“Our true nationality is mankind.”H.G.

”አፈረሱት አሉ ውቤ በረሃን…” ትንቢት ነበር?

ወንዶቹ በ1950ዎቹ የዘመኑ ፋሽን የነበረውን ኮሌታው ረዘም ባለ በሚያብረቀርቅ ሸሚዝ ደምቀው፣ አፍሯቸውን ከፍክፈው፤ ሴቶቹም በጊዜው ገትር በሚባለው ጉርድ ቀሚስ ሸሚዛቸውን ሻጥ አድርገው፣ ታኮ ጫማቸውን ተጫምተው፣ አፍሯቸውን አበጥረው ወደ ደጃች ውቤ (ውቤ በረሃ) አሰገደች አላምረው ቤት ጎራ ይሉ እንደነበር ፀሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ያስታውሳሉ።

“ከዚያማ የምሽቱ ህይወት ይጀመራል። ሙዚቃው ያለማቋረጥ ይንቆረቆራል። እኛም በምናውቀው ሩምባ፣ ቡጊውን ለመደነስ እንወናጨፋለን” ይላሉ።

ቯልስ ለመደነስ ሙከራ ቢያደርጉም መጠጋጋትን ስለሚሻ በጊዜው የነበሩ ሴቶች ይመርጡት እንዳልነበር ሲያስታውሱ ይስቃሉ።

የዱሮ አራዳ የሚባሉት የውቤ በረሃ አድማቂዎች እንደነበሩ አያልነህ ትውስ ሲላቸው በተለይ በጊዜው “ጀብደኛ” ይባል የነበረውና በቅፅል ስሙ ማሞ ካቻ ተብሎ ይጠራይ የነበረው ግለሰብ ስም ከአዕምሯቸው አይጠፋም።

ወደ ውቤ በረሃ መዝለቅ የጀመሩት ገና ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪና የ16 ዓመት አፍላ ጎረምሳ እያሉ ነበር።

በዚያን ጊዜ 1 ብር ይሸጥ የነበረውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ መጠጣት አቅማቸው ስለማይፈቅድ በ25 ሳንቲም ጠጃቸውን ጠጥተው ማስቲካ እንደሚያኝኩ እየሳቁ ይናገራሉ።

ይሄ ትዝታ እድሜ በጠገቡት ሰዎች ብቻ ሳይሆን በእድሜ ባልገፉት እንደ ታዋቂው ሙዚቀኛ ፍሬው ኃይሉ ልጅ ባሉትም የሚታወስ ነው። ዳዊት ፍሬውም ከትውልድ ትውልድ ተላልፎ በእሱ እድሜ በኮንጎ ነፃነት ታጋይ ስም ፓትሪስ ሉሙምባ የተሰየመውን የውቤ በረሃ ክለብን ያስታውሳዋል።

ከኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ጋር ተያይዞ ደጃች ውቤ ብዙ አስተዋፅኦ እንዳደረገ የሚናገረው ዳዊት “በከተሜነት” ዙሪያም ፈር ቀዳጅ ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ እንደሆነ ይናገራል።

በኢትዮጵያ የዘመናዊነት ታሪክ ትልቅ ስፍራ ያለውና በ1960ዎቹ የሥነ-ፅሁፍ፣ ሙዚቃና ጥበብ ትልቅ ቦታ ያለው ውቤ በረሀ ታሪካዊው አሻራው ላይመለስ ፍርስራሽ ሞልቶታል።

የአካባቢው የመፍረስ ዜና ሲሰማ ብዙዎችን እንዳስደነገጠ የሚናገረው ዳዊት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘንም የገለፀው ለውቤ በረሃ በማዜም ነው።

የሚኖረው ሰሚት አካባቢ ቢሆንም ዘወትር ወደ የደጃች ውቤ ያቀናል። የደጃች ውቤ ትዝታ አይለቅምና።

“ስምህ በወጭ ወራጁ የሚታወቅበትና ሁሉም እጁን ዘርግቶ የሚቀበልህ ቦታ ነው” ይላል።

በተለይም የአኮርድዮን ሙዚቃ መሳሪያን በመጫወት የሚታወቀውን አባቱን በማስታወስም ሲያልፍ፣ ሲያገድምም “ያባቱ ልጅ ውቤን ገዛሽው” ይሉት እንደነበር ያስታውሳል።

ዳዊት የውቤ በረሃ መፈራረስን ሲመለከት ደርግ ስልጣን በተቆጣጠረበት ወቅት ከተማ መኮንን የዘፈነው “አፈረሱት አሉ ዉቤ በረሃን” ለአሁኑ የውቤ በረሃ መፈራረስ ትንቢት እንደሆነ ይሰማዋል።

በጊዜው በሰዓት እላፊ ምክንያት በደጃች ውቤ አካባቢ ዘፈን እንዳይዘፈን በመደረጉ “አፈረሱት አሉ” እንደተዘፈነ ይናገራል። ደጃች ውቤ ሰፈር ከፈረሰ በኋላም ብዙዎች ይህን ዘፈን የስልክ መጥሪያ እንዳደረጉ በሀዘን ይገልፃል።

ከአዲስ አበባ መልሶ ማልማት ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ ጥንታዊው ደጃች ውቤ ሰፈር (ውቤ በረሃ) የመፍረስ ዜና ሲሰማ ብዙዎችን አስደንግጧል።

በዚህም ታሪካዊ የሚባሉ ቤቶች የፈረሱ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ እንደ አድዋ ሆቴል፣ የታዋቂው ሙዚቀኛ ፍሬው ሀይሉ ቤት፣ በአፄ ምኒልክ ዘመነ-መንግሥት ከቱርክ መሳሪያ ያመጣ የነበረው አርመናዊው ቴርዚያን ቤትና የአፈ-ንጉሥ ተክሌ ቤት ይገኙበታል።

ሰፈሩ አሁን የሚገኝበትን ሁኔታ በማየት ምን ያህል የደመቀ ስፍራ እንደነበር መገመት ይከብዳል።

“ምሽቱ አይነጋም” የተባለለት የዚህ ሰፈርን ዝና በጊዜው ያልነበሩት የሚናፍቁትና ሁሉም የእኔ የሚለው ዓይነት እንደሆነ ብዙዎች ይመሰክራሉ። ቦታው ባንድም ይሁን በሌላ ከብዙ ሙዚቀኞች ትዝታ ጋርም የተቆራኘ ነው።

ሙዚቀኞች ብቻም ሳይሆኑ አንቱታን ያገኙ የኢትዮጵያ ፀሀፊዎችና ገጣሚዎች ይህን ቦታ በሥራዎቻቸው ገልፀውታል።

ከእነዚህም አንዱ የስብሃት ገብረ-እግዚአብሔር በ”ሌቱም አይነጋልኝ” መፀሃፉ በሰፈሩ ያለውን የሴተኛ አዳሪ ህይወትና ሰቀቀኑን፣ ድህነትን፣ ሙዚቃውን እንዲሁም የማህበራዊ ህይወት ትስስሩን ቃኝቷል።

የፈራረሱ ቤቶች

የውቤ በር ውልደት?

ሙዚቃና ፖለቲካ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን (Music and Politics in Twentieth Century Ethiopia: Empire, Modernization and Revolution) በሚለው የስሜነህ ገብረ-ዮሀንስ የድህረ-ምረቃ የጥናት ፅሁፍ ምንም እንኳን የአዝማሪ ሙዚቃ በዚያን ጊዜ ታዋቂ ቢሆንም በጣልያን አምስት ዓመት ቆይታ ክለቦች ብዙ እንደተስፋፉ ያትታል። በዚያን ጊዜ ታዋቂ የነበሩት ቤላ ፖፑላ፣ ቪላ ቨርዲና ላ ማስኮቴ የሚጠቀሱ ናቸው።

የክለቦች ሀሳብ የተጠነሰሰው በልጅ ኢያሱ ጊዜ እንደሆነ የሚናገረው ስሜነህ ማዕከሉም ቤታቸውን በዛ አካባቢ ባደረጉት በንግሥት ዘውዲቱ ሁለተኛ ባል ደጃች ውቤ የሚል መጠሪያ እንደተሰጠው ይገልፃል።

የደጃች ውቤ ቤት አሁን አዲስ አበባ ሬስቶራንት የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን አካባቢውም ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያንን ይዞ አፍንጮ በር ይደርሳል።

በኋላም ብዙዎች በምሽትና በመጠጥ ህይወት ሰጥመው የሚቀሩበት በመሆኑ ውቤ በረሃ የሚል መጠሪያ እንደተሰጠው የስሜነህ ፅሁፍ ያትታል።

ደጃች ውቤም የኮሪያ ዘማች ወታደሮች ብዙ ገንዘባቸውን የሚያጠፉበት ቦታ እንደነበረም ይነገራል።

በጊዜውም ሬድዮ ድንቅ ስለነበር ዳጃች ውቤ አካባቢ በሚገኙ ክለቦች ብዙዎች መምጣት ጀመሩ።

እነዚህ መጠጥ ቤቶች (ክለቦች) የዚያኔ አዝማሪዎችን እንደተኳቸውና በተለይም የአሰገደች አላምረው እንዲሁም ከሶሪያ የመጡት ኮሪንፊሊ ታዋቂነትን ማትረፍ ችለዋል።

እነዚህ ክለቦች ታዋቂነታቸው እየቀነሰ ሲመጣ ሰዎች ዶሮ ማነቂያ አካባቢ ይገኝ ወደነበረው ሜሪ አርምዴ ክለብ ማምራት እንደ ጀመሩ የስሜነህ ፅሁፍ ያስረዳል።

የኮንጎ ዘማቾች መበራከት፣ የ1953 መፈንቅለ-መንግሥትን እንዲሁም የ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴን ተከትሎ ፈጥኖ ደራሾች ፖሊሶች በከተማው ውስጥ መንሰራፋታቸው የክለቦችን ቁጥር እንደጨመረው ፅሁፉ ያትታል።

ምንም እንኳን የክለቦች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም የደጃች ውቤ ማዕከልነት እየቀነሰ መጥቶ ትልልቅ ቪላዎች ወደ ክለብነት ተቀይረው ብዙዎች ንፋስ ስልክ አካባቢን ማዘውተር ጀመሩ።

ዳዊት ይፍሩImage copyrightFACEBOOK

ማፍረስ የመጨረሻው አማራጭ ነበር?

በአሁኑ ወቅት ደጃች ውቤ በፍርስራሾች ተሞልታለች። ምንም እንኳን መንግሥት ለልማት ነው ቢልም እነዚህ ታሪካዊ ሰፈሮች ከመጥፋታቸው በፊት የከተማዋ እቅድ ውስጥ ሊካተቱ እንደሚገባ የታሪክ አጥኚዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

በአዲስ አበባ መሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ የኮሚኒኬሽን አስተባባሪ አቶ ንጉሡ ተሾመ ሰፈሮቹ የተጎሳቆሉና የደቀቁ በመሆናቸው ምክንያት ለመልሶ ማልማት እንደሚፈርሱ ይናገራሉ።

ለመልሶ ማልማት ተግባር ከመዋላቸው በፊት ብዙ ጥናቶች እንደሚደረጉባቸው የሚናገሩት አቶ ንጉሡ እነዚህ ሰፈሮች መሰረተ-ልማታቸው ያልተሟላ እንዲሁም አደጋ ቢከሰት መውጫ የሌላቸው እንደሆኑ ይጠቁማሉ።

“ስያሜዎቹ አልተቀየሩም። አካባቢዎቹ ግን የተጎሳቆሉ ናቸው። ለመኖር ቀርቶ ለማለፍ የሚዘገንኑ ሰፈሮች ናቸው። ያንንስ ይዘን እስከመቼ እንዘልቃለን? ይህ ጥናት ደግሞ የህብረተሰቡን የተሻለ ኢኮኖሚያዊ አቅም መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ ነው” ይላሉ።

ዳዊት በአቶ ንጉሡ ሀሳብ ይስማማል። በአካባቢው አስር አባወራ በአንድ መፀዳጃ ብቻ ይገለገልበት የነበረበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሶ የነዋሪው ህይወት መሻሻል እንዳለበትም ያስረዳል። የእሱ ቅሬታ መፍረስ የሌለባቸው ቤቶች መፍረሳቸውና ነዋሪው መበተኑ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ቦታው ከፈረሰ በኋላ ምንም ሳይሰራበት መፀዳጃ መሆኑ ያሳዝነዋል። “የፈራረሰው ቤቴ ወደ መፀዳጃነት ተቀይሮ ሳየው በጣም ያሳፍረኛል” ይላል።

መልሶ ማልማቱ ታሪካዊ ቤቶችን፣ ሀውልቶችንና ቅርስ ተብለው የተመዘገቡትን ከባህልና ቱሪዝም ጋር በመተባበር ከግምት ውስጥ ቢያስገባም በአጠቃላይ ሰፈሮችን አሳቢ እንዳላደረገ ብዙዎች ይናገራሉ።

“የደቀቁ ቤቶች አድሶ ሰፈሮቹን መጠበቅና ነዋሪዎቹን መመለስ አይቻልም ወይ? አዳዲስ ግንባታዎችን አሁን በሚመሰረቱት አዳዲስ ሰፈሮች ማካሄድ አይቻልም? የነበረው ታድሶ እንደ ህንድ የመሳሰሉ ሀገራት ለሁለት የድሮና አዲስ በሚል መከፋፈል ይቻል አልነበረም?”

አቶ ንጉሡ ጥያቄው ተገቢ መሆኑን ቢያምኑም ከተማዋ በማስተር ፕላን እንደምትመራና የንግድ ማዕከላት፣ ትልልቅ ፎቆች፣ የህዝብ መገልገያ ተቋማትን ተለይተው በዚሁም መሰረት ግንባታዎች እንደሚከናወኑ ይገልፃሉ።

“ይህ ከተማ በአጠቃላይ ሲገነባ ነዋሪውን ሊያስወግድ በሚችል መልኩ አይደለም። አቅም ያለው እዚያው ላይ እንዲሰራ እድል ፈጥሯል። አቅም የሌለው ደግሞ መንግሥት ባስቀመጠው መሰረት” እንደሚስተናገድ ይናገራሉ።

ጠቅላላ የልማት ተነሽውን መንግሥት ቤት ሰርቶ በዚያ ሰፈር ያኑር ቢባል የማያስኬድ እንደሆነም ይገልፃሉ።

ከውቤ በረሃ በተጨማሪ ብዙ ታሪካዊ የሚባሉ ሰፈሮች የፈራረሱ ሲሆን በዚህ ዓመትም የመልሶ ማልማት ሥራዎች ይቀጥላሉ። በዚሀም መሰረት በአራዳ ክፍለ ከተማ ገዳም ሰፈርና አሜሪካን ግቢ ቁጥር ሁለት፣ ልደታ ጌጃ ሰፈር፣ ካዛንችስ ዕቅድ ውስጥ ገብተዋል። ይህም በአጠቃላይም 78 ሄክታር የሚሸፍን አካባቢ ነው።

ቢቢሲ አማርኛ 

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0