“Our true nationality is mankind.”H.G.

የመከላከያ ሰራዊቱ ለጠላቶች የፍርሃት፤ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ የኩራት ምንጭ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ

የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለጠላቶች የፍርሃት ምንጭ ለኢትዮጵያውያን እና ወዳጆች ደግሞ የኩራት ምንጭ መሆኑን የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።

7ኛው የመከላከያ ሰራዊትን ቀን “ህገ መንግስታዊ ታማኝነታችንና ህዝባዊ ባህሪያችንን ጠብቀን የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ እናስቀጥላለን” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዳማ ከተማ ተከብሯል።

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በተከበረው የመከላከያ ሰራዊት ቀን ላይም የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የኦሮሚያ ክልል ርእስ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ፣ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ጨምሮ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፣ ሚኒስትሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልእክትም፥ ለጠላቶች የፍርሃት ምንጭ ለኢትዮጵያውያንና ወዳጆቹ ደግሞ የኩራት ምንጭ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት ውስጥ በማገልገላችን ኩራት ሊሰማን ይገባል ብለዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ሀገሪቱ ከፍ እና ዝቅ ባለችባቸው ጊዜያት በሙሉ ታላቅ ሀላፊነት የተጣለበት ተቋም ነው ያሉ ሲሆን፥ ከሀገር አልፎም ሰላምን ለማስከበር የተለያዩ የዓለም ሀገራት ውስጥም ግዳጁን በአግባቡ የተወጣ ምስጉን ሰራዊት መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

Related stories   ኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃ ገብነትን " ወግድ አለች" መንግስት መግለጫ ሰጠ

ነገር ግን የመከላከያ ሰራዊቱ ውስንነቶች ነበሩበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፥ በተለይም በውስጣዊ አሰራሩ ግልጽነት ይጎድለው እንደነበረም አንስተዋል።

ይሁን እንጂ ላለፈው አንድ ዓመት ገደማ ከመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ጋር በተሰራው በተቋሙ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እንደ ሀገርም ዋነኛው ለውጥ የታየበት ተቋም መሆኑንም አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅትም የመከላከያ ሰራዊቱን በቴክኖሎጂ እና በተለያዩ ዘርፎች ለማዘመን እየተሰራ መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የተናገሩት።

በተለይም መከላከያን በቴክኖሎጂ ለማዘመን እየተሰራ ባለው ስራ ሲቪሉም ጭምር እንዲመለመል የአዋጅ ማሻሻያ መደረጉን በመግለጽ፥ በተለያየ የትምህርት ዘርፍ የተመረቁ እና ወታደራዊ ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶች እድሉን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

መከላከያን ማዘመን የአንድ ወቅት ስራ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ በየጊዜው ከሚቀያየር ዓለም ጋር አብሮ መዘመን ያስፈልጋል ብለዋል።
የመከላከያ ሰራዊት አባላትም ራሳቸውን ሁሌም ለአዲስ ነገር ዝግጁ በማድረግ ለመለወጠ መስራት እንዳለባቸውም መልእከት አስተላልፈዋል።

በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲቪል የሚቆጣጠርው ወታደራዊ ሀይል የአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ዋልታ እንደመሆኑ፥ መከላከያ ሰራዊት በየጊዜው ከሚወጣውና ከሚወርደው የሲቪል ስራ አስፈፃሚ ጋር እንዳይወርድ በገለልተኝነት መስራት እንደሚገባው ነው የጠቆሙት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ባስተላለፉት መልእክትም፥ ዛሬ እየተገነባ ያለው መከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን ሉአላዊነት የሚጠብቅ፤ ነገ እናንተ በምርጫ አሸንፋችሁ ስልጣን ስትረከቡም ተግባሩን የሚቀጥል ነው ብለዋል።

Related stories   “ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በአንድነት በመከባበር፤ በመተሳሰብ እና በመረዳዳት ሊያከብር ይገባል”

ስለዚህ መከላከያ ሰራዊትን በሁሉም ነገር በጅምላ መፈረጅ አይገባም በማለት ጥፋት ሲታይ እንዲስተካከል መጠቆም እንጂ ተቋሙን እንደ ተቋም ማጠልሸት እንደማይገባ ገልፀዋል።

የጅምላ ፍረጃ እንደ ሀገርም ጉዳት የሚያስከትል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አሁን ጅምላ ፍረጃን እስከወዲያኛው አሽቀንጥረን የምንጥልበት ወቅት ላይ እንገኛለን ሲሉም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለህዝቡ ባስተላለፉት መልእክት ደግሞ፥ መከላከያ ከህዝቡ አብራክ የወጣ እና ለሀገሩ ክብር ሌት ተቀን የሚዋደቅ ነው ብለዋል።
ሆኖም ግን ለመከላከያ ሰራዊታችን ክብር ያለመስጠት በብዛት እንደሚስተዋልም ጠቅሰዋል።

የደንብ ልብስ የለበሰ የመከላከያ ሰራዊት አባል በሙሉ በሁሉም አገልግሎት መስጫ ተቋማት ቅድሚያ በመስጠት የሚገባውን ክብር መስጠት አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር እብይ አህመድ፥ ለሀገር ነፃነት የተዋደቀን ወታደር ማክበር የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ መሆኑንም ገልፀዋል።

በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን፥ የመከላከያ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ጠብቆ በየዓመቱ የካቲት 7 ቀን እየከበረ መምጣቱን አንስተዋል።

እለቱ የሚከበረው የመከላከያ ሰራዊቱ ህገ መንግስቱን ለመጠበቅ የገባነውን ቃል በማደስ፣ ከህዝብ ጋር ያለውን ቅርርብ ለማጠናከር እና የተሰው የሰራዊቱን አባላት በማሰብ ነው ብለዋል።

Related stories   አሜሪካ ለጊዜው ሲባል የከረመ ሃሳብ ያካተተ መግለጫ አወጣች፤ ምርጫውን በተዘዋዋሪ ደግፋለች

ጄኔራል ሰዓረ መኮንን አክለውም በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር ለውጥ ተጀምሯል ያሉ ሲሆን፥ የመከላከያ ሰራዊት የለውጡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

የመለከላከያ ሠራዊት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተቋማዊ ለውጥ ውስጥ እንደሚገኝ የገለፁት ጀነራል ሰዓረ፥ በዚህም ጠንካራ እና ዘመናዊ ሰራዊት ለመገንባት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም በሀገሪቱ ውስጥ ተከስተው በነበሩ አለመረጋጋቶች በህግ አግባብ በቀረቡለት ጥያቄዎች መሰረት የማረጋጋት ስራ እየሰራ መቆየቱን እና በዚህም የህዝብ ድጋፍ እንዳልተለየው አግለው ገልፀዋል።

ከሀገር አልፎም በጎረቤት ሀገራት ሰላምን ለማስከበር አመርቂ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የጀመረችው ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲጎለብት የመከላከያ ሠራዊት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሆነና ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የመከላከያ ሠራዊት ህዝባዊ ባህሪ የተላበሰ በመሆኑ አሁንም መስዋትነት እየከፈለ የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በቀጣይም የመከላከያ ሰራዊቱ በሚያከናውናቸው ስራዎች የፌደራል መንግስትና የክልል መንግስታትና ሌሎች የፀጥታ አካላት የሚያደርጉለትን ያልተቋረጠ ድጋፍ አናክረው እንዲቀል ጥሪ አቅርበዋል።

በሙለታ መንገሻ – fana

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0