አዲስ አበባ ፣ የካቲት 22 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የአርበኛ እናቶቻችንና አባቶቻችን በአድዋ ድል የመቀዳጀታቸው እና የማሸነፋቸው ቁልፍ ሚስጥር ውስጣዊ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በህብረትና በአንድነት ተደምረው ለአንድ ሀገር በመቆማቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ 123ኛው የአድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸው እናት አባቶቻችን በአድዋ የተቀዳጁት ድል በኢትዮጵያ ምድር የኢትዮጵያ እንጅ የቅኝ ገዥዎች ሰንደቅ አላማ እንዳይውለበለብ ያደረገ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ነፃነት ታፍሮና ተከብሮ እንዲኖር ያስቻለ ደማቅ የታሪክ አሻራ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የደምና የአጥንት መስዕዋትነት የተከፈለበት ይህ ድል የዛሬውና የነገው ትውልድ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ትክሻው ጎብጦ አንገቱን ደፍቶ እንዳይኖር እንዳደረገውም ተናግረዋል።

የአድዋ ድል በዓል በዓለም ፊት በኩራት እንድንቆም አባቶቻችን ያወጁልን አክሊልም ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን በጣሊያን ጦር ላይ የተቀዳጁትና ከኢትዮጵያ ባለፈ ለመላው አፍሪካ ብሎም በባርነት ቀንበር ስር ለነበሩ የዓለም ህዝቦች ተስፋ የፈነጠቀና ወኔ የሰነቀ ታሪካዊ ክስተት እንደሆነም አስረድተዋል።

ድሉ ትናንትን ዘክረን ዛሬን መርምረን ነገን ለማቅናት ወሳኝ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ወደ ሌሎች ድርብ ድርብርብ ድሎች መሸጋገሪያ የድካም መርቻ ጉልበታችን በዛለ ጊዜም መበርቻ ነው ብለዋል።

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

ለዚህም ከአድዋ ድል ወዲህ በአድዋም ይሁን በሌላ መልኩ የተቀዳጀናቸው ስኬቶች ህያው ምስክሮች መሆናቸውን አንስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬው ትውልድ የሚገጥሙትን ፈተናዎችና ተግዳሮቶች በድል በመወጣት የአያቶቹን እና የአባቶቹን ታሪክ የሚደግምበት ጊዜ ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።

አድዋ ከትግልና ድል የሚሻገር ረቂቅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ህይወታዊ አስተምህሮ የያዘ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ፍልስፍና መሆኑንም ገልጸዋል።

የአድዋ ድል መላው ኢትዮጵያውያን ከጫፍ ጫፍ በመተባበር የማንነታቸውን ልክ ያሳዩበት የመስዋዕትነት ውጤት መሆኑንም አውስተዋል። ድሉ የሴት ኢትዮጵያውያን የአርበኝነት ተጋድሎና የላቀ ሚና መገለጫ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ የአድዋ ድልን የሚያከብር ህዝብም የሴቶች ክብር የገባው ሊሆን ይገባልም ብለዋል።

የአድዋ ድል ህዝብና መንግስት ሲተባበሩ የሚበግራቸው ነገር አለመኖሩን ማሳያ እንደሆነም አውስተዋል። በዓሉን ስናከብርም እንደ አዲስ ትውልድ በድሉ ውስጥ የተካተተውን ምስጢር በመረዳት መሆን ይገባልም ብለዋል በመልዕክታቸው።

በአድዋ ድል ውስጥ ህልውናን አፅንቶ መኖር፣ ዲፕሎማሲ፣ ወታደራዊ ስትራቴጂ፣ ታላቅ ውስጣዊ የህዝቦች ህብረትና አንድነት፣ ጥበብና ተግባቦት፣ ፍቅር እና መስጠት፣ ክብርና ጀግንነት ሞልቶና ሰፍቶ የነበረ መሆኑን እረዳለን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

Related stories   Ethiopia’s transition misrepresented. Reply to Obang Metho

በመልዕክታቸው አንድን ሀገራዊ ድል ለማስመዝገብ የሁሉንም አካላት ተሳትፎ የግድ እንደሚል እንማራለን ብለዋል በመልዕክታቸው።

የሀገር መሪዎች፣ የጦር አበጋዞች፣ ቃፊሮች፣ ወታደሮች፣ ስንቅ አዘጋጆች ሀኪሞች፣ አዝማሪዎች ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ እንጨት ፈላጮች፣ ውሃ ቀጂዎች፣ የእደ ጥበብ ባለሙያዎች ፣ ታሪክ መዝጋቢዎች ሌላ ቀርቶ ክብቶችና አጋሰሶች እንኳን ሳይቀሩ ለድሉ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ አድርገዋል። መደመር ማለት ይሄ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።

በጦር መሳሪያ አቅም፣ በሀብት፣ በወታደራዊ አደረጃጀት እና ዘመናዊ የጦር ስልት በወቅቱ ታላቅ ደረጃ ደርሻለሁ ብሎ ያሰበውን የኢጣሊያ ወራሪ ጦር ከዚህ በፊት ባልታየና በታሪክ ውስጥ ባልተስተዋለ ጀግንነት፣ አርበኛ እናቶቻችንና አባቶቻችን ድል የመቀዳጀታቸው እና የማሸነፋቸው ቁልፍ ሚስጥር ውስጣዊ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በህብረትና በአንድነት ተደምረው ለአንድ ሀገር በመቆማቸው ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ብልህ ትውልድ ከአድዋ የድል መሰዊያ ላይ ሊጭር የሚገባው ነገርም ይሄን ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን እንደ ትናንቶቹ ኢትዮጵያውያን በህይወት መስዋዕትነት ብቻ ሳይሆን እየኖርን በመስራት፣ በደም የተቀበልናትን ሀገር ነፃነቷን ጠብቀን ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ ጠንክረን መታገል ይገባናል ሲሉ አሳስበዋል።

በልዩነት ተቆራቁሰን እርስ በእርስ የምንጫረስና የምንጠፋፋ ሳይሆን የሀገሪቱን ችግሮች ለመቅረፍ እንድንችል በህብረትና በአንድነት፣ በፍቅርና በይቅርታ ወደፊት መራመድ እንደሚገባ ገልፀዋል።

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

መሪና ተመሪ በሁሉም ጉዳዮች ባይግባቡ እንኳን የሀገርን ነፃነት፣ አንድነት፣ እኩልነት፣ ፍትህና ዴሞክራሲን በተመለከተ ጉዳዮች ግን ተግባብተውና አንድ ሆነው ከራሳቸው አልፎ ለሌላው የሚተርፍ ድል ያስመዘግባሉም ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

በደምና አጥንት የተጠበቀን አንድነት ከስነ ልቦናና ከክብር ትሩፋትነት አልፎ ለኢኮኖሚ ፀጋነት እንዲተርፍ በደም ሳይሆን በላብ፣ በአጥንት ሳይሆን በጉልበት የምንከፍለው የመጭው ትውልድ እዳ አለብን ብለዋል።

ይህ የተጋድሎ ታሪክ በዓለም ፊት ተገቢውን ቦታ እንዲይዝ በሳይንሳዊ ምርምር እና በጥበባዊ ስራዎች ማረጋገጥ እና ማድመቅ እንደሚገባም ነው በመልዕክታቸው የጠቆሙት።

አድዋ እስካሁን በተከናወኑት ስራዎች ብቻ ተዘርዝሮ እና ተዘክሮ የሚያልፍ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ያገባናል የሚሉ ሁሉ ከስነ ጥበብ፣ ከእምነት፣ ከፍልስፍና፣ ከታሪክ እና ከሴቶች ተሳትፎ፣ ከመሪነት ጥበብ፣ ከሀገራዊ አንድነት፣ ከውትድርና ሳይንስ፣ በኢኮኖሚ ራስን ከመቻል ብሎም ከጥቁር ሀዝቦች የነፃነት እና የትግል ታሪክ ፋና ወጊነት ጋር በማስተሳሰር ዓለም አቀፋዊ ደረጃ ያለውን ስራ እንዲያከናውኑ ጥሪ በማቅረብ በዚሁ ውስጥም መንግስት የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

Source – FBC

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *