“Our true nationality is mankind.”H.G.

ከሪፖርት መረጃ ባለፈ

ሠራተኛን ዝቅ ብሎ መመልከት አርአያነት ያለው ተግባር ነው ሲሉ ወይዘሪት የሺ ከበደ ይገልጻሉ። በአንዳንድ መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ዘንድ የመኮፈስ ስሜት እንደሚስተዋል የሚናገሩት ወይዘሮ የሺ፣ በየትኛውም የስራ ክፍል፣ መደብ እና የስራ ሁኔታ ውስጥ ይሰራ ሠራተኛ መናቅ የለበትም ይላሉ፡፡

በባምቢስ አካባቢ በሚገኘው ፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዋና ፀሐፊነት የሚሰሩት ወይዘሪት የሺ፣ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መስሪያ ቤታቸውን መጎብኘታቸውን ለሌሎች የስራ ኃላፊዎች  ትምህርት የሰጠ ሲሉ ይገልጹታል፡፡

ጉብኝቱ የበለጠ እንዲሠሩ እንዳነሳሳቸው በተለይ ለአዲስ ዘመን የተናገሩት ወይዘሪት የሺ፣የአንድ ሀገር መሪ መስሪያ ቤቶችን እየተዘዋወረ ማየቱ የሠራተኞችን የሥራ ተነሳሽነት የበለጠ እንደሚጨምርም ነው የተናገሩት።

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቋሙ የተገኙት ድንገት ነው፤ ተቋሙን ስለመጎብኘታቸው የሚያቅ አልነበረም፤ ሁላችንም ስራ ሥራችንን ስንል ነው ከተፍ ያሉት›› ሲሉ ገልጸው፣ እሳቸውን እንዳነጋገሯቸውና በሆነውም በጣም መደሰታቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹ሠራተኛው ሥራ ገበታ ላይ ሆኖ ማግኘታቸው እሳቸውንም ያስደስታቸዋል ብዬ አስባለሁ፤ በግሌ ሥራችን ተመልካች አለው ብዬ እንዳስብ ያደርገኛል፤ ለውጡን የበለጠ ለማራመድ ተግተን እንድንሠራ የሚያበረታታ ጉብኝት ነው ይላሉ።

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሰው ኃይል አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ሞገስ ዐወቀ  ጠቅላይ ሚኒስትሩን ባዩ ወቅት ደስታ ተሰምቷቸዋል። ጉብኝቱ ሰራተኛውን ለሥራ የሚያነሳሳ ብቻ እንዳልሆነ ለተቋሙ የሰጡትን ትኩረት  እንደሚያመለክትም ይናገራሉ።

‹‹ሁላችንም መሪዎችን እንከተላለን፤አለቃህን ወይም የበላይህን ትከተላለህ፤ ከላይ ያለው የተስተካከለ ከሆነ ከታች ያለው ይስተካከላል፤ ከላይ ያለው ከሰረቀ ፤የበታቹም ይሰርቃል ፡፡›› አቶ ሞገስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወሳኝ ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

Related stories   በሃሰተኛ ሰነድ ሾፌር ሆኖ የጫነውን ከ6 ሚሊዮን በር በላይ የምያወጣ ቡና የዘረፈው ዕምነት አጉዳይ ተፈረደበት

የእሳቸውን ፈለግ እንደሚከተሉ፣ ለለውጡም ውጤታማነት እንደሚተጉ ይገልጻሉ፡፡‹‹ከአንድ ትልቅ መሪ የሚጠበቅ በጎ ተግባር እየሠሩ ናቸው፤ ከጎናቸው እንቆማለን›› ሲሉም ያመለክታሉ።

የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሰው ሀብት ሥራ አመራር ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬሕይወት ወልደማርያም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመስሪያ ቤቱ ሲገኙ በሠራተኛው ዘንድ ግር የማለት ስሜት ተፈጥሮ እንደነበር ጠቅሰው፣ በኋላ ላይ ግን በጣም መደሰታቸውን ይገልጻሉ። ሰራተኞቹ አይተው  የማያውቁትን አዲስ ነገር ማየታቸውን ተናግረው፣ የወደፊት ሥራቸው ላይም አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡

በየመሥሪያ ቤቱ ያሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በእያንዳንዱ የሥልጣን እርከን ላይ ያሉ ሁሉ ከሪፖርት መረጃ ባለፈ ወረድ ብለው ስራውንና ሰራተኛውን ማየት እንዳለባቸው ያስተማረ መሆኑን ይናገራሉ።

በካዛንቺሱ የመካከለኛ ግብር ከፋዮች መስሪያ ቤት ሰራተኞች ዘንድም ተመሳሳይ ስሜት ተንጸባርቋል፡፡ የገቢ ሂሳቦች የሥራ ሂደት ሠራተኛ ወይዘሮ ሰብለ ነጋሽ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሥሪያ ቤቱን መጎብኘታቸው የበለጠ እንድንሠራ ብርታት ሆኖናል።›› ብለዋል፡፡ በግብር ከፋዩም ዘንድ  የታየው ስሜት ተመሳሳይ እንደነበር ጠቅሰው፣ በእኔነት ስሜት ግብሩን እንድንከፍል የሚያነሳሳ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ሌሎች ባለስልጣናትም የእርሳቸውን አርአያነት ያለው ተግባር መከተል እንዳለባቸውም አመልክተው፣ ተግተን ለመስራት እንደሚረዳ ይገልጻሉ፡፡

በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች የትምህርትና መረጃ አገልግሎት የሥራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ ጌታቸው ጥላሁን ጉብኝቱን ማንም እንዳልጠበቀ፣ሥራ አስኪያጇም ጭምር እንደማያውቁ ይገልጻሉ።

Related stories   በሃሰተኛ ሰነድ ሾፌር ሆኖ የጫነውን ከ6 ሚሊዮን በር በላይ የምያወጣ ቡና የዘረፈው ዕምነት አጉዳይ ተፈረደበት

ግብር ከፋዩ ግብሩን የሚከፍለው በወሩ ማጠናቀቂያ ባሉት አምስት ቀናት ስለሆነ ሰው ይበዛል ያሉት አቶ ጌታቸው፣ በዚህ ወሳኝ ወቅት ጉብኝት ማድረጋቸውን ይናገራሉ።  አቶ ጌታቸው ግብር ከፋዮችን ወረፋ እያስያዙ ባሉበት ወቅት ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመስሪያ ቤቱ የተገኙት፡፡ አቶ ጌታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሰላምታ ተለዋውጠዋል፡፡

ግብር ከፋዩም ልዩ ስሜት እንዳደረበት ጠቅሰው፣ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ግብራችንን በአግባቡ እንከፍላለን እያሉ ሲናገሩ እንደሰሟቸውም አቶ ጌታቸው ይገልጻሉ፡፡ ሁሉም በየደረጃው ለውጡን ለማስቀጠል ተግቶ እንዲሠራ ኃላፊነት የሰጠ ጉብኝት ሲሉም ገልጸዋል።

በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ገቢ ግብር ከፋዮች ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ብርቱካን ግርማ በወቅቱ የነበሩትን በርካታ ግብር ከፋዮች ለማስተናገድ ተራ እያስያዙ ባለበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተፍ ማለታቸውን ይናገራሉ፡፡

ወይዘሮ ብርቱካን ጠቅላይ ሚኒስትሩን አነጋግረዋል፤ በዚህም ደስታ ተሰምቷቸዋል፡፡ እስከ ሦስተኛ ፎቅ ድረስ በእግራቸው በመውጣት የገንዘብ ተቀባዮችን ክፍል በመጎብኘት ሰራተኞችን ማነጋገራቸውንም ይገልጻሉ።

ወይዘሮ ብርቱካን እንደሚሉት፤ ጽህፈት ቤቱ አሁን ባለበት ህንጻ ስራ የጀመረው ባለፈው ታኅሳስ ወር መጀመሪያ ነው፡፡ በጽህፈት ቤቱም 4ሺህ 482 ግብር ከፋዮች ይስተናገዳሉ፡፡

ከጉብኝቱ በኋላ ብዙዎቹ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በትክክል ለመክፈል የበለጠ እንደሚያነሳሳቸው መናገራቸውን ወይዘሮ ብርቱካን ተናግረው፣ ይህ ደግሞ “ግዴታዬን እወጣለሁ፤ መብቴን እጠይቃለሁ” ለሚለው የግብር ንቅናቄ ዘመቻ ጥሩ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ይገልፃሉ። አንድ ግለሰብ ግብር ሲከፍል ስምንት ዓመት እንደሆነው ጠቅሶ፣ አንድ ኃላፊ ዞር ብሎ ሳይመለከተው በሀገር መሪ መጎብኘቱ እንዳስደተው ሲናገር መስማታቸውን አመልክተው፣ ጉብኝቱ ግብር ለመክፈል የበለጠ እንደሚያበረታታውም መናገሩን ይገልጻሉ፡፡

Related stories   በሃሰተኛ ሰነድ ሾፌር ሆኖ የጫነውን ከ6 ሚሊዮን በር በላይ የምያወጣ ቡና የዘረፈው ዕምነት አጉዳይ ተፈረደበት

‹‹የበላይ አመራሮቻችን ያዩናል፤ ወ/ሮ አዳነች አቤቤም ይጎበኙናል፤ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ምህረትም ግብር ከፋዮችን ሲያስተናብሩ የነበረበት ጊዜም አለ›› ያሉት  ሥራ አስኪያጇ ወይዘሮ ብርቱካን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድጋሚ ተቋሙን እንደሚጎበኙ እንደነገሯቸው ተናግረዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ሠራተኛው አቶ ተስፋዬ      ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ተቋማት ያደረጉት ጉብኝት በሠራተኛው ላይ ብቻ ሳይሆን በዜጎች ላይ ጥሩ ስሜት እንደሚያሳድር ይናገራሉ፡፡ ሌሎች አመራሮችም ምሳሌዎች ለመሆን ሰራተኛውን ቀርበው ማነጋገር እንዳለባቸው ያመላከተ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ጉብኝቱ ሠራተኛው ተግቶ እንዲሠራ እንደሚረዳ ያስገነዝባሉ፡፡ እንጀራ ለመብላት መሥራት እንዳለብን የሚያነሳሳ ይመስለኛል ይላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ያደረጉት ድንገተኛ ጉብኝት ተቋማቱና ሠራተኞቻቸው የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ መሆኑን ለማረጋገጥ እንደሚጠቅም፣ ጉብኝቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት መረጃ ያሳያል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና የመካከለኛ ገቢ ግብር ከፋዮች ቢሮን እንዲሁም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

አዲስ ዘመን የካቲት 5/2011

በኃይለማርያም ወንድሙ

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0