“Our true nationality is mankind.”H.G.

የኢትዮጵያና የአካባቢው ፀጥታ (Security) በሽግግር ወቅት (ከዳዊት ወልደጊዮርጊስ)

ለቪዥን ኢትዮጵያ 7ኛ ኮንፈረንስ
አዲስ አበባ ታህሣስ 18-19 የቀረበ የምርምር ወረቀት

ከዳዊት ወልደጊዮርጊስ

መግቢያ

ከሰላሳ ዓመት በኋላ ይህችን የተወለድኩባት፣ እትብቴ የተቀበረባት፣ የተማርኩባት፣ በውትድርና ሙያም፣ በሲቪልም በተለያዩ ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ የታገልኩላት፣ የቆሰልኩላት፣ ወድጄ ሳይሆን ተገድጄ ትቻት ሄጄ የነበረችውን ክቡር አፈር ለመርገጥ ላበቃኝ አምላክና ይህንንም ሁኔታ ላመቻቹልኝ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ምስጋናዬ ታላቅ ነው፡፡ በቀሪ ዕድሜዬ ይህንን እመሰክራለሁ ብዬ አልገመትኩም ነበር፡፡ የዶክተር አቢይን አመራርና ራዕይ እንድንደግፍ  ጥሪ ካስተላለፉት የመጀመሪያዎቹ ነኝ፡፡ Let us Rally around Prime Ministir Abiy በሚል ፅሑፍ  ድጋፌን፣ አድናቆቴን ቀደም ብዬ ገልጫለሁ፡፡ አሁንም አቋሜ ይህ ነው፡፡

በሀገራችን ውስጥ ዘለቄታ ያለው ሰላምና ዕድገት እንዲኖር ይህ ሥርአት መለወጥ እንዳለበት አጠያያቂ ሊሆን አይገባም፡፡ ይህም ማለት ኢህአዲግና ይህ ሕገ መንግሥት ተለውጦ ወደ አዲስ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ካልተሸጋገርን ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም አይኖርም ከሚለው  ፅንሰ ሃሳብ ተነስቼ ነው ይህንን ወረቀት ያዘጋጀሁት፡፡

ዛሬ የምንጣላው ከራሳችን ጋራ እንጂ ከውጪ ጠላት ጋር አይደለም፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ ህልውና በተለየ መልኩ ልዩ የሆነ ፈተና ውስጥ ገብቷል፡፡

ታሪካችን ባህላችን ማንነታችን የማይደግፈው ከጠባብ እውቀት የመነጨ አስተሳሰብ አሁን በሀያ እንደኛው ክፍለ ዘመን ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም ለመላው ዓለምም የሚያሳየው ኋላ ቀርነትን ብቻ ስለሆነ ይህች የታሪክ መሰረት ያላት ኢትዮጵያ ጥሩ አመራር ካላት በአጭር ጊዜ ውስጥ ልታጠፋው ትችላለች::እውነት ጠፍታ ከርማለች፡፡ የሚያድነን እውነት ነው::

ዛሬ ትኩረት እንዳደርግበት የተሰጠኝ ርዕስ “ሴኩሪቲ በአገሪቱና በአካባቢው በሽግግር ላይ ያለው ተጽእኖ” የሚል ነው፡፡ሰፋ ያለ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሸፈን አይደለም፡፡ ዋና፣ ዋና አንኳር የሆኑትን በኔ ግምት አቀርባለሁ፡፡

በአሁኑ ዘመን በአፍሪካ ውስጥ ያለው የጸጥታ ሁከት ካለፈው ዘመን የተለየ ነው፡፡ ፀረ-ኮሎኒያሊዝም ጦርነቶች ወረራዎች  ዛሬ የሉም፡፡ ዛሬ በአፍሪካ የሚታዩ የጸጥታ ችግሮች የመብት ጥያቄዎች፣ የነጻነት ጥያቄዎች፣ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች፣ ከዚሁ ጋር የተያያዙ በአክራሪዎች በተቋቋሙ ንቅናቄዎች የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ናቸው፡፡ እኔ የምሠራበት የምርምር ተቋም የአፍሪካ የጸጥታና የጸጥታ ስትራቴጂ ጥናት ማዕከል (AISSS) ኢትዮጵያን የመሰሉ ሀገሮች በሚያንዣብብባቸው ችግሮች ላይ ጥናት የሚያካሄድ ድርጅት ነው፡፡ ሙሉ ጊዜዬንም በዚህ ላይ ስለማሳልፍ ከብዙ ሰው የተሻለ ግንዛቤ አለኝ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት፣ በአፍሪካ አንድነት ድርጅቶች ንግግርና ስምምነት መሰረት ሴኩሪቲ የሚያተኩረው እንደቀድሞው በመንግሥትና በስርዓት ጥበቃ ላይ ብቻ ሳይሆን በሰውና በማህበረሰብ ላይ ነው፡፡ በእግንሊዘኛ (People Centric) ይሉታል፡፡ በሴኩሪቲ፣ በሰብአዊ መብቶች፣ በእኩልነት በጠቅላላው በእድገት ጥያቄ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ እነዚህ በመጓደላቸው ለሚፈጠረው የጸጥታ ጉድለት በመጀመሪያ ተጠያቂ መንግሥት ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የኢንተርናሽናል ህጎችን ይመለከታል::

የዛሬው ውይይታችን የሚያተኩረው በህዝቦች መሀከል እና በህዝብና በመንግስት መሀከል ስላለው ግጭት እና ጉዳያችን ጉዳያቸው ከሆኑት የጉረቤት ሀገሮች ጋር ስላለው ግንኙነት ነው::

የፀጥታ መደፍረስና የሀገር መሪዎች ሚና

ኢትዮጵያ በሰላም ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር በምትጥርበት በአሁኑ ወቅት፣ ብዙ የጸጥታ ችግሮች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ ከወጣሁ በኋላ ለሃያ አምስት ዓመት በአፍሪካ ጸጥታ በደፈረሰባቸው፣ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ችግሮች  ምክንያት የመንግሥታት አቅም ፈተና ላይ በወደቀባቸው ከሱማሊያ በስተቀር በሁሉም ሀገሮች በአማካሪነት ሰርቻለሁ፡፡ በሩዋንዳ፣ አንጐላ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን ሴራሊዮንና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐ የህዝብ እልቂትን፣ የመንግሥታትንና የሀገር ውድቀትን መስክሪያለሁ፤ ጽፌአለሁኝ፤ ፕሮጀክቶችንም አስተዳድሬአለሁ፡፡ በሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ በሞዛምቢክ፣ ማሊ፣ አይቬሪኮስት ለአጭር ጊዜ ጥናት ሄጃለሁ:: ስለዚህም ካነበብኩት ካዳመጥኩት ብቻ ተነስቼ ሳይሆን የምናገረው በቦታው ላይ ተገኝቼ በመሰከርኩትና ባገኘሁት ልምድ ላይ ተመስርቼ ነው::

በሁሉም ሀገሮች የውድቀት፣ የዕልቂት፣ የጦርነት ዋና ምክንያቶችና ተጠያቂዎች መሪዎች ናቸው፡፡ ምክንያቶቹ የመልካም አስተዳደር ጉድለትና የመሪዎች ሆዳምነት ለህዝብ ፍላጐት ተገዢ ለመሆን አለመፍቀድ፣ ወይንም የህዝብን ፍላጐት ለማወቅ አውቆም ለመረዳት አለመቻል ናቸው፡፡ የሀገሪቱ ታሪክ መጀመሪያም፣ መጨረሻም እኛ ነን ብለው የተነሱ ብዙዎች ነበሩ፡ አሉም::በዓለም ታሪክ ታላላቅ ስህተቶች ተሰሩ የሚባሉት ሁሉ የታሪክ ድግግሞሽ ናቸው፡፡ መሪዎች ካለፈው መማር አለመፈለጋቸው፣ አለመቻላቸው፣ ጤናማ አስተሳሰብን (Reason and common sense ) ለመከተል ፍቃደኛ ባለመሆናቸው የራሳቸው የግል ምኞት፣ ማለትም (Ego) እያሸነፋቸው ራሳቸውን ከሚያስተዳድሩት ህዝብ በላይ በማየታቸው ለእነሱም ለሀገሪቱም ውድቀት ምክንያት ሆነዋል እየሆኑም ነው፡፡

ከክርስቶስ ልደት በፊት በግሪክ ሥልጣኔ ከተጀመረ እስካለንበት ዘመን ያሉን ታላላቅ ስህተቶችን (folly) መርምራ ያቀረበች የታሪክ ሊቅ፣ አዋቂ ባርባራ ቱክማን፣ (The March of folly) በሚለው መጽሐፍ እንዲህ ትላለች፡፡

“A phenomena noticeable throughout history regardless of place or period is the pursuit by governments of policies contrary to their own interests…..why do holders of high office so often act contrary to the way reason points and enlightened self interest suggests? Why does intelligent mental process seem so often not to function?”

  • Misgovernment is four kinds(የተሳሳቱ አስተዳደሮች 4 ዓይነት ናቸው)
  • Tyranny or oppression ( አምባገነነትና ጭቆና)
  • Excessive ambition ( ከልክ በላይ የሆን የስልጣን ጥማት)
  • Incompetence ( የችሎታ ማነስና የትምህርት መዳከም )
  • Folly or perversity ( በትክክል ሁኔታን እለመገመትና ሆን ብሎ በጥፋት መንገድ መሄድ መሪዎች የዚህ ሰለባ ሲሆኑ ሀገር መውደቅና ሰላም ማጣት ትጀምራለች፡፡)

መሪዎች መፈለግና ማቅረብ የሚገባቸው የሚጠይቃቸውን፣ የሚከራከራቸውን፣ ነው፡፡ በታሪክ እንደታየው ብዙ መሪዎች ስህተታቸውን ማወቅ አይፈልጉም፡፡ ቢያውቁም ማረም አይፈልጉም፡፡ ከጊዜ በኋላ ሁሉን ነገር አዋቂ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ አካባቢያቸው በዕውቀትና በተሞክሮ ሳይሆን በሌላ መሥፈሪያ የተመረጡ ሰዎች እንዲሆኑ ሲደረግ በመሪዎች ፍላጐት ብቻ ሀገር ትመራለች፡፡ መከበር ቀርቶ መፈራት ይመጣል፡፡ መፈራት ሲመጣ በአካባቢው ያሉት ባለሙያዎች ሁሉ መሪው የሚፈልገውን እንጂ፣ እውነትን ከመናገር ይቆጠባሉ:: ያለው ሕገ መንግሥት ለእነሱ አገዛዝ መቆየት እንዲያመች ማረምና መለወጥ ይጀምራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ጥሩ ነገርን የጀመሩ መሪዎች መጨረሻቸው አያምርም፤ ከክፋትም ሆነ ከሞኝነት በመነጨ የግል ውሳኔ እየተመሩ ስህተት ውስጥ ይዘፈቃሉ:: የወደዳቸውን ያህል ህዝብ ይተፋቸዋል፣ ይወድቃሉ፣ አገርንም ለጊዜውም ቢሆን ያናጋሉ፡፡ ስለዚህ ነው መሪዎቻችንን በእክብሮት ግን በድፍረት ቀርበን የህዝብን ፍላጉትና ድምፅ ማሰማትና የሚወስዱ እርምጃዎች ሁሉ የተመከረባቸው የአብዛኛውን ህዝብ ፍላጎት ማንፅባረቅ እንዳለባቸው ማስገንዘብ ያለብን:: ከጥቂት ዓመታት በፊት የአፍሪካ Renaissance መሪዎች ተብለው ስማቸው ለጥቂት ጊዜ የገነነው መሪዎች የት እንደደረሱ መገንዘብ ያስተምራል፡፡ ስለዚህም ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ ከነዚህ ሁሉ ትምህርት ለመቅሰም የሚያስችል ዘመን ላይ ስላሉ ይህንን የመሰለ ታሪክን እንደማይደግሙ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡

ለሰላምና ለሀገር ሕልውና አጣዳፊ ተግባሮች

በአገራችን ውስጥ የሰፈነውና የጸጥታ ችግር በህግ የበላይነትን አለመጠበቅ ምክንያት ነው እየተባለ ብዙ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ አሻሽሎ ህዝብ እንደፈለገ መንቀሳቀስና መሥራት አብሮ መኖር እንዲችል የህግ የበላይነት ማስጠበቅ ተገቢ ነው ፡፡ ግን የህግ የበላይነት ሊከበር የሚችለው ህግ ሲኖር ነው::አለ የሚባለው ሕግ የሁሉም ሕጐች ምንጭና መሰረት ሕገ መንግሥት በህዝብ ምክክር (ፓርቲሲፔሽን) ያልተደነገገ ሕግ ስለሆነ፣ አብዛኛው ህዝብ ይህንን ሕግ ነው ብሎ ሊያከብረው አልቻለም፡፡ ሊያከብረውም አይገባውም፡፡ ሕጉ እራሱ ህዝብ ለህዝብ እንዲጋጭ በጥቂቶች ተጠንቶ ከጫካ በመጣ በጥላቻና ከፉፍሎ የመግዛት ርእዪት ላይ የተመሰረተ ነው:: ዛሬ ጥያቄው መሆን ያለበት እንዴት እዚህ ደረጃ ላይ ደረስን ሳይሆን እንዲት እስከዛሬ ህዝቡ ርስ በርሱ አልተላለቀም ነው? ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በርሱ የማይተላለቀው

እግዚአብሔርን ፈርቶ፣ ወይንም ባህሉ፣ የብዙ ዘመናት የአብሮነትና የኢትየጵያዊነት ስሜት ስላሸነፈው እንጂ፣ እንደ ሕግ መንግሥቱ ቢሆንማ  ይህ ህዝብ ከብዙ ዓመታት በፊት ተላልቆ አገሪቱ ተበታትና ነበር::

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አርቃቂ ኮሚቴ አባልና ሕገ መንግሥቱን ያፀደቀው አካል ሰብሳቢ ነበሩ፡፡ የምክር ቤቱም ሊቀመንበር እሳቸው ነበሩ፡፡ ለአዲስ ስታንዳርድ ጋዜጣ በሰጡት ኢንተርቪው ላይ እንዲህ ይላሉ፡፡

That is one of the major points where looking back in retrospect we did not think properly. We knew that there was no proper atmosphere where different parties could organize meetings with their members to discuss on the draft constitution before it became final. That is one of the biggest shortcomings ….እንደገና ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ሌላ ትልቅ የሽግግሩ ፓርላማም ረቂቁን ካፀደቀው በሁዋሏ We should have presented it back to the people of Ethiopia in a form of referendum where the people could have had the chance to decide on whether what we formulated was according to their own wish. That we did not do. I believe it was a mistake…. I fear if something is not done this constitusion will not hold the country together.

ዛሬ የህዝብ ጥያቄ ያ ስህተት ይታረም ነው:: ያ ሬፈረንደም ይካሄድ ነው:: በዚህ ህግ አንገዛም ነው:: ይህንን ታሪካዊ ስህተቶች አርመው የኢትዮጵያ ህዝብ የመከረበት ሕገ መንግሥት እንዲረቀቅና እንዲጸድቅ ነው ጥያቄው::

የኢትዮጵያ ህዝብ ዶ/ር አብይ አህመድን ነው እንጂ፣ ሕገ መንግስቱን ወይም ኢህአዲግን አይደለም የተቀበለው:: ኢህአዲግንማ  ሲዋጋው፣ ሲታገለው ኖረ፡፡ ሕገ መንግስቱንማ የዘር ፖለቲካ ኤትኒክ ፖሊሲ መስርቶ ህዝቡን ሲያፋጀው ነው የኖረው፡፡ ዶ/ር አብይ አህመድን ህዝብ የተቀበላቸው የዘር ፖለቲካን ያጠፋሉ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ያስተባብራሉ፣ ያስማማሉ በሚል እምነት ነው፡፡ ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያ ህዝብ አልመረጣቸውም፡፡ አንድ ፓርቲ ነው የመረጣቸው፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ አንድ ፓርቲ ተመራጭ ሳይሆን፣ እንደ ኢትዮጵያዊ ተመራጭ አድርጐ ነው የተቀበላቸው፡፡

ዶ/ር አብይ አህመድ የአንድ የብሄር ፓርቲ ሊቀመንበር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆናቸው ኃላፊነታቸው እንደሚጣረዝ ያውቃሉ፡፡ ፓርቲው ከፓርቲው መሪነት ቢያነሳቸው ከጠቅላይ ሚኒስትርነትም ይነሳሉ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ታላቅ ሁከት ይፈጥራል፡፡ የብሄር ተወካይ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ተመራጭ ሲሆኑ ብቻ ነው ነው ዶ/ር አብይ ሙሉ ስልጣን ከመላው ኢትዮጵያ ተረክበው ህግን ማስከበር፣ ኢትዮጵያን የዲሞክራሲያዊ የሰላምና የአንድነት ሞዴል አድርገው የኢትዮጵያዊያንን ፍላጐትና የአፍሪካን ምኞት ሟሟላት የሚችሉትና ታሪክ የሚሰሩት፡፡ ሐቁ ግን ይህ አይደለም፡፡

በዚህ ሁኔታ ዶ/ር አብይ የመጀመሪያ ኃላፊነታቸው ለመረጣቸው ፓርቲ ነው ወይስ ለኢትዮጵያ ህዝብ? የሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ ነው፡፡ ዶ/ር አብይ ከዚህ ወጥመድ ውስጥ መውጣት የሚችሉት ራሳቸውን ከፓርቲአቸው ተጽእኖ አላቀው የኢትዮጵያን አጀንዳ ይዘው ሲራመዱ ብቻ ነው፡፡ ይህንንም ማድረግ የሚያስችላቸው ብዙ አማራጭ እንዳለ እሳቸው ያውቃሉ፤ ወይዘሮ መስከረም አበራ ባቀረበችው ፅሁፍ ላይ በፓርሊያመንታሪ ስርአትና ፕሬዚዳንሺያል ስርዓት መካከል አማካኝ መንገድ እንዳለ ጠቁማለች:: ይህንንም ሌላ አማራጭ ለውይይት አቅርባለች ጥሩ የአዋቂ ተመራማሪ ትንተና ነው፡፡እኔ ደግሞ እንድንነጋገርበት የማቀርበው ሐሳብ ዶ/ር አብይ የኢህአዲግን ሕገ መንግሥትና ፓርላማ በአዋጅ እንዲያፈርሱ፣ እሳቸው በአዋጅ በሚሰጣቸው ሥልጣን መሰረትና የጊዜ ገደብ እስከ ምርጫው ድረስ በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲያገለግሉ፡፡ አዋጁ የብሔር የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሳይሆን ሀገራዊ አጀንዳ ያላቸውን ፓርቲዎች ብቻ ተፎካካሪ ፓርቲ እንዲሆን እንዲያውጅ፤ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲን ወደ ኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ለውጠው ሀገራዊ አጀንዳ ይዘው ለውድድር እንዲያቀርቡ፤ የብሔር ድርጅቶች የብሔረሰባቸውን መብት ለማስጠበቅ በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ የሲቪክ ድርጅቶች እንዲሆኑ ነው፡፡ ይህ የሆነ እንደሆን የዘር ፖለቲካ ቀስ በቀስ መጥፋት ይችላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከብሔር ፖለቲካ በላይ የሆኑ መሪ ይሆናሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የሙሉ  የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ ሊኖረው የሚችል የኢትዮጵያ አጀንዳ ይዘው በተጠናከረ ማዕከላዊ መንግሥት ሀገርን መምራት ይችላሉ፡፡ በግርድፉም ይህንን የሚመስል ሐሳብ አቀርባለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው የተለያዩ አማራጮችን መርምሮ ነው አዲስ ስርአት መገንባት የሚቻለው::

በዓለም ውስጥ በዘር ፓርቲ የተመሰረተ የፌዴራል ሲስተም ፈልጌ አጣሁ፡፡ በዘር የተመረጠ ፓርቲ ስልጣን ላይ የወጣ የትም ቦታ በዓለም ውስጥ የለም፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ሶስት አገሮች ናቸው የፌዴራል ስርዓት ያላቸው፤ ኮሞሮስ፣ ናይጄሪያና ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያ ብቻ ናት በዘር፣ በቋንቋ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም ያላት፡፡

ለምንድነው አዲስ ዲሞክራሲዎች በአፍሪካም በሌሎችም አሁጉሮች ቶሎ የሚፈርሱት? በሚለው ጥያቄ ላይ ሁለት ታላላቅ የፖለቲካና የታሪክ ሊቆች በጻፉት ላይ፣ Athoritorianizm and Elite origins of Democracy የሚለውን መጽሐፍ መመልከት ይጠቅማል፡፡ “Over 2/3 of countries that have transitioned to democracy since World War II have done so under constitutions written by the outgoing regimes”

በእብዛኛው እነዚህ ሀገሮች ናቸው ሰላምና መረጋጋት አጥተው ያሉት:: ምክንያቱም ሕገመንግስቱን የቀረፀው ያፅደቀው መንግስት በመሆኑ ነው::  በዲሞክራሲ ስርአት ሕገመንግስት ነው መንግስትን የሚወልደው:: ኢትዮጵያ ይህንን የማድረግ እድልዋ አሁን ነው:: ይህ ጊዜ ካመለጠ ኢትዮጵያ የዘወትር ሽብርና ምንዓልባትም የመበታተን እድሏ ከፍተኛ ይሆናል ብዬ እገምታለሁኝ:: የአገሪቱን ሁኔታ በጥሞና ለተከታተለ ይህ እማራጭ የሌለው መፍትሄ እንደሆነ የሚስማማበት ይመስለኛል፡፡

ለዶ/ር አቢይ ይህንን ማድረግ አስቸጋሪ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ግን ይህንን ውስብስብ ሁኔታ ጥሰው ለመውጣት የአብዛኛው የህዝብ ድጋፍ ይኖራቸዋል፡፡ ይህንን የመሰሉ ሀሳቦችን ይዞ ሕዝብ የሚነጋገርበት፤ ተነጋግሮም የሚስማማበት መድረክ ለመፍጠር እና የሀገርን አቅጣጫ ለመቀየስ ሁለት ጉባኤዎች ያስፈልጋሉ ብዬ አምናለሁ፡፡

  1. 1. የሽግግር ጐባኤ፡- የሽግግር ጉባኤ አስፈላጊነት

ኢትዮጵያ ውስጥ የዘለቄታ ሰላምን ለመመስረት የኢትዮጵያ ህዝብም ከርስ በርስ ግጭት እንዲድን ህልውናውም እንዲጠበቅ የሚያስችል፣ ንድፈ ሀሳብ  የሚቀርጽ፣ ከህዝቡ ጋር ቀጥታ የሚያነጋግር ጉባኤ ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የኢትዮጵያን አቅጣጫ የሚቀይሰው ህዝብ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ዶ/ር አብይ አህመድን የሚያግዝና ህዝባዊ የሆነ አቅጣጫ ሊሰጣቸው የሚችል ጉባኤ በአስቸኳይ መጠራት አለበት፡፡ ሁሉም ብሔረሰቦች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሰብአዊ መብት ጠባቂዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የወጣት ማህበራት፣ አክቲቪስቶች የተወከሉበት ጉባኤ ተጠርቶ የጥቂት ቀናት ወይም እንደ አስፈላጊነቱ የብዙ ቀናት ውይይት አድርጐ አቅጣጫ (Road Map) የሚያሳይ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ መደረግ አለበት፡፡ እዚህ ጉባኤ ውስጥ ለመግባት መመዘኛው በግልጽ የማያጠያይቅ መሆን አለበት፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት፣ በዳር ድንበሯ፣  በህዝቦቿ እኩልነት፣ በዲሞክራሲ ስርዓትና በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ መሆን አለባቸው፡፡ ይህንን የማያሟሉ ድርጅቶች እዚህ አገርም፣ እዚህ ጉባኤም መገኘት የለባቸውም፡፡ አለበለዚያ የሚፈለገውን አጠቃለይ ስምምነት ላይ መድረስ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ይህ ጉባኤ የሚነጋገርባቸው ዋና ዋናዎቹ፣ ህግ መንግሥቱን ስለማረም ወይንም ስለመለወጥ፣ የምርጫ ቦርድን ስለመመስረት የእውነት፣ የእርቅና የፍትህ ኮሚሽንን ስለማቋቋም በሚሉት ርእሶች ላይ ነው:: እነዚህ እባላት የሚመረጡት በመንግስት ሳይሆን በህዝብ ነው:: ይህንን አመራረጥ ዘዴ የሚያጠና ቡድን ማቋቋም የመጀመሪያው ሥራ ሊሆን ይገባል::

Related stories   ‹‹የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠነክራል››

በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚደረስባቸውን ስምምነቶች እንዴት አድርጐ ለህዝብ ማቅረብና ህዝብ እንዲወያይበት ለማድረግ ይህን ጉባኤ የሚቀርጽ አዘጋጅ ኮሚቴ ከመንግሥት ተቋማት ሳይሆን ከህዝብ መካከል ይመረጣል፡፡ ይህ ሁሉ ረጅም ጊዜ ሊወስድ ይችላል፤ ግን ይህ ፕሮሰስ እስከተጀመረ ድረስ ህዝቡ ወዴት አቅጣጫ እንደሚሄድ ስለሚያውቀው ተረጋግቶ የእለት ኑሮውን ሊቀጥል ይችላል፡፡

  1. 2. ሁለተኛው ጉባኤ

የሰው ልጅ ኑሮ ከእግዚአብሔር ሕግ ባሻገር በሀገራዊና በኢንተርናሽናል ሕግ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ መንግሥታት በሀገራቸው ውስጥ በተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ፣ ወንጀለኞችን ህግ ፊት ለማቅረብ ይገደዳሉ፡፡ ይህንንም ለማድረግ አቅም ከሌላቸው ወይንም ሁኔታው የማያመች ከሆነ ገለልተኛ ለሆኑ አቅሙ ላላቸው የኢንተርናሽናል ፍርድ ቤቶች ወይም ትሪቡናሎች ያቀርባሉ፡፡ እንደ Hague, ICC, Tribunal በሩዋንዳ ጉዳይ ላይ አሩሻ ላይ የተቋቋመ ኢንተርናሽናል ትሪቡናል ምሳሌ ነው፡፡ በላይቤሪያና በኬንያ፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ ለደረሰው ግፍ ተጠያቂ የሆኑ ወደ ICC ተልከዋል፡፡ አሁን በባለፈው ዘመን የተፈጠረ አዲስ ሀሳብ (transitional justices) ወይም የሽግግር ፍትህ (restorative justices)  በተወሰኑ የአፍሪካ ሀገሮች ተሞክሯል፡፡ ይህም የመጀመሪያው የሀቅ፣ የዕርቅና የፍትህ ኮሚሽንን በማቋቋም ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ካልሆኑና ብዙ ኢሰብአዊ ድርጊቶች ከፈጸሙ ስርዓት ወደ ዲሞክራሲያዊያና ሰላማዊ ስርዓት ለመሸጋገር ብሔራዊ ዕርቅና መረጋጋት ያመጣል ተብሎ በብዙ ታዛቢዎችና አዋቂዎች ታምኖበታል፡፡ መንግሥት የጥፋቱ አካል ሆኖ፣ ተጠያቂ ሆኖ የጥፋቶች ሁሉ የበላይ ተመልካች ሆኖ ራሱ ይህንን አይነት ኮሚሽን ሊያቋቁም አይችልም፡፡ ትርጉምም አይኖረውም፤ ይህ አሰራር ከአፍሪካ ውስጥ ሶስት አገሮች ውስጥ ተሞክሯል፡፡ በመጀመሪያ ደቡብ አፍሪካ፣ ከዚያም ሩዋንዳና ላይቤሪያ በሶስቱም ሀገሮች ሰርቻለሁ፡፡ የሶስቱንም ሀገሮች የኮሚሽን የስራ ውጤት በቅርብ ተከታትያለሁ፡፡ ይህ አሰራር የሚያጠቃልለው አራት ነጥቦችን ነው፡፡ በወንጀል መጠየቅ(Criminal prosecution) እውነትን ፍለጋ (Truth seeking) ካሳ የመክፈል (Reparations) አዲስ ህጉችን(Reform laws) ስለማውጣት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ (Prescriptive) ወይም ቋሚ የሆነ የአሠራር ሕግ ሣይሆን መንፈሱን ያዘለ ከሀገሩ ባህልና ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተዛመደ አሰራር እያንዳንዱ ሀገር መፍጠር ይኖርበታል፡፡

ኢትዮጵያን ወደፊት የሚያራምዳት ፍትህና ብሔራዊ እርቅ ነው፡፡ ብሔራዊ እርቅ ያለእውነት ሊኖር አይችልም በማናቸውም ወገን የተፈጸመው ግፍ ጥርት ብሎ መውጣትና መነገር አለበት፡፡ ያጠፉ ሰዎች በይፋ መውጣት አለባቸው፡፡ በዳይና ተበዳይ ፊት ለፊት መተያየት አለባቸው፡፡ የተበደለውም ካሳ ሊያገኝ ይገባል፡፡ አለፍትህና አለእውነት እርቅ አይኖርም በሚለው  ጽንሰ ሐሳብ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

በደቡብ አፍሪካ በቢሾፕ ዴዝሞንድ ቱቱ ይመራ የነበረው ትሩዝ ኤንድ ሪኮንሲሌሽን ኮሚሽን ለብዙ ዓመታት በይፋ ተካሂዷል፤ ውጤቱ አከራካሪ ነው፤ አብዛኛው ህዝብ አውነቱ በሚገባ አልወጣም፣ ፍትህም አልተሰጠም ይላል፡፡ ስለዚህ ነው ዛሬ የአፓርታይድ ውርስ በሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ያልተገፈፈው፤ የርስ በርስ ጥላቻ በሀገሪቱ ውስጥ በእኩልነት ለመኖር የሚያስችል ሁኔታ ኮሚሽኑ አላመቻቸም እየተባለ የሚነገረው፡፡ የደቡብ አፍሪካ ህዝብ እንደተከፋፈለ ነው፡፡ በሶስቱ ዋና ህብረተሰቦች መካከል ያለው ግንኙነትና የሚያነጋግር ጥላቻ ገና ብዙ ጊዜ ይቀረዋል፡፡ እንደታሰበው በዳይና ተበዳይ ኮሚሽን ፊት ቀርቦ ለምን ያን ሁኔታ እንደተፈጸመ ተነጋግረው፣ ተላቅሰው፣ በኋላም ተባርከው በሰላም ይኖራሉ የሚለው ግምት ብዙ አከራክሯል፡፡ ምክንያቱም የአፓርታይድ መሪዎች ኢሰብአዊ ድርጊቶች በፈጸሙት ላይ ፍትህ አልሰጡም፡፡ ለተበዳዮችም ካሳ አልተሰጠም፤ ሁሉም እውነት አልወጣም የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከአፖርታይድ በኋላ በነጻዋ ደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ፕሬዝደንት የMr Nelson Mandela ባለቤት የነበሩት  ወ/ሮ ዊኒ ማንዲላ የባለቤታቸውን ውሳኔና ይህንን አሰራር አውግዘዋል::

ወ/ሮ ዊኒ ማንዴላ ሲናገሩ እንዲህ አሉ “look at the truth reconciliation shared He should never have agreed to it what good dose a truth do how does it help any one where and how their loved once were killed and buried”

ከሀያ ስምንት ዓመት በፊት ያከተመው  የአርባ ሶስት ዓመታት የአፓርታይድ ስርአት ቁስልና መከፋፈል አልተፈወሰም፡፡

ላይቤሪያም ነበርኩኝ፤ በኮሚሽኑ ብዙ ስብሰባዎች ላይ ተገኝቻለሁ፡፡ ባጠቃላይ ከባድ ግፍ ፈጽመዋል የተባሉት አንዳንዶቹ በህዝብ ተመርጠው አዲስ መንግሥት ውስጥ ገቡ፡፡ ሌሎቹም በተፈጸመው ግፍ የሚጠየቁት ከተለያየ አቅጣጫ ድጋፍ ስላገኙ ትሩዝ ኤንድ ሪኮንሲሊዬሽን ኮሚሽን በአስራአራት ዓመት ውስጥ ለሞቱት፣ ለተሰደዱት፣ ለተቆራረጡት፣ ለተሰቃዩት እና ለቤተሰቦቻቸው ፍትህም፣ እርቅም ሳያገኝ ካሳም ሳይከፈል በብዙ መቶ ሺህ ገጾች የሚቆጠር ሪፖርት አቅርቦ ተበትኗል፡፡ የላይቤሪያ ችግር ኮሚሽኑን ያቋቋመው መንግሥት ስለሆነና የመንግሥቱ አባሎች አብዛኞቹ በወንጀሉ የሚጠየቁ በመሆናቸው ህዝቡን የሚያሰባስብ፣ የሚያቀራርብ፣ የሚያስታርቅ ባለመሆኑ ፋይዳ የሌለው ሙከራ ነበር:: የኢትዮጵያ ጉዳይ ይህንን አቅጣጫ የያዘ ይመስላል፡፡

ሩዋንዳ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ከተገደሉ በኋላ የመጀመሪያውን የዩናይትድኔሽን አርዳታ ሰጪ ቡድን የመራሁት እኔ ነበርኩ፡፡ ሬሳዎች ሲለቀሙ፣ ሲሰባሰቡ አገሪቱ ከባድ ትርምስ ውስጥ ላይ ሆና የሩዋንዳ ፓትሪዮቲቭ ፍሮንት(Ruwanda Patrotive Front) አገሪቱን ለማረጋጋት በሚሞክርበት ጊዜ እዚያው ነበርኩ፡፡ ሩዋንዳ ከዚያ እልቂት በኋላ ህዝቡን አንድ ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርጋለች፡፡ እነዚህ ብዙ የተለያዩ ቅን ሙከራዎች፣ ህዝቡን አረጋግቶ ወደ እርቅ ጉዞ ማሸጋገር ተችሏል፡፡ እርቅ በአንድ ቀን በጥቂት ዓመታት የሚመጣ አይደለም፡፡ ጉባኤ ላይ ተገኝቶ በማጨብጨብና በመተቃቀፍ፣ በመላቀስ የሚፈታ አይደለም፡፡ ጊዜ፣ ጥረት፣ ትዕግስት እና መልካም አስተዳደር ይጠይቃል፡፡ በሩዋንዳ ጉዳይ ላይ እውነት ወጥቷል:: ያልተነገረ እውነት የለም፡፡ ከፍተኛ ወንጀል የሰሩ በአገር ውስጥ ፍርድ ቤትና በአሩሻ ትሪቡናል(Arushia Tribunial) እንዲሁም በሄግ(Hague) ፍርድቤት ቀርበው ፍርድ አግኝተዋል፡፡ በመካከል ላይ የሚገኙ ገዳዮች፣ አጥፊዎች፣ ተባባሪዎች በህብረተሰቡ ውስጥ ተቀላቅለው እንዲኖሩ፣ ጋቻ በሚባል ባህላዊ ስርዓት ህብረተሰቡ የእያንዳንዱን አጥፊዎች ወንጀል እየተመለከተ የሚቀጡበትንና ወይንም ከህብረተሰብ ውስጥ ተቀላቅለው የሚኖሩበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡ አጥፊዎች ብዙ ስለነበሩ፣ ተበዳዮችም ብዙ ስለነበሩ የሀገሪቱን አንድነት ለማስከበር ሀገሪቱ በአንድነት ወደ እድገት እንድታተኩር እነዚህ የተለያዩ እርምጃዎች በመወሰዳቸው ዛሬ ሩዋንዳ በእድገት ከፍተኛ እምርታ አስመዝግባለች፡፡ ቁስሉ በቀላል የሚረሳ ስላልሆነ በጥንቃቄ ተይዞ ብዙ መሻሻል አሳይቷል::

የኢትዮጵያ ሁኔታ በመጠንም በአይነትም ከዚህ ጋር የሚወዳደር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በግልጽ የወጡ ወንጀሎች ተፈጽመዋል፡፡ በቅርቡ እንደተፃፈውና በይፋ በሚዲያ እንድተገለፀው መንግስት በህዝብ ላይ የፈፀመው በደል በጣም ዘግናኝና አስቃቂ ነበር:: ብዙ ጊዚያት በፅሁፍም በንግግርም ኢትዮጵያ እንደ ሩዋንዳ እንዳትሆን መጠንቀቅ አለብን ስል ብዙ ሰው እሹፎብኛል:: ” የኢትዮጵያ ህዝብ እንደዚህ ያለ ጨካኝ አይሆንም:: ባህል፣ ታሪክና እምነቱ ይህንን እንዲያድርግ እይፈቅድለትም ” ይሉኝ ነበር:: ህግና አመራር ሲጠፋ የባህልና የእምነትን መስመሮች አልፎ በስው ውስጥ ያለ ክፋት ገሀድ ይወጣል:: ማን እንደዚህ ያሉ ድርጊቶች በአገራችን ይፈፅማል ብሎ አስቦ ያውቃል? በህብረተሰቡ መካከል ዘርን አስመልክቶ ብዙ መፈናቅል፣ ብዙ የጥላቻ ዘመቻ፣ ብዙ ተነግሮ የማያልቁ ወንጀሎችና ጭካኔዎች ተፈፅመዋል:: እነዚህ ሁሉ በህዝብ መካከል በቀላሉ የማይሽሩ የአካልና የስነልቦና ጉዳቶች አድርሰዋል፡፡ ህዝቡም ተባብሮ፣ ተቻችሎ እንዳይኖር እንቅፋት ሆነዋል፡፡ እውነቱም አልታወቀም፤ እውነቱን ከውሸት አጥርቶ አውቆ ከፍተኛ ወንጀል የፈጸመ ፍርድ የሚያገኝበት ቀላል፣ ወንጀል የፈጸሙ ወይንም ተባባሪ የነበሩ፣ ጥላቻ ያሰራጩ ሁሉ በተበዳዮች ፊት እውነቱን ተናግረው በዳይና ተበዳይ ይቅርታ ሰጪና ይቅርታ ተቀባይ አብረው ሆነው ኢትዮጵያን ለመገንባት ብሔራዊ የእውነት፣ የይቅርታና የፍትህ፣ ከመንግስት ነፃ የሆነ ኮሚሽን መቋቋም አስፈላጊነቱ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ ይህንን ሊያደርግ የሚችል ግን ኢህአዴግ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ራሱ ተጠያቂ ስለሆነ፡፡ እነዚህ የተፈፅሙት ብዙ ወንጀሎች ጥፋቶች በስርአቱ ተቋማት የተፈፅሙ እንጂ በግለስብ የተፈፀሙ አድርጎ ማቅረብ ትልቅ ስህተት ነው:: እያድበሰበሱ ማለፍ ችግሮችን ማካበት ነው:: ስለዚህ የመጀመሪያ ተጠያቂ ይህ መንግስት ነው:: ይህ መንግስት ከሳሽም ተከሳሽም ሊሆን አይችልም:: ፍትሃዊ ሥርዓት ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው የስርአት ሽግግር ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ሰላምም በመላው ኢትዮጵያ ሊስፍን የሚችለው ለግጭት ምክንያት የሆኑት ተጠይቀው እውነት ሲወጣ፣  ካሳ ሲከፈልና ፍርድ ሲሰጥ ብቻ ነው::

ወጣቱ ትውልድ

ይህንን ለውጥ ያሽከረከረው ታላቁ ሞተር ወጣቱ ትውልድ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የመምራት ኃላፊትም፣ ብቃትም ሊኖረው የሚገባው ወጣቱ ነው፡፡ ታላቁ ፈላስፋ አርስቶትል እንዳለው፣ “ወጣቱ ተስፋ ለማድረግ ስለሚጣደፍ ስህተትም ይሰራል፤ በቀላሉም ይታለላል (youth is easly decived because it is quick to hope)”

ወጣቱ ትውልድ ለኢትዮጵያ እድልም ነው፣ ስጋትም ነው፡፡ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሎ የኢትዮጵያን ህዝብ እዚህ አድርሷል፡፡ ነገር ግን ባለመማር፣ ባለማወቅ፣ ባለማንበብ፣ በስሜት በመገፋት፣ አውቆም ሆነ ሳያውቅ ከኢትዮጵያ አንድነት ውጪ ሌላ አጀንዳ ባላቸው የብዙዎች መሳሪያ ሆኗል፡፡ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በተጠና መንገድ ሲሰራጭ በነበረው የመንግሥት ፕሮፖጋንዳ በመታለሉ የአጥፊ ተልእኮ ያላቸው ለፈጠሩት ሐሰት ታሪክ የተጋለጠው ወጣቱ  ነው:: በዚህ ሁኔታ ላይ የሚገኘውን የወጣቱን አንድ ክፍል ወደ ኢትዮጵያ አጀንዳ ለመመለስና ገንቢ እንጂ አፍራሽ እንዳይሆን የሰላምና የአንድነት ዘብ እንዲሆን ብዙ ትግል ይጠይቃል፡፡ በትምህርት ቤት ከሚሰጠው መደበኛ ትምህርት ውጪ ለወጣቱ በያለበት ስለሚሰጠው ትምህርት አዲስ ስትራቴጂና ተቋማት መፈጠር አለባቸው፡፡ ካድሬዎች፣ አክቲቪስቶች አሰባስቦ በየቦታው በየቦታው ኢትዮጵያዊነትንና የጋራ ባህሎችን እሴቶችን፣ ስነምግባሮችን ለመስጠት ታላቅ አብዮታዊ ዘመቻ(Revolutionary Campain) ለመስጠት የሚያስችል ታላቅ የረዥም ጊዜ ዘመቻ (Revolutionary Campain) መከፈት አለበት፡፡ ይህ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የብሔረሰብ ድርጅቶችን ትብብር ይጠይቃል፡፡

በ2018 ዓ.ም. አልሙንዲ ኢንዴክስ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞግራፊ ከ0-14፣ 43.4%፣ ከ15-24፣ 20.11%፣ ከ25-54፣ 29.58%፣ ከ55-64፣ 3.9% ከ65 በላይ 2.8% ነው የህዝቡ አከፋፈል፡፡ ይህ የሚያሳየው ምንድነው፣ 64% የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ እስከ 24 ዓመት ህጻንና ወጣት መሆኑን ነው፡፡ ከዛሬ 27 ዓመት ጀምሮ ከሰባት ዓመት በላይ የሆኑት ከ 10 እስከ 54 ያሉት ብቻ 70% በኢህአዴግ ጊዜ ያደጉ የተማሩ የሰሩ ወጣቶች ናቸው፡፡ ዛሬ 54 ዓመት የሆኑት የኢህአዴግ ሲገባ 27 እድሜ ስለነበራቸው ወጣቶች ነበሩ፡፡ በስራም ሆነ በትምህርት ዓለም ኢህአዴግ የዘር ፖለቲካ የተበከሉ፣ ወይንም የተጎዱ፣ ወይንም የተጋለጡ ናቸው፡፡ ይህ አስደንጋጭ ነው፡፡ አብዛኛው ሥራ አጥ እዚህ ውስጥ ይጠቃለላል፡፡ አብዛኛው የታሰረ፣  ወንድሙ፣ እህቱ፣  የቅርብ ዘመድ የታስረባቸው፣ የተገደለባቸው፣ በተለያዩ መንገዶች የተጠቁ ሁሉ እዚህ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ይህ ህዝብ በጣም የተቆጣ ህዝብ ነው:: ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያን ወደ ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገር ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ ነው፡፡

በተባበሩት መንግሥታት (UNFPA) ጥናት መሰረት፣ በ2050 ከ0-24 ያለው ትውልድ ብዛት አፍሪካ ወስጥ በ50% ይጨምራል፡፡ በ2050 አፍሪካ በወጣት ህዝብ ብዛት ታላቋ አህጉር ትሆናለች፡፡ ከ18 ዓመት በታች ካሉት ወጣቶች በዓለም ውስጥ ከሰላሳዎች አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት በ2050 መቶ ሰማንያ ስምንት ሚሊዮን አራት መቶ ሃምሳ(188,450,000) ሺ ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡ ከናይጄሪያ ቀጥሎ በአፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ሀገር ሆና ትቀጥላለች ማለት ነው:: ኢትዮጵያ ዛሬ ከ18 ዓመት በታች ያለው ህዝብ ብዛት 48.7% ከሠላሳ ዓመት በኋላ ይኸው ትውልድ ከሚወልዳቸው ልጆች ጋር ተደምሮ ምን ዓይነት ደሞግራፊ እንደሚኖር ስንረዳ አሳሳቢነቱ ግልጽ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በዚያን ጊዜ የ72 ዓመት ዕድሜ ላይ ይደርሳሉ፡፡ በጡረታ ዘመናቸው ይህንን የመሰለ መድረክ ላይ ወጥተው ዛሬ ስላዘጋጁት ወይንም ስላላዘጋጁት ወጣት በጸጸት ወይንም በኩራት የሚናገሩበት ወቅት ይመጣል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ዛሬ እንደምናውቃት ትቆያለች በሚል ግምት ነው::

ያልተማረ፣ ስራ የሌለው፣ ማንበብ፣ ማዳመጥ፣ የማይፈልግ፣ የማይችል፣ ሁሉን የሚያውቅ የሚመስል፣ እውቀትን የሚያጣጥል፣ ከማናቸውም ወገን በሚነዛ ወሬ እንዳመቸው የሚዋዥቅ ወጣት በበረከተ ቁጥር የኢትዮጵያ ሴኩሪቲ ስጋት እየከረረ ይመጣል፡፡ እያደገ በሚመጣው ሥራ አጥነት ድንበር አቋርጦ የሚሄደው ቁጥር ብዛት ሌላ አማራጭ በማጣት ሽብርተኞች ሰፈር በመግባት(Rdicalization) በሰውና በመሳሪያ ሕገ ወጥ ትራፊክ ውስጥ በመሳተፍ የአካባቢውም የሀገሪቱም  የጸጥታ ችግሮች ምንጮች የሚሆኑት የዛሬዎቹ ወጣቶች ስለሚሆኑ፣ በሰውና በሰው ኃይልና ላይ ከባድ ኢንቨስትመንት (በማስተማር፣ በማሰልጠን፣ በማደራጀት) ካልተደረገ የኢትዮጵያና የአካበቢው ጸጥታ ወደ አልታወቀ አደገኛ ሁኔታ ያመራል፡፡

ህገወጥ የመሣሪያ ዝውውር

የህገወጥ መሣሪያዎች እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ውስጥ እየጨመረ መሄዱ ይነገራል፡፡ ለግል ጥበቃና ዝና ከሚያስፈልገው በላይ ብዙ መሣሪያዎች በአንድ ማህበረሰብ፣ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ይገኛሉ ይባላል፡፡ ይህ ከፍርሃት ከስጋት፣ በመንግሥትና በክልል ሃይሎች  እምነት ማጣት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በቅርቡ ዘአበሻ በሚለው ድረ ገጽ እንደ አዳመጥኩት፣ መትረየስ፣ ስናይፐር፣ ሽጉጥ፣ ክላሽ፣ ጥይቶችና ቦንቦች በይፋ  ኢትዮጵያ ውስጥ ይሸጣሉ ይባላል፡፡ አርፒጂ መቶ ሃያ ሺ(120,000)ብር፣ ክላሽ ከስልሳ አምስት እስከ ሃምሳ ሺ (65,000-50,000) ብር፣ ሽጉጥ ከአርባ ሺ እስከ አስራ ሁለት ሺ(40,000-12000) ብር መግዛት ይቻላል ይባላል፡፡

ኢትዮጵያ አምስት ሀገሮችን ታዋስናለች፣ ከድንበሮች ባሻገር ያሉ ብዙ ጊዜ አንድ ባህል ያላቸው፣ ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩ አንድ ቤተሰብ ናቸው፡፡ የኢሚግሬሽን መስሪያ ቤቶች ወይንም የድንበር ኬላዎች ካሉባቸው አንዳንድ ስፍራዎች በስተቀር ከሀገር መውጣትም ወደ ሀገር መግባትም ቀላል ነው፡፡ በመኪና የሚገቡም በቀላሉ ድንበር  ያሉ ሰዎችን ጉቦ በመስጠት ያልፋሉ፡፡ በዚህም መልክ በዛሬ ጊዜ የሰው፣ የድራግ፣ የመሣሪያ፣  ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች በቀላሉ ይፈፅማሉ:: የተደራጁ ደላሎችና ነጋዴዎች በሽብርተኞች አማካይነት እንደልብ መንቀሳቀስ ችለዋል:: ኤኤክስኤክስ አፍሪካ (AXX Africa) የሚባለው በእንግሊዝ አገር የሚገኝ መረጃ ኢንቲትዩት ባለፈው ነሐሴ ወር “Arms Trade in the Horn of Africa” በሚል ርእስ ባወጣው ጥናት ላይ ጅቡቲ ዋና የህገ ወጥ መሣሪያ ማመላለሻ ማዕከል እየሆነች መሄዷን ዘግቧል፡፡

ነጋዴዎችና መሳሪያዎች የሚያገኙት ጦርነት ካለባቸው ሀገሮች ነው፡፡ በጅቡቲ የሚመጣው ከየመን ጦረኞች የሚገዛ ነው፡፡ ከሱማሊያ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን ከነሱ አዋሳኝ ሀገሮች፣ ሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ከዲሞክራቲክ ኮንጐና ከሊቢያ መሣሪያዎች በገፍ ይዘዋወራሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በመሣሪያ አጠቃቀምና አያያዝ ልውውጥ ንግድ ለየት ያለ ሕግ አውጥቶ የጠበቀ ቁጥጥር ካላደረገ ሕግ ማስከበር ከመንግሥትና ከክልሎች ቁጥጥር ውጭ ሆኖ ሀገሪቱ ወደ ውድቀት እየተንሸራተተች ትሄዳለች፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት በኡጋንዳ ካምፖላ ዋና መስሪያቤቱ ለሆነው ዩናፍሪ ( UNAFRI) በአፍሪካ ውስጥ የቀላል መሣሪያዎች ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ጥናት እንዳደርግ ተመድቤ ለአንድ ዓመት ጥናቱን አከናውኛለሁ፡፡ የጥናቱንም ውጤት በአፍሪካ አህጉር የሚገኙ ሀገሮች ፖሊሲ ኮሚሽነሮች  ስብሰባ ላይ አቅርቤአለሁ፡፡ አቅራቢው እኔ ስለሁንኩ ይመስለኛል፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ተጠሪ አልላከም፡፡ ይህን ጥናት ባደረኩበት ጊዜ በመሳሪያ አምራቾች፣ በመሳሪያ ደላሎች፣ መሣሪያውን በሚያጓግዙት የትራንስፖርት ባለቤቶች እና በተጠቃሚዎቹ መካከል (End users) ያለው ግንኙነት የተወሳሰበ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ ምንም እንኳን ይህ ጥናት ትንሽ የቆየ ቢሆንም ሁኔታው ከመባባስ በስተቀር ሆዳሞች መሣሪያ ለመሸጥ ሲሉ በአንድ ሀገር ውስጥ እንዴት አድርገው ሽብርና ስጋት እንደሚፈጥሩ ለዚህም ሁኔታ የመንግሥት አካላት ሳይቀሩ ተባባሪ እንደሚሆኑ የሚያመለክት ነበር፡፡

Related stories   ‹‹የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠነክራል››

ከአራት ዓመት በፊት በተደረገ ጥናት The Gulf of Guinea ብዙ የምዕራብ አፍሪካ ጠረፎችን የሚያካትተው ባህረ ሰላጤ The most dangerous maritime zone in the world ተብሎ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት የኛው አጠገባችን ያለው Gulf of Eden ነበር አስጊው አካባቢ፡፡ ቀደም ብሎ ከኮሎምቢያ ድራግ ካርቴል በአውሮፓ አድርገው የሚያመላልሱት  ሕገ ወጥ እንቅስቃሴም መንገድ ለውጦ አሁን Gulf of Guinea የተመረጠ ሆኗል፡፡ በGulf of Guinea አድርጐ እስከ ሊቢያና በሜዲቴራንያን ጠረፍ አገሮች ለማጓጓዝ በጣም ቀላል ሆኖ አግኝተውታል:: ከባህረ ሰላጤው ጀምሮ እስከ ሜዲታራንያን ባህር ድረስ በቦኮሃራምና በሌሎች ህገወጥ እንቅስቃሴዎች የተወረረ ምድረበዳ ኮሪደር ፈጥረው አለብዙ ችግር ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ይህ እንቅስቃሴ መሣሪያዎችን ይጨምራል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጊኒቢሳውም Narco Capital of the Wrold ተብላ ተሰይማለች፡፡ የጊኒቢሳው አድሚራል ዋናው ለዚህ ድራግና መሳሪያ አመላላሽ ካርቴል ኃላፊ ነው ተብሎ ተጠርጥሮ በFBI ተይዞ ፍርድቤት ቀርቧል፡፡ ብዙም የመንግስት ባለስልጣኖች ከዚህ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቀርበዋል:: ይህን ያነሳሁበት የመንግስት ባለስልጣኖች በዚህ የተወሳሰበ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ዋና ተዋንያን ሊሆኑ እንደሚችሉ ለማሳየት ነው::

ሕገ ወጥ መሣሪያ እንቅስቃሴ ብዙ ዘርፎችን ስለሚነካ ጦርነት ለመቀስቀስም ለማፋፋምም የንግድ ብቻ ሳይሆን እንደ ፖለቲካ አጀንዳ የተያዘ ስለሆነ ሕግና ቁጥጥር ያስፈልገዋል፡፡

የፅጥታ ሀይሎች ጥራት

የመከላከያና የፖሊስ ሀይሎች በአመራር ደረጃም ሆነ በሠራዊቱ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ብቃት አላቸው ብሎ ለመናገር ያስቸግራል፡፡ አንዳንድ የኢትዮጵያ የጦር መሪዎችን ሩዋንዳም፣ ሱዳን፣ ላይቤሪያም አግኝቻዋለሁ፤ አልኮራሁባቸውም፡፡ እኔ በተለያዩ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ውስጥ  የሰለጠንኩ ወታደር ስለሆንኩኝ መመዘን እችላለሁኝ:: ብዙ ታላላቅ አዋቂ እዛዦችም ጋር ስርቺአለሁኝ:: ዛሬ በሜቴክ ሙስና የተያዙ ለክስ የቀረቡ ከፍተኛ ማዕረግ ያላቸው የሰራዊቱ አባሎች በሥነ ምግባራቸውና በዕውቀታቸው የሚያሳፍሩ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ህዝባችን በኃፍረት ነው የተሸማቀቀው:: በየደረጃው ያሉ ይህንን የመሳሰሉ አለቆች ለፀጥታው መደፍረስ መፍትሔ ሳይሆኑ ችግሮች ይሆናሉ፡፡

በየክልሉ ያሉት ኃይሎች ፖሊስና ልዩ ኃይል የሚባሉት የክልሉን ጥቅም ወይም መመሪያ የሚጠብቁ እንጂ በፌዴራል መንግሥት የሚመሩ ባለመሆናቸው ታላቅ ቀውስ ፈጥሯል፡፡ የፖሊስና የልዩ ኃይሎች ገደብ የሌለው ሥልጣን አደገኛ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ በመከላከያ ኃይልና በልዩ ኃይል የሥራ ኃላፊነት ልዩነት የለም፡፡ በተግባር ሲታይ በክልል ያሉ ፖሊስና ልዩ ኃይሎች ኃላፊነታቸውን የሚመለከቱት ሰፋ ባለ ኢትዮጵያዊነት መነጽር ሳይሆን በክልላቸውና በብሔራቸው መነጽር ነው:: የክልል ሕገ መንግሥቱ የፌዴራል ሕገ መንግሥቱን ይጣረዛል:: የየክልሉ ሠራዊቶች ይዋጋሉ፣ ይገድላሉ:: ልክ የሁለት ሀገሮች ጦርነት የሚመስል በየድንበሩ ጦር አሰልፈው ያጠቃሉ፤ ይከላከላሉ: አቅም ሲያጥራቸው የፌዴራል መንግሥቱን ኃይሎች ይጠራሉ፣ ባላቸው ኃይል ከሥልጣናቸው በላይ የሆነ ምንም ነገር የለም፡፡

ወደ ምርጫ እየተቃረብን ባለንበት ወቅት እንዴት አድርጐ ነው አንድ ክልል አቋርጦ ሌላ ክልል ሲገባ፣ ሌላ አገር የገቡ በሚመስል በተወጠረ የፖለቲካ ሁኔታ ህዝብ ተንቀሳቅሶ የፖለቲካ ፖርቲዎች እንደልብ ተናግረው፣ አስተምረው ህዝቡን አደራጅተው ነው ለምርጫ የሚያዘጋጁት? ይህ ስንት ዓመት ሙሉ በካድሬዎች ሲታጠብ የነበረ ሰራዊት እንዴት አድርጐ ነው ኢህአዲግ ውጪ ለሌላ ተመራጭ ሁኔታውን ማመቻቸት የሚቻለው? ከስር ጀምሮ   ኢትዮጵያ በሚለው ታላቁ ስእል ክልል ውስጥ ለማሰብና ለመስራት እንዲቻል በሠራዊቱ ውስጥ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም ብዙ ይቀራል፡፡

ትጥቅ መፍታትና ከህብረተቡ ጋር መቀላቀል

(Demobilization Re-Intigration)

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የትጥቅ ትግል በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ከምናያቸው የተለየ ቢሆንም፣ የትጥቅ ትግልን በመጠቀም መንግሥትና ሥርዓትን እንለውጣለን ብለው የተነሱ ኃይሎች ነበሩ፡፡ አሁን ዶ/ር አብይ እንደ ጀመሩት፣ እነዚህ ኃይሎች፣ የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር እየተመለሱ ናቸው፡፡ እኔ የአንጎላ ጦርነት ሲቆም፣ የትጥቅ መፍታትና ከህብረተቡ ጋር መቀላቀል (Demobilization Re-Intigration Technical Officer) ሆኜ በተባበሩት መንግሥታት ፕሮግራም ውስጥ ሰርቻለሁ፡፡ ትጥቅ ማስፈታትና ከህብረተሰቡ ጋር መቀላቀሉ ለዘለቄታዊ መፍትሔ ወሳኝ ነው፡፡ ይህም አካሄድ ሥርዓት አለው፡፡ ሥርዓቱ ካልተጠበቀ ሰላምን ሊያደፈርስ የሚችል ሁኔታ ይፈጠራል ተብሎ ይታመናል፡፡ የአንጎላን ፕሮግራም ስንሰራ ከሞዛምቢክ ልምድ ለመውሰድ የሞዛምቢክንም ተሞክሮ ፈትሸናል፡፡ የናሚቢያ ነፃነት በሁዋላ የነበረውን የትጥቅ መፍታትና ወደ ሰላማዌ ሕይወት መቀላቀል ስኬታማ የሆነውን እንደ ሞዴል አድርገን ተጠቅመንበታል፡፡ የሩዋንዳ Ministry of Rehabilitation Social Intigraion ሲቋቋም አማካሪ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ የታጠቁትንም ያልታጠቁትንም በGenocide ጊዜ የተፈናቀሉትን፣ የተሰደዱትን መልሶ ህብረተሰቡ ውስጥ ለመቀላቀል እንዲቻል የተቋቋመ ሚኒስትሪ ነበር፡፡ እነዚህ የተለዩ ሁኔታዎች ቢሆኑም ከልምዶቻቸው ብዙ ተመክሮ መውሰድ ይቻላል፡፡

ትጥቅ መፍታት በመንግሥስትና በታጣቂ ኃይሎች መካከል ከሚኖር ስምምነት ይጀምራል፡፡ በስምምነቱ መሰረት የታጠቁ ኃይሎች ስም ዝርዝር፣ የታጠቁት መሳሪያ ብዛትና ዓይነት ይመዘገባል፡፡ ትጥቅ የፈቱት ኃይሎች አንድ ማረፊያ ሰፈር ይገባሉ፡፡ በዚህም ማረፊያ ሰፈር ህብረተሰብ ውስጥ ተቀላቅለው በሰላም እንዲኖሩ የሚያስደርጋቸውን ትምህርት ይቀበላሉ፡፡ በሀገሩ የመከላከያ ኃይል ውስጥ ለመቀላቀል ብቃትና ፍቃደኝነት ያላቸው ወደ ሰራዊቱ ይቀላቀላሉ ሌሎቹም እንደ ጥያቄአቸው ሥራ እየተፈለገ ይሰጣቸዋል፡፡ በሙያ ለመሰልጠን የሚፈልጉ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ የመቋቋም ችግር ያለባቸው በስምምነቱ መሰረት እርዳታ ይደረግላቸዋል፡፡ ይህ ሳይደረግ የቀድሞ ተዋጊዎችን ህብረተሰቡ ውስጥ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ለሰላም ጠንቅ ሊሆን ይችላል:: ይህንንም በተመለከተ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን እገነዘባለሁኝ፡፡

ራስን የመግለጽ ነፃነት (Freedom of Expression)

ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትና ግዴታ በተለይም አዲስ የዲሞክራቲክ ስርዓት በሚገነቡ ሀገሮች በሚገባ ባለመታወቁ፣ በአንዳንድ ሁኔታ ውስጥ ሰላምን ሊያናጋ ይችላል፡፡ በአንድአንድ ሀገር እንደ ሁኔታው፣ በግዴታና በመብት መካከል መስመር መዘርጋት ይኖርበታል፡፡ ችግሩ መንግሥት ትንሽ ፍንጭ ሲያገኝ፣ ስንዝር ሲሰጡት አንድ ክንድ ይወስዳል፡፡ የፀረ ሽብርተኛ አዋጁ በምሳሌነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

በ2001 እ.አ.አ. ከደረሰው የአሜሪካ የሽብር ጥቃት (Nine Eleven) በኋላ ብዙ ሀገሮች የፀረ ሽብርተኛ አዋጅ እንዲኖራቸው አሜሪካ አበረታታለች፡፡ በአፍሪካና በሌሎች አህጉሮች ያሉ መንግሥታት ይህንን ሀሳብ ያለምንም ማንገራገር ቀለብ አድርገው ለራሳቸው መጠቀሚያ አደረጉት፡፡ ሽብርተኝነት የጠራ ዓለም አቀፍ የሆነ ትርጉም ስለሌለው እያንዳንዱ መንግሥት እንዳመቸው እየተረጐመ ነፃነትን፣ ክርክርን፣ ሰላማዊ ሰልፎችን፣ በአጠቃላይ ስላማዊ ትግልንና የሀሳብ መግለፅን ነፃነት ማጥቂያ ህጋዊ ዘዴ አድርገው ተጠቅመውበታል::

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ እውነትና ውሸትን መለየት በጣም ያስቸግራል፡፡ የመንግሥትን ሚዲያ እያዳመጥን ምንጫችን ከአንድ ወገን ብቻ ሲሆን እውቀታችን ውስን ይሆናል፤ ወይንም የመንግሥስት መሣሪያ እንሆናለን፡፡ የግል ሚዲያዎች የሚናገሩትን፣ የሚጽፉትን በሁሉም ሶሻል ሚዲያና ሌሎችም ወይንም ገንዘብ ለማግኘት፣ ወይንም ሰንሴሽን ለመፍጠር የፖለቲካ ተልዕኮ አጀንዳ ያላቸው፣ ወይንም የማያውቁ ሰዎች ሚዲያ ለመቅረብ እድል በማግኘታቸው የሚናገሩት፣ የሚጽፉት ሁሉ ሀገሪቱን ምን ያህል አደጋ ላይ እየጣለ እንደሆነ ማጥናት አስፈላጊ ነው፡፡

በተለይ ወጣቱ ከብዙ ዓይነት አስተማማኝነታቸው ካልተረጋገጠ ምንጮች በሚያገኘው ዜና ወይም ወሬ እየተዋከበ ለመወገን፣ ለማገዝ ይቸኩላል፡፡ ይህ ወጣት ትውልድ ብዙ የማያነብ ግን ብዙ የሚናገር፣  ለማሞጐስም ለማውገዝም የሚቸኩል፣ ሶሻል ሚዲያ ላይ ጥቂት አረፍተ ነገሮችን አንብቦ በታላላቅ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ አቋም መውሰድ የሚደፍር፣ በስድብ፣ በዘለፋ፣ የሃቀኞችን ልሳን የሚዘጋ፣ ከአንድ ከሚፈልገው አቅጣጫ ብቻ መረጃዎችን የሚቀበል፣ ሳያውቅ ሳያመዛዝን የጠላት መሣሪያ ሊሆን የሚችል በመሆኑ ለሀገራችን ጸጥታ ትልቅ ስጋት ይሆናል፡፡

አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት በጣም ስስ፣ በቀላሉ የሚሰበር (Fragile) አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ውስጥ አንድ የሀሰት ወሬ ብዙ ህዝብ ሊያስጨርስ የሚችልበት ሁኔታዎች ብዙ ናቸው:: በሚዲያ አማካኝነትም ሆነ በአደባባይ ወጥቶ የሚነገረው ገደብ እንዲኖረው አንድ ሕግ መፈጠር አለበት፡፡ አሁን ባለበት ዲጂታል ጀነሬሽን መቆጣጠር በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም በማስተማር፣  ግዴታንና ሀላፊነትን ከማሰወቅ ጋር የተያያዘ ፖሊሲ ሊቀየስ ይገባል::

ይህ በኢንተናሽናል ሕግም የተደገፈ ነው፤ የአፍሪካ ቻርተር Human and Peoples Right Freedom of Speech Shall be exercised in respect of the right of others collective security morality and common interest ይላል፡፡ ከዚያም ቀጥሎ ይህ ገደብ ዓላማው ምን መሆን እንዳለበት በዝርዝር አስቀምጦታል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት የሽግግር ወቅት በግልጽ የኢትዮጵያን አንድነት የማይደግፉ፣ ድብቅ አጀንዳ አላቸው ተብለው የሚጠረጠሩ አናርኪስቶች ይሁኑ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተቆጡና የግልም ችግር ያለባቸው፣ ሀገር የመከፋፈል፣ ህዝብ የሚያጣላ ህዝብን ከማያቀራረብ፣  ከይቅርታ፣ ከፍቅር የሚያርቁ በሀሰት ላይ የተመሰረቱ ማስረጃ የሌላቸው ታሪክና ዜና በሚያስራጩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ ትኩረት መደረግ አለበት፡፡

የሚዲያና የፓለቲካ ድርጅቶች የገንዘብ ምንጫቸውን ለመንግሥት ማሳወቅ አለባቸው:: ይህ በሁሉም ዴሞክራቲክ ሀገሮች በሕግ የተደነገገ ነው:: ይህም የኢትዮጵያ የውስጥ ፓለቲካና የፀጥታ ሁኔታ በውጭ አጀንዳ እንዳይመራ ያረጋግጣል:: በንግግር በጽሁፍና በመሳሰሉት በfreedom of expression ነፃነት ሽፋን አድርገው የኢትዮጵያን አንድነት የሚጐዱ ግለሰቦች ካሉ የሚታገዱበት ሕግ ሊኖር ይገባል::

የአካባቢ ሁኔታና ሽግግር

የአካባቢያችንን የፀጥታ ሁኔታ ከውስጥ የፀጥታ ሁኔታ ለይቶ ማየት አስቸጋሪ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሁኔታ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የዲሞክራሲ መመስረት፣ የሰብአዊ መብት መጠበቅ፣ ከአካባቢው ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርብም በሩቅም በአይነቁራኛ የሚከታተሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ በአሁኑ ጊዜ The most militarized zone in the world ይባላል፡፡ ታላላቅ ሁኔታዎች በዓለም በተለይ በመካከለኛው ምስራቅና በአረቡ ዓለም ሲከሰቱ አዲስ የሃይል አሰላለፍ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ እየታየ ነው፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ሁኔታ ግልጽ በሆነ መንገድ ለሁለት መከፈሉና የአፍሪካ ቀንድ ከዚህ ሁኔታ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ ትኩረት የሚሰጡት ቦታ መሆኑ ኢትዮጵያን በቀጥታ ይመለከታታል::

ኤርትራ

ስለጎረቤት ሀገሮች ስንነጋገር በመጀመሪያ ከላይ ከጠቀስኩት ሁኔታ ጋራ ያልተያያዘ ስለ ኤርትራና ኢትዮጵያ ግንኙነት ትንሽ መናገር እፈልጋለሁ፡፡ እኔ የኤርትራ ፌዴሬሽን ከመፍረሱ ስምንት ወር በፊት በምክትል የመቶ አለቃ ማዕረግ ኤርትራ ነበርኩ፡፡ ፌዴሬሽኑ የፈረሰ ዕለት ጦር ይዤ አስመራ አካባቢ ተሰማርቼ ነበር፡፡ ከእዛን ጊዜ ጀምሮ የኤርትራን ሁኔታ በቅርብ ተከታትያለሁ፡፡ ኤርትራ በውጊያ ግንባር ተሰልፌአለሁ፣ ክፍለሀገሩን በበላይ አስተዳዳሪነት መርቻለሁ፡፡ ከአገር ከወጣሁም በኋላ ከኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ አባሎች ጋር በግል ጓደኝነትም፣ በፖለቲካም በቅርብ ሰርተናል፡፡ የኤርትራን ህዝብ፣ የኤርትራን ፖለቲካ ከብዙ ሰዎች በተሻለ ሁኔታ አውቃለሁ፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ እጣ ፋንታ ወደፊት አብሮ እንጂ ተለያይቶ እንደማይሆንም መገንዘብ ይቻላል፡፡ እኔ የአንድነት ወገን ነበርኩኝ:: ያ አልተቻለም፤ ነገር ግን ተቀራርቦ መስራት ለጋራ ጥቅም፣ ለጋራ ህልውና አማራጭ የለውም፡፡ በመንፈሴ አሁንም ኤርትራንና ኢትዮጵያን መለየት አልችልም፡፡ ከዚህ በፊትም፣ ከዚህ በኋላም ኤርትራ ኢትዮጵያ ነች፤ ኢትዮጵያ ኤርትራ ነች ብዬ ነው የማምነው፡፡ ግን በግልፅ መታወቅ ያለበት ኤርትራ እሯሳን የቻለች ዳር ድንበሯ በዓለም አቀፍ ሕግ የታወቀች ሀገር sovereign state  ነች፡፡ የሁለቱ መንግሥታት መለያየት የህዝቡን አብሮነትና አንድነት አይለውጠውም፡፡ በኤርትራ ላይ የሚመጣ ጉዳት ኢትዮጵያን ይጎዳል፤ በኢትዮጵያ ላይ የሚመጣ ጉዳት ኤርትራንም ይጎዳል፤ ይህ የመልካም ጉርብትና ፖሊሲ መሰረታችን መሆን አለበት:: ዶ/ር አብይ በወሰዱት እርምጃ በግል በጣም ተደስቻለሁ፡፡  “The moment of Truth: Eritrea and Ethiopia” በሚል ርእስ ድጋፌን ለመግለፅ በወቅቱ በሰፊው የተነበበ ጽሁፍም አቅርቤአለሁ፡፡

በሁለቱ ህዝብ መካከል ብዙ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይህንን ያህል ዘመን በኤርትራ ምድር ላይ በአንድነትና በነፃነት ኃይሎች መካከል ውጊያ ሲካሄድ  ይህ ጦርነት ህዝባዊ ጦርነት(Civil War) ሆኖ አያውቅም፡፡ ጦርነቱ በሁለቱ ኃይሎች መካከል ነበረ፡፡ ህብረተሰቡ ተጋብቶ ተዋልዶ ባሕሉን አክብሮ እንደ አንድ ቤተሰብ ተቀራርቦ ጦርነቱ እንዲቆም ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖር እየተመኘ እየፅለየ እዚህ ደርሰናል፡፡ በሁለቱም ወገን ብዙ ተዋጊዎች አልቀዋል፡፡ የኤርትራ ተዋጊዎች የሚገባቸውን ክብር አዲሱ መንግሥት ሰቷቸዋል፡፡ ነገር ግን አሁን የተጀመረው አብሮ የመኖርና የማደግ ፍላጐትና ምኞት እውነት ሊሆን የሚችለው ህዝባዊ ዕርቅ ሲፈፀም ብቻ ነው፡፡ የሁለቱ መንግሥታት መሪዎች መጨባበጥና መተቃቀፍ መሰረታዊ የሆነ ብሔራዊ ዕርቅ አያመጣም፡፡ በኢትዮጵያ በኩል በሰላሳ ዓመት ውስጥ ከመቶ ሺህ በላይ ወታደሮች በኤርትራ ምድር ላይ አልቀዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸው ከመቀሌ ጀምሮ እስከ አዲስ አበባና ከዚያም ባሻገር በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራት ከተሞችና መንደሮች ተበትነው በጉስቁልና የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ቆስለው፣ ተሰናክለው፣ የተጣሉም የተረሱም ብዙዎች ናቸው፡፡ ኤርትራ ውስጥ የሞተ፣ የቆሰለ፣ ዘመድ የሌለው ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ጦርነቱ የታሪካችን ጠባሳ ነው፤ ታሪክ ይዘግበዋል፡፡ የዛሬውና የሚመጣው ትውልድ ግን የተፈጸመውን ታሪክ ትቶ እንዴት እንደዚህ ያሉ ጥፋቶች እንደደረሱ የሁለቱን ህዝቦች የታሪክ ቅርበት ያገናዘበ ውይይት በማካሄድ  ከእንግዲህ ወዲያ መቼም እንደዜህ ያለ ሁኔታ አይፈጠርም (Never again) ብሎ ተነጋግሮ፣ ተላቅሶ፣ ተቃቅፎ፣ እውነቱን አውቆ፣ እርቅ የሚመሰርትበት ህዝባዊ ጉባኤ ማመቻቸት ተገቢ ነው::

ይህም ጉባኤ የትዮጵያ ሰማዕታትም የሚከበሩበት፣ የሚታወሱበት ኃውልት ከኤርትራ መንግሥት ጋር ተነጋግሮ ፈቃድ እንዲሰጥና በመንግሥት ወጪ ሳይሆን ከህብረተሰቡ በተዋጣ ገንዘብ እንዲቆም ይነጋገርበታል፡፡  መንግስትም ድጋፍ ሊሰጥ ይገባል:: በኤርትራ ምድር ላይ የፈሰሰው ደም፣ ያለፈው ሕይወት በሁለቱም ሀገሮች ታሪክ ውስጥ አቻ የለውም፡፡ ይህንንም የመሰለ ጉባኤ በሁለቱም ህዝቦች መካከል የሃይማኖት አባቶች፣ ወገኖቻቸውና ዘመዶቻቸው፣ የጠፋባቸው፣ የተጎዱባቸው ሰዎች፣ በሁለቱም ወገን በውጊያው ወቅት የነበሩ ታጋዮች፣ መስካሪዎች፣ ታሪክ አዋቂዎች ተሰባስበው ይህንን ምዕራፍ ዘግተው ለታሪክ አስረክበው በሰላም እንዲኖሩ ማድረግ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይህ ዘላቂ ሰላምን ያስገኛል ያረጋግጣል፡፡

ሶማሊያ 

ሶማሊያ በ1978 ዓ.ም.  ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ እኔ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቋሚ ተጠሪ ነበርኩ፡፡ ይህንን በወቅቱ እጅግ አሳሳቢ የሆነ ሁኔታ ለInternational Community ለማስረዳትና ድጋፍ ለማግኘት ወደ United Nation delegation መርቼ ሄጃለሁ፡፡ በገለልተኛ ሀገራት መንግሥታት ስብሰባ አቤቱታችንን አሰምተናል፤ ድጋፍ ጠይቀናል፡፡ በኩባ፣ በአውሮፓ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በየመን ተመላልሰን ድጋፍ ለማግኘት በዲፕሎማቲክ ዘርፍ ብዙ ትግል አድርገናል::

በሜዳ ላይ የሶማሊያ ጦር ጅጅጋን ያዘ፤ ሐረርንም፣ ድሬደዋንም ከበበ፤ አርሲ፣ ባሌ ሐረርጌን ማስታጠቅ ጀመረ:: በዚያን ወቅት በኮለኔል ብርሃኑ ባዬ የሚመራ ልጅ ጌታቸው ክብረት፣ ልጅ ሚካኤል እምሩ እና እኔ ያለንበት የልዑካን ቡድን ሶቪየት ዩኒየንን ለመማፀንና ለሶማሊያ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያቆሙ አስራ ሰባት ቀናት የቆየ ውይይት አካሂደናል፡፡ ሶማሊያ  ወረራ የፈጸመችው ነፃነት ካገኘችበት ጊዜ ጀምሮ በሕገ መንግሥቷ አንቀጽ 6 እና በባንዲራዋ ላይ የተመለከተውን አምስቱን የሱማሌ ህዝብ የሚኖርባትን ሀገሮች አጠቃላ ታላቋ ሶማሌያን ለመፍጠር ነበረ፡፡ ለዚህም ወረራ ሽፋን እንዲሆን የምዕራብ ሶማሊያ ነፃነት ንቅናቄ ግንባር (Western Somalia Libration front) ብላ አቋቋመች፡፡ መሪዎቹም ከዚያው ከሱማሊያ ጦር ውስጥ ኃላፊዎች የነበሩ ታላላቅ የጦር መሪዎች ነበሩ፡፡ የONLF መሪ በዚያድ ባሬ መንግስት ወቅት  ከፍተኛ መኮንን የነበረው Rear Admiral Mohamed Omar Osman ነው፡፡

Related stories   ‹‹የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠነክራል››

ሶማሊያ ከነፃነት ጊዜ ጀምሮ ወቅት እየመረጠች ኢትያጵያን ወራለች፡፡ በጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጊዜ ኢትዮጵያ ተዳክማለች ብላ በዳኖት በኩል ጦርነት ከፈተች፤ ተሸንፋ ተመለሰች፡፡ በደርግ ጊዜ አገሪቱ በአብዮተኞችና በፀረ አብዮተኞች መካከል በነበረው የሥልጣን ትግል፣ ከዚያም በሀገሪቷ ሰሜናዊ አካባቢ የነበረው ጦርነት ተፋፍሞ ስለነበረ ኢትዮጵያ ተዳክማለች በሚል ግምት በሶቭየት ዩኒየን የመሣሪያ ድጋፍ፣ ህዝብ ያለቀበት ወረራ ፈጸመች፡፡ ለዚሁም ሽፋን ያደረጉት የዚያድ ባሬ መንግሥት ያቋቋመው በራሱ ጄኔራሎች የሚመራው ይኽው የምዕራብ ሶማሊያ ነፃነት ንቅናቄ ግንባር (Western Somalia Libration front) በስሩ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት አውጪ ግንባር (Ogaden National Libration Front) ኦብነግ እና ከዚያም ደግሞ የሐረርጌን፣ የባሌና የሲዳሞን ኦሮሞዎች ሶማሌ አቦ የሚሏቸውን እያደራጁ፣ እያስታጠቁ ጦርነት ከፈቱ:: በተከታታይም ኦጋዴን የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት እያሉ በየኢንተርናሽናል  መድረክ ብዙ ፕሮፖጋንዳ መንዛታቸው ይታወቃል፡፡ ዛሬ የምናየው ኦብነግ (ONLF) ይህ ነው፡፡ ክህደት በደም መሬት በሚለው መጽሐፌ ገጽ 49 ያለውን እጠቅሳለሁ፡፡

ኢብራሂም አብደላ የተባሉ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር ተጠሪ በአንድ ወቅት ሲናገሩ የሚከተለውን ብለዋል፡፡

“ድርጅታችን የሚከተሉት ዓላማዎች አሉት፡- የእስልምናን ልዕልና ማረጋገጥ፣ እስላማዊ ትምህርት በሕዝቡ ዘንድ ሰርጎ እንዲገባ ብርቱ ትግል ማድረግ፣ ኦጋዴንን ከኢትዮጵያ ቅኝ አገዛዝ ነፃ በማውጣት ነፃ መንግሥት መመሥረትና የሕዝቡን ፍላጎትና ምኞት እውን ማድረግ፣ በእስልምናና በዲሞክራሲያዊ አመራር ሥር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነፃነቱ የተረጋገጠ እስላማዊ ኀብረተሰብ መገንባት፣ ከሶማሊያ ሕዝብ ጋር ያለውን የወንድማማችነትና የትግል አንድነት እንዲጠነክር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከዓረቡ ዓለምና ከሙስሊሙ ጋር ያለንን ግንኙነት በጋራ ጥቅሞች ላይ ተመርኩዞ የሚያድግበትን መንገድ መሻት…”

የኢትዮጵያ የደህንነት ሥጋቶችና የኡጋዴን ኢትዮጵያዊነት በሚሉ ርዕሶች ሰፊ ጥናት በመጽሐፌ ውስጥ እና ከዚያም በድረ ገጾች ላይ አስመዝግቤአለሁ፡፡ በቅርቡም የኢህአዲግ መንግሥት ከ ኦብነግ (ONLF) ጋር ኬንያና ዱባይ ላይ ድርድር በጀመረበት ጊዜ ይህ የሚፈጥረውን አጠቃላይ ሁኔታ እኔ፣ ዶ/ር ዲማ ነገዎና ፕ/ር ጌታቸው በጋሻው ያለንን ስጋት የሚጠቁሙ ጽሁፍ በትነናል፡፡

የሱማሌ ሕገ መንግሥት ብዙ ችግር ነበረበት፣ Transitional Federal Government አባል የነበረው የIsIamic Court የስልጣን ተቀናቃኝ በነበረበት ጊዜ ONLF ከIslamic Court ጋር በቅርብ ይሠራ እንደነበረ ታሪክ ውስጥ የተመዘገበ ነው፡፡ የlslamic Court በታላቋ ሶማሊያ ዓላማ እንደሚያምንም የታወቀ ነው:: በንግግሮቹም፣ በጽሁፎቹም ላይ ይህንኑ ጠቁሟል፡፡ የIslamic Court ከሥልጣን ሲባረር ወደ አልሻባብነት ተለወጠ፡፡ አልሻባብን የመሰረቱት Islamic Court ኃላፊዎችና አባሎች ናቸው፡፡ አሁን ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ፎርማጆ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ጉርብትና ስለሚፈልግ ኦብነግን አውግዟል፡፡ ከማውገዝም አልፎ ሽብርተኛ ነው ሲል ፈርጆታል፡፡

ኦብነግ (ONLF) ማን ምን እንደሆኑ ሥር መሰረታቸውን እንቅስቃሴአቸውን እናውቃለን፡፡  የኢትዮጵያ አንዱና ትልቁ የፀጥታ ሥጋት ONLF ነው፡፡ የሶማሊያ መንግሥት ቢለወጥ አቋማቸው እንደሚዋዥቅ ጥርጣሬ ሊኖር አይገባም፡፡ ዛሬ በዶ/ር አብይ አመራር የአፍሪካ ቀንድ መሪዎች ሰላማዊ የሆነ አካባቢን ስለፈጠሩ ONLF ዋና መስሪያ ቤቱ ያደረገባት ኤርትራም ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ጉርብትና ስለመረጠች፣ ሶማሊያ ውስጥም እንቅስቃሴ ማድረግ ስላልቻሉ ከዚህ አሰላለፍ ቢወጡ በInternational Community ሽብርተኛ ተብለው ስለሚመዘገቡ፣ ስለሚወገዙ እና ጥቁር ሊስት ውስጥ እንሚገቡ ስለሚያውቁት እንጂ አጀንዳቸውን ለውጠዋል ማለት አይደለም፡፡

ሶማሊያን እንድትንኮታኮት ያደረጋት ይህ ፖሊስዋ ነው፡፡ ብዙ ሕይወት ከጠፋበት ከ1978 ዓ.ም. ወረራ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ሶማሊያን ለማዳከምና ሽብር ውስጥ ለመክተት አማራጭ የሌለው ፖሊሲ ሆኖ አገኘው፡፡ በሶማሌያ ውስጥ ያሉትን ተቃዋሚ ኃይሎች ማስታጠቅና ማደራጀት ጀመረ:: ዛሬ የምናያት ሱማሊያ የዚያው ውጤት ነች፤ አዲሱ መንግሥትም፤ መልካም ጉርብትናን መርጧል፡፡ ONLF እስከዛሬ የተናገረውን፣ የፃፈውን ሁሉ ቀልብሶ በኦጋዴን ኢትዮጵያዊነት የሚያምን በዚህ ውስጥ በህዝቦች መካከል የሚፈፀሙ ልዩነቶችን  በሰላማዊና በአንድነት መንፈስ እንደሚፈፅም ለኢትዮጵያ ህዝብ መግለጽ አለበት፡፡ በ1978 ዓ.ም. ጦርነት ምክንያት በአስቸኳይ ዘመቻ ጥሪ ተደርጐ ምስራቅ ግንባር ከተሰማራ ሁለት መቶ ሺ ሠራዊት ውስጥ አንድ ሶስተኛው እዚያው ኡጋዴን ውስጥ አልቋል፡፡ የነበርን ሰዎች አንረሳውም:: የአሁኑም ወጣቶች እና መሪዎች ሊረሱት አይገባም፡፡ ኦብነግ በጥንቃቄ መያዝ ያለበት ድርጅት ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬ ONLF ያንን በፕሮግራሙ የተቀመጠውን አቋም ሰርዞ፣  በኢትዮጵያዊነት አምኖ ለመስራት መዘጋጀቱንና ፕሮግራሙንም መለወጡን በስምምነት አፅድቆ ለህዝብ በግልፅ ማሳወቅ አለበት፡፡

አካባቢው

በካባቢያችን ያለው የኃይል አሰላለፍ ያስደነግጣል፡፡ የአሜሪካን የውጭ ፖሊሲ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ በፀረ ሽብርተኝነት ዘመቻ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ዛሬ ከዚህ ፖሊሲ እየራቀ America First የሚለውን የአሜሪካ ጥቅም የሚያስጠብቅ አዲስ ፖሊሲ እየቀየሰ ነው፡፡ አንድ የአሜሪካ የመከላከያ ሀላፊ እንደተናገሩት “Great power competition not terrorism is now primary focus of national interest” በአንድ ሀገር ውስጥ የሽብርተኛ እንቅስቃሴ ኖረም አልኖረም አንድ መንግሥት ራሱ ሽብርተኛ ሆኖ State Terorism ቢያካሂድም፣ ቀዳሚነት የሚሰጠው የአሜሪካ የኢኮኖሚ ጥቅምን ነው፡፡ ይህም በቅርቡ በግልጽ በሳውዲ ጋዜጠኛው ጀማል ካሹጊ ላይ የተፈጸመው ግድያና የአሜሪካ ዝምታ ብዙ መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ ይህንን በተመለከተ በቅርቡ የፃፍኩት  “The Unholy Alliance Between the most Democratic and the most Autocratic Washington and Riad Should we be worried” የሚለውን ጽሁፍ ማንበብ ይቻላል፡፡

Global politics 09 Nov, 2018 G.C የወጣው ጽሁፍ እንዲህ ይላል “The new Cold War brewing in the Gulf has rapidly rewritten the geo political rule book in the Horn of Africa….Saudi Arabia and the UAE versus their bitter adversaries Qatar and Turkey are looking to forge closer connections with Ethiopia…..in the background you have Iran which is an enemy of Saudi and ally of the US. It is very complex background”

ዛሬ በጅቡቲ ላይ ያሉት የጦር ሰፈር ክምችቶች አፍሪካ ቀንድ የብዙ መንግሥታት ጥቅም መነኸሪያ መሆኑን ያመለክታል፡፡ አሜሪካ ቀድሞ የፈረንሳይን ቤዝ ካምፕ አድሳ፣ አስፋፍታ ታላቅ የጦር ሰፈር አድርጋዋለች፡፡ ፈረንሳዮችም እንዳሉ ናቸው፡፡

በተጨማሪም ለመጀመሪያ ጊዜ ጃፓን እና ቻይና  በጂቡቱ ጦር ሰፈሮች ሰርተዋል፡፡ ህንድም በቅርቡ ትልቅ የጦር ሰፈር ጅቡቲ ላይ እያቋቋመች ነው፡፡ ጣሊያንም እዚህ የሀያላን ስብስብ ውስጥ ገብታለች፡፡ ዩናይትድ አረብ ኢሜሬትና ሳውዲ አረቢያ ትልቅ የጦር ሰፈር አቋቁመዋል፡፡ ባህረ ሰላጤውንም ከመቆጣጠር ባሻገር የመን የሚያካሂዱትን ውጊያ የሚያግዝ የሎጅስቲክስ ቤዝ አድርገውታል፡፡ ኳታር በጅቡቲና በኤርትራ መካከል በነበሩ የድንበር ግጭት ሰበብ ሰላም ለማስጠበቅ ጦር ሰፈር ነበራት፡፡ በሳውዲና ዩናይትድ አረብ ኢሜሬት ግፊት ከጅቡቲ ተባራለች፡፡

ሳውድ አሪቢያም በአሰብ ላይ ጦር ሰፈር እንዳላት የታወቀ ነው፡፡ የመን ከኤርትራ የ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ነው የሚለያያት:: የደቡብ የመን ጦር ከኢትዪጵያ ጦር ጋር ተስልፌ ከኤርትራ ህዝብ እርነት ግንባር ጋር መዋጋቱን ማስታወስ ይጠቅማል::

ጅቡቲ ያለችው በቀይ ባህርና በኤደን በህረ ሰላጤ በስዊዝ ካናል አገናኝ ሥፍራ ላይ ስለሆነች በባህር ላይ ለሚደረገው እንቅስቃሴ ታላቅ የሴኩሪቲ የኤኮኖሚ ሚና ትጫወታለች፡፡ ዩናይትድ አረብ ኢሜሬት በሶማሌ ላንድ በርበራ ወደብ ላይ ጦር ሰፈር ከማቋቋም በላይ አዲስ አይሮፕላን ማረፊያም እየስሩ ናቸው፡፡ ቱርክ በሱማሊያ፣ ሩሲያም በሱዳን፣ ግብጽ በደቡብ ሱዳን፣ ቱርክን የሱዳን ደሴት የሆነችውን ስዋኪን ላይ ጦር ሰፈር ለመመስረት መሞከሩ ይህንን የመሳሰሉ በየጊዜው በፈጣን ሁኔታ የሚለዋወጠው ለኢትዮጵያም ለአፍሪካ ቀንድም በጥቅሉ አስጊ ነው::

ሁሉም ሀይሎች የየራሳቸው አጀንዳ አላቸው፤ ኢትዮጵያ እዚሁ መካከል ነው ያለችው::

ለጊዜው ይህንን የአረቦች በአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚፈፅሙት ርብርቦሽ እንዲፈጠር ያደረገው የየመን ጦርነትና በባህረሰላጢው ባሉት አብዛኛው የአረብ አግርችና በኢራን መካከል ያለው ፍትጊያ ቢሆንም ከጥንት ጀምሮ አረቦች ቀይ ባህርን የአረብ ሃይቅ ለማድረግ ካላቸው ምኞትም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህንንም በተመለከተ በቅርቡ በጣም ሰፋ ያለ ጥናት አቅርቤ አለሁ፡፡ ጊዜ ካላችሁ The Iran Saudi Rivalry and the Scramble for the Horn of Africa በሚል ርዕስ ያዘጋጀሁት ጽሁፍ The Africa Institute For Strategic and Security Studies(AISSS) ድረ ገጽ ላይ ይገኛል፡፡

ስዊዝ ካናል ከተከፈተበት ከ1869 ዓ.ም. ጀምሮ አረብና አፍሪካ ቢቀራረቡም በግሎባላይዜሽን ጊዜና ዓለም በሀይማኖትና በሌሎችም ምክንያቶች የአረብ አንድነት እየተፍረከረከ ታላቅ የነበረው የአረብ (Nationalism) ብሔርተኛነት ሲፈርስ አሁን አዲስ ሃይሎች ዩናይትድ አረብ ኢሜሬትና ሳውዲ የሚመሩት ብቅ ብሎ Gulf Alliance በሚል አሜሪካ የተወውን ባዶ ሥፍራ ለመሙላት አካባቢውን በገንዘብ ሃይል ለመቆጣጠር እየቻሉ ነው፡፡ አሁን ቀይ ባህር የአውሮፓና የአሜሪካ ጉዳይ ሳይሆን የአፍሪካና የአረብ ሀገሮች ጉዳይ እየሆነ መጥቷል፡፡ አካባቢው በጣም ተከፋፍሏል፡፡ በዩናይትድ አረብ ኢሜሬትና በሳውዲ አረብያ የሚመራው አሊያንስ፣ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያሉ ሀገሮችን ለመያዝ ለመቆጣጠር የሚፈፀመውን ሁለንተናዊ ዘመቻ ኢትዮጵያ በጥንቃቄ ልትመለከተው ይገባል፡፡ በቅርቡ 30 Nov, 2018 The National Interest በሚባል የonline ፅሁፍ አንድ የፖለቲካ ሰው እንዲህ ይላል፡፡

“Somalia remains troubled largely by foreign agents who weaken its government, who divide its people and who threaten to reverse its gains” ይህም የተባለበት ምክንያት የአረብ ኤሜሬትስ በሕግ የሶማሊያ አካል በሆነችው ፑንትላንድና ሶማሌ ላንድ ላይ እንቅስቃሴ በመጀመራቸው ነው:: ኬንያም በበኩሏ በአካባቢው ያለው እንቅስቃሴ የሚያሳስብ መሆኑን አሰምታለች::

የመን ውስጥ የሚደረገው ጦርነት የየመን ህዝብ ጦርነት አይደለም፡፡ ኢራን በአንድ ወገን፣ ሳውዲ አረቢያ በሌላ በኩል በአሜሪካ ድጋፍ የሚካሄድ የእጅ አዙር ጦርነት ነው፡፡ የመን ውስጥ ሃያ ሚሊዮን ህዝብ በረሃብ ላይ ይገኛል፡፡ አስራ አንድ ሚሊዮን ህፃናት በሞት እና በሕይወት አፋፍ ላይ ናቸው፡፡ የመን የምትባል ሀገር ጠፍታለች፡፡ ስንት ሺ ሞቷል ስንት ሺ ቆስሏል፤ የእጅ አዙር ጦርነቶች እየተበራከቱ ሲሄዱ ኢትዮጵያ ከእያንዳንዱ ልትማር ይገባል፡፡ ከሱዳን እና ከግብጽ ጋር ኢትዮጵያ ያላት የተፈጥሮ ቁርኝት ማለትም ኢትዮጵያ ለሁለቱ ሀገሮች የህልውና ጥያቄ ስለሆነች የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርብ ይከታተላሉ፡፡ በሚታይም በማይታይም መንገድ ዘወትር በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት አይቆጠቡም፡፡

ኤርትራና ኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲያቸው እንዳይጋጭ ከባድ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ ኤርትራ በየመን ጦርነት ላይ አቋም ይዛለች፡፡ በሌሎችም በአካባቢው ካሉ የአረብና የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ጋር አቋም አላት፡፡ ኢትዮጵያም እንደዚሁ አቋም አላት፡፡ ይህ አቋማቸው ሁል ጊዜ ተመሳሳይ ሊሆን አይችልም፡፡ እይገባምም:: ልዩነቶችን ማጥበብና ማጥፋት በማይቻልባቸው ሆኔታዎች አንዱ የአንዱን አቋም አክብሮ የመኖር ባሕል ሊገነቡ ይገባል፡፡

ከኤርትራ ብዙ ስደተኞች ነን የሚሉ ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ናቸው:: ከዚሁ ጋር ተያይዞ ብዙ የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎች ኢትዮጵያ ምድር ገብተው በኤርትራ መንግሥት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለማሰማት ቢሞክሩ ምንድነው የሚደረገው? ከኢትዮጵያ አኩርፈው ወንጀል ፈጽመው ኤርትራ ለሚገቡ ምን አይነት አቋም ነው ኤርትራ የምትወስደው? በንግድም፣ በሌሉችም ሁለቱን ህብረተሰቦች በሚያገናኙ ጉዳዮች ሁሉ አለመግባባት እንዳይፈጠር ውይይት ተደርጎ ወረቀት ላይ የሰፈረ ስምምነት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በሁለቱም በኩል ሊኖር የሚገባው ግዴታና ኃላፊነት በዝርዝር መጠቀስ ይገባዋል::

በአጠቃላይ የውጭ ፖሊሲን በተመለከተ በዚህ ሙያ ልምድ ያላቸው የፃፉ፣ የተመራመሩ አዋቂዎች ያሉበት እንደ አስፈላጊነቱ የሚሰበስብ ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢያቋቁሙ ይረዳቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡

መደመደሚያ::

በመጨረሻም የሀገር ውድቀት የሚመጣው በአንድ ጊዜ አይደለም ቀስ በቀስ ነው፡፡ በየጊዜው የሚከሰቱ ጉዳዮች ውጤት ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ከባድ ሥጋት ላይ ነች ዛሬ ክልሎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ቁጥጥር ውጭ እየሆኑ ከፌዴራሊዝም ያለፈ ስም የለሽ ሥርዓት ውስጥ ተሸጋግረዋል፡፡ አብረው የኖሩ በአንድነት ታሪክ የሰሩ፣ በእምነታቸው በባህላቸው ተሳስረው የኖሩ፣ ተጋብተው ተዋልደው የኖሩ፣ ቢጣሉም ልዩነታቸውን ሳያስቀድሙ ሀገርን ጠብቀው ሞቱን በአንድነት ሞተው ስቃዩን፣ ችግሩን ተደጋግፈው አሳልፈው ኢትዮጵያን አንዳልገነቡ ሁሉ ዛሬ በመጣው የዘር ፖለቲካ ምክንያት ጋብቻ በዘርቆጠራ፣ የትምህርትቤት ጓደኝነት በዘር ቆጠራ፣ እየሆነ በመምጣቱ የሚያስተሳስሩን እሴቶች እየጠፋ ለመራራቅ አመቺ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡  የተደራጁ ተዋጊ ኃይሎች በግልፅ አይታዩም፡፡ አሁን ጸጥታውን የሚያደፈርሱት ትንንሽ ቡድኖችና የማይታዩ ሃይሎች ናቸው፡፡ የተደራጀ ኃይልን መቋቋም አያስቸግርም ግን የተበታተኑ ቡድኖች ግን አመጽና ወንጀል ለመቋቋም አስቸጋሪ ነው፡፡  ከሥር ጀምሮ ያሉ የመንግሥት ተቋሞች እየፈረሱ ከማዕከላዊ መንግሥት ቀርቶ ከክልላዊ አመራሮችም ቁጥጥር ውጪ ሲሆኑ፣ የታጠቁ ግለሰቦች ተከታይ እየመለመሉ አካባቢያቸውን መቆጣጠር ሲጀምሩ ሥልጣን እየጣማቸው የመንግሥት ሃይልን መቋቋም ሲጀምሩ ሊገቱ የማይችሉ የሰፈር ጦር መሪዎች (War Lords) ይፈጠራሉ፡፡ ይህንን ክፍተት ያዩ ሌላ አጀንዳ ያላቸው፣ መሳሪያና ድጋፍ በገፍ ያቀርባሉ፡፡ ክፍተቱ እና ጣልቃ ገብነቱም  እየሰፋ ሲሄድ የራሳችው ውጊያ መሆኑ ቀርቶ የሌሎች ውስጣዊ ኃይሎችና የባዕዳን ጉዳይ ፈፃሚዎች ይሆናሉ:: ጦርነቱ ኃይል መጠቀም ሲጀመር ሰላማዊ ህዝብና አማፂያንን መለየት ያስቸግራል፡፡ ቁጣውና ኩርፊያው ይበራከታል፤ ጠላትም ይጠቀምበታል፤ የዚህንም ሂደት መተንበይ ያስቸግራል፡፡

እዚያ ሳንደርስ ሳይቃጠል በቅጠል የምንለው ለዚህ ነው፡፡ መስረታዊ የስርአት ለውጥ ጊዜ የሚስጠው አይደለም:: የዘመናት ትርምስ ዛሬ ወሳኝ ደረጃ ላይ ደርሶአል:: ህዝብ በቀጥታ የተሳተፈበት ህገመንግስትን ማውጣት፣ በዘር ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝምን ማጥፋት፣ ማዕከላዊ መንግሥትን ማጠናከር፣ በአካባቢያችንና ከዚያም ባሻገር ካሉ አገሮች ጋር የተጠና ሚዛናዊ ወዳጅነት መፍጠር፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ተፈርተው፣ ተከብረው የመልካም አስተዳደርና የአብሮነት ኑሮ ምሳሌ ሆነው የጥቁር ህዝብ ተስፋና ኩራት እንደነበሩ ሁሉ ዛሬም እንደሚሆኑ ሊያረጋግጡ ይችላሉ፡፡

በዶ/ር አብይና በመንግሥታቸው የሚፈጸመውንና የታቀደውን ባለማወቅ ተሳስቼ ከሆነ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ዓላማችን ለማገዝ፤ የተለየ ሐሳብን ለማቅረብና ለማንሸራሸር እንዲረዳ በዕድሜና በተሞክሮ ከበለፀግን፤ ስልጣንና መታየትን ከማንፈልግ ወገኖች በቅንነት የቀረቡ  ጥናቶችና ሐሳቦች ናቸው፡፡

አመሰግናለሁ፡፡

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0