በረከትና ስብሃት ሃሳብ ክፉኛ ተችተዋል

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜና እሁድ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በሃገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በተካሄደው ውይይት በአቶ በረከት ስምኦንና በሌሎች ምሁራን የመነሻ ፅሁፍ የቀረበ ሲሆን የአቶ በረከትና የአቦይ ስብሃት ሃሳብ ጠንካራ ትችትና ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡


በዚህ ውይይት መድረክ ላይ አቶ በረከት ባለፉት 27 ዓመታት የገዥው ፓርቲ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ሆነው የመሩትን የአቶ መለስ ዜናዊን፣ የአቶ ኃ/ማርያምን ደሳለኝና የዶ/ር ዐቢይን የአመራር ዘመን እያነፃፀሩ ገምግመዋል፡፡ 


በአቶ መለስ አመራር ውስጥ ህግ የተከበረባት፣ ልማት የተሳለጠባትና አመራሩም ጠንካራ የነበረበት መሆኑን ያወሱት አቶ በረከት፤ በአንፃሩ በአቶ ኃ/ማርያም ዘመን “ልፍስፍስ” አመራር የነበረበትና አገሪቱ የኋልዮሽ ጉዞ የጀመረችበት ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡ አሁን ያለውን የዶ/ር ዐቢይ አመራር ደግሞ ህገ መንግስቱን የሚጥስ፣ ህግን ማስከበር ያልቻለና ሰላም የደፈረሰበት ሲሉ ገልፀውታል አንዳችም በጎ ነገር ሳይጠቅሱ፡፡ 


በአቶ መለስና በአቶ ኃይለማርያም የጠ/ሚኒስትርነት ዘመን ቁልፍ ስልጣን ላይ የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን፤ እሳቸው በአመራሩ ውስጥ የነበራቸውን ሚና በግምገማቸው አይጠቅሱም፡፡ 
በትግራይ ዋነኛውን ተቃዋሚ ፓርቲ “አረና” የሚመሩት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ አቶ አብርሃ ደስታ ግን እውነቱ ከአቶ በረከት አተያይ በተቃራኒ ነው ይላሉ፡፡ አሁን  ሃገሪቱ ለገባችበት የሰብአዊ መብት ጥሰትና ለሙስና ቅሌት መሰረቱ የተጣለው በአቶ መለስ አመራር በመሆኑ የሳቸው መንግስት ጠንካራ ነበር ማለት አይቻልም የሚሉት አቶ አብርሃ፤ የሃገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች መነሻም የአቶ መለስ አመራር ነው ብለዋል፡፡ 


በአቶ መለስ ጊዜ በኢትዮጵያ የአፈና ቁጥጥር እንደነበር የሚገልፁት ምሁሩ፤ ስርአቱም በባህሪው አፋኝ ነበር ይላሉ፡፡ ከዚህ አፋኝነቱ የተነሳ ኢህአዴግ የሚፈልገው አይነት ዝምታና ስርዓት ሰፍኖ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ “ስርአቱም የአፈና ቁጥጥርና የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት ውጤት ነበር” የሚሉት የአረናው ሊቀመንበር፤ “አቶ ኃ/ማርያም የተረከቡት አፈናን ነው” ባይ ናቸው፡፡ 

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው


አቶ ኃ/ማርያም አፈናውን በአግባቡ መያዝ ስላልቻሉም፣ ሃገሪቱ አሁን የደረሰችበት የችግር ማጥ ውስጥ ልትገባ ችላለች ያሉት አቶ አብርሃ፤ ለዚህ ሁሉ ችግር ዋነኛ ተጠያቂው ግን አቶ መለስ እንደነበሩ” ይሞግታሉ፡፡ የአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ አመራርን በተመለከተ ከአቶ በረከት ሃሳብ ጋር የሚስማሙት አቶ አብርሃ፤ “በእርግጥም ውጤታማ መሪ አልነበሩም” ሲሉ ያረጋግጣሉ፡፡  


አሁን በዶ/ር ዐቢይ ጊዜ ከለውጡ ጋር አብሮ የመጣ፣ ለውጡን በቅንጅት የመምራትና የህግ የበላይነትን የማስከበር ጉድለት መኖሩን የሚጠቅሱት የአረናው ሊቀ መንበር፤በፖለቲካና በዲሞክራሲው ረገድ ግን በርካታ ለውጦች መምጣታቸውን አልሸሸጉም፡፡ 
“መንግስት ሊገድለኝ፣ ሊያፍነኝ ይችላል የሚል ስጋት በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች መቅረቱን የሚጠቅሱት አቶ አብርሃ፤”በትግራይ ግን ይህ የተለየ ገፅታ አለው” ይላሉ – “አሁንም እንደ ቀድሞው ፖለቲካ በስጋት የሚከወንበት ቀጠና ነው” በማለት፡፡


“አሁን በአገሪቱ የለውጥ ብርሃን ጭላንጭል አለ፤ ይህ የለውጥ ጭላንጭል በጥሩ መንገድ ከተመራ ወደ መልካም ሁኔታ ሊያሻግረን ይችላል” ሲሉም ተስፋ ያደርጋሉ፤ ምሁሩና ፖለቲከኛው፡፡ 
የአቶ አብርሃን ሃሳብ የሚያጠናክሩት የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህሩና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ አቶ ስዩም ተሾመ በበኩላቸው፤ “በትግራይ ለውጡን ሸሽተው የመሸጉ ኃይሎች ተስፋ የቆረጡ ስለሆኑ የሚያቀርቧቸው ትንታኔዎች፣ የድሮው ይሻለናል የሚል ቅኝት ያላቸው እንደሚሆኑ ይጠበቃል” ብለዋል፡፡ 


“የሃገሪቱን ሉአላዊነት ለአደጋ ባጋለጠ የውጪ እዳ የዘፈቀ፣ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀመና በሌብነት የተጨማለቀ ስርአት፣ አሁን ካለው ሃገርን በማዳን ስራ ላይ ከተጠመደ መንግስት ጋር ፈፅሞ ለንፅፅር አይቀርብም” የሚሉት አቶ ስዩም፤”ይሄ ፀረ ለውጥ – እንቅስቃሴዎችን የሚያደርግ ቡድን፣ ተስፋ የቆረጠ በመሆኑ፣ ሃገር ከማተራመስ ወደ ኋላ አይልም” ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ፡፡ 


ከብዙ ዓመታት ስደት በኋላ ወደአገራቸው የተመለሱት የህወሃት መስራች ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ከአቶ በረከት ትንተና ጋር ፈፅሞ አይስማሙም፡፡ “አቶ መለስ አብዮታዊ ዲሞክራሲን አራምዳለሁ ብሎ ዲሞክራሲያዊም አብዮታዊም ያልሆነ፣ የተደናበረ ርዕዮተ ዓለም ይዞ ነው ሀገር ሲመራ የነበረው” ያሉት ዶ/ር አረጋዊ፤ “በዚህም ምክንያት የነበረው ስርአት ፀረ-ዲሞክራሲ ነበር” ብለዋል፡፡  

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል


አቶ መለስ አምባገነናዊ መሪ እንደመሆኑ መጠን፣ በሃገሪቱ የታየው የሰብአዊ መብት ጥሰትና የዜጎች ጭቆና የአምባገንነቱ ውጤት ነው” ይላሉ ዶ/ር አረጋዊ። ቀጥሎ የመጡት አቶ ኃ/ማርያም፤ የመለስን ራዕይ አስቀጥላለሁ፤ ብለው የተነሱ ስለነበሩ የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል ለማለት ያስቸግራል፤ አመራራቸውም ያልተረጋጋና የእርስ በእርስ መተማመን የጎደለው ነበር ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ 
አሁን ለውጡን እየመሩ ያሉት እነ ዶ/ር ዐቢይ ኢህአዴግ ቢሆኑም የሚያራምዱት ሃሳብ ይዘት ግን ፀረ ኢህአዴግ ነው ባይናቸው፡፡ 
“ዲሞክራሲን ለማስፈን ቆርጠው መነሳታቸውን በተግባርም ብዙ ርቀት ሄደው የፖለቲካ እስረኞች በመፍታት፣ በውጭ የነበሩ ፖለቲከኞች ወደሃገር ቤት እንዲገቡ በማድረግ፣ አፋኝ አዋጆችን በማሻሻል … በይዘት ፀረ ኢህአዴግ አቋም ያለው እርምጃ እየወሰደ ያለ ቡድን ነው” ሲሉም በምሳሌ ያስደግፋሉ፡፡
ሌላው አነጋጋሪ የነበረው ጉዳይ በመቀሌው ስብሰባ ላይ አንጋፋው የህውሓት መስራችና መሪ አቶ ስብሃት ነጋ “ዶ/ር ዐቢይ የተመረጡት በአሜሪካኖች ነው” ማለታቸው ነው፡፡ 


ይህ የአቶ ስብሃት ሃሳብ በስም ማጥፋት የሚያስጠይቅ፣ ማስረጃ የሌለው ውንጀላ ነው ይላሉ – ዶ/ር አረጋዊ፡፡ “አነጋገሩ ማስረጃ የሌለው ቀጥተኛ ስም ማጥፋት ነው፣ ዶ/ር ዐቢይንም ሆነ የለውጥ ኃይሉ መሪ አቶ ለማ መገርሳን ወደ ስልጣን ያመጣቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ነው” ያሉት ዶ/ር አረጋዊ፤ ከሙስሊሙ የ“ድምፃችን ይሰማ” እንቅስቃሴ ጀምሮ የነበሩ የህዝብ እንቅስቃሴዎች ናቸው የለውጥ ኃይሉን ወደ ስልጣኑ ያመጣው” ብለዋል፡፡ 
አቶ አብርሃ በበኩላቸው ዶ/ር ዐቢይ በኢህአዴግ ም/ቤት እና ጠቅላላ ጉባኤ መመረጣቸውን ነው የምናውቀው” ይላሉ፡፡ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ሊባል በሚችል መልኩ ጠ/ሚኒስትሩን እንደመረጠ ያስታወሱት አቶ አብርሃ ከዚህ ውጪ አቶ ስብሃት ያሉት ነገር ውሃ የሚቋጥር አይደለም ይላሉ፡፡

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

የአቶ አብርሃን ሃሳብ የሚያጠናክሩት አቶ ስዩም በበኩላቸው፤ የአቶ ስብሃት ንግግር በርካታ ጉዳዮችን የሚያመላክት ነው ይላሉ፡፡ የቀድሞው  የኢህአዴግ አመራር ሃገሪቱን በውጭ ሃገር እዳ በመዝፈቅ፣ ሉአላዊነቷን አደጋ ላይ ጥሎ ነበር የሚሉት መምህሩ፤ በዚህ ሁኔታ ሃገሪቱ በቻይና ብድርና እዳ ተሰንጋ በጭንቅ ላይ በነበረችበት ጊዜ ነው ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን የመጡት ይላሉ፡፡ “ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ሲመጡ አሜሪካኖቹ ወዳጅነታቸውን ማጠናከር የፈለጉት ቻይና በአፍሪካ ሃገራት ላይ የደቀነችውን አደጋ ከራሳቸውም ጥቅም አንፃር በማስላት እንጂ ዶ/ር ዐቢይን ለመደገፍ አይደለም” ብለዋል፡፡ 

“ሃገሪቱን በከፍተኛ የእዳ ጫና ለቻይና ሉአላዊነቷን አሳልፎ ሲሸጥ የነበረ ስርአት፣ አሁን ሃገሪቱን ለመታደግ የሚታገልን መሪ በውጭ ኃይሎች የተመረጠ ብሎ የሚያጥላላበት ሞራላዊ ብቃት የለውም” ሲሉ አቶ ስዩም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ፡፡ 

በዚህ ስብሰባ ላይ የአረና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምዶም ገ/ሥላሴ የሰላ ትችታቸውን ያነሱበት ንግግራቸው በጭብጨባ የመቋረጡ አንድምታ፣ ለውጡን ሸሽቶ መቀሌ የመሸገው ኃይል የተለየ ሃሳብና አስተሳሰብን የማፈን ፍላጎቱ ያለመስከኑን ያመላክታል – ብለዋል ምሁሩ፡፡ ይሄ ሃሳብን አጋችና አፋኝ ኃይል በሃገሪቱ የመጣውን ለውጥ ቢያጥላላ ውሃ የሚቋጥር አይሆንም፤ ለውጡንም የሚገታው አይደለም” ብለዋል – አቶ ስዩም፡፡ 
ለውጡን የሚቃወሙ ኃይሎች አሁን አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸው እርግጥ ሆኗል የሚለው አቶ ስዩም፤ ከዚህ በኋላ በተስፋ መቁረጥ ያልተገቡ የሀይል እንቅስቃሴዎችን ሊያደርጉ ስለሚችሉ መንግስት ሁኔታውን በጥንቃቄ መከታተል አለበት ብለዋል፡፡ 

የአሜሪካ መንግስት በበኩሉ፤በአዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲው በኩል በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫው፤ አቦይ ስብሃት “ዶ/ር ዐቢይ የተመረጡት በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ነው” ማለታቸው መሰረተ ቢስ ውንጀላ ነው ብሏል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ የተመረጡት በኢህአዴግ ም/ቤት፣ በአብላጫ ድምፅ እንደሆነ እናውቃለን ያለው ኤምባሲው፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚካሄደውን የለውጥ እንቅስቃሴ ግን እንደግፋለን ብሏል፡፡ 

አዲስ አድማስ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *