“Our true nationality is mankind.”H.G.

በደኅንነት ተቋም ውስጥ ተገኘ የተባለው አደገኛ መርዝ የቀድሞ ምክትል ዋና ዳይሬክተርን እንደሚመለከት ተጠቆመ

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ተገኘ የተባለው አደገኛ መርዝ በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀሎች የተጠረጠሩትን የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተርን በቀጥታ ይመለከታቸዋል የሚል እምነት እንዳለው፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤት ተናገረ፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቆች በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ፣ ደንበኛቸውን ስለመርዙ ጠይቀዋቸው ከአሸባሪዎች እጅ መያዙን እንደነገሯቸው ለፍርድ ቤት ገልጸዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት እንደተናገረው፣ ምክትል ዳይሬክተርና የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ያሬድ ዘሪሁን ሳያውቁ መርዙ አይቀመጥም፡፡ ለምን እንደተቀመጠና እንዳልተወገደም ያውቃሉ ብሎ እንደሚጠረጥርና በቀጣይ ምርመራ ሊደረስበት እንደሚችል እምነቱን ገልጿል፡፡

መርማሪ ቡድኑ አደገኛ የተባለውን መርዝ በሚመለከት አቶ ያሬድ ዘሪሁንን በቀጥታ እንደሚመለከታቸው ጥርጣሬ እንዳለው ለፍርድ ቤቱ ያስረዳው፣ ቀደም ብሎ በዋለው ችሎት ተፈቅዶለት በነበረው 14 ተጨማሪ ቀናት ውስጥ የሠራውን የምርመራ ሒደት በሚመለከት ሲያስረዳ ነው፡፡

በተሰጠው 14 ቀናት ውስጥ ተጠርጣሪው የአራት ምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸውን 60 ግለሰቦች ከጎንደር፣ ከባህር ዳርና ከሻሸመኔ ማነጋገሩን ገልጿል፡፡ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ከማፍራት ጋር በተያያዘ በዱከም በአቶ ያሬድና በባለቤታቸው ስም፣ በባለቤታቸው ወንድምና እህት ስም የተመዘገበና ከ140 እስከ 200 ካሬ ሜትር የሚሆን ቦታና የይዞታ ማረጋገጫ ማግኘቱን፣ በለገጣፎና በለገዳዲ በአቶ ያሬድና በባለቤታቸው ስም፣ በባለቤታቸው ወንድም አባት ስም መሬት መገኘቱን፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በአቶ ያሬድና ባለቤታቸው 94 ካሬ ሜትርና 400 ካሬ ሜትር ቦታ መገኘቱን አብራርቷል፡፡ ዱከም ከተማ ውስጥም በአንድ ሚሊዮን ብር የተሸጠ ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃም መገኘቱን አክሏል፡፡

Related stories   በሃሰተኛ ሰነድ ሾፌር ሆኖ የጫነውን ከ6 ሚሊዮን በር በላይ የምያወጣ ቡና የዘረፈው ዕምነት አጉዳይ ተፈረደበት

መርማሪ ቡድኑ የቀሪ ምስክሮችን ቃል መቀበል፣ የተገኘውን ከባድ መርዝ በሚመለከት ማጣራት፣ የተገኙትን በርካታ የመሬት ይዞታዎችና ቤቶች ለሦስተኛ ወገን መተላለፍ አለመተላለፉን ማጣራት፣ በዘመዶቻቸው ስም የተያዘው ቦታና ይዞታ ከተጠርጣሪው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጣራትና የተገኙ ሌሎች ጥቆማዎችን ወደ ማስረጃነት መቀየር እንደሚቀረው ገልጾ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ተፈቅዶለት በነበረው 14 ቀናት ውስጥ ምንም ያሰባሰበው አዲስ ማስረጃ እንደሌለው በመግለጽ መከራከሪያ ነጥቦቻቸውን ያስረዱት የአቶ ያሬድ ጠበቆች፣ ሰብስቤያለሁ ብሎ ለፍርድ ቤቱ የተናገረውም ደንበኛቸው ከተጠረጠሩበት ጉዳይ ጋር እንደማይገናኝ ተናግረዋል፡፡ በደንበኛቸው ላይ የጥርጣሬ መነሻ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል የሚል እንደነበር ያስታወሱት ጠበቆቹ፣ ለፍርድ ቤቱ ምርመራ አካሂጃለሁ በሚል ያቀረበው የምርመራ ሥራ ወደ ሙስና ያመዘነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ቀደም ብሎ በነበረው የክርክር ሒደት እንደሚሠራቸው ገልጾ ያቀረባቸውንና ፍርድ ቤቱም የፈቀደለት የአስከሬን ምርመራ ውጤት፣ የባለቤታቸውን እናት የሀብት ምንጭ፣ ያከራያሉ ስለተባሉት ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ነገሮች እንደነበር ያስታወሱት ጠበቆቹ፣ የጀመረውን ትቶ ሌላ ነገር ላይ የሠራው ለጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Related stories   በሃሰተኛ ሰነድ ሾፌር ሆኖ የጫነውን ከ6 ሚሊዮን በር በላይ የምያወጣ ቡና የዘረፈው ዕምነት አጉዳይ ተፈረደበት

በተቋሙ ውስጥ ተገኘ የተባለውና ደንበኛቸውን በቀጥታ ይመለከታል የተባለው መርዝን በሚመለከት አቶ ያሬድን እንዳነጋገሯቸው የገለጹት ጠበቆቹ፣ መርዙ በወቅቱ ከአሸባሪዎች ላይ የተያዘ መሆኑን እንደነገሯቸው ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በደንብ እንዲያብራሩትና ከየት እንደተኘ እንዲገልጹ ሲጠይቃቸው፣ በአሸባሪነት ተጠርጥረው ተይዘው ከነበሩ ተጠርጣሪዎች ላይ በርካታ ነገሮች ስለተሰበሰቡ፣ መርዙም ምናልባት ከተሰበሰቡት መካከል ሳይሆን እንዳልቀረ ለማለት ፈልገው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ቤትንና መሬትን በሚመለከት አንስቶ የተከራከረው ቋሚና የማይንቀሳቀስ ንብረት በመሆኑ የሚፈልገውን ሰነድ ከሚመለከተው የመንግሥት ተቋም መውሰድ እንደሚችል ጠቁመው፣ ደንበኛቸው ባለሥልጣን ስለሆኑ ሀብት እንዳያፈሩ የሚከለክል ሕግ ስለሌላ ማፍራት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የቤተሰቦቻቸው ሀብት ከእሳቸው ጋር ስለማይገናኝ ለክርክር መቅረቡ ተገቢ እንዳልነም አክለዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ እንደሚሠራ ገልጾ ለፍርድ ቤቱ ያስመዘገበውን ትቶ፣ አዳዲስ የወንጀል ግኝት ፍለጋ ስለሚሄድ እየሠራ ባለመሆኑ፣ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድለት እንደማይገባም ተቃውመው ተከራክረዋል፡፡ በምርመራ ወቅት ስላገኛቸው ይዞታዎች፣ ቦታዎችና መሬቶችን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡን እንዲመለከትላቸውም ጠበቆቹ ጠይቀዋል፡፡

Related stories   በሃሰተኛ ሰነድ ሾፌር ሆኖ የጫነውን ከ6 ሚሊዮን በር በላይ የምያወጣ ቡና የዘረፈው ዕምነት አጉዳይ ተፈረደበት

መርማሪ ቡድኑ ለሁለተኛ ጊዜ በተሰጠው የመከራከሪያ ዕድል በሰጠው ምላሽ ተገኙ ከተባሉት ቤቶች፣ ቦታዎችና መሬቶች ጋር በተያያዘ ሕጋዊ ሰነዶችን ማግኘቱን፣ ተጠርጣሪው ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ቤተሰቦቻቸው ሀብት እንዲያፈሩ ማድረጋቸውንና እሳቸውም ቢሆን ከገቢያቸው በላይ ሀብት ያፈሩት ሥራ ከጀመሩ ከ2000 ዓ.ም. ወዲህ በመሆኑ፣ ሥልጣናቸውን ያላግባብ ተጠቅመው ያገኙት ነው የሚል ጥርጣሬ እንዳለው አስረድቷል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡን አስቀርቦ ከተመለከተ በኋላ መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው ጊዜ ሥራውን ማከናወኑን መገንዘቡን በመግለጽ፣ የተጠርጣሪው ጠበቆች ያቀረቡትን የመከራከሪያ ነጥቦችና የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ የምርመራ ቡድኑ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ 12 ቀናት በመፍቀድ ለጥር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

reporter amharic

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0