28 በሙስና የተጠረጠሩ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሰራተኞች እና በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ 36 የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ሰሞኑን በእነዚህ ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች የቀረቡት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት ነው።

በሙስና ወንጀል እነ ብርጋዲየር ጀኔራል ጠና ቁርዲን ጨምሮ 28 ተጠርጣሪዎች በመዝገብ ቁጥር 225176  የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ቁርጥራጭ ብረቶችን በመሸጥና ለግል ጥቅማቸው በማዋል እንዲሁም ከስኳርና ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ በ21 መዝገቦች የተደራጀ መረጃ ቀርቦባቸዋል።

አቃቤ ህግም ተጠርጣሪዎቹ የግዢ መመሪያን በመተላለፍ ካልቀረቡት ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመመሳጠር፥ ሁለት መርከቦችን በህገ ወጥ ንግድ ማሳተፋቸውን ጠቅሷል።

ከዚህ ባለፈም ለአየሁ ማዳበሪያ ፋብሪካ የመሳሪያ ግዢ ሳይፈጸም ክፍያ እንዲፈጸም አድርገዋልም ነው የተባለው። ከታላቁ የህዳሴ ግድብ የምንጣሮ ስራ ጋር በተያያዘ በዚህ ስራ ላይ ለሚሳተፉ አካላት ክፍያ መፈጸሙንና ክፍያ የተፈጸመላቸው አካላት መሰወራቸውም ለችሎቱ ቀርቧል።

መርማሪ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀ ሲሆን፥ ፍርድ ቤቱም ጥያቄውን በመቀበል ለህዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩት አነ ኖሃ አጽባሃን ጨምሮ 36 ተጠርጣሪዎች በመዝገብ ቁጥር 225177 የጊዜ ቀጠሮ ሊጠየቅባቸው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ኤፍ.ቢ.ሲ

በታሪክ አዱኛ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *