“Our true nationality is mankind.”H.G.

ወደ ዜግነት ፖለቲካ መሸጋገሪያው ድልድይ፣ ሀቀኛ የማንነት ፖለቲካን ማራመድ ነው!!

እንደ  መግቢያ
ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ኦዴፓ፤ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤ የፌዴራሊዝም ጉዳይ ለድርድር የማይቀርብ ነው ብሏል። በዚህ አቋም የማይስማማ የህብረተሰብ ክፍል ወይም የፖለቲካ ቡድን ይኖራል፤ ድሮም ነበር፤ ወደፊትም ይኖራል፡፡ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ለየት ያሉብኝን ሁለት ነገሮች ልጥቀስ።
አንደኛ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በአራቱም የአገሪቱ ጫፎች ከመቼውም ጊዜ በላይ በነገሰበት በዚህ ወቅት፣ በማንነት ላይ ያተኮረ ፖለቲካን እርግፍ አድርገን እንተወው ማለት አንድም ከእውነት ሌላም ከምክንያት መጣላት ነው። ሁለተኛ፤ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይን ከሀዲ አድርጎ መቁጠር ኦዴፓን የሚመሩት አሳቸው መሆናቸውን መዘንጋት ነው፡፡ ፓርቲው ደግሞ ስሙን ከኦህዴድ ወደ ኦዴፓ ሲለውጥ፤ ፌዴራሊዝሙን ለመቀየር ሳይሆን ለፌዴራሊዝሙ መርሆች በቁርጠኝነት ለመቆም  ቃል ገብቶ ነው። ይህ ምን ማለት ነው? ይህ ማለት በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ በነጻነት የመኖርና የመስራት ህገ መንግስታዊ መብታቸውን አክብሮ ማስከበር ነው። ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ባደረጓቸው ሁሉም ንግግሮቻቸው በይፋ የገለጹት ይህን ሆኖ ሳለ፣ዛሬ  ወቀሳ በዘመቻ መጀመሩ፣ ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ እንደሆነ ግራ አጋቢ ነው።
የዚህ ጽሑፍ አላማ አሁን ካለው ተጨባጭ አገራዊ እውነታዎች አንጻር በቋንቋና (ወይም) ማንነት ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት አማራጭ የሌለው መሆኑን ጽንሰ ሀሳባዊ አስረጅ ማቅረብ ነው።
***
ብሔር ምንድነው? ብሔርተኛስ ማነው?
በዘልማድ አንድን ግለሰብ ወይም ቡድን እየጠቀስን፣ እገሌ እኮ ብሔርተኝነት ያጠቃዋል፣ ለሀገር ስጋት ነው ወዘተ…. እያልን መፈረጅ፣ በተደጋጋሚ ከምታዘባቸው የማህበራዊ ሚዲያ ልውውጦች አንዱ ነው። ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን በብሔርተኝነት ስንፈርጅ፣ እውን ብሔርተኛ የሚለውን ቃል መዝገበ ቃላታዊ እና (ወይም) ጽንሰ ሐሳባዊ ትርጉም ተረድተነዋል? ግለሰቦቹን የምንኮንንበት አግባብ ምንድነው? በምክንያት ወይስ የብየናችን መሠረት ግለሰባዊ ጥላቻ (personal animosity)፣ የእውቀት ማነስ (illiteracy)፣ የስሚ ስሚ (heresay)፣ ወይንስ …?
በአማርኛ የፖለቲካ መዝገበ ቃላት ውስጥ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከበዘበዝናቸው ቃላት (abused) መካከል አንዱ ብሔርተኝነት የሚለው ነው። ብሔርተኛ የሚለው ቃል ሁለት መልክ አለው፤ አንደኛው የትርጉም ሲሆን ሌላው የይዘት ነው። ከትርጉም አንጻር አሉታዊ ትርጉም የመስጠት፣ ከይዘት አንጻር ደግሞ የቃሉን መግለጫ የምንረዳበት አጥብበን እና(ወይም) አድሏዊ በሆነ መንገድ የመረዳት ሁኔታ ይታያል፡፡
በመሠረቱ ማህበረሰባዊ የሆነ ጽንሰ ሐሳብን መረዳት ያለብንመ ከወል ወይም ከቡድን አንጻር እንጂ ከግለሰባዊነት አይደለም። እናም የአንድ ማህበረሰብ ስሪቶች (social fabrics) መገለጫዎች፣ የጋራ ወይም ቡድናዊ ሊሆኑ ይችላሉ። ተፈጥሯዊ የጋራ (ቡድናዊ) መገለጫ ከሆኑ የማህበረሰብ ስሪቶች መካከል ጾታ፣ ዘር፣ ጎሳ፣ ሀይማኖትና ብሔር ጥቂቶቹ ናቸው። እያንዳንዱ የማህበረሰብ አባል ማንነት የእነዚህ ሁሉ ድምር ነው።
ብሔር ሲባል….
የተለያዩ ማህበረሰቦች እንደየ እድገት ደረጃቸው ብሔረሰብ ወይም ብሔር ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ። በብሔረሰብ ደረጃ የሚፈረጁ ማህበረሰቦች የጋራ ጉዳያቸው በአመዛኙ መንፈሳዊ የሆነ ፣ ማለትም የጋራ ቋንቋ ያላቸው፤ በታሪክ፣ በባህልና ትውፊት የተዛመዱ ናቸው። እነዚህ በብሔረሰብ ደረጃ ያሉ ማህበረሰቦች እየበረከቱ፣ እናም የማህበረ ኢኮኖሚያቸው ውስብስቦሽ (sophesticated socio-economic setup) ሲጨምር፣ ትስስራቸውና የጋራ ጥቅማቸው መንፈሳዊ እሴቶች ከመጋራት በዘለለ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞች ይኖራቸዋል። በመሆኑም ብሔር የምንለው  የጋራ ማንነትና የፖለቲካ ኢኮኖሚ ትስስር(ዝምድና) ያላቸው የተለያዩ ማህበረሰቦች ድምር ነው። የጋራ መንፈሳዊ እሴቶቻቸው የብሔሩ ማንነት የምንለው ሲሆን የጋራ ቁሳዊ ጥቅማቸው ደግሞ አንድ የፖለቲካና  ኢኮኖሚ ማህበረሰብ መሆናቸው ነው።
ብሔርተኛ  ሲባል…
ከላይ እንደተመለከተው ብሔር አንዱ የማህበረሰብ (ህዝብ) ክፍፍል መገለጫ ሲሆን ብሔርተኝነት ማለት የጋራ መንፈሳዊ–የማንነት  ሆነ ቁሳዊ ጥቅሞች- ያላቸው ማህበረሰቦች፣ የጋራ መለያቸው ወይም ጥቅማቸው ሲነካባቸው እንደ ማህበረሰብ የሚሰጡት ምላሽ ብሔርተኝነት እንለዋለን። የተለያዩ ፍላጎቶች ያሏቸው ማህበረሰቦች ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው፣ በአንድ በመቆም የጋራ መንፈሳዊ (ማንነታዊ) ሆነ ቁሳዊ (ፖለቲካ-ኢኮኖሚ) ድንበራቸውን ለመከላከል ለሚያደርጓቸው መተባበር የሚገቡት ዉል ብሔርተኝነት ይባላል።
በመሆኑም የብሔርተኝነት መገለጫዎች፣ ማህበረሰቦቹ የሚገቡት የተጻፈም ሆነ ያልተጻፈ  ስነ ባህሪያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና (ወይም) ኢኮኖሚያዊ ዉል ነው። ዉሉ የጋራ ጥቅም ስጋቶቻችን አልጠፉም፣ በመሆኑም ምላሻችን መቀጠል አለበት ብለው የጋራ መግባባት እስከያዙ ጊዜ ድረስ ይጸናል።
ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ከጋራ ማንነት አልፎ የጋራ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ህልዉ ያላቸው ማህበረሰብ ስብስቦች አሉ የሚል እምነት የለኝም። ስለሆነም ጭቆና አለ ካልን በማንነት የመጨቆንና ያለመጨቆን ጉዳይ ነው ያለው። የጸረ ጭቆና ትግሉም ማንነትን መሠረቱ ያደረገ ትግል ነው። በመሆኑም ከዚህ በኋላ ባለው የመጣጥፉ ክፍል፣ ብሔር ተብሎ የተጠቀሰው ሁሉ ከብሔር ስሪቶች አንዱ ከሆነው ማንነት አንጻር ነው።
***
የብሔር ፖለቲካ ‘የቢቸግር’ ፖለቲካ ነው!
የማህበረሰብ ክፍሎች የጋራ በሚያደርጋቸው ነገር፣ ማለትም በዘር፣ በብሔራቸው፣ በሀይማኖታቸው፣ በጾታቸው ወይም በሞያቸው ከተጠቁ፣ ልዩነቶቻቸውን ትተው የተጠቁበትን ነገር ይዘው፣ ራሳቸውን ከጥቃት ለመመከት ምላሽ ይሰጣሉ። ምላሻቸው በተለያዩ መደበኛ ወይም ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ሊሆን ይችላል።
ታሪክ ከሚያነሳቸው ታላላቅ እውነቶች፣ በቡድናዊ ጭቆናዎች ገፊ ምክንያት ጨቋኞችን ለመታገል የተደረጉ የጸረ ጭቆና ትግሎች፣ ትልቁን ስፍራ ይይዛሉ። ለአብነትም፦ በዘር መሠረታቸው የተጨቆኑ፣ የተሰባሰቡበት በአሜሪካ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ትግል፣ በኢኮኖሚ ደረጃቸው የተበዘበዙ፣ ብዝበዛውን ለመታገል የተሰባሰቡበት የወዛደሮች ትግል፣ ወይም የሶሻሊስት ንቅናቄ፤ ሀይማኖታቸውን መሠረት አድርጎ የተቃጣባቸውን ጥቃት ለመመከት የተቋቋሙ የሀይማኖት ንቅናቄዎች፤ በጾታ ክፍፍል በወንዶች ተጨቁነናል ያሉ ሴቶች የጾታ ጭቆናን ለመታገል በሚል የመሠረቱት የእንስታይ ንቅናቄ (feminist movement)፤ በብሔር ማንነታቸው የተበደሉ በማንነት ወይም በብሔር ፖለቲካ አደረጃጀት መሰባሰብ ወዘተ መጥቀስ ይቻላል።
***
የማንነት ፖለቲካ (Identity Politics) መከተል ወደ ዜግነት ፖለቲካ የሚያሸጋግረን ድልድይ ነው!
የትኛውም የጸረ ጭቆና ትግል አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች የህልውና ጉዳይ ነው፣ ምክንያቱም ጭቆና ሰዎችን ወደ አክራሪነት ይመራልና። የአክራሪነት መገለጫዎች የሆኑት ጥላቻ፣ ኢ-ምክንያታዊነት፣ ፍርሃት፣ ጭካኔ የጭቆና ልጆች ናቸው። የጭቆና የበኩር ልጅ ጥላቻ ነው፤ ቀጥሎ ኢ-ምክንያታዊነት ይወለዳል፤ ስሜታዊነትና ፍርሃት ደግሞ ይከተላሉ። የጭቆና የመጨረሻ ልጁ ጭካኔ ይባላል።  ከሁሉም የጥላቻ ልጆች ጭካኔ የተባለው ልጅ እጅግ አደገኛ ነው። ጭካኔ የሰብአዊነት እና (ወይም) የማህበረሰብ መሠረቶች የሆኑትን እምነት፣ ሞራልና ግብረገብን በመሸርሸር፣ እንደ ግለሰብ ወይም እንደ ማህበረሰብ የመቆም ህልውን ይነፍጋል።
የአክራሪነት መሠረቱ ጭቆና በመሆኑ የየትኛውም አይነት አክራሪነት፣ ማለትም ፦ የጾታ፣ የሀይማኖት፣ የብሔር፣ የኢኮኖሚ፣ ወዘተ ፍትህንና እኩልነትን በማስፈን፣ ጭቆናን በመታገል ይፈታል።  ስለዚህ አክራሪ ብሔርተኝነትን ለመዋጋት ብሔርና ማንነትን መሠረት ያደረገ አድልኦ እንዳይኖር ወይም ጭቆናን በመታገል ይፈታል።
በብሔር መደራጀት ብሔራዊ ጭቆናን ለመዋጋት አንዱ መንገድ ቢሆንም በራሱ ግን ግብ አይደለም፤  ዓላማውም ብሔራዊ ጨቋኞችን መበቀል፣ ማሳደድ ወይም መጨቆን አይደለም፤ ብሔራዊ ማንነትን ከማስከበርም አልፎ ለሌሎች ብሔራዊ ጭቆና ስር ላሉ (ለሚገጥማቸው) ማታገያ ሐሳብ ማዋጣት ነው። በመሆኑም በብሔር መደራጀቱ ግብ የሚሆነው ትግሉ በሀሳብ የተመራ ሲሆን ነው፤ ሀሳቡ አድጎና ዳብሮ ቢያንስ በየትኛውም ጊዜ እና በየትኛውም ቦታ የብሔር ጭቆናን ለመዋጋት የሚችል ኃልዮት (theory) ለመገንባት የራሱ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሉ ነው።
ልክ የኢኮኖሚ ጭቆና የደረሰባቸውን የአውሮፓ ወዛደሮችን ለማታገል እነ ካርል ማርክስ የሳይንሳዊ ህብረተሰብአዊነት (scientific socialism) ኃልዮት ነድፈው፣ በአለም ላይ ያሉ ወዛደሮችን ለማታገል እንደ ርዕዮት መሣሪያ እንደዋለው ማለት ነው።
የብሔር መደራጀት ዓላማ፣ ማንነታዊ ጭቆናን መታገል ቢሆንም፣ ግቡ ግን ከብሔሩ የተሻገረ መሆን አለበት ነው ነገሩ፤ በሌላ አማርኛ ሀቀኛ የማንነት ፖለቲካ መከተል ወደ ዜግነት ፖለቲካ ለመሸጋገር አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው።
ከአዘጋጁ፡- ሀብታሙ ግርማ፤ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው

Related stories   ‹‹የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠነክራል››

Written by  ሀብታሙ ግርማ (በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል )

ruhe215@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

Addisadmass news

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0