ፍልስፍና፤ እውነት ምንድን ነው? ውበትስ? ተፈጥሮ ምን አላት? ጥበብስ እንዴት ትገኛለች? በሚሉ እና ሌሎች ጥያቄዎች አንድን አስተያየት ለምንና እንዴት እውነት ወይም ሀሰት መሆኑን ስለማጠየቅ እና ስለማወቅ የሚደረግ ምርምር ነው። ፈላስፋ የሚባሉ ሰዎችም አብዛኛውን ጊዜ አንድን ጉዳይ ሳይፈትሹ ከመቀበል ይልቅ አመክንዮአዊ ላይ መሰራት አድርገው ይመራመራሉ።

ሶቅራጠስ፣ ፕላቶ፣ ኒቼ፣ ኦሾ እና ሌሎችም ደግሞ በፍልስፍናው ዓለም ከሚጠቀሱ ስመጥር ሰዎች መካከል ተመድበው በአዳዲስ ሃሳቦቻቸው የበርካቶችን ቀልብ መግዛት የቻሉ ሰዎች ናቸው። ወደፍልስፍና የሚመራ መንገድ በአንክሮ መጠበብ ወይም ማሰብ መሆኑንም ግሪካውያን ጠበብት ይመሰክራሉ። ግሪክ የአውሮፓውያኑ የፍልስፍና መናኸሪያ መሆኗም ይነገርላታል።

ይህ የግሪካውያኑን ዕውቀት መሰረት ያደረጉ የምዕራባዊያኑ ፍልስፍና አቀንቃኞች፤ ፍልስፍና የተጀመረው በምዕራቡ ዓለም እንደሆነና፣ ሌሎች ማህበረሰቦች ለፍልስፍና መዳበር ምንም ዓይነት አስተዋፅኦ እንደሌላቸው ሲሞግቱ ይደመጣሉ። እዚህ ላይ የአፍሪካ ፈላስፎች አፍሪካ ውስጥ ሀገር በቀል ጥበብና ፍልስፍናዊ የሆነ አስተሳሰብ እንዳለ የመከራከሪያ ሃሳብ ከነማስረጃው ያቀርባሉ። አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙት የላቀ ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦች ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርአያዕቆብን ዋቢ ማድረግ ይቻላል።

ሀተታ ዘርአ ያዕቆብ በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የፈላስፋው የግዕዝ መጽሀፉ ኢትዮጵያውያን ፍልስፍናን በሚገባ ለዓለም ያሳዩበት ማስረጃ አድርጎ መቁጠር ይቻላል። ሀተታ ዘርአያዕቆብና ዘመናዊ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ስንመረምር አውሮፓውያኑ መጻሕፉ በብዕር ስም ስለተጻፈ ስሙ ኢትዮጵያዊ ሆነ እንጂ ጸሐፊው አውሮፓዊ ነው የሚል ክርክር ያነሳሉ። ይህም ዕውቀት ሁሉ የእኛ ነው ከሚለው የመታበይ ባህሪ የመጣ ይሆናል። በመሆኑ እዚህ ላይ በመጠኑ ስለፈላስፋው ኢትዮጵያዊነት እና የህይወት ጉዞ ማንሳት የግድ ይላል።

ሀተታ ዘርአያዕቆብን በ2006 ዓ.ም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጎሙት የኮሌጅቪል (ሚኒሶታው) ጌታቸው ኃይሌ፤ ዘርአያዕቆብ በሚባል ስም የሚታወቀው ሰው ወርቄ ነው ይሉናል። እንደ ተርጓሚው ከሆነ ወርቄ ለድርሰቱ ርዕስ ወይም ስም አልሰጠውም። ሐተታ ዘዘርአያዕቆብ (የዘርአ ያዕቆብ ትችት) የሚል ርእስ የሰጠው የጽሑፉን ቅጂዎች ከኢትዮጵያ ወደ ፓሪስ የላከው ፓድሬ ዳኡርቢኖ የተባለው የውጭ ዜጋ ነው። ደራሲው ወርቄ ግን ድርሰቱን የጀመረው “እግዚአብሔር ለነፍሴ ምን ያህል እንደሠራላት ልንገራችሁ” በማለት ብቻ እንደሆነ ይገልጹልናል።

ስለህይወት ታሪኩ ሲነግሩንም ደራሲው ስለራሱ በመጽሐፉ እንደሚነግረን የተወለደው በያዕቆብ መንግሥት በ3ኛው ዓመት ነሐሴ 25 ቀን 1592 ዓ.ም. አክሱም አካባቢ ከአንድ የገበሬ ቤተሰብ ነው። ሲወለድ ወርቄ በሚል ስም ቢጠራም ክርስትና ሲነሣ ደግሞ ዘርአያዕቆብ የሚል ስያሜ በቤተክርስቲያን ይሰጠዋል። በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሰው መጠሪያው የሚሆነው በዓለም ስሙ እንጂ በክርስትና ስሙ አይደለም። ራሱም ጸሐፊው የሚለው ይኸንኑ ነው፤ “ክርስትና ስነሣ ዘርአያዕቆብ ተባልኩ፤ ሰዎች ግን ወርቄ ነው የሚሉኝ” ብሎ መናገሩን ተርጓሚው አቶ ጌታቸው ጽፈውታል።

ከትርጉም መጽሐፉ ላይ እንደተገለጸው ወርቄ ወይም ዘርአያዕቆብ የፍልስፍና ምርምሩን የጀመረው በወቅቱ በኢትዮጵያ ነግሦ በነበረው አፄ ሱስንዮስ ዘመን ነው። ታሪክ እንደሚያስረዳው የአፄ ሱስንዮስ ዘመን አስተዳደር የሚታወቀው የኢትዮጵያን መንግስት ሃይማኖት ከኦርቶዶክስ ወደ ካቶሊክ በመቀየሩ ነው። በዚህም የህዝብ ቁጣ ተቀስቅሶ ነበር። ሱሰኒዮስ ካቶሊክ ሃይማኖትን የተቀበለበት ምክንያት አንደኛው ፔድሮ ፔዝ የተባለው የጀስዩት ሰባኪ ስላግባባው እና በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከፖርቹጋል እና ስፔን ወታደራዊ ድጋፍ ለማግኘት አልሞ ነበር።

ነገር ግን ከስፔን አልፎንሶ ሜንዴስ የተባለ ጳጳስ በኢትዮጵያ ላይ ተሹሞ ስላመጣ እና ህዝቡም አሻፈረኝ በማለቱ አገሪቷ አልተረጋጋችም። በሃይማኖት የተነሳው አመጽ እየጨመረ ስለመጣ፤ በርካቶችም ከንጉሡ ዘንድ እየተከሰሱ ቅጣት እና ሞት ይደርስባቸዋል። በወቅቱ ፍቅር በመጥፋቱና ብዙዎችም በመሰደዳቸው በርካቶች ለችግር ተጋልጠው ሳለ ፈላስፋው ግን ያስተምር ነበር። ይሁንና የውሸት ትምህርት ይሰጣል የሚል ክስ ይቀርብበት ጀመር። ክሱንም የሚያቀርበው ጓደኛው ከአክሱም ካህናት አንዱ የሆነ ወልደ ዮሐንስ የሚባል ሰው ሲሆን በየጊዜው ወደ ንጉሡ እየሄደ የዘርያዕቆብን ነፍስ አደጋ ላይ ሊጥላት ይሞክራል። ይህ ክስ የኋ ላኋላ እየጠነከረበት የመጣው ፈላስፋው ለህይወቱ በመስጋት ተሰደደ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፍልስፍና መምህሩ ፋሲል መርአዊ፤ በኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርአያዕቆብና የፖለቲካል ኢኮኖሚው ምሁር ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ሥራዎች ላይ በመመርኮዝ፤ ዘመናዊነት በኢትዮጵያ ያለውን ገፅታ የሚዳስስ ጽሑፍ አሰናድቷል። ከጽሑፉም ስለዘርአያዕቆብ የሚያወሳውን የፍልስፍና ክፍል እናያለን።

ፋሲል እንደሚለው፤ ዘርአያዕቆብ የሃይማኖት ትምህርትን በሚያስተምርበት ወቅት ከተለያዩ የሃይማኖት ተከታዮች ጋር በቀን ተቀን ህይወቱ ውስጥ ክርክር ውስጥ ይገባ ነበር። በዚህ ጊዜም የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች ፀረ-ሃይማኖታዊ የሆነ የአስተሳሰብ እንደሚከተልና የነሱን አስተሳሰብ ለመናድ እንደተነሳ አድርገው ይቆጥሩ ነበር። ዘርአያዕቆብ እንደሚያሳየን ከሆነ በአካባቢው የሃይማኖትን ትርጓሜ ሲያስተምር ከሁሉም የሃይማኖት ተከታዮች ጋር ግጭት ውስጥ ገባ። ከጊዜ በኋላም በአስተሳሰቡ ምክንያት ቅጣት ይደርስብኛል ብሎ ስላሰበ ዘርአያዕቆብ ስደትን መረጠ።

ወርቄ በመጽሐፉ እንደሚገልጸው፤ ለስደት ሲነሳ የጸሎት መጻሕፉን፣ መዝሙረ ዳዊቱን እና ሶስት ወቄት ወርቅ ይዞ ወደ ሸዋ ሲሄድ ሰው የሌለበት አንድ ዱር ያገኛል። እዚያ ከአንድ ትልቅ ገደል ስር ጥሩ ዋሻ ይመለከታል። ሰዎች በማያውቁት ሁኔታ በዚህ ዋሻ ተቀመጠ። ሲርበው ወጣ ብሎ ይለምናል፤ አልፎ አልፎም ገበያ እየሄደ የሚያስፈልገውን ይገዛዛል። በዚያም ይዞት የሸሸውን ዳዊቱን ከደገመ በኋላ ሥራ ፈትቶ ቁጭ ሲል ጥልቅ ጥያቄዎችን ማንሳትና መጣል ጀመረ።

በዋሻዋ ውስጥ ተደብቆ በሃሳቡ ሲመራመር ዘርአያዕቆብ ሐተታ የተሰኘ የፍልስፍና መንገድን ማዳበር ጀመረ። በዚህ ጊዜም በፈጣሪ ህልውናና በዓለም ላይ ስለሚታየው ስቃይ፣ የሃይማኖት አስተምህሮና በሃይማኖት መካከል ስለሚገኘው ግጭት ለማሰብ ይሞክር ነበር። ዘርአያዕቆብ እንደሚነግረን ከጊዜ በኋላም ራሱን ሲጠይቅ «ሁሉ በቅድሳን መጻሕፍት ላይ የተጻፈው ነገር እውነት ነው?» ማለቱን እና በመጨረሻም ለሰው ልጅ በጐ ህሊናን የሰጠ አምላክ ለዓለምና ለነገሮች መፈጠር ምክንያት መሆኑን፤ ዓለም ላይ የሚታየው እልቂት በሰው ልጅ ገደብ የለሽ ፍላጐት መምጣቱንና ሁሉም ሰዎች በፈጣሪ ፊት እኩል መሆናቸው ድምዳሜ ላይ መድረሱን ይገልጻል። ይህም የፍልስናው መሰረት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

የፍልስፍና አስተሳሰብ የቀሰቀሰበት የተማረው የኦርቶዶክሱና የካቶሊኩ ሃይማኖት አለመስማማትና ሥራ ፈትነቱ እንደነበር ይናገራል። ከሁለቱ ሃይማኖቶች ትክክለኛው የትኛው ነው? ከማለት አልፎ ሰዎች ይህን ያህል ጨካኝ እና እርስ በርስ ተጨቃጫቂ ሲሆኑ ለምን እግዚአብሔር ዝም አላቸው? ወደሚል እና ለመሆኑ ፈጣሪ እግዚአብሔር አለ ወይ? ከሚል ጥርጣሬ ገባ። በኋላ ላይ ግን የሰው ልጅ ፈጣሪ ካልሆነ የፈጠረው አምላክ እንዳለ እና ሰው ግን በምድር ያለውን ሁሉ መመራመር እንደሚገባው አመነ። ፈጣሪ በሰው ልብ ውስጥ ባስቀመጠው ንጹሕ ልቦና የሚመረምር ሁሉ የተፈጥሮን ሥርዓትና ሕጎች አይቶ እውነትን ያገኛል እያለም ተመራመረ።

በሐተታውም ላይ እንዲህ ይላል፤ «በዋሻ ሳለሁ ከጸሎት በኋላ ሥራ ስለሌለኝ ሁልጊዜ ቁጭ ብዬ ስለሰው ጭቅጭቅ፣ ስለክፋታቸውም ሰዎች በስሙ እያመፁ ጓደኞቻቸውን ሲያሳድዱ ወንድሞቻቸውን ሲገድሉ ዝም ስለሚለው ስለፈጣሪያቸው ስለ እግዚአብሔር ጥበብ አስብ ጀመርኩ። ምክንያቱም በዚህ ዘመን ፈረንጆቹ ኃይል አግኝተው ነበረ። ግን ፈረንጆቹ ብቻ ሳይሆኑ የአገር ሰዎችም ከነሱ የባሰ ከፍተዋል። የፈረንጆችን ሃይማኖት የተቀበሉት ግብጻውያን እኮ ትክክለኛዋን የጴጥሮስ መንበርን ሃይማኖት ክደዋል፤ የእግዚአብሔር ፀሮች ናቸው ይላሉ፤ በዚህም ያሳድዷቸዋል።

ግብጻውያንም ስለራሳቸው ሃይማኖት እንደዚሁ ያደርጋሉ። ሰው ሁሉ ሃይማኖቴ ትክክለኛ ነች፤ በሌላ ሃይማኖት የሚያምኑ በውሸት ያምናሉ። የእግዚአብሔር ጠላቶች ናቸው ይላሉ። ዛሬም እኮ ፈረንጆች የኛ ሃይማኖት ጥሩ ናት፤ የእናንተ ሃይማኖት መጥፎ ናት ይሉናል። እኛም ደግሞ እንደዚህ እንደምትሉት አይደለም፤ የእናንተ ሃይማኖት መጥፎ ናት፤ የኛ ሃይማኖት ልክ ናት ብለን እንመልስላቸዋለን። እንዲሁም እስላሞችንና አይሁዶችን ብንጠይቃቸው እነሱም እንደዚሁ ባሉን። በዚህ ክርክር ማን ፍርድ ሰጪ ይሆናል? ከሰው ማሀል አንዱም ፍርድ ሰጪ አይሆን፤ ምክንያቱም ሰዎች ሁሉ እርስ በርሳቸው ከሳሽና ተከሳሽ ናቸው።

በዚህ ባለንበት ዘመን ክርስቲያኖቹ የእግዚአብሔር ትምህርት ከእኛ ዘንድ በቀር አይገኝም ይሉናል። አይሁድም፣ እስላሞችም፣ ህንዶችም፣ ሌሎችም እንደዚሁ ይላሉ። ደግሞ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው አይስማሙም። ፈረንጆቹ የእግዚአብሔር ትምህርት ያለው እኛ ዘንድ እንጂ እናንተ ዘንድ የለም እያሉ ይናገራሉ። እኛም ስለራሳችን እንደዚሁ ነው የምንለው። አንዱ ‘እንዲህና እንዲህ እውነት ነው’ ሲል ሌላው ‘የለም እሱማ ውሸት ነው’ ይላል። የሰውን ቃል የእግዚአብሔር ቃል እያደረጉ ሁሉም ይዋሻሉ። እስቲ እናስብ፤ ለምንድነው?» እያለም ያጠይቃል።
ከዚህ በኋላ አስቤ እንዲህ አልኩ ይለናል ወርቄ፤ በተተረጎመው መጻሃፉ ላይ፤ «ሰዎች ብጠይቃቸው በልባቸው ካለው በተቀር ሌላ ምን ይመልሱልኛል? በዚህ በትልቅ ጉዳይ ሰዎች ራሳቸውን ለማጥፋት ለምን ይዋሻሉ? የሚዋሹት ምንም ስለማያውቁ የሚያውቁ እየመሰላቸው መሰለኝ። በዚህም ምክንያት እውነትን ለማግኘት አይመራመሩም። ዳዊት ‘ልባቸው እንደወተት ረግቷል’ ይላል። እነርሱም ከቀደሟቸው ሰዎች በሰሙት ልባቸው ረግቶ እውነት ይሁን ሐሰት አልተመራመሩም» እያለ ይተቻቸዋል። «አንተ በእውነት ገሥጸኝ፤ በምሕረትም ንቀፈኝ። የኃጢአተኞችንና የሐሰተኞችን መምህሮች ቅባት ግን ራሴን አልቀባም፤ አስተዋይ አድርገህ ፈጥረኸኛልና ግለጽልኝ» በማለትም አምላክን ይጠይቃል።

በመጽሐፉ እንደሰፈረው፤ ‘ሰዎች ሁሉ ሐሰትን እንጂ እውነትን የማያስተውሉት ለምንድነው?’ ምክንያቱ የሰው ተፈጥሮው ደካማና ስልቹ ስለሆነ ሳይሆን አይቀርም። ሰው እውነትን ይወዳል፤ አጥብቆም ያፈቅራታል። የተፈጥሮን ስውር ነገሮች ማወቅ ይፈልጋል። ግን ነገሩ አስቸጋሪ ነው፤ ያለ ትልቅ ጥረትና ትዕግሥት አይገኝም፤ ሰሎሞን እንዳለው ‘ከፀሐይ በታች ስለተፈጠረው ሁሉ ልቤን ለምርመራና በጥበብ ለመፈተን ሰጠሁ፤ ምክንያቱም ይደክሙበት ዘንድ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ክፉ ድካምን ሰጥቷቸዋል።’ ስለዚህ ሰዎች መመራመርን አይፈልጉም፤ ከአባቶቻቸው የሰሙትን ያለ ምርምር ማመንን ይመርጣሉ እንጂ። ለተመራማሪ ግን እውነት ፈጥና ትገለጣለች፤ ምክንያቱም ፈጣሪ በሰው ልብ ውስጥ ባስቀመጠው ንጹሕ ልቦና የሚመረምር ሁሉ የተፈጥሮን ሥርዐትና ሕጎች አይቶ እውነትን ያገኛል።

እንደ ዘርአያዕቆብ ከሆነ፤ የሰው ሃይማኖት ከእግዚአብሔር ባትሆንም ቅሉ በሰዎች ዘንድ ትፈለጋለች፤ ደግ ሥራ እንዲሠሩ ታስገድዳቸዋለች። ይህም ማለት ክፉዎች ክፉ ሥራ እንዳይሠሩ ታስፈራራቸዋለች፤ ደጎችን ደግሞ በትዕግሥታቸው ታበረታታቸዋለች። «ለእኔ እንደዚህ ያለችው ሃይማኖት ባሏ ሳያውቅ በዝሙት እንደወለደች ሚስት ትመሰላለች» ዘርአያዕቆብ።

ምክንያቱም ባሏ ልጁ በመሰለው ሕፃን ይደሰታል፤ እናቲቱንም ያፈቅራታል። ከዝሙት እንደወለደችው ቢያውቅ ያዝናል፤ ሚስቱንም ከነልጇ ያባርራታል። እንደዚሁም «እኔ ሃይማኖቴ ዘማ ወይም ውሸተኛ መሆኗን ካወቅሁ በኋላ ስለሷና በዝሙቷ ስለወለደቻቸው ልጆቿ አዘንኩ» ይለናል። ልጆቿ የሚለው ደግሞ ወደ እዚህ ዋሻ የሰደዱትን ጥልን፣ ስደትን፣ ዱላን፣ እስራትን፣ ሞትን መሆኑን ይገልጻል። በዚህ ዘመን ግን ሰዎች የወንጌልን ፍቅር ወደጥል፥ ወደጨቋኝነት፥ ወደእባብ መርዝ አዞሩት። ሃይማኖታቸውን ከመሠረቷ ንደው ከንቱ ነገር ያስተምራሉ፤ አመፃ እየሠሩ በውሸት ክርስቲያን ስለመባላቸው እያሰበ ይመራመራል።

ቢዚህ ፍልስፍና ላይ እንዳለ ንጉሥ ሱስንዮስ በ1625 ዓ.ም ሞተ። ራሱ ፈላስፋው እንደሚነግረን፤ በምትኩ ልጁ ፋሲለደስ ነገሠ። በዚያን ጊዜ ከዋሻው ወጥቶ ወደ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ሄደ፤ በኋላ ወደ በጌምድር ተሻገረ። ፈረንጆችን ለሚጠሉ የጊዜው ሰዎች ሁሉ ፈረንጆችን ከሚያቀርበው በንጉሡ በሱስንዮስ ዘመን ከሸሹት መነኮሳት መካከል አንዱ መስሏቸውም አቀረቡት፤ ምግብና ልብስም ሰጡት። እንደዚህ ከሀገር ወደ ሀገር ሲሄድ ግን ወደ አክሱም ለመመለስ አልፈለገም ነበር። «ምክንያቱም የካህናቷን ክፋታቸውን አውቅ ነበረ» በማለት ከዋሻ ከወጣ በኋላም ወደሚያስተምርበት ቦታው ለመመለስ ለህይወቱ ይሰጋ እንደነበር ይገልጻል።

«ከዚያም ወደ ጐዣም ተሻግሬ እዚያ እንድኖርም አሰብኩ። እግዚአብሔር ግን ወደ አላሰብኩበት መራኝ። ከዕለታት በአንዱ እንፍራዝ ውስጥ ሀብቱ ወይም ሀብተእግዚአብሔር ከሚባል አንድ ሀብታም ሰው ዘንድ ደረስኩ» በማለት ዘርአያዕቆብ ስለራሱ ይተርካል። እዚያ አንድ ቀን ከቆየ በኋላ በማግስቱ አክሱም ላሉ ዘመዶቹ ደብዳቤ ለመጻፍ ይፈልግና ያረፈበትን ቤት ባለቤት ቀለምና ክርታስ ይጠይቀዋል። በዚህ ጊዜ ጽሕፈት እንደሚችል ይታወቃል።

ሀብቱ የተባለው ሰው ከእርሱ ጋር ጥቂት ጊዜ እንዲቀመጥና መዝሙረ ዳዊትን እንዲጽፍለት ይጠይቀዋል። በዚህም ጊዜ ደስ ይለውና ጽፎ ሰጠው፣ በመልሱም ክፍያ አገኘ። ለአገሩ ሰው ሁሉ የጸሎት መጻሕፍንትም እየቀዳላቸው የተከበረ ሰው ሆኖ ገንዘቡን እየተቀበለ ኖረ። በኋላ በዚያው አካባቢ ሚስት አግብቶ ሃያ አምስት ዓመት ሲኖር የልጁን የልጅ ልጆች አይቶ ፍልስፍናውን እያሰራጨ መቆየቱን አቶ ጌታቸው ይገልጻሉ።

ፋሲል እንደሚለው ደግሞ፤ ይህ ሁሉ ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም። በዘርአያዕቆብ ፍልስፍናዊ አመለካከት ውስጥ የወግ የባህልና የሃይማኖት ትችት እናገኛለን። የዘርአያዕቆብ ሐተታ በተፈጥሮው የነገሮች መሠረት በመመርመርና በመጠየቅ ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህ ፍልስፍና ውስጥ ዘርአያዕቆብ ከፈጣሪ ህልውናና የሰው ልጅ ተፈጥሮ፣ የማኅበረሰባዊ ፍትህና የግበረገብ መርሆች ጋር የተገናኙ ጥያቄዎችን ለማንሳት ጥሯል።
ፍልስፍናው ግብረገባዊ መልዕክትም ያስተላልፋል። በዘርአያዕቆብ ግብረገብ አስተምህሮት ውስጥ በሰው ልጅ ምክንያታዊ የሆነ ተፈጥሮ፣ የተፈጥሮ ህግጋትና የፈጣሪ ህልውና መካከል ቅርብ የሆነ ቁርኝነት እንዳለ እንመለከታለን። ስለሆነም ለዘርአያዕቆብ እውነትና የግብረገብ መርሆዎች ዓለም አቀፋዊ የሆነ ተፈጥሮ አላቸው። ይህንንም ተፈጥሮ የሰው ልጅ በተፈጥሮ በተሰጠው ምክንያት አንጂ በጊዜና በቦታ በተወሰኑ አመለካከቶች መረዳት አንችልም።

የፍልስፍና መምህሩ ፋሲል እንደሚገልጸው፤ የዘርአያዕቆብ ፍልስፍና መሠረት በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው የሃይማኖቶች አለመግባባትና ክርክር ነው። ዘርአያዕቆብ እንደ ፈላስፋ በሃማኖታዊ ሥርዓትና ትምህርት ውስጥ ነው ያደገው። ሐተታ በተሰኘ ሥራው ውስጥም ሀሳቡን ሲያዳብር ፈጣሪ የፍልስፍና ጉዞውን እንዲያቀናለት በመጠየቅ ነው። ዘርአያዕቆብ በፍልስፍናው ውስጥ እንደሚጠይቀው ከሆነ የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች የራሳቸው እምነት ከሌሎች የተሻለ እንደሆነ ለማሳየት ይኖራሉ። በመሠረታዊነት ደረጃ ግን እውነት አንድ ናት። ለዘርአያዕቆብ የአንድን ሃይማኖት አስተሳሰብ ከመከተል ይልቅ በበጐ ህሊና የእውነት ተፈጥሮን መመርመር ያስፈልጋል። የአንድ ማኅበረሰብም ዕድገት በሰዎች እኩልነት፣ በምክንያታዊነትና ማህበረሰባዊ ፍትህ ላይ መታነፅ እንዳለበት ዘርአያዕቆብ ያሳየናል።

የዘርአያዕቆብ ፍልስፍና የአንድ ማህበረሰብ መሰረት በምክንያታዊነት የተመራ የግለሰብ ጉዞ እንደሆነ ያመላክታል። ስለዚህም የማኅበረሰባዊ ለውጥ አብሮ የመኖር ምስጢር እንደሆነና የማኅበረሰባዊ ፍትህ በግለሰባዊ ነፃነትና ምክንያታዊ የሆነ ተፈጥሮ ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ያሳያል። በተጨማሪም ፍልስፍናው የሁሉንም ሰዎች መሠረታዊ አኩልነት እንደ መነሻ አድርጐ ይቆጥራል። አንድን ሃይማኖት ከሌላው ከማስበለጥና በሃይማኖት አስተምህሮት ላይ የተመረኮዘ እሴትና የስነምግባር ህጐች ከማዳበር ይልቅ ዘርአያዕቆብ ህገ ልቦና እንዴት የእውነት መሠረት እንደሆነ ሊያሳየን ይሞክራል። ይህም ህገ ልቦና በሁሉም የሰው ልጆች ውስጥ በተፈጥሮ የሚገኝ የማሰብና የማመዛዘን ችሎታ ነው።

በፍልስፍና መስክ ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርአያዕቆብ፣ የባህልና የወግ አስተሳሰቦችን ትችት በማዳበር በማህበረሰቡ ውስጥ ምክንያታዊነትና ማህበረሰባዊ ፍትህ እንዲሰፍን ያበረከተው አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም። በነዚህ ሙከራዎች ላይ ተመርኩዘን ዘመናዊነት የበለጠ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲዳብር ምክንያታዊ የሆነ ማህበረሰብ እንዲያብብ ያለውን የፍልስፍና ጥቅም መረዳት ይቻላል።
እንደ ፋሲል ከሆነ፤ ዘመናዊነት ከግለሰአባዊ ነፃነት፣ ማኅበረሰባዊ ለውጥና በምክንያት ከሚመራ የህሊና አብርሆት ጋር ይገናኛል። የሰው ልጅ ከወግና ከባህል ራሱን ነጻ በማውጣት ምክንያትን ተጠቅሞ ራሱንና አካባቢውን የበለጠ መረዳት ይችላል በሚል ሃሳብም ላይ ተመርኩዟል። በአሁኑ ወቅት ምንም እንኳን ዘመናዊነት ከምዕራባዊው ዓለም ሰልጣኔ ጋር መነጣጠል እንደማይችል ቢታሰብም፣ ነገር ግን የዘመናዊነት ሀሳብ በተለያዩ ማኅበረሰቦችና የታሪክ አጋጣሚዎች በተለያዩ የዓለም ክፍላት ተንፀባርቋል።

እዚህ ላይ ዘመናዊነት በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና አመለካከት ውስጥ ምን ይመስላል? የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርአያዕቆብ ሐተታ በተሰኘው መጽሐፍ የቀረበው የፍልስፍና መንገድ በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የሃይማኖት ግጭትና አለመግባባት መፍትሄ ለማስቀመጥ ይሞክራል። በዚህ ፍልስፍና ውስጥም ከፈጣሪ ህልውና፣ የእውነት ተፈጥሮ፣ በዓለም ላይ ያለውን ግጭትና መንስኤውና የስነምግባር ፍልስፍና ለማዳበር ይጥራል። በዚህም ዘርአያዕቆብ በኢትዮጵያ ውስጥ በሀገር በቀል ባህልና የዘመናዊነት እሳቤዎች፣ በተጨማሪም ሀገር በቀል የሆነ የዘመናዊነት እሳቤ ለማዳበር በሚደረገው ጥረት ውስጥ መሰረታዊ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው መረዳት ያስፈልጋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የዘመናዊነት ሃሳብ በአብዛኛው ማዕከላዊ የሆነ መንግሥት ከመመስረትና የምዕራቡን ዓለም ስልጣኔ ከመከተል ጋር ይቆራኛል። እንደ አፍሪካዊው ፈላስፋ ዲስማስ ማሶሎ ከሆነ የአፍሪካ ፍልስፍና በከፊል የምዕራቡን ዓለም ቅኝ ግዛታዊ የሆነ አስተሳሰብ ትችት ተደርጐ ሊቆጠር ይችላል። ሐተታ ዘርአያዕቆብ የተሰኘው የዘርአያዕቆብም ፍልስፍና በተለያዩ ሀገራት ሃይማኖቶች ላይ የሰላ ትችት የሚያቀርብበት መንገድ አለው።

ዘርአያዕቆብ በምክንያት የሚመራ ማኅበረባዊና ግለሰባዊ አስተሳሰብ ለአንድ ማህበረሰብ መሠረት እንደሆነ ያሳያል። የዘርአያዕቆብ ፍልስፍና የሃይማኖትን ግጭትን ለማስቀረትና በዓለም ላይ በሃይማኖት ስም የሚደረገውን እልቂት ለማስቀረት በህገ ልቦና ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ መዳበር እንዳለበት መንገድ አመላካች ነው። ይህ የሃይማኖት የሞራል እና የዘመናዊነት እሳቤዎችን አጭቆ የያዘው ሐተታ ዘርአያዕቆብ የተሰኘው ፍልስፍና ልዩ የስነጽሑፍ ሀብት ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያዊውን ዘርአያዕቆብን በፍልስፍናው ልንማርበት የምንችል ታላቅ ሰው እንደነበር መመስከር ይቻላል።

አዲስ ዘመን ጥር19/2011

ጌትነት ተስፋማርያም

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *