“Our true nationality is mankind.”H.G.

” የትምህርት ሂደቱ ሰላማዊ ሆኖ እንዳይቀጥል ፍላጎት ያላቸው አካላትበተማሪዎች መካከል ግጭት እንዲፈጠር እየሰሩ ነው ” አቶ ገዱ

የግለሰቦችን ጸብ የብሄር መልክ በማስያዝ ለትምህርት የሄዱ ተማሪዎች ማንገላታት ተቀባይነት እንደሌለው የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ሰሞኑን በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች እየታዩ ያሉ አዝማሚያዎችን በተመለከተ ለአማራ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ የአካባቢው ህብረተሰብ መልካም አቀባበል እንዳደረገላቸው ጠቅሰው፥ ይህም ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸውን አንዲማሩ የታሰበ እና ህብረተሰቡም ቃል የገባበት ነበር ብለዋል።

ይህንን ተከትሎ በሁሉም የሀገሪቱ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በተረጋጋ መልኩ የመማር ማስተማር ሂደቱ ተጀምሮ እንደነበረም ነው አቶ ገዱ ያስታወሱት።

ነገር ግን የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ ሆኖ እንዳይቀጥል ፍላጎት ያላቸው አካላት ሰሞኑን በተማሪዎች መካከል ግጭት እንዲፈጠር እየሰሩ ነው ብለዋል።

ይህንን ተከትሎም በተለያዩ አካባቢዎች በተማሪዎች ላይ ጉዳት ደርሷል ያሉት አቶ ገዱ፥ በግጭቶቹ ህይወታቸውን ላጡና ጉዳት ለደረሰባቸው ተማሪዎችና የተማሪ ቤተሰቦች በክልሉ መንግስትና በራሳቸው ስም ከፍተኛ ሀዘን እንደተማቸው ገልፀዋል።

ግጭቶቹ የተከሰቱት የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው እና የተረጋጋ የመማር ማስተማር ሂደት እንዳይኖር የፈለጉ ጥቂት አካላት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ መለስተኛ ግጭቶችን ወደ ከፋ የአካል መጉደልና ህይወት መጥፋት እንዲባባስ ግፊት ሲያደርጉ እንደነበረ እንገነዘባለን ብለዋል።

የዚህ እኩይ ተግባር ማሳያም ሰሞኑን በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተው አንዱ ማሳያ ነው ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ገዱ በመግለጫቸው ተናግረዋል።

ብዙ ተማሪዎች በሚኖሩበት ግቢ በግለሰቦች መካከል ግጭት ሊፈጠር ይችላል ያሉት አቶ ገዱ፥ እንዲህ ኣይነት ግጭትን በሰላማዊ መንገድ መፍታት በህግ የሚያስጠይቅ ከሆነም ለህግ ማቅረብ እንጂ የብሄር መልክ አሲዞ ለትምህርት የሄዱትን ተማሪዎች ማንገላታት ተቀባይነት እንደሌለውም አስታውቀዋል።

የግለሰቦችን ፀብ ሆን ብሎ በማቀድ የብሄር መልክ እንዲይዝ በማድረግ ወንድማማች የሆኑ እና ለተመሳሳይ አላማ ወደ ዩኒቨርሲቲ የገቡ ተማሪዎችን የሚያጋጩ አካላት ለህግ መቅረብ መቻል አለባቸው፤ መንግስትም በዚህ ረገድ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል ብለዋል።

ህብረተሰቡም ከተማሪዎች ጎን እና ከመንግስት ጎን በመቆም አጥፊዎችንም ማጋላጥ አለበት ሲሉም ጥሪ አስተላልፈዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች የሰላም፣ የእርስ በእርስ ወንድማማችነት የሚስተዋልባቸው እንጂ የግጭት እና የፀብ ማዕከል እንዳይሆኑ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

አጋጣሚ ሆኖ ግጭቶች ከተፈጠሩም የሚመለከተው አካል በሙሉ በአፋጣኝ ርብርብ ማድረግ እንዳለበትም አስታውቀዋል።

የክልሎችም ይሁን የፌደራል የፀጥታ አካላትም እንዲህ ዓይነት ክስተት ሲያጋጥም በፍጥነት የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው በመግለፅ፤ አጥፊዎችንም በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ ማቅረብ አለባቸው ብለዋል።

በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መግስት ውስጥ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ስራ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ የክልሉ መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን እንደሚሰራም ገልፀዋል።

እያንዳንዱ የህብረተሰብ አካልም ተማሪዎቹን እንደራሱ ልጆች በመመልከት ጥበቃ እና እንክብካቤ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ በመግለፅ፤ በሌሎች ክልል ለሚገኙ የአማራ ክልል ተማሪዎችም ተመሳሳይ እንክብካቤ እንዲደረግ ጥሪ አስተላልፈዋል።

(ኤፍ.ቢ.ሲ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   አሜሪካ ለጊዜው ሲባል የከረመ ሃሳብ ያካተተ መግለጫ አወጣች፤ ምርጫውን በተዘዋዋሪ ደግፋለች
0Shares
0