑት ሜዳይዎችና ኒሻኖች መሠረት በጦር ሜዳ ሜዳልያዎቹ ዝርዝር ውስጥ፣ የጦር ሜዳ ሜዳልያዎችና ዓርማ የሚባሉት የኅብረተሰባዊ ኢትዮጵያ ወደር የሌለው ጀግና ሜዳይ፣ የላቀ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ፣ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሦስተኛ ደረጃና የጦር ሜዳ ቁስለኛ ሜዳይ፣ እንዲሁም የአብዮታዊ ዘማች ዓርማ የሚባሉ ተደንግገዋል፡፡ እነዚህ የሜዳይ ሽልማቶች ለማንና ምን ለፈጸመ እንደሚሰጡና ተሸላሚውም የሚያገኘው ልዩ መብት በዝርዝር ተወስኗል፡፡

በዚሁ ፈርጅ ውስጥ የተወሰኑ የሥራና የአገልግሎት ሜዳልያዎችም አሉ፡፡ የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ የሥራ ጀግና ሜዳይ (ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ)፣ የከፍተኛ ውትድርና አገልግሎት ሜዳይ፣ የብሔራዊ አገልግሎት ሜዳይ (አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ)፣ የውትድርና አገልግሎት ሜዳይ (አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ)፣ የፖሊስነት አገልግሎት ሜዳይ (አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ)፣ እንዲሁም የአገልግሎት ዘመን ሪባን የሚባሉ አሉ፡፡ ሕጉ የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ታላቅ የክብር ኮከብ ኒሻን፣ የየካቲት 1966 አብዮት ኒሻን (ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ)፣ የቀይ ባህር ኒሻን (ባለሦስት ደረጃዎች)፣ የጥቁር ዓባይ ኒሻን (ባለሦስት ደረጃ)፣ የአፍሪካ ኒሻን (ባለ ሦስት ደረጃ) የሚባሉ የኒሻን ዓይነቶችንም መሥርቷል፡፡ እነዚህ ሁሉ ለማን እንደሚሰጡ፣ የሚያገኘው ሰው የሚኖረው ልዩ መብት፣ የሜዳሊያዎቹና የኒሻኖቹ ቅርፅ፣ መጠንና አካል ምንነት በዝርዝር ተደንግጓል፡፡ የሜዳይና የኒሻን ሽልማት ኮሚሽንም ተቋቁሟል፡፡ ከርዕሰ ብሔሩ ፈቃድ ሳያገኝ ኢትዮጵያዊ የውጭ አገር ሜዳይ ወይም ኒሻን መቀበል የተከለከለ መሆኑም ተደንግጓል፡፡ ይህም የአገር ሕግ ሆኖ እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ዘለቀ፡፡ ደርግ ወደቀ፡፡ ኢሕአዴግ መጣ፡፡

በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን በወታደራዊው ዘርፍ እንኳን የሜዳይ፣ የኒሻንና የሽልማት ጉዳይ የመከላከያ ሠራዊት የ1987 ዓ.ም. አዋጅ ውስጥ የተካተተው በ1990 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በአዋጅ ቁጥር 123/1990 (የመከላከያ ሠራዊት ማሻሻያ አዋጅ) ነው፡፡ በዚህ ሕግ የዓድዋ ድል ሜዳይ የሚባል ወደር የሌለው ጀግንነት በዓውደ ውጊያ ለፈጸመ ኢትየጵያዊ ግለሰብ ወይም የሠራዊት አሃድ ወይም ቡድን የሚሰጥ የመጨረሻ ከፍተኛ የጀግና ሽልማት ሆኖ የተቋቋመውን ጨምሮ የተለያዩ የሜዳሊያዎች፣ የሪባንና የምስክር ወረቀት ሽልማቶች ተመሠረቱ፡

ፖሊስን የሚመለከት የሜዳይ፣ የሪባንና የምስክር ወረቀት ነገር በቀዳማዊ ሕግ ደረጃ (ፓርላማ በሚያወጣው ሕግ) የተነሳው ገና አሁን በቅርቡ በ2004 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 720 ነው፡፡ እሱም ለፖሊስ አባላት የሚሰጡ ሜዳዮች፣ ሪባኖችና የምስክር ወረቀቶች በፌዴራል ፖሊስ መተዳደሪያ ደንብ ይወሰናል ሲል ወሰነ፡፡ በዚህም መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 268/2005 የጀግንነት ሜዳይ (ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ)፣ የላቀ ሥራ ውጤት ሜዳይ፣ የፖሊስ አገልግሎት ሜዳይ (ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ) እና የፖሊስ አገልግሎት ሪባን የሚባሉ የሽልማት ዓይነቶችን አቋቋመ፡፡

አገር ባለውለታነቷን ከምታረጋግጥበት፣ ውለታዎችን ከምትስታውስበትና ለወደፊትም እንዲበረታቱ ከምታደርግበት መንገዶች አንዱ ይህ የሜዳይና የኒሻን ሽልማት ሥርዓት የአገሪቱን ያህል ረዥም ዘመን ያለው ቢሆንም፣ ተከታታይ መንግሥታት እየወረሱ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ባህልና የአገር ሀብት አልሆነም፡፡ ይህ ሳያንስ የተከታታይ መንግሥታት ይህንን የመንግሥት ታላቅ ሥራ የሚከናወንበትን የሕግና የተቋም ጎዶሎ፣ ቶሎና ወዲያውኑ መሙላት አለመቻላቸው፣ በተለይም በዚህ የኢሕአዴግ መንግሥት ዘመን እንደተመሰከረው አወቅነውም፣ አላወቅነውም ብሔራዊ/የአገር ማፈሪያ እየሆነ ነው፡፡ እስካሁን እንደተመለከትነው በኢሕአዴግ/በኢፌዴሪ መንግሥት የመከላከያው ጎን (የፖሊስን ጨምሮ) የሜዳይና የኒሻን ሽልማት እንኳን የተሟላው ከረዥም ጊዜ ግዴለሽነትና ቸልተኝነት በኋላ ነው፡፡ አገር ባለውለታዊነቷን የምትገልጽበትና የምታረጋገጥበት የሲቪል የመንግሥት ሽልማት ሥርዓት ግን ዛሬም ያልተሟላ ጎዶሏችን ነው፡፡

የሚሰማ ስለሌለ፣ ደንገጥ የሚልና የሚደንቀው ሰው ስለጠፋ እንጂ፣ ጉዳዩ በተለይም ጎልቶ የተነሳው የኢትዮጵያ ሚሊኒየም በተከበረበት ወቅት ‹‹ለማይመለስ ውለታህ . . . ›› (የተሟላ ትክክለኛ መጠሪያው ምን እንደተባለ እርግጠኛ አይደለሁም) የሚል ዓይነት አስቀድሞ በሕግ ያልተቋቋመ ሜዳሊያ ስንሰጥ/ሰጠን ስንል ነው፡፡

ከዚያ በፊትና ከዚህ ወዲህም ባለሥልጣኑና ሥልጣን አለኝ የሚለው ሁሉ እየተነሳ ‹‹የከተማውን ቁልፍ››፣ ‹‹የክብር ዜግነት›› ሲሰጥ ዓይተናል፡፡ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የክብር ዶክትሬት አሰጣጥና አጠራርም ጭምር በጣም ግራ የተጋባና መሳቂያ ሆኖ አርፎታል፡፡ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን እነዚህን ቁም ነገሮች የሚገዙ ሥርዓትና አሠራር መዘርጋት፣ ለመንግሥትና ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለምን የቸገረ ነገር ይሆናል፡፡

ያኔ ፕሬዚዳንት ኦባማ በአቶ ኃይለ ማርያም የአስተዳደር ዘመን ኢትዮጵያን ሲጎበኙ በአጋጣሚው ‹‹ማሳሰቢያ›› ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ ኢትዮጵያ ለዜጋም ሆነ ለውጭ ሰው የምትሰጠው የሲቪል ሜዳሊያ ወይም ኒሻን ወይም ሌላ በሕግ የተቋቋመ ሽልማት የሌላት መሆኑ ነበር፡፡ ያ ከሆነ በኋላ ሚያዝያ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ለአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ለባለቤታቸው ‹‹ሜዳሊያ›› እና ‹‹የአገሪቱ ከፍተኛ የክብር ዲፕሎማ›› ሲሰጡ ዓይተናል፡፡ ከዚያም በኋላ አሁን ለዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ለተሰናባቹ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት (ለባለቤታቸውም) ‹‹ኒሻን›› እና ‹‹ከፍተኛ የክብር ዲፕሎማ›› ሲሰጣቸው መስክረናል፡፡

ሽልማቱ በተሰጠበት የሥር ምክንያት ላይ ተቃውሞም ሆነ ክርክር የለኝም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ለአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ስለተደረገው አሸኛኘትና ስለተሰጠው ሽልማት በሐዋሳ በዚያው ሰሞን ባደረጉት ንግግር ውስጥ ያነሱትንና ያቀረቡትን ምክንያት በሚገባ እረዳለሁ፡፡ የአገራችን የለውጥ መንኮራኩር የሚጠይቀው ግራሶ እንዳለም አውቃለሁ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የመንግሥት ወይም የአገር መሪዎች ኒሻንና ሜዳሊያ የመስጠት የአገርን ባለውለታነት በክብር የመግለጽና የማረጋገጥ ትክል ሥልጣን (ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ባይኖር እንኳን) እንዳላቸው አውቃለሁ፡፡ ጥያቄው ግን ኢትዮጵያን የመሰለች ከዚህ በላይ አንደተባለው፣ ‹‹ . . . በዓለም ላይ የሚገኙ የሠለጠኑ መንግሥታት እንደሚያደርጉት ሁሉ) ሳይሆን ለእነሱ ጭምር ትምህርት የሰጠች የተቋቋመ የሚያስቀና (Honour System) የነበራት አገር፣ እንዴት አድርጋ ይህን ጎዶሎ ይዛ ትኑር? እንዴትስ ይህን ዝግጁነት የሚያመለክት ባለሥልጣንና ባለ አገር ትጣ?

ይህ ጎዶሎ በገዛ ራሱ ምክንያት ካለው አሉታዊ ውጤትና ጉዳት ይልቅ፣ ዛሬ በዚህ ጊዜ የለውጥ ተቀናቃኞች ‹‹ሕገ መንግሥት ተጣሰ›› የሚል ዱላ ሆኖ ሲያገለግልም ዓይተናል፡፡

የዴሞክራሲው ለውጥ በደረሰበት ደረጃ ልክ ቆንጠጥና ጠበብ አድርገን በጥንቃቄ እንድንረማመድ መገደዳችን ሳያንስ፣ እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን ዝም ብለን እያየን የለውጡ ተቀናቃኞች የጭቃ ጅራፍ እንዲሆኑ መፍቀድ የለብንም፡፡

የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት በሕግ መሠረት ኒሻኖችንና ሽልማቶችን ይሰጣል (አንቀጽ 71/5)፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚያወጣው ሕግ ወይም በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት ኒሻኖችንና ሽልማቶችን ለፕሬዚዳንቱ አቅርቦ ያሰጣል በማለት ይደነግጋሉ፡፡ ሁለቱም ድንጋጌዎች ውስጥ ‹‹ኒሻኖችና ሽልማቶች››ን በእንግሊዝኛው “Medals, Prizes and Gifts” ብሎ ውንብድብዱን ቢያወጣውም፣ የአገርን ባለውለታነት የማረጋገጥ የክብር ሥራ አስቀድሞ የወጣ ዝርዝር ሕግ የግድ ይፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የውጭ ተሞክሮ መቅሰም ያለባት አገር አይደለችም፡፡ የዓለም ሙዚየሞች የሚያውቁት የተቋቋመ የባለውለታነት ዕዳ መመስከሪያ የሽልማትና የማዕረግ ሥርዓት የነበራት አገር ናት፡፡

አገር በየመስኩ አስተዋጽኦ ላደረጉላትና መስዋዕት ለሆኑላት ወይም ለከፈሉላት ባለውለታነቷን ማረጋገጥ ውለታቸውን ማወቅ፣ ማሰብ፣ ማስታወስና ለወደፊቱም እንዲበረታቱ ማድረግ ያለባት መሆኑ የአገር የውለታ ባለዕዳነት ከሚረጋገጥባቸው መንገዶች፣ ከመስዋዕትነቱና ከአስተዋጽኦው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የሜዳልያና የኒሻን ሽልማት መስጠት እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣም የመንግሥት አሠራር ነበር፡፡ በዚህ በተያያዝነው የዴሞክራሲና የለውጥ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም ከአንድ ሁለት ጊዜ ተሰናባች የአገርና የመንግሥት መሪዎችን በሸኙበት ወቅት ተገልግለውበታል፡፡ ወይም የአገልግሎቱን አስፈላጊነት በተግባር አረጋግጠዋል፡፡ በሚያዝያ 2010 ዓ.ም እና በጥቅምት 2011 ዓ.ም. ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የሚመሩት መንግሥት የአገርን የውለታ ባለዕዳነት ልወጣ ሲል ግን፣ አገር አስቀድሞ የተዘጋጀ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 71(5) እና 74(11) መሠረት ስንዱ ሆኖ የሚጠብቅ፣ በተለይም የሲቪል የሜዳይና የኒሻን ሥርዓት አልነበራትም፡፡ ‹‹የሽልማት፣ የአድናቆትና የአክብሮት ሰርተፊኬት››፣ ‹‹የሻኒን አዋርድና ከፍተኛ የክብር ዲፕሎማ›› ‹‹የአገሪቱ ከፍተኛ የክቡር ዲፕሎማ›› ማለት ዓይነት ‹‹መቀባጠር››ም የመጣው ጉዳዩ የቢሻኝ ውሳኔ በመሆኑ ነው፡፡

የቢሻኝ ውሳኔ የሆነው መሸለሙ አይደለም፡፡ መሸለም የአገርና የመንግሥት ትክል (Inherent) ሥልጣኑ ነው፡፡ ዝርዝሩ ግን በሕግ መደንገግ አለበት፡፡ ከሁሉም በላይ፣ ከሌሎች መካከል በሕግ መደንገግ ያለበት የሽልማት ቅርፅ (በዝርዝር)፣ መጠንና አካል (ወርቅ፣ ወርቃማ፣ ወዘተ) አስቀድሞ በወጣ ሕግ ይወሰናል፡፡ ሜዳሊያና ኒሻን በትዕዛዝ የሚሠራ እንጂ የ‹‹አውርድልኝ›› ዕቃ አይደለም፡፡ መንግሥት ይህን ማስተካከልና ይህንን ጎደሎ መሙላት አለበት፡፡

መንግሥት ይህን ማድረግ ያለበት ከ‹‹አውርድልኝ›› ዕቃ በዕውቅ የሚሠራ ዕቃ ይሻላል ተብሎ ብቻ አይደለም፡፡ በተሻላሚው ሰው አንገት ላይ በአደባባይ ሲጠለቁ የምናያቸው ሜዳይና ኒሻን መሳይ ቁሳቁሶች መጀመርያ የወንጀል ሕግ ጥበቃ የሚያገኙት (ከመንግሥት ፈቃድ ሳይሰጥ ሜዳይ፣ ኒሻን፣ ዓርማና ሪባን መሥራት፣ መጠቅምና አስመስሎ መሥራት ወንጀል) በሕግ ሲወሰን ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ (የመንግሥትና የሃይማኖት መለያዎች ድንጋጌ) ተጣሰ የሚለው ስሞታም ሆነ ክስ የሥር የመሠረት መከላከያም የሜዳዩን ዓይነት፣ ቅርፅና አካል አስቀድሞ በሕግ በመወሰን ነው፡፡

ይህን ጎዶሎ ከመሙላት ጋር ሌላም መፈጸም ያለበት ሌላ ጉዳይ አለ፡፡ በተለያዩ  ዘመናት በየትግል ዘርፉ ባለውለታ ሆነው የተከበሩና የተሾሙ ኢትጵያውያን (የውጭ አገር ዜጎችም አሉ)፣ መንግሥት በተለዋወጠ ቁጥር ባለውለታነታቸው እንደ ቆሻሻ የሚደፋበትና የሚደመሰስበት ያልተጻፈ ባህልና ሕግ አንድ ሊባል ይገባል፡፡     

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

Reporetr Amharic

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?
0Shares
0