“Our true nationality is mankind.”H.G.

ኦሮሞ ነቃ!!ወደ ሽፍታነት የተቀየረው ኦነግ ሸኔ በሞት አፋፍ፤ የጃዋርና በቀለ ገርባ የህልም እቅድ- ሪፖርታዥ

አደራዳሪዎች፣ ክልሉን የሚመራው ፓርቲ፣ መንግስት፣ ነዋሪዎች፣ ህዝብ፣… የዳውድ ኢብሳ ኦነግ ሸኔ ምን እንደሚፈልግ ሊገባቸው እንዳልቻለ ነው የሚናገሩት። ለምን በሰላማዊ መንገድ ወደ ምርጫ እንደማይሄዱ መረዳት አልተቻለም። ከሁሉም በላይ አሁን ግንባር ፈጥረው ከህወሃት ጋር መስራታቸው እንዲተፉ እያደረጋቸው ነው …

ከአስተያየት ሰጪዎች አንዱ

የአቶ በቀለ ገርባ ከተለመደው የትግል መድረካቸው ዙሪያ አለመታየታቸው መነጋገሪያ ሆኗል። ጠፍተዋል እንዳይባል ባልተለመደ ሁኔታ የክተት አዋጅ ሲያውጁ ይሰማሉ። ኦፌኮ ከሚያምነው ውጪ የተሳከረ ፖለቲካ እያራመዱ ነው። አዳማ ላይ ከህዝብ ጋር እንደወትሮው በመድረክ አይታዩም። አሁን የሚታዩት ከጃዋር መሐመድ ጋር ሲሆን ውሏቸውና ቀልባቸው ወደ ትውልድ ቀዬያቸው ውለጋ ሆኗል። ይህ አካሄዳቸውና ከጃዋር ጋር የገቡበት ፍቅር የት ይወስዳቸው ይሆን ወይም ….

እብሪትና የፖለቲካ ስልጣን ጥማት ስውር አጀንዳ እንደ እስስት የሚቀያይረው ጃዋር መሐመድ እንዲህ አለ። ” ከግራኝ መሐመድ ቀጥሎ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆንኩ ሰው እኔ ብቻ ነኝ” ጃዋር በተለያዩ ጊዚያት ልክ እንዳሻው መረን በወጣ አነጋገር ” አፈርሳለሁ፣ እነቅላለሁ፣ እተክላለሁ፣ እቆርጣለሁ …” በማለት በሚመራው ሚዲያ እንዳሻው የሚናገረው ከዚህ ራሱን ከሰቀለበት መሰላል ላይ ሆኖ ነው።

የፖለቲካ ስልጣን እንደማይፈልግ የሚናገረው ጃዋር በተግባር አገሪቱን የመምራት ህልሙን በስውር ነገር ግን በግልጽ እያራመደ መሆኑንን በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ። መንግስትም ይህንን ጠንቅቆ ያውቃል። መንግስት ቸልታን የመረጠው ግን ጃዋር አግባብ ባለው የምርጫ ሂደት ህልሙን ማሳካት እንደማይችል ጠንቅቆ ስለሚረዳ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን አጥብቆ የሚጠላው ጃዋር መንግስት የተረዳውን የምርጫ ስሌት በወጉ ስለሚገነዘብ ወደ ስልጣን የሚወስደውን ጨዋታ በሚዲያና በጠለፋ በተለያዩ መልኮች ሲያካሂድ መቆየቱን፣ አሁንም እያካሄደ መሆኑን ታውቋል።

ስማቸውን ለጊዜው መጥቀስ ያልፈለጉ የኦፌኮ አመራር ” አካሄዱን እናውቃለን። ዝምታን የመረጥነው ጨዋታው ከሃሳብና ራስን ከትዝብት ከመጣል የሚያልፍ አይሆንም” ሲሉ ጠቅለል ያለ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በቀለ ገርባ – ታላቁን ምክር ረግጠው የሚባትቱ ፖለቲከኛ

አቶ በቀለ ገርባ በህዝብ የሚወደዱና ክብር የሚሰጣቸው፣ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ መንገድ እንዲመሩ ከሚታሰቡት ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ነበሩ። በእስር ዘመናቸውና ከዛ አስቀድሞ ህዝብ ያቀፋቸው ከስሜታዊነት የራቁ በሳል ሰው ስለመሆናቸው አብዛኞች የሚመሰክሩላቸው ታጋይም ነበሩ። ከእስር ተፈተው ወደ አሜሪካ ካቀኑ በሁዋላ ግን ሌላ ሰው ሆኑ። ይህ ሁሉ ከመሆናቸው በፊት እዛው አሜሪካ ምድር አንድ ታዋቂ የሕዝብ ልጅ መከራቸው።

” አንተ ትልቅ ሰው ነህ። ሕዝብ ይወድሃል። ሕዝብ ልዩ ቦታ ይሰጥሃል። የዲያስፖራው ፖለቲካ ቅዠት የተቀላቀለበት በመሆኑ ተጠንቀቅ። ሁለት ምርጫ ነው ያለህ። ህዝብ ወይም በቅዠት የሚነዳ ሃይል። ስትናገር፣ ስብሰባዎች ላይ አስተያየት ስትሰጥ ይህንን ምርጫህን አስልተህ ይሁን። ህዝብን ካልመረጥክ ችግር ውስጥ ትገባለህ። አሁን ያለው አቀባበልና ግርግር እንዳያሳስትህ። ሁሌም አገር ቤት ያለውን ህዝብህን አስብ ”

Related stories   “የግድቡ ግንባታ ውሃ ይቀንስብኛል የሚለው የግብጽ ጩኸት የማጭበርበሪያና የተለመደ የሃሰት ክስ ነው››
Image result for jawar mohammed v bekele gerba
ፎቶ ቪኦኤ

በቀለ ገርባ ይህንን ምክር ከበርካታ ማስረጃዎችና እውነቶች ጋር ሲነገራቸው ጠንቅቀው ሰምተዋል። ይህንን ምክር የለገሳቸው ሰው ዛሬ ” ነግሬው ነበር። ስምቷል። ግን በነፋስ ተወሰደ። አሁንም ግን የመመለስ እድል አለው” በሚል ሃዘን የተሞላበት አስተያየት ሰጥተዋል።

አዳማ ላይ እጅግ ሰፊ ህዝብ አቅፏቸው የኖሩት በቀለ ገርባ ሚኖሴታ ደርሰው ሲያበቁ ጃዋር ጉያ ውስጥ ገቡ። እንደውም ጠፉ። ከጠፉበት ብቅ ሲሉ አዲስ በቀለ ሆኑ። በማይታወቁበት የማክረር ፖለቲካ ተጠምቀው ተከሰቱ። ኦፌኮ ከሚታወቅበት የፖለቲካ እምነትና የአብሮነት ስሜት አፈንግጠው ወጡ። ፓርቲያቸው በዚህ አካሄድ ደስተኛ ባይሆንም ዝምታን መምረጡ ሆን ተብሎ የተመረጠ አካሄድ እንደሆነ ያነጋገርናቸው አመልክተዋል።

Image result for መረራ ጉዲና አምቦ
መረራ ጉዲና በአምቦ ከእስር ከተፈቱ በሁዋላ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ሲቀበላቸ ሲያነቡ

በዝግ በተደረገ ስብሰባ የኦፌኮን ጸሃፊ አቶ አዲሱ ቡላላን እና ክቡር መረራ ጉዲናን ከርብቶ ኦፌኮን ከነ ፕሮፌሰር ሕዝቄል እጅ፣ የአነ ጃዋር ንብረት ለማድረግ በተወሰነ ሰዓታት ጊዜ ውስጥ መረራ ሪፖርቱ ደረሳቸው። ጀርባቸውን ጥንቅቀው የሚያውቁት መረራ ጉዳዩ በፈገግታ አለፉት። ሩጫው የትም እንደማያደርስ ሲረዱ ዝምታን መረጡ።

ሁሉም አልፎ ለውጡ ይፋ ከሆነ በሁዋላ አቶ በቀለ ወለጋን አዘወተሩ። በቄሮ አደረጃጀት ውስጥ እጅግ መጠነኛ ተሳትፎ አላቸው የሚባሉት በቀለ የትውልድ ስፋራቸው በሆነው ወለጋ መመላለሳቸው፣ ውለው ማደራቸው፣ ከጃዋር ጋር ሚኖሴታ ተጀምሮ ዛሬ ድረስ በቆሎ አብሮ እስከመጋጥና የካው ቦይ ልብስ እየተላበሱ በፌስ ቡክ እንደ አፍላ ጎረምሳ መታየት ማብዛታቸው ጉዳዩን ለሚከታተሉት ከበቆሎ አገዳና ከካው ቦይ ባርኔጣ የዘለለ ትርጉም አለው። ከዚህም በላይ በይፋ በሚወደዱበት መኖሪያቸው አዳማ ስለምን ተሳትፏቸው ተመናመነ፣ በፓርቲያቸው ኦፌኮ ውስጥስ ለምን ሚናቸው ደበዘዘ የሚሉት ጉዳዮች የሃሳቡ ማጠናከሪያ ካስማዎች እንደሆኑ ያነጋገርናቸው ይናገራሉ።

በወለጋ የተስፋፋው ሽብር፣ ግድያ፣ ዘረፋና ዓላማው በውል የማይገለጽለት ስውር ሩጫ ጋር ተያያዥነት አላቸው የላቸውም የሚለው ጉዳይ ላይ በቀጥታ አስተያየት ለመስጥት የማይደፍሩት ክፍሎች፣ ” ነገር አለ። ነገሩ ይታወቃል። ግን ጊዜ ያሸዋል” ሲሉ በደምሳሳው ያልፉታል። በቀለ ገርባ ነገሮች መልካቸውን በቀየሩበት ወቅት ወደ ትውልድ ስፍራቸው ማቅናታቸውና በቅርቡ በጃዋር አዲስ መጽሄት ” ከዚህ በላይ መዘግየት ለአምባ ገነንነት መንገድ ይከፍታል” በማለት መናገራቸው ግን ትርጉሙ የዶክተር አብይን መንግስት እንብላው ስለመሆኑ የሚስማሙ ጥቂት አይደሉም። አቶ ጃዋርም ቢሆን ” ስጋቴ አብይ አሕመድ አምባ ገንን እንዳይሆን ነው” ሲል በተደጋጋሚ ሲናገር መክረሙምም ይታወሳል።

በመጠኑም ቢሆን በምስራቅ ሃረርጌ ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ተሰሚነት ያላቸው አቶ ጃዋር በኦነግ በኩል ፍጹም ተቀባይነት የላቸውም። ዳውድ አስመራ እያሉ እጅግ ከፍተኛ የሚዲያ ቦንብ ሲያወርድባቸው የነበረው ጃዋር በወለጋ አካባቢ ህዝብም ቢሆን አይወደድም። አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ወለጋ ውስጥ እሳቸውንና አቶ ለማ መገርሳን የመግደል እቅድ እንዳለ መረጃ በመኖሩ ወደ ወለጋ እንደማይሄዱ መግለጻቸውን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ትርጉም በማሳት ለወለጋ ህዝብ ተቆርቋሪ መስሎ የቀረበው የእንቀራረብ ማመልከቻ መሆኑንን ነው። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን አቶ በቀለን እየተጠቀመ መሆኑ ግን ጎልቶ ይወጣል። ለይቶ እሳቸውን የያዘበት መንገድ እና ዶክተር አብይን ነጥሎ የሚቃወምበት አግባብም የስውር ፍላጎቱ መነሻ መሆኑንን በሪፖርቱ ያነጋገርናቸው ሰዎች ሃሳብና እምነት ነው።

Related stories   የኢትዮዽያ የቁርጥ ቀን ልጅ "ስለአባይ እውነቱን እንካችሁ" – መካ አደም አሊ

በጠወለገ ተስፋ፣ በተመናመነ እድል፣ እየሞተ በሚሄድ የጽልመት ጉዞ ውስጥ ሆኖ ኤርትራ ሲዳክር የኖረው የዳውድ ኢብሳ ሸኔ ለውጡ ነጻ አውጥቶት አገር ቤት ከገባ በሁዋላ እየወሰደ ያለው እርምጃ የሱ ብቻ አይደለም። ከጀርባው አንድ የተደራጀ አጋዥ ሃይል አለው። ይህ ሃይል ለውጡ የጎረበጠው ሲሆን እጁም ኪሱም ሰፊ ነው። በዚሁ ሰፊ እጁና ኪሱ የዘረጋው መስመር ዳውድ ኢብሳን በቅጡ አይሰማም የሚባለውን ሃይል ፈጥሯል።

ይህ በማጅራት መቺነት፣ በግድያ፣ በአፈና፣ በዝርፊያ የተሰማራ ሃይል በየጫካው ማሰልጠኛ ከፍቶ ህጻናትን እየመለመለ ሃይል ያከማቸውና የታጠቀው በዚሁ ገንዝብ በነፋው፣ መሳሪያ እስከ አፍንጫው ባለው ሃይል መሆኑ ቢታመንም አሁን አስጊ የሆነው ዳውድ ይህንን ሃይል መቆጣጠር የማይችልበት ደረጃ መደረሱ እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ይናገራሉ። በድርድር ላይም ዳውድ ከሳቸው ቁጥትር ስር ያፈነገጡ ሃይሎች መኖራቸውን እንደተናገሩ በስፍራው የተገኙ ይናገራሉ። እና ይህንን ሃይል የሚመራውና የሚያዘው ማን ነው ለሚለው ምላሽ ማፈላለግ የኦሮሞ ድርጅቶች ሁሉ ፈንታ ነው።

የአብይ በትር

ብዙም ይፋ አልሆነም እንጂ በወለጋና አካባቢው ሆነው መንግስትን ሲያዋርዱ፣ ክተት ሲያውጁ የነበሩ፣ ታዘው የአመጽ ጥሪ ሲያስተጋቡ የነበሩ ተለቅመዋል። በርካታ ህጻናት ከነ ትጥቃቸው እጅ ሰጥተዋል። የተያዙት በሙሉ በፈቃዳቸው መረጃ ሰጥተዋል። መዋቅራቸው፣ አደረጃጀታቸው፣ አፈጣጠራቸውና አላማቸው በሙሉ ታውቋል። ይህ ለሕዝብ ይፋ የሚሆነው ኦፕሬሽን እስካሁን ይፋ እንዳይሆን ሆን ተብሎ ቢደረግም ሕዝብ መሮታል። ” አዋረዳችሁን፣ ከወንድሞቻቸን ጋር አጋደላችሁን” በሚል ቅሬታ እያሰማ ነው።

ከኦፕሬሽኑ በላይ ግን በፖለቲካው መስመር ይህንን ሃይል ክፉኛ የሚያሽመደምድ ስራ ተሰርቷል። ሰፊ ቁጥር ባለው በመካከለኛው ኦሮሚያ ቀውሱን ለማራባት የተያዘው እቅድ ሙሉ በሙሉ በሕዝብ ተቀባይነት አጥቷል። ከዚሁ ጉዳይ ጋር የሚሰሩ እንዳሉት ሰማኒያ አምስት በመቶ የሚሆነው የቄሮ ሃይል ድጋፍ ከልክሏል። እጅግ ውስን የሁኑ ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ጠይቋል። ጥቂቶች ግራ ተጋብተዋል።

የዳውድ ኢብሳ አጣብቂኝ – ጠቅላላ ጉባኤ፣ ህዝብና ሽማግሌዎች

ዳውድ ኢብሳ አገር ቤት ከገቡ በሁዋላ የተወጠሩበት አንዱና ትልቁ ችግር ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠሩ መወትወታቸው ነው። ጠቅላላ ጉባኤው ከተካሄደ አዲስ ምርጫ ይካሄዳል። አዲስ ምርጫ ከተካሄደ ዳውድ በድርጅቱ ህገ ደንብ መሰረት መቀጠል አይችሉም። ይሰናበታሉ። በጠቅላላ ጉባኤው ውስጥ የሚሳተፉት አብዛኞቹ የሸዋ ኦሮሞ በመሆናቸው የዳውድን ካቢኔ ያራግፉታል። ለዛጎል መረጃ የሰጡ የድርጅቱ አባላት እንዳሉት ዳውድ የድርጅቱ ህግና ደንብ የሚያዘው ሁለት የምርጫ ዘመን ስምንት ዓመት ቢሆንም፣ አስራ ዘጠኝ ዓመት በመሪነት ቆይተዋል። ስለዚህ እጣ ፈንታቸው በክብር መወረድ ነው።

Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

አሁን ድርጅቱን የሚመሩት የአቶ ሌንጮ ለታ ወንድም የሆኑትን አባ ጫላ ለታን ጨምሮ ሁሉም የአንድ አካባቢ ልጆች መሆናቸው ቅሬታ ያስነሳና የድርጅቱ ትግል አንድ እርምጃ ወደፊት እንዳይራመድ ያደረገ የአድገቱ ጋንግሪን ነው። እናም አባላቱ እንደሚሉት ይህ የቤተሰብ ይዘት ያለው ድርጅት መላውን ኦሮሞ አይወክልም የሚለው የኖረ ቅሬታ ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ሊሰጥ የመስመር ዝግጅት እያደረገ ነው።

በኦነግ ስም የሚጠሩና ተበጣጥሰው የነበሩ አካሎች በሙሉ አንድ ለመሆን ተስማምተው ፊርማቸውን ካኖሩ በሁዋላ አቶ ዳውድ ማፈንገጣቸው አሁን ላይ ከፍተኛ ችግር እንደፈጠረባቸው የሚናገሩ ሌሎች ክፍሎች ደግሞ ትልቁ ፈተና ከፊት ለፊት መብራት አብርቶ መቆሙን ያስረዳሉ።

እነዚህ ክፍሎች እንደሚሉት በሽግግሩ ወቅት ኦነግን ይመሩ የነበሩት አቶ ገላሳ ዲልቦ አገር ቤት መግባታቸውን ነው። የነቀምቴ ተወላጅ የሆኑት ገላሳ ዲልቦ ኦነግ የሚለውን ስም በይፋ የመውረስ ህጋዊ መብት አላቸው። ከዚህም በላይ አገር ቤት ገብቶ በሰላማዊ መንገድ ከሚሰራው ከእነ ሃይሉ ጎንፋ ኦነግ ጋር ወደ ስምምነት የሚቀርቡበት መስመር ላይ ናቸው።

አባ ነጋ እና አቶ ገላሳ ህብረት ከፈጠሩ በድፍን ሸዋ፣ ባሌና አርሲ ተቀባይነት ያለው የአባ ነጋ ወይም የነ ጀነራል ሃይሉ ጎንፋ ኦነግ በአቶ ገላሳ አማካይነት ወለጋና ሃረር ላይ ሰፊ ህዝባዊ መሰረት እንደሚያጎናጽፋቸው ጉዳዩን የሚከታተሉ እየገለጹ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ኦቦ ለማ መገርሳ ፓርቲያቸው ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት በዝግ ከስምምነት መድረሳቸውና በሂደት ወደ ውህደት የመሄዳቸው ጉዳይ የማይቀር በመሆኑ የዳውድ ኦነግ ሸኔ፣ እነ ጃዋርም ሆኑ ወዳጆቻቸው ከምርጫ በዝረራ እንደሚሸነፉ ከውዲሁ ሳይታለም የተፈታ ሃቅ ነው።

ድፍን ጅማን፣ ሸዋን፣ እንዲሁም መሃሉን የመመልከ ያህል የሚወደዱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን እንደመጡ ” በፓርላማ ዳር ቁጭ ብለው ዘወትር ስለማክረር የሚያወሩ ይኖራሉ” እንዳሉት የዳውድ ኢብሳ ኦነግ በጥቂት ወንበር ፓርላማ ገብቶ መቃወም፣ ማክረር፣ የመጨረሻ ወርቃማ እድሉ እንደሚሆን ጥርጥር የለም።

ይህንን የተገነዘቡት ሃይሎች አሁን የመረጡት የነውጥ መንገድ በድርድር የሆነ ነገር ለመያዝ ካለ ስሜት በ፣እነሳት መሆኑ አሁን አሁን በመላው ኦሮሞ ዘንድ ግልጽ እየሆነ በመሄዱ፣ ሽምግለና የጀመሩት ሃይሎችም በዳውድ በኩል በቂና አጥጋቢ እንዲሁም ግልጽ ያለ ምላሽ፣ መከራከሪያ እንዲሁም የድርድር ሃሳብ እንዳላገኙ እየተሰማ ባለበት በአሁን ወቅት የዳውድ መጨረሻ ወዴት እንደሚሆን ለመገመት አያስቸግርም።

ይቀጥላል

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0