በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የሚገኙ ተፈናቃዮች መንግስት በቂ የሆነ የምግብ እና ቁሳቁስ ድጋፍ እያቀረበላቸው አለመሆኑን ገለጹ። በሁለቱ ዞኖቹ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ 39 ሺህ በላይ ዜጎች መንግስት በቂ የሆነ የምግብ ፣ውሃ ፣ጤና እና ቁሳቁስ ድጋፍ እያቀረበላቸው አለመሆኑን ተናግረዋል ። በተለይም በሳንጃ፣አይምባ ፣ትክል ድንጋይና ጭልጋ የሚገኙ ተፈናቃዮች መንግስት እየተደረገ ነው የሚለው ድግፍ እየደረሳቸው አለመሆኑን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል የአደጋ መከላከል ምግብና ዋስትና ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዋና የስራ ሂደት አቶ እያሱ መስፍን ተፈናቃዮች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ መሰረትም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተከማችቶ የነበረን 600 ኩንታል የምግብ እህል ለተጎጂዎች ለማዳረስ እየተጓጓዘ ነው ብለዋል ። ከዚህ በፊት በአካባቢው ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት አቅርቦቱን ለተጎጂዎች በተፈለገው ጊዜ እና ስዓት ማድረስ አለመቻሉንም አንስተዋል ።

የመጠጥ ውሃንና የጤና አገልግሎትን በተመለከተም ክልሉ በሰጠው አቅጣጫ መሰረት የውሃና የጤና ተቋማት ሃላፊት ተሰጥቷቸው እየሰሩ መሆኑን ነው የገለጹት። በቀጣይም ችግሩ እንዳይፈጠር የክልሉና የፌዴራል መንግስት በጋራ እና በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል ።

በዚህም የፌዴራል መንግስት በክልሉ ለሚገኙ ሁሉም ተፈናቃዮች 13 ሺህ ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል ። በሌላ በኩል የክልሉ መንግስት ደግሞ 5 ሺህ ኩንታል የምግብ እህል ገዝቶ በማከፋፈል ላይ መሆኑን አቶ እያሱ መስፍን ተናግረዋል።

በናትናኤል ጥጋቡ – FBC

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *