“Our true nationality is mankind.”H.G.

መንግስት ጎንደርና አካባቢዋን አደራጅቶ ሊያስታጥቅ ነው፤ ” ሥዕሉ ግልጽ ነው” ብ/ጀ/አሳምነው ጽጌ

…በዚህም መሰረት ሕብረተሰቡ በየአካባቢው ራሱን አደራጅቶ እንዲጠብቅ ከመንግሥት በኩልም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግለት ተነጋግረናል፤ ተግባብተናል…

ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ጽጌ የአማራ ክልላዊ መንግሥት የደህንነትና ሰላም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ  ሰሞኑን  በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር አካባቢ በተፈጠረው ግጭትና በአካባቢው ስላለው የጸጥታ ሁኔታ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ ይከታተሉት፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከሰሞኑ በጎንደር የተከሰተውን ግጭትና ያጋጠመውንሁኔታ ቢገልጹልን?

ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው፡- ሰሞኑን እንደሰማችሁት ካለፉት የቀጠሉ ችግሮች       አሉ፡፡ በስፋት ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡-  ቀኑ መቼ ነው?

ብርጋዴር  ጀኔራል  አሳምነው፡- ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ፣ ረቡና ሐሙስ ነው ችግሮች በስፋት የተከሰቱት፡፡

አዲስ ዘመን፡-  ግጭቱ የተፈጠረው በማን ነው? 

ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው፡- የተደራጀ የታጠቀ ቀጥተኛ ስምሪት የተሰጠው ኃይል ነው ጥፋት ያደረሰው፡፡ በሁለት ቡድን የተከፋፈለ ነው፡፡ አንደኛው ቡድን ቤቶችን የሚያቃጥል  ራሱን የቻለ የተደራጀ ቡድን ሲሆን፤ ሁለተኛው ቡድን ደግሞ የመጀመሪያው ቡድን ይህን ሥራ ሲፈጽም እንቅፋት ቢያጋጥመው ሊከላከል በሚችልበት ሁኔታ ተደራጅቶ  ነው የመጣው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአለዎት መረጃ መሰረት ጥፋቱን ለማድረስ የተሰማራው አካል ምን ያህል የሰው ኃይል እንዳለው ይገመታል?

ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው፡-  አንደኛው ቡድን ከ200 በላይ የታጠቀ የሰው ኃይል እንዳለው ይገመታል፡፡ ሁለተኛው ከ70 አስከ 80 ሰው የሚገመት ኃይል ያለው የታጠቀና የተደራጀ ቡድን ነው፡፡ የነፍስ ወከፍ (በግል የሚያዝና) የቡድን መሳሪያም ታጥቀዋል፡፡ በቤቶቹ ላይ የእሳት ቃጠሎው እንደተጀመረ በቀጥታ መከላከያም ልዩ ኃይልም ገብተው ነበረ፡፡ በተለመደው የሽምግልና መንገድ ሄዶ ለማደራደር ሞከሩ፡፡ እሺ ብለው ተመለሱ፡፡

ጥፋት የፈጸመው ኃይል የነበረበትን አቅጣጫ ትቶ በሌላ አቅጣጫ ዞሮ በመሄድ ላዛ፣አዳዛና አንከራ የምንላቸውን ማዕከላዊ ጎንደር ያሉ አካባቢዎች ላይ ጥቃት ፈጸመ፡፡ በአይከልና በጎንደር መካከል ያሉ የአስፋልቱን መንገድ ተከትለው የሚገኙ ከጓንግ አካባቢ በግራና በቀኝ የሚገኙ ስፍራ ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአጠቃላይ ባለዎት መረጃ መሰረት ምን ያህል ሰው ሞተ፤ምን ያህል ቤቶች ተቃጠሉ፤የተፈናቀለውስ ሕዝብ ብዛት ምን ያህል ነው?

     ብርጋዴየር ጀኔራል አሳምነው፡- መረጃውን እያጣራን ነው፡፡ ከ30 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ከ300 በላይ የአርሶ አደር ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ከአሁን በፊትም የተፈናቀሉ ስለነበሩ የተፈናቃይ ዜጎች ቁጥር አሻቅቧል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ተፈናቃዮችን በተመለከተ አንዳንድ አሃዛዊ መረጃዎች እየወጡ ነው፤ እርስዎ ባለዎት ግርድፍ መረጃ መሰረት ምን ያህል ዜጎች ተፈናቅለዋል?

ብርጋዴር  ጀነራል አሳምነው፡-  18 ሺህ የሚደርስ ሕዝብ እንደተፈናቀለ የሚያሳይ መረጃ አለ፡፡ የዕለት ዕርዳታ  የሚሰጣቸው የአደጋና መከላከል ዝግጁነት አካሎች የሚደግፏቸውና የተለያዩ ኃይሎች የሚረዷቸው ዜጎች በአራት መጠለያ ይገኛሉ፡፡ ይሄ ውጪ ያለውን ሳይጨምር ማለት ነው፡፡

Related stories   “…ለዛሬ ብለን ነገን ከምናበላሽ፣ ለነገ ስንል ዛሬን እንሠዋ” አብይ አህመድ

አዲስ ዘመን፡-  ውጪ ካለው ተፈናቃይ ጋር ምን ያህል ይሆናል?

ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው፡- ትክክለ ኛው ቁጥር የለኝም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ከቀድሞው ተፈናቃይ በ2000 እና 3000 ሕዝብ ቢጨምር ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡-  የችግሩ አሳሳቢነት ምን ያህል ነው?

ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው፡- ያለው ሁኔታ አሳሳቢም ነው፡፡ አሳሳቢም አይደለም፡፡ ታቅዶ በጥናት የሚሠራ ሥራ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ እዚህ አካባቢ ያለውን ኃይል ለመሳብና የሕብረተሰቡን አመለካከት ቀልብሶ በተለያየ መንገድ ለመሄድ የሚደረግ ሙከራ ነው፡፡ እዚህ ብቻ ሳይሆን  በከሚሴም አካባቢ በተመሳሳይ ሰዓትና ጊዜ በተቀናጀ መንገድ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ ሕይወት አልፏል፡፡ አውራ ጎዳናዎችን ለመዝጋት ተሞክሯል፡፡

ይህ በሚገባ የተደራጀ፣ የተቀናጀና ይህችን ሀገር ያው በታሪክ አጋጣሚ በዚህ መንገድ እንድትገኝ ለማድረግ የሚሞክሩ ኃይሎች  የሚሠሩት ሥራ ነው፡፡ ይሄ ሕብረተሰብ ራሱን እንኳን ለመከላከል ያልተዘጋጀ ነው፡፡ ይህን የመሰለ ጥቃት ከወንድሞቹና ከቤተሰቦቹ ይደርስብኛል ብሎ ፍጹም በማይጠብቅበት ባልገመተበት ሰዓትና ሁኔታ ነው ጥቃት የተፈጸመበት፡፡ ለምሳሌ አሁን ላዛ የምልህ አካባቢ አስፋልት ዳር ነው ያለው፡፡

የተወሰኑ ቀበሌዎችና መንደሮች ቀርተው ነበረ፡፡ እነዚህን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋትና ሕብረተሰቡንም ለመዝረፍ የተደረገ ሙከራ ነው፡፡ ያው መከላከያና ልዩ ኃይሉም ባለበት ይሄ ጥቃት ይፈጸማል፡፡ በሌላም መንገድ ይፈጸማል፡፡ ዞሮ ዞሮ የተቀናጀ የተደራጀ እንቅስቃሴ ነው፡፡ አሁን ሕብረተሰቡ ገብቶታል ጥንቃቄ በማድረግ ላይ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከሚሴ ላይስ ምን ያህል ጉዳት ደረሰ ?

ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው፡- ከሚሴ ላይ የደረሰው ጉዳት አሁን በምዕራብ ጎንደር አካባቢ በደረሰው ጉዳት መጠን የሚገለጽ አይደለም፡፡ ተደራጅተው ሕብረተሰቡን ከአ ንድ አካባቢ ለማፈናቀል የሞከሩበት መንገድ ነበረ፡፡ ስትራቴጂው ተመሳሳይ ነው፡፡ የተወሰኑ  የታጠቁ ቡድኖች ይመራሉ፡፡ ሌላው ሕዝብ ይከተላል፡፡ መንገድ ይዘጋል፡፡ ዛፍ ይቆርጣል፡፡የሚከላከልበትን መንገድ ይፈጥራል፡፡ ከሕብረ ተሰቡም የሞተ የቆሰለ እንዳለ ሰምቻለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በጎንደር በቅማንት ስም የሚንቀሳቀሰው ኃይል ነው ይሄን የሚያደርገው?

ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- በዚያ መንገድ የሚገለጽ ነው፡፡ ይሄኛው ኃይል ራሱን ለመከላከል ሞክሯል፡፡ ሌላው በዚያ መንገድ ራሱን አልተከላከለም፡፡ በሰላማዊ መንገድ  በአካባቢው በግብርናና በተለያየ ሥራዎች ተሰማርቶ የሚኖረው ይህን ዓይነት ሁኔታ ይፈጠራል ብሎ አይገምትም፡፡ የተወሰነ ማህበረሰብ በተለየ መንገድ ታጥቆ አንተን ከቤት ንብረትህ አፈናቅሎ እንዲህ ያደርጋል ብለህ በፍጹም አትገምትም፡፡

Related stories   ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ማጣራቱ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎችን እንደሚያካትት አስታወቀ፤ መንግስትና አማራ ክልል በማይካድራ ጉዳይ ተኝተዋል

አዲስ ዘመን፡- ጥቃት የሚፈጽመው ኃይል መነሻው ከየት ነው፤ ከዚያው አካባቢ ነው ወይንስ ከራቀ ቦታ ነው የመጣው?

ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው፡-  ከሌላ ቦታ ተጭኖ በተለየ መንገድ ሰርጎ እየገባ የሚመጣ ኃይል ነው፡፡ ይህ በአብዛኛው ከምዕራባዊ ጎንደር ነው፡፡ በጎንደር አካባቢ ብዙ ለመቆጣጠር አዳጋች የሆኑ ሰርጎ ለመግባት የሚመቹ ቦታዎች አሉ፡፡ በተፈጥሮው አካባቢው አስቸጋሪ መሬት አለው፡፡ በሕብረተሰቡ ውስጥ ሰርገው ለመግባት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ የጸጥታ አካል በኩል ምን ዓይነት የመከላከል ዕርምጃ ተወሰደ፤ በቀጣይ ይህ ዓይነት ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይፈጠር ከሕብረተሰቡ ጋር ምን እየሠራችሁ ነው ?

   ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው፡- ዞሮ ዞሮ አደጋና ጥቃትን ከማንም በላይ የሚከላከለው ሕብረተሰቡ ነው፡፡ ሕብረተሰቡ ደግሞ በየአካባቢው ተደራጅቶ እራሱን ከጥቃት መከላከል ተፈጥሯዊ መብቱ ነው፡፡ ማንም የሚሰጠው መብት አይደለም፡፡ በዚህም መሰረት ሕብረተሰቡ በየአካባቢው ራሱን አደራጅቶ እንዲጠብቅ ከመንግሥት በኩልም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግለት ተነጋግረናል፤ ተግባብ ተናል፡፡

ከዚህም በላይ ደግሞ የአካባቢ ሚሊሺያ አለ፡፡ እነዚህ አንዳንድ የጸጥታ ችግሮች ሲፈጠሩ ተደራጅተው የሚከላከሉ  ናቸው፡፡ በዚህ መንግሥት ውስጥ የተፈጠሩ የተደራጁ የሰለጠኑ ናቸው፡፡ ሰላምና ጸጥታን ለማስከበር በየአካባቢውና በየቀበሌው የተደራጁ ሚሊሺያዎች አሉ፡፡ በቅርቡ በቀበሌያቸው በወረዳቸው በሚገባ ተደራጅተው አካባቢያ ቸውን እንዲጠብቁ ስምሪት ተሰጥ ቷል፡፡

አዲስ ዘመን፡- መከላከያ ይሄንን ጥቃት በሕዝቡ ላይ የሰነዘሩትን ኃይሎች ተጋፍጧል?

 ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው፡-አዎ፡፡ እዚያ  አካባቢ ከፍተኛውን ሥራ የሠራው መከላከያ ነው፡፡ የተዘጉትን መንገዶች ሁሉ ከፍቷል፡፡ መሀል ላይ ገብቶም ግጭቱን ለማብረድ ሞክሯል፡፡ ዞሮ ዞሮ መነሻው ግጭቱን የሚፈጥሩት አካላት ደረጃውን እያሳደጉ  አካባቢውን ከትራንስፖርትም  ከግንኙነትም እየቆረጡ የማወክ ሥራ ነው በሁሉም አቅጣጫ ለመሥራት እየሞከሩ ያሉት፡፡ ሕብረተሰቡ አደጋው ሴራው ከየት አካባቢ እየመጣበት እንዳለ አውቋል፡፡ ውጤቱ በምን መልኩ እየተገለጸ እንዳለ ተረድቷል፡፡ ይሄ ተቀናጅተው በብዙ አካባቢዎች እየሠሩት ያለ  ሥራ ነው፡፡ ሥዕሉ ግልጽ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በግጭቶቹ  ቅንብርና ስልታዊ አካሄድ ሲታይ ፕሮፌሽናል (ሙያ ተኛ) የሆነ ወታደራዊ እውቀትና ችሎታ ባላቸው ሰዎች የሚመራ ውጊያ ዓይነት ነው ማለት ይቻላል? በተኩስ ልውውጡ ወቅት ባለዎት መረጃ መሰረት ከቀላል መሳሪያዎች ውጪ የተጠቀሙበት ከባድ መሳሪያ አለ ?

ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው፡- ብሬንና ድሽቃ ሁለቱም በከባድ መሳሪያ ምድብ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ እነሱን በመደበኛ ሁኔታ ይጠቀማሉ፡፡ ይሄ አሁን የተለመደ ሆኗል፡፡ የቡድን መሳሪያዎችን ነው የሚጠቀሙት፡፡ ይሄን የሚያደርገው በሚገባ የሰለጠነ ፕሮፌሽናል የሆነ ኃይል ነው፡፡ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

Related stories   እስራኤል አልጃዚራ ቴሊቪዥን፣ አሶሲየትድ ፕሬስና ሌሎች ሚዲያዎች የሚጠቀሙበትን ህንጻ አወደመች

አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ሁለት ቀናትስ የግጭቱ አካባቢ ተረጋግቷል፤ ሰላም ሰፍኗል፤ ቁስለኞችስ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል፤ ምን የተለየ ነገር አለ ቢገልጹልን ?

ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው፡- አንዳንድ ቦታዎች ካልሆነ በስተቀር  ደህና ነው፡፡ የተወሰኑ ችግሮች ብቅ ብለዋል፡፡ ከጓንግ ወደዚህ  ወደ 7 እና 8 ኪሎሜትር ወደጎንደር መጥተህ ማለት እዛ አካባቢ የተወሰኑ ምልክቶች ዓይተናል፡፡ በአንጻራዊነት ይህን ሁለት ሦስት ቀን ጥሩ ነው፡ያው ጥሩ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ያለ ጥሩነት ማለት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ደብረታቦርና ጋይንት አካባቢስ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል ?

ብርጋዴር ጀኔራል፡- እዚያ አካባቢ ሰላም ነው፡፡ እንደውም ሰላም ለማምጣት በሚደረገው  ሥራ ውስጥ ተባባሪ ኃይል ነው፡፡ ይሄ ነው የሚባል ያልተለመደ ክስተት አላየንም፤ አላስተናገ ድንም፡፡ ያ ደግሞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እናስባለን፡፡ በአካባቢው የተለያዩ ችግሮች ነበሩ፤ እነሱ ተስተካክለው  ሁሉም ከስርዓቱ ጋር ለመጓዝ ጥረት እያደረገ ነው ያለው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአጠቃላይ ለሕዝቡ የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድነው ?

ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው፡- አንደኛ  ሕብረተሰቡ በአንድ አካባቢ የተፈጠረን ክስተት የአንድ አካባቢ ችግር አድርጎ እንዳይረዳው ማስገንዘብ እፈልጋለሁ፡፡ በአብዛኛው የአማራ ክልል ምዕራባዊ አካባቢዎች በአማራ ክልል ምሥራቃዊ አካባቢዎች በአማራ ክልል ደቡባዊ አካባቢዎች በስፋት እንዲህ ዓይነት ክስተቶች ይታያሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ክስተቶች ሌላም ቦታ አሉ፡፡ ስለዚህ ዋናው ጉዳይ ሕብረተሰቡ በየአካባቢው ራሱን ተደራጅቶ መጠበቅ እንዳለበት እኛ ያገኘነው ትልቅ ትምህርት ነው፡፡

የበለጠ አጀንዳውን ለሚያራግቡ አጀንዳው በዚህ መንገድ እንዲሄድ ለሚቀጥሉ ሀገር ለመበታተን ለሚዘጋጁ ኃይሎች ሕብረተሰቡ ራሱን አሳልፎ እንዳይሰጥ፤ የበለጠ ነቅቶ ራሱን፣ ቤተሰቡንና አካባቢውን እንዲጠብቅ ራሱን እንዲከላከል ከምንም ነገር በላይ ደግሞ የራሱ አካባቢ ባለቤት ራሱ መሆኑን አውቆ መጠበቅ መቻል አለበት ብዬ አሳስባለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ወቅታዊ ማብራሪያ እጅግ በጣም እናመሰግናለን!

ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው፡- እኔም አመሰግናለሁ!

አዲስ ዘመን የካቲት 4

ወንድወሰን መኮንን

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0