“Our true nationality is mankind.”H.G.

የኦሮሞ ልሒቃን የብዙሃን ተፅዕኖን የማረጋገጥ ጉዞ ?


[አንሙት አብርሐም]

በድህረ-ደርግ ኢትዮጵያ የ’Nation Building’ ሂደት ውስጥ ቋንቋን (ብሔራዊ ማንነትን) መሠረት ባደረገው ፌደራላዊ ስርዓት ተሠርተዋል የሚባሉ አወንታዊ እና አሉታዊ መገለጫዎች ከመሪ ድርጅቱ ኢህአዴግና ከተቃዋሚዎቹ ይነሳል፡፡ 
[ቅድመ ዐቢይ ] ኢህአዴግ፡ “የቅራኔ ምንጭ የነበረውን ብሔራዊ ጭቆና አስወግጀ የማንነት እኩልነትን አስፍኛለሁ፡ ህዝቦችን የሚያስተሳስር ልማትም ማምጣት ጀምሪያለሁ” በማለት አወንታዊ የNation building ስራው አድርጎ ይመለከታል፡፡ 
የስልጣን ፍትሐዊ ውክልናና ተጠቃሚነትን ከፌደራል ስርዓቱ አወቃቀር ጋር በማያያዝ፡ ይበልጡንም ብሔር ተኮር አገራዊ መዋቅሩን የኢትዮጵያ ህልውና ስጋት አድርገው በአሉታዊነት የሚተቹትም የኢህአዴግን መከራከሪያ በተቃራኒው ያዩታል፡፡

ኢትዮጵያን በመሠለ የብዙ ማንነቶች አቃፊ አገር የNation building አቅጣጫና ተግባራት ላይ የተግባባን አገርና ህዝብ አይደለንም፡፡ አሸናፊ ኃይሎች በመሠላቸው መንገድ ጀምረውት በተረኛ ኃይል ሲጨናገፍ የstate formation and state building ጉዳያችን በተቃርኖ ተሞልቶ ቀጥሏል፡፡
አሁን ባለተራው የኦሮሞ ልሒቅ ነው፡፡ [የአማራው ሚና ÷ ከአማራው ጋር የነበረው አጋርነትና መጭው ጊዜ ግንኙነት አንድምታ ለብቻው ይታያል]
ስልጣን የተቆጣጠረው አዲሱ የኦሮሞ ልሒቅ የኢትዮጵያን ‘Nation building’ ለመወሠን የነደፋቸው አቅጣጫዎች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? የሚለውን በዚህ ፅሁፍ አነሳለሁ፡፡

ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታን በተመለከተ የብዙዎች ጥያቄ “የኢትዮጵያ ጉዞ ወዴት ነው?” የሚል ነው፡፡ ዛሬ ይህንን ጥያቄ በተሟላ መልኩ የሚመልስ እምብዛም አይገኝም፡፡ አንድም Disorientation & Diversion የአገሪቱ ርዕሰ መንግስት መገለጫ መሆኑ፡ ሁለትም የአገሪቱም ሆነ የመንግስት ጉዞ የሚታወቅና የሚተነበይ መዳረሻ የሌለው ከመሆኑ ወይም ካለመታወቁ ነው፡፡
የጥያቄው መልስ ፍለጋ መነሻ የሚሆነው፡ ወደ ስልጣን የወጡ የኦሮሞ ልሒቃን ምን ይፈልጋሉ? የሚለውን ከመመርመር ነው፡፡

ለእኔ የሚመስለኝ ግን አቅጣጫዎቹ ፡ በአዲሱ አመራር ቀደም ብሎ ይነሱ ከነበሩ ጉዳዮችና ባለፉት ወራቶች ከታዩ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች በመነሳት የያዝኩት የግል ትዝብት የሚያሳየኝ የአገሪቱም ሆነ ስልጣን የያዘው አካል ጉዞ የኦሮሞን የብዙሃን ተፅዕኖ የማስረገጥ ጉዞ ነው፡፡ በሌላ አባባል በኦሮሞ ልሒቃን ቅኝት በኦሮሞ ቃና የምትመሠረት ኢትዮጵያን መፍጠር ነው፡፡ እንዴት የሚለውን እናያለን፡፡
በአንድ የNation Building አገራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ሊታዩ የሚገባቸው ጉዳዮች ሠፊ ቢሆኑም ልማት ÷ አገራዊ መገለጫ እና የብዙሃን-አናሳ ግንኙነቶችም አሉ፡፡ በድህረ-ደርግ በአዲስ መልክ የተዋቀረችው ኢትዮጵያ አሁን በኦሮሞ ልሒቃን እንደገና የመከለስ አካሄድ ምን ይመስላል? የሚለዉን እንፈትሻለን::
—–
➊ በቅድሚያ ኢትዮጵያዊነት እና የኦሮሞ ልሒቃን አቀራረብ

አሁን የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግስት ስልጣን የያዙት የኦሮሞ ልሒቃን መነሻቸው በዋናነት የኦሮሞው ብሔራዊ ጥቅም አልተከበረም የሚል ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ውስጥ ኦሮሞው የህዝብ ቁጥሩን ያህል÷ የኢኮኖሚ አቅሙን ያህል ÷ ወዘተ…ድርሻና ስልጣን የለውም ከሚል ቁጭት ነው፡፡ የፖለቲካ አስተሳሰብ እና ጉዞ ማዕከሉ ይህ ነው! 
ከታሪክ ፡ ከዛሬ ነባራዊ ሁኔታ እና ከመጭው ጊዜ ሁኔታ አኳያ ነገሮችን የሚመለከተው “የቲም ለማ” የኦሮሞ ሚና መነሻው በኢትዮጵያ የሶስት ሺህ ዘመናት ታሪክ ቢያንስ ደግሞ ባለፉት 150 ዓመታት የሰሜን ሰዎች (አማራና ትግሬ) እየተፈራረቁ የገዟት አገር ነች፡ ኦሮሞው ግን ተመልካች ሆኗል የሚል ነው፡፡
ይህ አተያይ ህወሓታውያን ከአፄ ዮሐንስ በኻላ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት ተመልካች ሆንን (የኢትዮጵያ ታሪክ መሠረት ሳለን-‘በገዛ ዳቧችን’ ተገፋን ) በሚል ከተነሱበት አስተሳሰብ ጋር ይመሳሰላል፡፡ 
ከምንም በላይ ልሒቃኑ ” የኦሮሞ ህዝብ በተጠቂነት አስተሳሰብ (Victim mentality) የተያዘ ÷ በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ከአናሳ ማህበረሰቦች ብዙም የማይሻል የባይታወርነት ስነልቦናና ይስሙላ የሚታይበት ÷ የሽሽት አስተሳሰብ ያልጠፋበት፡ በኢትዮጵያዊነት የምንጠረጠር ÷ በተገንጣይ ፖለቲካ የምንባዝን ÷ ኦሮሚያ እንጂ የኢትዮጵያ ነገር የማይጨንቀን÷….ተደርገን እንሳላለን” የሚል ነው፡፡ “ኦሮሞ አገር መምራት አይችልም እንባላለን” ነው የሚሉት፡፡
አሁን የማዕከላዊ መንግስት ስልጣን ከያዙ በኻላ እንኳ በህግም፡ በአሠራርም የሚነሳን ትችት “ከመጠርጠር እና አይችሉም” ከሚል የሚነሳ አድርገው ይመዝኑታል፡፡

በኦሮሚያ ከሶስት አመታት ወዲህ ንቅናቄውን የጀመረው ‘Team Lemma’ አንድም “የእኛ ተራ ነው: ብዙ ነን ስልጣን ይገባናል” ፡ ሁለትም “ኢትዮጵያዊነትን በማቀንቀን” ነው ወደ ስልጣን ጉዞ የጀመረው፡፡ 
ኦሮሞን “በኢትዮጵያዊነት ከመጠርጠር : ከተገንጣይነት እና የባይታወርነት ስሜት” ለመውጣት መጀመሪያ ራሱ የኦሮሞ ህዝብ ከዚህ እይታና Negative victim mentality እንዲወጣ ነው Team Lemma የሠራው፡፡ “የትናንት ነገስታትን በደል እየቆጠርን ልንኖር አይገባም፡ ኦሮሞ ሌላውንም የሚያቅፍ አካታች ስነልቦና ያለው ነው” ሲሉት ነበር፡፡ 
በመቀጠልም ‘በኦሮሞ ላይ እምነት የለውም’ የሚሉትን ኢትዮጵያዊ ልሒቅ ለማሳመን ኢትዮጵያ አዲስ ግኝት እስክትመስል አብዝተው ተረኳት፡፡ ተወልደው ባደጉባት አገር የታሪክና የፖለቲካ ቅራኔያቸውን አፍነው “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ÷ ኢትዮጵያ ማህፀነ – ለምለም ናት ÷ ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ” አሉ:: ብዙዎችም ይህን እያነቡ መስማታቸውን መሠከሩ፡፡ በተገንጣይነት የሚታማው ኃይል የጠቅላይነት ስሜትን አንፀባረቀ፡፡ ይህ በኦሮሞ ልሒቃን ያልተለመደ አቀራረብ ነው አንዳንዶችን ጉዳዩ “ስሜት ነው እውነት” በሚል እንዲጠራጠሩት ያረገው፡፡
“ቲም ለማ” ያሰቡት ስልጣን ከተሳካም በኻላ በሁሉም ክልል እየዞሩ የየህዝቡን ታሪክና ታላቅነት አብዝተው መሠክረዋል፡፡ እንዳሠቡትም በኢትዮጵያዊነት መጠርጠር ይቅርና የኢትዮጵያ መድህን ተደርገው ተሳሉ፡፡
በዚሁ ላይ በልዩ ልዩ ቅራኔና ወንጀል እስርቤትም፡ ስደትም ላይ የነበሩትን በይቅርታና ምህረት መልቀቅና መመለስ መቻል ተዓማኒነታቸውን በከፍተኛ መጠን የጨመረ ነው፡፡ 

ይህን የኦሮሞ ልሒቃን የኢትዮጵያዊነት ትርክት የተለያዩ አካላት በየራሳቸው መንገድ ተመልክተውታል፡፡

ሀ) ብሔርተኛ ኃይሎች፡- ይህ የኢትዮጵያዊነት ትርክት “አሀዳዊነት ነው ÷ የአማራዉን ኃይል ድጋፍ ለማግኘት የሚደረግ ማስመሠል” ነው÷ የትምክህት ኃይሉን ለማስደሰት ነው÷ ዞሮ ዞሮ የመገንጠል ዓላማውን ለመደበቅ ነው..ወዘተ ” እያሉ ጠረጠሯቸው፡፡

Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?

ለ) በቲም ለማ ክበብ ውስጥም ከቡድኑ ውጭም ያሉ አንዳንድ የኦሮሞ ብሔርተኞች ደግሞ ” ቲም ለማ ኢትዮጵያዊነትን ከደርግ ባልተናነሰ እያሞካሹት ነው ÷ ለስትራቴጂ እንስራበት ያልነውን ጉዳይ ከአኃዳዊያን ብሠው ሠበኩት” የሚል ቅሬታ ያሠሙ ነበሩ፡፡ አንዳንዶችም የጠሚር አብይ አህመድን ”ኦሮሞነት የመጠራጠር እና በአኃዳዊ ኃይሉ ተጠልፏል” የሚል ሃሳብ እንዲያንፀባርቁ ሆነዋል፡፡

ሐ) ወትሮም በድህረ-ደርግ ኢትዮጵያ አዲስ መዋቅርና ይዘት ይዛ በተመሠረችው ኢትዮጵያ ደስተኛ ያልነበረው የአንድነት ኃይል ደግሞ “በTeam Lemma” ትርክት በጣም የተደሠተ ነው፡፡ በድህረ-ደርግ የኢትዮጵያ ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የተነሳ በማስመሠል ከፍተኛ ድጋፍ ቸራቸው፡፡ ብዙዎች የፖለቲካ ድርጅትም ይዘው ከተቃዋሚነት ወደ ደጋፊነት ዞሩ፡፡ ‘ህወሓት መራሹ መንግስት በግል ጎድቶናል’ ለሚሉም ÷ በአገርና ፖለቲካ ጉዳይ ቅራኔ የያዙም፡ የህወሓት አመራር ከማዕከላዊ መንግስት ቁጥጥር በመወገዱ: ይህን ያደረጉ ያሏቸውን የአዲሱን አመራር ግለሰቦች በተለየ አመሠገኑ፡፡ 
የማንነት ፌደራሊዝምን የኢትዮጵያ ህልውና ስጋት አድርገው የሚመለከቱት የዜጋ ብሔርተኞች አዲሱ የኢትዮጵያ አመራር ብሔር ብሔረሰብ የሚባልን አስተዳደራዊ መዋቅር የሚያፈርስ አድርጎም ተስፋ አደረገ፡፡
ከሞላ ጎደል “Team Lemma የኢትዮጵያ ተስፋ ነው” የሚለው አመለካከት መሪዎቹን ከኦሮሞነት ባለፈ እንዲያይ ቢያደርግም፡ ሂደቱ ውስጥ በሚታዩ ተግባራት የሚጠራጠረውም እየጨመረ መጥቷል፡፡

ከስልጣን አኳያ “የእኛ ተራ ነው: ብዙ ነን ስልጣን ይገባናል” የሚለውን ጉዳይ በኢህአዴግ መድረኮች ሲያንፀባርቁ፡ ከድርጅት አሠራርና መርህ የወጣ ፍላጎት ነው በሚል ትችት ውስጥ ቢወድቁም፡ የያዙት ትልቁ ስዕል ታሪካዊ ሚናን የመቀየር ነውና የመርህና አሠራር ጉዳይ ብዙም የሚጎረብጣቸው አልነበሩም፡፡

Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ

በአጠቃላይ የስልጣን ሂደቱ የድርጅት መርህና አሠራር በስፋት ሲጣስ፡ ከዚያም አልፎ በህቡዕ የተደራጀ ወጣት የህግና ስርዓት ፈተና በሚሆንበት ደረጃ በነበረበት ወቅት ሁሉ በኢህአዴግ መድረክ አብረው አውግዘው በጓሮ ይደግፉ ነበር፡፡ ምክንያቱም ለዋናውና ‘የኦሮሞን ሚና በመቀየር፡ በልኩ የምትሠራውን ኢትዮጵያ’ ለመፍጠር ስልጣኑን መያዝ ያስፈልጋል፡፡ 
ለዚህ ዓላማ የትም ያለ የኦሮሞ ልሒቅ በጋራ ተሠልፎ እየሠራ እንደነበር የተረዳ የለም፡፡ “Tokumma Oromo” የትግሉ መርህ እንደነበር ባለቤቶቹ ብቻ ነበሩ የሚያውቁት፡፡ 
እናም የስልጣን ጉዞ ሂደቱን “የቀለም አቢዮት ነው ቢባል፡ መርህ አልባነት ነው ቢባል፡ ኦነግነት ነው ቢባል፡ የውጭ እጅ አለበት ቢባል…” የተፈለገውን ስልጣን ለመያዝ እስከጠቀመ ግድ አልነበራቸውም፡፡ የሆነውም ይኸው ነው፡፡ በ30 ዓመታት የኢህአዴግ ዘመን ታይቶ የማይታወቅ ‘የስልጣን ይገባናል’ ሙግት አንዳንዶቹ ታጋዮች፡ ‘አፍ በእጅ የሚያስይዝ ነውረኝነት’ አድርገው አይተውታል፡፡ እስካሁንም “ምን ጉድ ነው?” ማለታቸውን የቀጠሉ አይጠፉም፡፡ 
እናም አዲሱ የኦሮሞ ልሒቅ :- ኢትዮጵያ የምትባል አገር ኦሮሞውን ያለ ልኩ ያለበሰች ነች ብሎ ÷ ኦሮሞና ኢትዮጵያዊነት አይቃረኑም ብሎ÷ ስልጣን የሚገባኝ እኔ ነኝ ብሎ ነው ስልጣን የጨበጠው ፡፡ ጥያቄው ግን ያች በኦሮሞ አሻራ እንደገና ልትሠራ የተፈለገችው ኢትዮጵያ፡ ሌላውን ‘አቃፊ ነች አግላይ?’ የሚለው ነው፡፡

Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ

[ልማትና ልሒቃኑ÷ ብዙሃን ተፅዕኖን ማረጋገጥ..ይቀጥላል]

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0