“Our true nationality is mankind.”H.G.

ተመከሩ!! “የብሔር አክቲቪስቶች ምናልባት ለመንደር ኤፍ ኤም እንጂ ለሶሻል ሚዲያ አይመጥኑም”

#ተመከሩ

“የብሔር አክቲቪስቶች ምናልባት ለመንደር ኤፍ ኤም እንጂ ለሶሻል ሚዲያ አይመጥኑም” ከጽሑፉ የተወሰደ፡፡

*በዘመነ አብይ ከታዩት ክስተቶች አንዱ ዜጎች ያለምንም መሸማቀቅ ሓሳባቸውን በነጻነት ሲገልጹ መታየታቸው ነው፡፡ ምንም እንኳን በአፈና የቆየ ሕዝብ የመናገር ነጻነቱን ያላግባብ ሊጠቅም የመቻሉ ዕድል የሚጠበቅ ቢሆንም ‘በአዋቂ ነን’ ባዮች የመናገሩ ነጻነት አስከ ‘እናጠፋችኋለንና እናፈርሳለን’ መድረሱ አሳሳቢ ሆኗል፡፡

ጎበዝ! አሜሪካ ያልደረሰችበትን freedom of speech በቅጽበት መጎናፀፋችን አይገርምም?
በየትም ሀገር እንደፈለጉ አፍ ማለቅቅ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ የመጻፍ እና የመናገር ነጻነት ሕጋዊ ገደብ ያለውና የሕግ ተጠያቂነት የሚያስከትል ነው፡፡ 
የግለሰብን ሰብአዊ ክብር ማዋረድ፣ በዘር ይሁን በጾታ ላይ የሚደረግ የጥላቻ ንግግር፣ የጦርነት ጥሪ ፣ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማነሳሳት መሞከር፣ ሀገር ለማተራማስ መንቀሳቀስ የትም ቢሆን በሕግ ያስጠይቃል፡፡ እንኳን ‘ሀገር እናፈርሳለን’ ማለት ቀርቶ ንጉሱንና ቤተሰቦቻቸውን መሳደብ በብዙ አረብ አገራት ክልክል ነው፡፡ 
እነ ታይላንድ ኔዘርላንድም ተመሳሳይ ሕግ አላቸው፡፡ ፖላንድን ብንጠቅስ እንኳን የራሳቸውን መሪ ወደ ፖላንድ የገቡትን የሌሎች ሀገራት መሪዎች ቢሳደቡ እስከ 3 አመት እስር ያስቀጣል፡፡ 
ወዳጄ! በመናገር ነጻነትና በልቅነት መሐል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡

ክፋቱ ይህ መሰል ግድፈት በአብዛኛው የሚፈጽሙት እራሳቸውን የብሔር ወኪልና አክቲቪስት አድርገው የሾሙት ናቸው፡፡ ምክንያቱም በግላቸው ተቃውሞ ቢደርስባቸው ”ይኼው ከእንዲህ ብሔር በመሆኔ ዘመቻ ተከፈተብኝ” በማለት ብሔርን እንደ መሸሸጊያ ይጠቀሙበታል፡፡ የነዚህ አክቲቪስቶች የተንሸዋረረው ቅስቀሳቸው ጆሮ ቢያገኝ ሊፈጠር የሚችል ማህበራዊ ቀውስ ቀላል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን እነ አሉላ ሰለሞን የያዙት “ትግሬዎቹ ከሀገር ይወጡ” እየተባለ ብሎ ሕዝብን ለማመስ መሞከር ፍጽም ኃላፊነት የጎደለውና በሕግ የሚያስጠይቅ ነው፡፡

አክቲቪዝም የራሱ ፖሮቶኮል አለው፡፡ እስቲ መጀመሪያ ጥሩ አክቲቨስት ለመሆን ምን ምን ኳሊቲ ያስፈልገኛል ብሎ ቁመናን ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡

ጥሩ አክቲቪስት ጠጥቶ አይጽፍም፡፡ ግልብና ያልታረመ ስሜት ይዞ፣ በንዴት እየተንተከተከ አይጽፍም፤ አንባቢን አያሸማቅቅም፡፡ የጓደኛቹን አንገት አያስደፋም፡፡ በሳል አክቲቪስት አስቦ፣ አገናዝቦ ይፅፋል፤ ይናገራል እንጂ ከፃፈና ከተናገረ በኋላ አያስብም፡፡ የትኛውንም ሓሳቡን በሰከነና በዲፕሎማቲክ ቋንቋ ያቀርባል እንጂ በግልብና ባልታረመ አንደበት አካባቢን በሰድብና በአሽሙር አያቆሽሽም፡፡ ደግሞም የፈለገ አጀንዳ ቢያራምድ በሚጽፈውም ሆነ የሚያራምደው አቋም ሌሎችን offend አያደርግም፡፡ ጥሩ አክቲቪስት እወክለዋለሁ ለሚለው ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም የሚጨነቅና የሚታመን እንጂ ግለሰባዊ ጥቅሙንና ፍላጎቱን በሕዝቡ ላይ አይጭንም፡፡ እኔ አውቅልሃለው በሚል እብሪት የሌሎች ድምፅ አይደፈጥጥም፡፡

በነገራችን ላይ የብሔር አክቲቪስቶች!. ግደላችሁም ሶሻል ሚዲያ ይቅርባችሁ! ምክንያቱም ሶሻል ሚዲያው እጅግ ሰፍቶባችኋል፡፡ 
የብሔር አክቲቪስቶች ምናልባት ለመንደር ኤፍ ኤም እንጂ ለሶሻል ሚዲያ አይመጥኑም፡፡ ጎበዝ ቀላል እኮ ነው ለፐብሊክ ያቀረብነውን ፖስት ሁልጊዜ ‘የራሳችን ብሔር’ የሆኑ ሰዎች ብቻ ላይክና ሼር የሚያደርጉት ከሆነ ከውቅያኖስ ወጥተን ኩሬ ውስጥ ነን ማለት ነው፡፡ በአንዴ ኩሬም ውቅያኖስም ውስጥ መሆን አይቻልም፡፡

እና ምን ለማለት ነው?! አክቲቪሰቶች ሆነ እራሳችሁን አክቲቪስት ያደረጋችሁ እባካችሁ ፖስት ከማድረጋችሁ በፊት ደጋግማችሁ አስቡ፡፡ የሚታዩ ሁነቶችን accurately ከመግለጽ ባሻገር sensational ለማድረግ አትድከሙ፡፡ 
በዚያ ላይ የፃፋችሁት ሆነ ሼር ያደረጋችሁት ፖስት ጉዳት ካደረሰ በኃላ ፖስቶቻችሁን ተመልሳችሁ በማጥፋት ብቻ ነውራችሁን አትሸፍኑም፤ ያደረሳችሁትንም ጉዳት አያጠፋውም፡፡ ከሁሉ በላይ ላጠፋችሁት በግልጽ ይቅርታ ጠይቁ!!!

በመጨረሻም የምትፈጽሟቸውን ግድፈቶች እዚህ እያመጡ ፖለቲካችሁን ከንቱ፣ የናንተን reputation ዜሮ ማድረግ የሚቻል ቢሆንም ምናልባት ብትታረሙ በሚል ይህንን ጻፍኩላችሁ፡፡

ተመከሩ! ተመከሩ!
#BeSmart!
#WeAreWatching

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ
0Shares
0