“Our true nationality is mankind.”H.G.

ሕወሓት/ ኢህአዴግን ውኃ ውስጥ እንደገባ “ጥሬ ጨው” የሟሟት ስትራቴጅ!

በአሁኑ ወቅት ዶ/ር አብይ የሚያራምዱትን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በጽሞና ለመረመረ ሰው፤ሰውየው እየተከተሉት ያለው ስትራቴጅ፤ኢህአዴግና ሕወሓትን ወኃ ውስጥ እንደገባ “ጥሬ ጨው” አሟሙቶ የማክሰም ስትራቴጅ መሆኑን አያጣውም፡፡ ሰውየው ይህንን ስትራቴጅ ካስቀመጡ በኋላ፤ወደዚህ ስትራቴጅ የሚያደርሷቸውን ልዩ ልዩ ታክቲኮች ነድፈው ወደ መተግበር ከተሸጋገሩ ሰነባብተዋል፡፡ በዝች ረዘም ያለች ጽሁፌ፤ የሰውየውን እንደ ጨው አሟሙቶ የማዳከም ስትራቴጅ፤የሚከተሏቸውን ስልቶችና የወደፊት ጉዟቸው ምን ሊሆን እንደሚችል፤ ገለልተኛ በሆነ መልኩ የግል ትንታኔየን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
ኢህአዴግ- ሕወሓትን ውኃ ውስጥ እንደገባ “ጥሬ ጨው” አሟምቶ የማዳከም ስትራቴጅ ፡-

ዶ/ር አብይ በግልጽ አይወጁት እንጅ፤በተግባር ግን ኢህአዴግና ሕወሓት የተባሉትን መዋቅሮች፤በግልጽ ከነሱ ጋር ሳይጋጩ/ ሳይላተሙ በዘዴ ግን እያዳከሟ ቸው ነው፡፡ ሕወሓትና ኢህአዴግ የምለው፤ ኢህአዴግ የሚባለው ድርጅት፤ ብአዴን/አዴፓንና ኦህዴድ/ኦዴፓን አቅፎ መኖሩን/አሁንም ያቀፈ መሆኑን በመዘንጋት አይደለም፡፡ ነገርግን እውነቱን ካየነው፤ ቢያንስ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የኢህአዴግ እውነተኛ መገለጫ ሕወሓት ስለሆነ ነው፡፡ ብአዴንና ኦህዴድ “መናጆ” ሆነው ነው የኖሩት፡፡ ለዚህም ነው፤ሕወሓት-ኢህአዴግ የምለው፡፡

ለሁሉም ዶ/ር አብይ ኢህአዴግ-ሕወሓትን እያዳዳከሙት ነዉ። የማዳከም ስልቱም ልክ ውኃ ውስጥ እንደገባ “ጥሬ ጨው” አይነት ነው፡፡ ጥሬ ጨውን ውኃ ውስጥ ስናስገባው እጣ ፋንታውን እናውቀዋለን፡ይሟሟል : ዉስጣዊ ጥንካሬዉም ይዳከማል። በርግጥ ውኃ ውስጥ የገባን ጨው፤ ሙሙት ማፋጠን ወይም ማዘግት ይቻል ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ትነቱ እንዲፈጥን ከፈለግን፤ጨውን በሞቀ ውሀ ውስጥ ወይም፤ ማሟሟያውን ገበታ/ሳህን ውኃ ፀሀይ ላይ ማስቀመጥ ነው፡፡ ይሄ ሁኔታ የመሟሟቱን ሂደት ሊያፋጥነዉ ይችላል፡፡ ውኃ ውስጥ ያስቀመጥነው ጨው ቀስ እያለ እንዲሟሟ ከፈለግን ደግሞ፤ውኃ የያዘውን ሳህን ከፍተኛ ሙቀት በሌለዉ ቦለ ላይ በማስቀመጥ የሙሙትን ሂደት ዘገምተኛ ለማድረግ ይቻላል፡፡ ሁለቱም ዘዴዎች ግን ጨውን ከማሙሟት ወደሁዋላ አይሉም።

ዶ/ር አብይ ሕወሓት-ኢህአዴግን አሟሙተዉ ማጥፋት የፈለጉበት ዘዴ በሁለተኛው መንገድ ነው፡፡ ይሄም ማለት ግልጽ የሆነ ውስጣዊ ግጭት በማይታይበት፤ በጣም ባልሞቀ፤ግን ደግሞ ለብ ባለ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሕወሀትን -ኢህአዴግን በቁሙ መግደል፡፡ በዚሁ አግባብ የሕወሓት-ኢህአዴግን ገመናዎች ወደ አደባባይ በማውጣት ጠቅላላ የድርጅቱን አሰራር ግልብጥብጡን ማውጣት፡፡ ዶ/ር አብይ ሕወሓት-ኢህአዴግን እስከወዳኛው የማሰናበት እቅድ ይዘው እሰሩ እንደሆነ ግምቴ ከፍተኛ ነው (አያያዙን አይተው ሸክሙን ይቀሙታል ነውና)፡፡ ይሁን እንጅ ሰውየው ሕወሓት-ኢህአዴግን የማፍረስ እቅዳቸውን መተግበር የፈለጉት፤ በግልጽ ሳይሆን፤ቀስ እያደረጉ ሕወሓት ተላምዷቸው ኖሩትን አሰራሮች በመቦርበር ነው፡፡ ስለሆነም፤ሰውየው ሕወሀት- ኢህአዴግን አሟሙቶ ለማጥፋት አማራጭ አድርገው የወሰዱት፤አዳዲስ ፖለቲካዊና ህጋዊ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?

ቀጥሎ ባለው ክፍል፤ዶ/ር አብይ ሕወሓት-ኢህአዴግን፤ ስልታዊ በሆነ ዘዴ እንዴት ውኃ ውስጥ እንደገባ “ጥሬ ጨው” አሟሙተዉ እያዳከሙት እንደሆነ በአጭሩ አነሳለሁ፡፡

1. የሕወሓትንና መንግስታቸውን ገመና በግልጽ ማሳጣት፡-

ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን እንደመጡ፤ሳይውሉ ሳያድሩ በዝች አገር ብዙ ግፍ ሲፈጸም መክረሙን፤”አሸባሪ ሆኖ የከረመውም ራሱ መንግስት” መሆኑን በይፋ አወጁ፡፡ በዚህ ሳይገቱ፤በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የከረመውን ሙስናና ሰባዊ መብት ጥሰት በይፋ እንዲወጣና ህዝብ እንዲያውቀው አደረጉ፡፡ አንዳንድ የዋሆች፤ዶ/ር አብይ ይሄንን እርምጃ መውሰዳቸውን፤ በበጎ አይመለከቱትም፡፡ ሰው የራሱን መንግስትና ራሱ የተሳተፈበትን መንግስታዊ ሥርአት፤ እንዴት እንዲህ አጋልጦ ይሰጣል ሲሉም ይደመጣሉ፡፡

ዶ/ር አብይ ግን ይሄንን የሚያደርጉት ሆን ብለው ነው፡፡ ምክንያቱም ለፖለቲካው ሲባል በዝች አገር የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግስትና ኢህአዴግ የተባለ ገዥ ፓርቲ/ ድርጅት አለ ቢባልም፤የአለም አቀፉ ማህበረሰብም ሆነ የአገራችን ህዝቦች የሚያውቁት እውነታ ግን፤በዝች አገር የከረመዉ ሕሓሀት-ኢህአዴግ የተባለ የአንድ የፓርቲ- መንግስት- ሕወሓት-ኢህአዴግ የተባለ አንድ ጨቋኝ ፓርቲ መሆኑንሆ ነው፡፡በዚህ በኩል የኢህአዴግ አባል ድርጅት ለሚባሉት ብአዴንና ኦህዴድ ብዙም ክብደት ሚሰጣቸው አልነበረም ይልቁንስ የሕወሓትን አገዛዝ ቅቡልነት ለማስፈን ይቻል ዘንድ፤በሽፋንነት የተፈጠሩ አስመሳይ ድርጅቶች አድርጎ ሚወስዳቸው ሰው ቁጥሩ ቀላ አይደለም፡፡

ስለሆነም፤ላለፉት አመታት በዝች አገር ተፈጸሙ ለሚባሉ ማናቸውም ችግሮች ትልቁ እዳ ሚወረወረው ወደ ሕወሓት-ኢህአዴግ እንደሚሆን የሚያውቀው ዶ/ር አብይ፤የከረመውን የኢትዮጵያ መንግስትና ኢህአዴግ- ሕወሓት ገመና እንደጉድ ዘረገፈው፡፡ይሄ ሁኔታም በኢህአዴግ-ሕወሓት የሚመራውን መንግስት፤ከድሮውም የከረመበትን የተቀባይነት ችግር፤ወደ ከፍታ በማምጣት፤በተለይም የአገራችን ሕዝብ በኢህአዴግ በተለይም በሕወሓት ላይ የነበረውን የእምነት ማጣት ችግር ከፍ አደረገው፡፡ በዚህ በኩል ዶ/ር አብይ ተሳክቶላቸዋል፡፡ ይሄንን እርምጃ በመውሰዳቸው፤ የድርጅታቸውን ኦዴፓንና የግላቸውን ስእብና እና ተወዳጅነት በእጅጉ መገንባት የቻሉ ሲሆን፤ኢህአዴግ-ሕወሓትን ደግሞ ከመቸውም ጊዜ በላይ በህዝብ እንዲጠላና እንዲነጠል ማድረግ ቻሉ፡፡ ይሄንን ያደረጉት ደግሞ በስልትና በጋራ ውሳኔ መሆኑን ስናይ፤እጅግ እንገረማለን፡፡

2. የሪፎርም ስራዎች ሕወሓት- ኢህአዴግ እንደ “ጨው ማሙቶ ” እንዲዳከ በማድረግ በኩል እየተጫወቱት ያለው ሚና!

ዶ/ር አብይ ሕወሓት- ኢህአዴግን ውኃ ውስጥ እንደገባ ጨው አማሙተዉ ለማዳከም ሌላው የተከተሉት ስልት፤ልዩ ልዩ የሪፎርም ስራዎችን በህጋዊ መንገድ ወደ መተግበር በመሸጋገር ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናስተውሰው፤የሕወሓት የኑሮ ምሰሶና ስልጣን ምርኩዝ ሆነው የከረሙ የተመረጡ መንግስታዊ ተቋማት ነበሩ፡፡ ከነዚህ መካከል፤ መከላከያና ተቋማቱ(ሜቴክን ጨምሮ)፤ ደህንነት፤ ምርጫ ቦርድ፤ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፤ፍ/ቤቶች፤ የፍትህ ተቋማት፤የሚዲያ ተቋማት፤ፓርላማ፤የፌደሬሽን ም/ቤት ወዘተ…ዋናዋናዎቹ ናቸው፡፡

ይሄንን ሁኔታ በደንብ የሚያውቀው ዶ/ር አብይ ፤ስልጣኑን እንደተረከበ ብዙም ሳይውል ሳድር፤ነገሩን ሁሉ እንዳልነበረ አደረገው፡፡ ከላይ ያነሳኋቸውን አብዛኛዎቹን የሕወሓት ምርኩዞች ሰባበራቸው፤ በህዝብ እጅ አስገባቸው፤ በዚህም የሕወሓት ጉልበት ተብረከረከ፡፡ ቢያንስ እስካሁን ባለው ሁኔታ ሕወሓት-ኢህአዴግ እንደፈለገ ሲያሾራቸው የከረሙት ህዝባዊ ተቋማት በተለይም፤-የመከላከያና ደህንነት፤ፍ/ቤትና የፍትህ ተቋማት፤የምርጫ ቦርድ፤ሚዲያ፤ፓርላማ ወዘተ…የመሳሰሉት ወሳኝ ተቋማት ከሕወሓት እጅ ወጥተው በህዝብ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ይሄ ሁኔታ ሕወሓት-ኢህአዴግን ክፉኛ ጎድቶታል፤ገናም ይጎዳዋል፡፡ የህዝብን አቅምና ገንዘብ ተጠቅሞ ተቃዋሚውን ሲያፍን ለኖረ ድርጅት፤ይሄንን አቅም ማሳጣት ማለት በቁሙ እንዲሞት ማድረግ፤ወይም ውኃ ውስጥ ገብቶ ማሙቶ እንዲዳከም ከተፈረደበት ጨው ተለይቶ ሊታይ አይችልም፡፡

Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ

ብቻ በአሁኑ ወቅት፤ዶ/ር አብይ ሕወሓት- ኢህአዴግን በተመለከተ የሚከተሉት ስትራቴጅና የሚወስዷቸው ታክቲካዊ እርምጃዎች፤ሕወሓት-ኢህአዴግን፤በቁሙ እየገደለው ስለመሆኑ የሚጠራጠር ሰው ካለ እሱ የዋህ ነው፡፡

በትላንትናው እለት የጸደቀው፤የማንነትና ወሰን ኮሚሽን አዋጅም አንዱ ሕወሓት-ኢህአዴግን ከጨዋታ ውጭ የማድረግ፤ በህጋዊ መንገድ በቁም የመግደያ ስልት ተደርጎ መወሰድ ይችላል፡፡ ሕወሓት ጣማትም አልጣማትም፤ ህጉ ሕገ-መንግስታዊ አይደለም አለች አላለች፤ሕጉ ስልጣን ባለው አካል ወጥቷልና ህግ ሆኗል፡፡ ሕወሓት በአሁኑ ወቅት በብቸኝነት ሊባል በሚችል ደረጃ በእጇ ከቀሯት ተቋማት መካከል: አንዱ በህዝብ ዘንድ እምነትን ማግኘት ያልቻለው አቅመ ቢሱ የፌደሬሽን ም/ቤት ነው፡፡ ሕወሀት የትላንቱ ህግ ጉዳይ በዚህ ተቋም ነበር እንዲታይ ፈልጋ የነበረው ፤ግን አልሆነም ምክንያቱም ነገሩ ሁሉ “ጨዋታ ፍርስርስ፤ያደረ እንጀራ ቁርስርስ” ሁኗልና፡፡

ነገሩ የገባው ዶ/ር አብይም ቢሆን ይሄ ጉዳይ በፌደሬሽን ም/ቤት እንዲታይ አልፈለገም፡፡ ይሄንን ተቋም ያውቀዋላ! ስለዚህ የትላንቱ ህግ፤ቢያንስ ሕወሓትን በህጋዊ መንገድ አፍ ለማስዘጋት ትልቅ ጉልበት እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ ተግባራዊነቱ ግን እጅግ ውስብስብና ከባድ እንደሚሆን ከወዲሁ መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም ሕወሓት ነገሮችን መፍታ የፈለገችው በጉልበት እንጅ በህግ አግባብ ባለመሆኑ፤ለዚህ ህግ በቀላሉ እጇን ሰጥታ ወደሰላም ትመጣለች ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ጥሩው ነገር ሕወሓትን በህጋዊ መንገድ ለመታገል የሚያስችል ቁልፍ መሳሪያ በጃችን ማስገባታችን ነው፤ሌላው ወሬና ጉራ ትርፍ ነው፡፡ዋናዉ ነገር ህጋዊ መሳሪያዉን በጃችን ማስገባታችን ነዉ።

3. የዶ/ር አብይ ቀሪና እስከ ዛሬ ያልተሳኩ ስራዎቹ ፡

እስካሁን ባለው ሁኔታ( 9ወር) ዶ/ሩ የሰሩት ስራ እጅግ በጣም ጥሩ ነው፡፡ የትላልቱን ማስታወስ ጥሩ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሁኖ አሁንም ግን ዶ/ር ያልነካቸውና ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ፤ሞክሯቸውም ያልተሳኩለት የስራ መስኮች አሉ፡፡ ከነዚህ መካከል፡-

1. የዜጎችን ግጭትና መፈናቀል ማስቆም አልቻሉም፡፡ ነገር ግን ይሄ ሁኔታ አቶ በረከት ሥምኦን እንደዛበረው የደካማ መንግስት መገለጫ/ ምልክት አይደለም፡፡ ችግሩ ዶ/ር አብይ ሁሉንም ነገር በሰላም ለመፍታ ከመፈለግ የመጣ የለዘብተኝነት አቋም ያስከተለው ጣጣ ነው፡፡ ስለሆነም ለዘብተኝነትም ቢሆን ገደብ አለውና፤ዶ/ር ሳይውሉ ሳያድሩ መንግስታቸው ደካማ አለመሆኑን ለነ በረከት፤አቦይ ስብሀትና ኦነግ በግልጽ ቋንቋ ማሳወቅ አለባቸው፡፡ይሄን ማድረግ ካልቻሉ፤ ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ ራሳቸው የነደፉት ሕወሀት-ኢህአዴግን እንደ ጨው አሟሙቶ የማዳከም ስትራቴጅ፤ በራሳቸው ላይ ሊተገበር ይችላ፡፡

Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ

2. አሁንም ወንጀለኞች(ሙሰኞችና ከባድ የሰብአዊ መብትጥሰት ያደረሱ) መጠየቅ በሚገባቸው ልክ አልተጠየቁም፡፡እዚህም ላይ ጠንከር ማለትና ለነ በረከትና ጌታቸው አፋ ብርቱ መልእክት ማስተላለፍ ይኖርባቸዋል፡፡

3. ዶ/ር አብይ አሁንም አንዳንድ ቀሪ የሕወሓት ምርኩዝ ሆነው የከረሙና እስካሁን እጅ ያልሰጡ መንግስታዊ መ/ቤቶችን ከሕወሓት ተጽእኖ ማላቀቅ አለባቸው፡፡ በተለይም የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የፌደሬሽን ም/ቤት(ፓርላማችን ነጻ ወጥቷል) የሚባሉ ተቋማትን ተሎ ብሎ በህዝብ ቁጥጥር ስር ማስገባት ያስፈልጋል፡፡

4. ሕወሀት-ኢህአዴግን ውኃ ውስጥ እንደገባ ጨው አሟሙቶ እንዲዳከም የማድረግ ስትራቴጅ ለምን?

በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ሰዎች የተለያ መልስ ይኖረናል፡፡ ነገሩ ከገባን ግን ዶ/ር አብይ ገና ወደስልጣን እንደወጡ ራእያቸውን ነግረውናል፡፡ ይሄውም ገና በ7 አመታቸው እናታቸው የኢትዮጵያ “7ኛው ንጉስ” እንደሚሆን እንደነገሯቸው፡፡ ዶ/ርም ይሄንን የናቱን ትንቢት እንደ እውነት ወስዶ፤ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ የሚያስችለውን የረዥም ጊዜ እቅድ ነድፎ ሲተገብር እንደኖረ ነግሮናል፡፡ አላማውንም አሳክቷል፡፡ በነገራችን ላይ አንድ የቅርብ ጓደኛው የሆነ ሰው እንዳጫወተኝ፤ ዶ/ር አብይ ከ10 አመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆን፤የሚመርጠው የመከላከያ ሚኒስትርም ከአማራ እንደሚሆን ነግሮት እንደነበር፤ዶ/ር ጠሚ ሆኖ ከመመረጡ በፊት አጫውቶኛል፡፡

ብቻ ዶ/ር አብይ፤ እንዲህ በአገራችን የመንግስት አስተዳር ዘመን ያልተለመዱና አዳዲስ እርምጃዎችን በድፍረት የሚወስደው ለምንድን ነው? የሚል ጥያቄ አንስቸ ስመረምር ያገኘሁት መልስ፤ሰውየው ልክ እንደነ አጼ ምኒሊክና አጼ ቴወድሮስ፤አጼ ዮሀንስ፤ ጀግናዉ አብዲሳጋና ሌሎቹም ባለታሪኮች፤በአገሩ ሲታወስ የሚኖርበትን ታሪክ ሰርቶ ማለፍን ቅድሚያ አድርጓል፡፡ ምኞቱ ስልጣንና በስልጣን መኖር ሳይሆን፤ታሪክ ሰርቶ በታሪክ ሲታወስ መኖርን ነው፡፡

በግሌ ምኞቱ እንዲሳካለት እመኛለሁ፡፡ፈተናዎቹ ግን ከባድ ናቸው፡፡ በተለይም በዶ/ሩ ዙሪያ የተኮለኮሉት የኦሮሞን ልእልና (Hegemony) በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ለማስፈን የሚውተረተሩትን ወንድምና እህቶቹን ተጽእኖ ተቋቁሞ፤ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያን መገንባት ከባድ ሊሆንበት ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ዶ/ር አሁን በያዘው አስደሳችና ኢትዮጵያዊ አቋሙ እስከጸና ጊዜ ድረስ፤ ተባበሪዎቹ ብዙ ናቸውና፤ታሪክ ሰርቶ የማለፍ እቅዱን የማሳካት እድሉ ጎላ ብሎ ይታየኛል፡፡

(ከመለስተኛ ኢዲቲንግ ጋር) (Impartial Analysis- From Bdr.)

Chuchu Alebachew face book

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0