“Our true nationality is mankind.”H.G.

የወሲብ ቪዲዮ ህይወቷን ያሳጣት ወጣት

ጣሊያናዊቷ ቲዚአና ካንቶን ራሷን እንድታጠፋ ያስገደዷት ሁነቶች በቅጽበት የተከሰቱ ናቸው።

እንደ አውሮፓውያኑ መጋቢት 2007 ላይ የ31 ዓመቱ ጣሊያናዊ በርካታ የወሲብ ቪዲዮዎችን በዋትስአፕ ለአምስት ሰዎች አጋራ።

 

የወሲብ ቪዲዮዎቹ ከተላከላቸው ሰዎች መካከል የቲዚአና የቀድሞ ፍቅረኛ ሰርጂዎች ዲ ፓሎ ይገኝበታል። ሰርጂዮ እና ቲዚያና በፍቅራቸው ዘመን ጥሩ ግንኙነት አልነበራቸውም።

በዋትስአፕ የተላኩት ቪዲዮዎች ቲዚያና ማንነታቸው ካልታወቁ የተለያዩ ሰዎች ጋር ወሲብ ስትፈጽም ያሳያሉ።

ቪድዮዎቹ በፍጥነት ተሰራጩ

ቪዲዮዎቹ በፍጥነት ተሰራጩ። በተለያዩ ልቅ የወሲብ ድረ ገጾች ላይም ተጫኑ። ሰዎች ቪዲዮዎቹን ይመለከቱ፣ ይጋሩም ጀመር። ቲዚአና ግን ይህ እንዲሆን አልፈቀደችም ነበር።

 

የቲዚአና የ15 ዓመት ጓደኛ ቴሬሳ ፔተሮሲኖ ”እጅግ ውብ እና ስሜቷ በቀላሉ የሚጎዳ ሴት ናት” በማለት ትገልጻለች። ”ትክክለኛ ባልሆነ ሰዓት፣ ትክክል ካልሆኑ ሰዎች ጋር ነበረች” ትላለች።

ቲዚአና ”ቪዲዮ እየቀረጽክ ነው?” ስትል ወሲብ እየፈጸሙ ሳሉ ካሜራ የያዘውን ሰው ትጠይቃለች። ከዚያም ”በጣም ጥሩ” ትላለች።

ይህ ንግግር ወሲብ እየፈጸመች በቪዲዮ መቀረጽ “ያስደስታታል” በሚል በርካቶችን አስማማ። ቪዲዮን ለመመልከት እና ለማጋራትም ምክንያት ሆናቸው።

ሰዎች ቪዲዮዎቹን ከመመልከት እና ከማጋራትም አለፉ። የቲዚአና ምስል በካናቴራዎች ላይ ይታተ ጀመር። ስሟም ማፌዣ ሆነ።

“ወዳ እና ፈቅዳ የፈጸመችው ነው” ተብሎ ስለታሰበ ቪዲዮዎቹን ማየትና ማጋራት በቲዚአና ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተጽዕኖ ማንም አላሰበም። “ወዳ እና ፈቅዳ የፈጸመችው ነው” የሚለው አስተሳሰብም ስህተት ነበር።

ቲዚአና ቪድዮው ሲቀረጽ በአደንዛዥ ዕጽ ተጽዕኖ ስር ወድቃ ነበር። ቪዲዮዎቹን መቀረጽ የሚያስከትልባትን ጉዳት ማገናዘብ የማትችልበት ሁኔታ ውስጥ ነበረች።

”ከቲዚአና ጋር ስለ ቪዲዮቹ በዝርዝር አላወራንም።” ስትል ጓደኛዋ ቴሬሳ ትናገራለች። ”በቪዲዮዎቹ ምክንያት ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ገብታ ነበር” ትላለች ቴሬሳ።

ጉዳዩን ፍርድ ቤት ወሰደችው

ቲዚአና ቪዲዮዎቹን ለማስጠፋት ቆርጣ ተነስታ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወሰደችው። ቪዲዮዎቹ በተለያዩ ድረ ገጾች ላይ የተጫኑት ያለፍቃዴ ነው ስትል አቤቱታ አቀረበች። ነገሮች ግን ጉዳዩን እንዳሰበችው ቀላል ሆኖ አላገኘችውም።

”የሆነ ደረጃ ላይ ስትደርስ የምትወጣው ነገር እንዳልሆነ ተረዳች። እኚህ ቪዲዮዎች እንደማይጠፉ እርግጠኛ ሆነች። ወደፊት ባለትዳር ስትሆን ባሏ እኚህን ቪዲዮዎች መመልከቱ አይቀርም። የልጆች እናት ስትሆንም ልጆቿ የእናታቸውን የወሲብ ቪዲዮ ማየታቸው አይቀርም” በማለት ጓደኛዋ ቲዚአና የገባችበትን ጭንቀት ታስረዳለች።

የቲዚአና እናት ማሪያ ቴሬሳአጭር የምስል መግለጫየቲዚአና እናት ማሪያ ቴሬሳ

ቲዚአና ካንቶን ሽሽትን መርጣ ከከተማ ርቃ ወደ ቤተሰቦቿ መኖሪያ መንደር አቅንታ ከእናቷ ጋር መኖር ጀመረች።

የቲዚአና እናት ”ልጄ በጣም መልካም ሰው ነች” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ወላጅ እናት ጨምረውም፣ ቲዚአና ያለ አባት ማደጓን እና ይህም በህይወቷ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳሳደረባት ይናገራሉ።

ቲዚአና በደስታ ትኖር በነበረበት ጊዜ ሙዚቃ ማድመጥ እና ፒያኖ መጫወት ታዘወትር ነበር። ቪዲዮዎቹ የአደባባይ ሚስጥር ሲሆኑ ግን ይህን ሁሉ ማድረጓን አቆመች።

ለፍርድ ቤት ያቀረበችውን አቤቱታ ተከትሎ ቪዲዮዎቹ ከበርካታ ድረ ገጾች ላይ እንዲነሱ ቢደረግም፣ ፍርድ ቤቱ ለሂደት ማስፈጸሚያ በሚል 20 ሺህ ዩሮ እንድትከፍል ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።

በወቅቱ እየሆነ የነበረው ነገር ከአቅሟ በላይ የሆነ ይመስል ነበር።

”እሷ የሞተች እለት የእኔ ህይወት የፍጻሜ ቀን ነበር”

መስከረም ላይ የቲዚአና እናት በሥራ ገበታቸው ላይ ሳሉ የሰልክ ጥሪ ደረሳቸው።

”የደወለችው የወንድሜ ሚስት ነበረች። በተረጋጋ ድምጽ ወደቤት እንድመጣ ጠየቀችኝ። ወደ መኖሪያ ቤቴ ስቃረብ የፖሊስ መኪኖች እና አምቡላንስ ስመለከት ወዲያው መጥፎ ነገር እንደከሰተ ተረዳሁ” ይላሉ የልጃቸውን መሞት የተረዱበትን ቅጽበት ሲያስረዱ።

”ጎረቤቶቼ ከመኪናው ውስጥ እንዳልወጣ አደረጉኝ። ትንፋሽ አጠረኝ። እራሴን ልስት ተቃረብኩ። ወደ ቤት ውስት ዘልቄ እንዳልገባ ስለከለከሉኝ ለመጨረሻ ጊዜ እንኳ ሳላያት ቀረሁ።”

የተዚአና ጓደኛ ቴሬሳ ”እሷ የሞተች እለት የእኔ ህይወት የፍጻሜ ቀን ነበር” ትላለች ።

ጣሊያናውያን በቲዚአና ሞት እጅጉን ተደናግጠው ነበር። የቲዚያና ቀብር በበርካታ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ተሰጥቶ ነበር።Image copyrightALAMY አጭር የምስል መግለጫጣሊያናውያን በቲዚአና ሞት እጅጉን ተደናግጠው ነበር። የቲዚያና ቀብር በበርካታ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ተሰጥቶ ነበር።

”ሆነ ተብሎ ይህችን ምስኪን ልጅ ለማዋረድ የተቀነባበረ የወንጀል ተግባር ነው”

ቲዚአና እነዚያን የወሲብ ቪዲዮዎች ሰዎች አንዲረሷቸው ስትል ራሷን ብታጠፋም፣ ይልቁንም በርካቶች ቪድዮዎቹን እንዲመለከቷቸው ምክንያት ሆነ።

እናቷ ሳይቀሩ ቪዲዮዎቹን ለመመልከት ተገደዱ።

”ቪዲዮዎቹን መመልከት ምን አይነት ስሜት ሊፈጥር እንደሚችል መገመት ከባድ አይሆንም። እውነታውን ማወቅ ስለፈለኩ ቪዲዮዎቹን በዝርዝር ተመለከትኳቸው።” በማለት ቴሬሳ ትናገራለች።

እናቷ እንደሚሉት ቲዚአና ቪዲዮዎቹን የተቀረጸችው በአደንዛዥ እጽ ተጽእኖ ስር ሳለች ነበር። ቪዲዮዎቹ በስፋት የተሰራጩትም በአጋጣሚ አልነበረም።

”ሆነ ተብሎ ይህችን ምስኪን ልጅ ለማዋረድ የተቀነባበረ የወንጀል ተግባር ነው።”

እናትየው፣ የቲዚአና ፍቅረኛ የነበረው ዲ ፓሎ ምን እንደተፈጠረ በዝርዝር እንዲያስረዳቸው ይፈልጋሉ።

ቲዚአና እና ወላጅ እናቷ ቴሬሳ
አጭር የምስል መግለጫቲዚአና እና ወላጅ እናቷ ቴሬሳ

ቪዲዮዎቹን ማን አሰራጫቸው?

ቲዚአና ከሞተች ከሁለት ወራት በኋላ መርማሪዎች የቀድሞ ፍቅረኛዋን ለአስር ሰዓታት ምርመራ አድርገውበት ነበር። ለሞቷ ተጠያቂ ሰው ካለ በሚል ተጨማሪ ምርመራም አድረገዋል።

ቲዚአና ካንቶን ራሷን ካጠፋች በኋላ በጣሊያን የወሲብ ግንኙነት ስለሚያሳዩ ቪድዮዎች ያለው አመለካከት ተቀይሯል። በግዴለሽነት ይዘግቡ የነበሩ ጋዜጠኞች ሳይቀሩ ጥንቃቄ ማድረግ ጀምረዋል።

የቲዚአና ቪዲዮዎች አሁንም ከኢንተርኔት ላይ አልወረዱም። የቲዚአና እናት ጣሊያን እና የአውሮፓ ህብረት ግላዊ የሆኑ ምስሎች ላይ ቁጥጥር እንዲያደርጉ ግፊት አደርጋለሁ ብለዋል።

Read the original story on BBC Amharic

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0