ዛሬ ዛሬ አይናችሁን ላፈር የተባሉ የመንግስትና የድርጅት ሚዲያዎች ተናፋቂ እየሆኑ ነው። ዛሬ ዛሬ ዜና ፍለጋ ዜጎች የባህር ማዶ መገናኛዎችን ፍለጋ ሲባትቱ አይውሉም። ዶክተር አብይ ገና እርካቡን ሲጨብጡ ያሉት ትልቅ ነገር ሜዳውን ማስፋት እና ማራጭ ማብዛት ህዝብ መርጦ እንዲያይ ያደርጋል ነበር ያሉት።

ያሉት አልቀረም ልክ እንደ ሰለጠነው አገር ሚዲያ ዜናዎችን ከቦታው በምስል እያስደገፉ ማቅረብ ችለዋል። ለሚዘግቡት ዘገባም ሲሸማቀቁ አይታዩም። ዛሬ የሆነው ይህ ነው። ይህ ጅምር ተጠናክሮና ይበልጥ ብስለትን አካቶ ከስሜት በመጽዳት እንደሚቀጥል የበርካቶች እምነት ነው።

እድሜ ለመንግስት ሚዲያዎች የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጀነራል ክንፈ ዳኘው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ የማህበራዊ ሚዲያዎች፣ የድረ ገጽ የዜና አውታሮች ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ዜናውን እየተቀባበሉት ነው። ዛሬ ማምሻውን ፋና ባቀረበው ሜቴክን የተመለከተ ዘገባ ስለ ሜቴክ ከተሰማው በተጨማሪ አዲስ መረጃ ቀርቧል። ሜቴክ ልክ እንደ ባንክ ገንዘብ ያበድር ነበር። የህዳሴው ገንዘብ ስራ የቆመው የማንቀሳቀሻ ገንዘብ በመጥፋቱ ነው። ለድጎማ በማስታወቂያ ስም ብር የበሉ ሚዲያዎችና የኪነት ሰዎችም አሉ። ደደቢት እግር ኳስ ክለብም በሚሊዮኖች ደርሶታል።

የአገሪቱን ሃብት ብቻ ሳይሆን ፕሮጀክቶቿን እምሽክ አድርጎ የበላው ሜቴክን ሲመሩ የነበሩት ሜጄር ጀነራል ክንፈ ዳኘው በቅርቡ ለአንድ የዩቲዩብ ቲቪ የሚወራው በሙሉ ውሸት ነው በሚል የሚመሩት ድርጅት ለሌሎች ተቋማት ሁሉ ምሳሌ እንደሆነ ሲናገሩ ነበር። ቀደም ሲል የኢንሳው መሪ የነሩትን ጨምሮ ዶክተር አብይን ሲያንጓጥጡ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ጀነራሉ ወደ ሁመራ ሲያመሩ ተቆርቋሪ ዜጎች የተሳፈሩበትን መኪና ፎቶ በማስደገፍ መረጃ ሲሰጡ ነበር። ይህንኑ መረጃ ተከትሎ ይሁን በመንግስት ክትትል በቁጥጥር ስር መሆናቸው ይፋ ከሆነ በሁዋላ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተጠርጣሪው በሁመራ በኩል ከሀገር ለመውጣት ሲሞክሩ በትግራይ ክልል ልዩ ሀይል ነው አማካይነት መያዛቸውን አስታውቋል። 

 

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

ዳንኤል ብርሃኔ የሚባለው የሆርን አፌርስ መስራች ጀነራሉ ለመንግስት ስራ ወደ ሁመራ እንዳቀኑ መያዛቸውን በፌስ ቡክ ገጹ አስፍሯል። የትግራይ ክልል ልዩ ሃይል ጀነራሉ በሁመራ በኩል ሊጠፉ ሲሉ እንደያዛቸው በይፋ እየተገለጸ ዳንኤል ለመንግስት ስራ ሲል የትኛው መንግስት፣ ለምን ዓይነት ስራ፣ ለምን ተግባር ወደ ሁመራ ሻንጣ አሲዞ እንደላካቸው አላብራራም። የትግራይ ክልልም ልኳቸው ከሆነ መልሶ ሊያስራቸው አይችልም። በቅርቡ በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ በህግ የሚፈለጉ እንዲያዙ አቋም ሲያዝ ህወሃትም ተስማምቶ እንደነበርና ዶክተር ደብረጽዮንም ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ መስማማታቸው የተዘነጋ ይመስላል።

መላው የትግራይ ህዝብ ተነስ ሲል ቀደም ሲል ጥሪ ያቀረበው ዳንኤል ብርሃኔ የአቃቤ ህግ መግለጫ በተለይ የቱርክ ባለሃብቶች በሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ለማካሄድ ያቀዱትንና ኳታር ለመጀመር ያሰበችውን ኢንቨስትመትን ለማኮላሸት ሆን ተብሎ የተደረገ እንደሆነ ፣ ጉዳዩን ከሳዑዲና ከአረብ ኢምሬትስ ጋር የሚገናኝ ተንኮል እንደሆነ በፌስ ቡክ ገጹ አትሟል።

ጀነራሉ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በሁዋላ እንደተሰማው ከሆነ አብዛኞች የትግራይ ተወላጆች “ጀነራል ክንፈ ወንጀለኛ ከሆኑ ይታሰሩ፣ ሌሎችም ወንጀለኞች ካሉ ህግ ፊት ሊቀርቡ ይገባል፣ ከትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን ከሁሉም አካባቢ ወንጀል የሰሩ ሊጠየቁ ይገባል” የሚል አስተያየት እየሰጡ ነው።

Related stories   Ethiopia’s transition misrepresented. Reply to Obang Metho

ጉዳዩን በሰከነ መልኩ የሚከታተሉ ደግሞ ጉዳዩ የሚያስፈነድቅ ሊሆን እንደማይገባ፣ አንድ ሰው በህግ ወንጀለኛ ሳይባል እንደ ቀድሞው አይነት የፍረጃ ስራ መታየት እነደማይገባ ይመክራሉ። አያይዘውም የሚሰማው ሁሉ እጅግ የሚያሳዝንና ወደ ጅምላ ጥላቻ የሚወስድ በመሆኑ መረጃዎችን በአግባቡ አጥፊዎቹን ከሰላማዊ ዜጎች በመለየት መጠቀም እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ።

 

 

 

 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *