“Our true nationality is mankind.”H.G.

ለማ መገርሳ ጨፌ ስብሰባ ላይ ተናገረ የተባለው ሊያስበረግገን አይገባም!!

ዛሬም ግልጽ ውይይት የሚሹ ጉዳዮች አሉን በሚል አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ሳተናው ድረገጽ ላይ  ያቀረበውን ጽሑፍ አነበብኩት፣ እንደወትሮውም በርካታ ቁም ነገሮችን አንስቷል። መወያየት ነገሮችን በተሻለ ለመረዳት ይጠቅማል በሚልም  ባነሳቸው ነጥቦች ላይ የኔን ምልከታ ለማጋራት በሚል ይሄን አጭር አስተያየት አቀርባለሁ።

አቶ ያሬድ ‘ህዝብ ለዚህ ሃይል ከወራት በፊት ይሰጥ የነበረው ድጋፍ እና የነበረው አመኔታ እጅግ እያቆለቆለ መምጣቱን በግልጽ ማየት ይቻላል ‘ የሚል እምነት እንዳለውና ለዚህም  ምክንያቱ ‘የለውጥ ሃይሉ የክሽፈት ምልክቶች’ እንደሆኑ በማመን ፣ እነዚህን ምልክቶች ያላቸውን ደግሞ ዘርዘር አድረጎ አቅርቧቸዋል።

አቶ ያሬድ እነዚህን ምክንያት ያላቸውንና ዘርዘር አድርጎ ያቀረባቸውን በገሃድም የሚታዩ ድክመቶችና አጠቃላይ በሀገሪቱ የሚታዩ ያለመረጋጋት ምልክቶች ለለውጡ ሃይልም ሆነ ፣ በኔ እምነት እንደውም በዋናነት ለሀገራችን ፈታኝ ችግሮች መሆናቸውን የምጋራ ቢሆንም፣ የለውጥ ሃይሉን ቁርጠኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚከትና ድጋፋችንን እንድንነሳው የሚያደርግ ነው የሚል እምነት የለኝም ። እርግጥ አቶ ያሬድም፣ ከነቀሳቸው ችግሮችም ጋር ቢሆን አሁንም የለውጡን ሃይል እንድሚደግፍ ገልጿል።

ይሄም ሆኖ ግን መንግስት አስፈላጊውን ትኩረት ሰጥቶ ችግሮቹን ከስር ከስር ለመቅረፍ መንቀሳቀስ እንዳለበት አጠያያቂ ባለመሆኑ የሁላችንም ግፊት አስፈላጊ ነው።

የለውጥ ሃይሉን አስመልክቶ ከጠቅላይ ምኒስትር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት ጋር ተያይዞ በመላ ሀገሪቱ ሊባል በሚችል መልኩ የታየው ታላቅ ደስታና ፈንጠዚያ (euphoria and exuberance) ለለውጡ ሃይል ብቻ የተቸረ አድርጎ መመልከት፣ ምናልባት አሁን የተቀዛቀዘ የሚመስለውን ፈንጠዚያ ስናይ፣ የለውጥ ሃይሉ፣ ህዝብ ሰጥቶት የነበረውን ድጋፍ እያጣና ቅቡልነቱም የቀነሰ ሊመስለን ይችላል።

በርግጥ የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል በኢህአዴግ ውስጥ የተደረገ ለውጥና መሸጋሸግ መካሄዱን  ዘንግቶ ያልሆነ ህልም ውስጥ ገብቶ ስለነበር፣ ቀን እያለፈ ሲሄድና፣ ባኖ ከነባራዊ ሁኔታ ጋር ሲላተም፣ ጉድ ሆንን የሚል ስሜት እንዳደረበት ግልጽ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ህብረተሰባችን ሀይማኖተኛና ባህላዊ አስተሳሰቦችም በስፋት የሚያስተናግድ በመሆኑና፣ አብይም ራሱ የፈጠረው ትርክት(የ እናቱ ራዕይና የግልም እምነቱ አንድ ቀን መሪ እንደሚሆን…  ወዘተ) ተዳምረው ኢትዮጵያን ከገባችበት አዘቅት ለማዳን የሰማያዊ ሃይል ያመጣው ነው የሚለው እሳቤ፣ በተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ መኖሩ ግን አሁንም ያለ ነው።

በኔ እይታ ከለውጥ ሃይሉ ወደፊት መምጣት ጋር  በህዝብ መሃል የታየው ታላቅ ደስታና ፈንጠዚያ፣ የህወሃት /ኢህአዴግ የረጅም ጊዜ የግፍ አገዛዝ አንገፍግፎት በበርካታ የሀገሪቱ ክፍል ይካሄድ የነበረው ያልተቀናጀና መሪ አልባ ይመስል የነበረው ህዝባዊ ትግልና፣ በአንጻሩ ደግሞ  ርህራሄ የሌለው የመንግስት ጭፍጨፋ፣ ምናልባት የርስ በርስ ጦርነት ፈጥሮ ሀገር ሊያፈርስ ይችላል የሚል ስር የሰደደ ፍርሃት ስለነበረ፣ የለውጥ ሃይሉ ወደፊት መምጣትና ፣ አብይም ፓርላማ ቀርቦ ስልጣኑን ሲረከብ ያደረገው ንግግር ፍርሃቱን ገፎ ጊዜያዊ ቢሆንም፣ ታላቅ እፎይታን ስላስገኘለት ነው የሚል እምነት አለኝ ።

Related stories   “ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በአንድነት በመከባበር፤ በመተሳሰብ እና በመረዳዳት ሊያከብር ይገባል”

ባንዳንድ ክልሎች የሚታየው ግጭት፣ የሰው መፈናቀል፣ ይባስ ብሎ የመንደር ጎረምሳ ተሰብስቦ የሚፈጥረው ሁከትና ስርዓተ አልበኝነት በርግጥም በሽግግር ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮች ናቸው። ሆኖም በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ይሄን የጥፋት አካሄድ የሚቆሰቁሱና የሚያራግቡት ፣ በኔ ግምት በዋነኛነት በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ ፣ መጣልን ሳይሆን መጣብን ብለው በሚያስቡ ከገዥው ፓርቲ ተገፍተው የወጡ ወይንም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር አይቀርልንም ብለው በሚያስቡ ግለሰቦችና ስብስቦች ነው።

የጸጥታ ሃይሉ ባለፉት 27 ዓመታት ያደርግ አንደነበረው ጅምላ ግድያና ጭፍጨፋ ማድረግ እንደማይችል፣ ከለውጥ ሃይሉ የተሰጠው መመሪያ በመኖሩ ፣ በአንድ በኩል በተለወጠው ሁኔታ ውስጥ ጸጥታ ማስከበሩን በምን አይነት ማካሄድ እንዳለበት የሚያሳየው ግራ መጋባትና ፣ በሌላ ደግሞ በዚህ ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም፣ በውስጡም ያሉ የለውጡ ተቃዋሚዎችና  ከውጭ ያሉ ሃይሎች የሚካሄድ በመሆኑ ሁኔታዎች ረግበው ከሞላ ጎደል ሰላም እስኪሰፍን ትንሽ ይዘገያል የሚል አምነት ቢኖረኝም፣ ሀገር የማፍረስ አቅም ግን አለው ብዬ አላምንም።

ከዚህ ይልቅ ትልቅ ችግር ብዬ የምገምተው፣ በኢህአዴግ ውስጥ፣ ድንገት ሳያስበውና ባልጠበቀው ሁኔታ የበላይነቱን ተነጥቆ መቀሌ የመሸገው የህወሃት አመራር ፣እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አስተሳሰብ ውስጥ ከተዘፈቀና አንዳንዴም እንደሚፎክረው ከአጎራባች ክልሎች ጋር ጦርነት ከለኮሰ ነው።

ይሄም ቢሆን ግን አንዳንድ የአመራር አባላት እንደሚያሰሙት ቀረርቶ ሳይሆን፣ በህወሃት በራሱ ውስጥ የሃሳብ አንድነት እንደሌለና፣ ከዚህ ቀደምም እንዳልኩት ከነአብይ ጋር የሃሳብ አንድነት ያላቸው ሰዎች መኖራቸው እውነት በመሆኑ አክራሪው ወገን ላይ ፍርሃትን አጭሯል ።

ለዚህ እንደ ማሳያ አቦይ ስብሃት ከጥቂት ቀናት በፊት በሰጡት ‘ጋዜጣዊ መግለጫ’ (ለብዙ ጊዜ ተራ የህወሃት አባል ነኝ  ይሉ ስለነበር በምን ሁኔታና የስልጣን እርከን ሆነው ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት በራሱ ግራ የሚያጋባ ቢሆንም) በውስጣችን፣ ድርጅታችንን አፍርሶ ለነአብይ እጅ ሊሰጥ የሚሰራ ሶስት የባንዳ ቡድን ስላለ አጥብቀን መታገል አለብን ማለታቸው ፍርሃቴን ትንሽም ቢሆን ቀንሶልኛል።

Related stories   “…ለዛሬ ብለን ነገን ከምናበላሽ፣ ለነገ ስንል ዛሬን እንሠዋ” አብይ አህመድ

ሌላው አቶ ያሬድን ያሳዘነውና ቅር ያሰኘው በቅርቡ፣ ተቀንጥቦ ተተርጉሞ የቀረበ የአቶ ለማ አስተያየት ነው። የተተረጎመው የአቶ ለማ ንግግር በምን አውድ ውስጥ እንደተነገረ ማወቅና ሙሉውን ንግግር ሰምቶ የመጨረሻ ድምዳሜ ላይ መድረስ ተገቢ ቢሆንም፣ ከተተረጎመውም ተነስቶ ቢሆንም ግን አስተያየት መስጠት  ይቻላል።

በበኩሌ  ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ወገኖችን ፣ ለመፈናቀላቸው ምክንያት የሆነውን ችግር ቀርፎ፣ በጉልበት በመፈናቀላቸውም ምክንያት የደረሰባቸውን የስነ ልቦና ቀውስ አስታሞና አረጋግቶ፣ እንዲያገግሙ ከተደረገ በዃላ ፣  ሰዎቹን ወደቀያቸው መመለሱ ተቀዳሚ ተግባር መሆን ነበረበት የሚል እምነት አለኝ።

አቶ ለማና ድርጅታቸው አጋጣሚውን ተጠቅመው ሰዎቹን ሳያማክሩና ይሁንታቸውን ሳያገኙ ፣ ከተሜ ብናደርጋቸውና፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የክልሉ ከተሞች ብናሰፍራቸው፣ ይሄኛው ትውልድ የመከራ ገፈቱን ቀምሶ ልጆቹ ወደፊት ያልፍላቸዋል የሚል አካሄድ ተከትሎ ከሆነ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ትልቅ ስህተት ይመስለኛል።

500,000 ሰውም በነዚህ ከተሞች ለማስፈር ምን ያህል ዝግጅት ተደርጓል፣ ባብዛኛው ከግብርና የመጣው ህዝብስ በከተማዎቹ ውስጥ ምን አይነት የስራ ጓእድል ተዘጋጅቶለታል ፣ መጠለያውስ በቂና ለዘለቄታው የሚሆን ነው ወይ ፣ የልጆቹ ትምህርት ቤትስ ፣ የሰፈሩባቸው ከተሞችስ የመሸከም አቅም አላቸው ወይ…   ወዘተ በርካታ ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ናቸው።

አዲስ አበባን አስመልክቶ ግን 6,000ም ሆነ 60,000 ወይንም 600,000 ሰው ቢጨመር፣ ድህነቱን ቢያባብሰው እንጂ የከተማውን የህዝብ ስብጥር ለውጦ የፖለቲካ ትርፍ  ለማምጣት ይቻላል የሚል የዋህነት አቶ ለማ አለው ብዬ ለማሰብ ትንሽ ይቸግረኛል።

‘የዴሞግራፊ ለውጥ’ የሚለው የንግግሩም ይዘት፣ ምናልባትም ገጠሬውን ከተሜ  የማድረግ እሳቤው እንጂ አዲስ አበባን አስመልክቶ አይደለም  የሚል ግምት አለኝ ። ይሄም ቢሆን ግን በዘፈቀደ ወይንም በፖለቲካ መሪዎቹ ፍላጎት ብቻ የሚካሄድ ከሆነ ፣ከትርፉ ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ የሚመለከተው  አካል በቅጡ ሊያስብበት የሚገባ ነው።

በደርግ ዘመን ያለበቂ ዝግጅትና ምክክር  በረሃብ የተጎዱ ወገኖችን፣ ይበጃቸዋል ከሚል የመንግስት ውሳኔ በመነሳት ብቻ፣  በጭነት መኪናና በአውሮፕላን ጭኖ የተካሄደው መጠነ ሰፊ ሰፈራና ያደረሰውን ዘርፈ ብዙ ችግሮችና መዘዙን ማጤን ለዚህ ተግባርም አስተማሪ ሊሆነው ይገባል።

በዋነኛነት በኢህአዴግ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት የተንቀሳቀሱት ሃይሎችን  ያስተባበረው ‘የለማ ቡድን’ መሪ  ከ 25-30% የሚሆን ሥራ ፈት ያለበት ፣ በ 10ሺዎች ቤት አልባ ሆነው የጎዳና ተዳዳሪ በሆኑበት፣ በመቶ ሺዎች ላያቸው ላይ ጣራ አለ ከማለት ውጭ ቤት አላቸው ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር በማይቻልበት ከተማ ፣ቀውስ ለመፍጠር ካላሰበ በቀር በሺና መቶሺ ሰው ለማስፈር አስቧል የሚል ስጋት የለኝም።

Related stories   የኢትዮዽያ የቁርጥ ቀን ልጅ "ስለአባይ እውነቱን እንካችሁ" – መካ አደም አሊ

በመጨረሻም አቶ ያሬድ ያነሳው የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችን አስመልክቶ ያለውን ጉዳይ ነው።

ባለፉት 27 አመታት ውስጥ ኢህአዴግን በሚመለከት የተዋጣለት ሥራ ሰርቷል ሊባል የሚችለው በኢትዮጵያ ምድር ሁነኛ ተቃዋሚ እንዳይደራጅ በማድረጉ ላይ ነው ብል የተሳሳትኩኝ አይመስለኝም ።

በዚህ መንገድ የተጠቀመባቸው የተለያዩ ዘዴዎች፣ የውሸት ተቃዋሚ ከመፈብረክ ፣ ሰላይና የደህንነት አባሎቹን ሰርጎ በማስገባት ማፍረስን፣ ይሄንን ሁሉ ተቋቁሞ መሰረት መጣል የጀመሩትን ደግሞ፣ አፍ አውጥተው እንደፎከሩት እግር እስኪያወጡ ጠብቀው፣ እግራቸውን ሲቆርጡ በመክረማቸው ፣የኢህአዴግን ስርዓት ያንገዳገደው ህዝባዊ አመጽ ሲቀጣጠል አቅጣጫ የሚያሳይ ይቅርና ሱሪውን በቅጡ ታጥቆ የትግሉ አካል ለመሆን የበቃ ድርጅት አልነበረም።

እነ አብይም ቢሆን በኢህአዴግ ውስጥ የበላይነት ሲቀዳጁ፣ ከዚህ ወገን ይሄ ነው የሚባል ችግር ይገጥመናል ብለው ስላላሰቡ፣ ሀገርቤት ውስጥ ያለውን ብቻም ሳይሆን አስመራም ሆነ ሌላ ስፍራ መሽጎ የነበረውን፣ ና ብለው በር ከፍተው በስብሰባና በግብዣ ጠምደው ስለያዟቸው፣አቶ ያሬድ እንዳለው ባለፈው አስር ወር ይሄ ነው የሚል ሥራ ሲሰሩ አይታይም።

ምናልባት መረጃው የለኝ  ካልሆነ በቀር ‘የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቦ አላሰራ አለን ‘ እያሉ ሲጮሁ የነበሩ ድርጅቶች  በዚህ ባሳለፍነው አስር ወር ውስጥ ይሄ ነው የሚባል የህዝብ ጥያቄ አንስተው ሰው ሲያደራጁ ፣ የድርጅታቸው ልሳን የሆነ፣ አማራጭ ሃሳብ የሚያቀርብና በህዝብ ውስጥ ተሰሚነት ለመፍጠር የሚያገለግል ጋዜጣ ወይንም መጽሄት በማተም ሲንቀሳቀሱ አላየሁም።

አሁን ያሉት አብዛኛው የፖለቲካ ድርጅት አመራር አባላት ከድርጅት ቦርድ አባልነት አስከ  ትልልቅ ሃላፊነት ያላቸው የመንግስት ተቋማት ውስጥ ሹመት ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ውስጥ በመካተታቸው፣ በአብይ የሚመራው ኢህአዴግ ላይ የፖለቲካ ጫና አሳርፈው ይሄ ነው የሚል አበርክቶ ይኖራቸዋል የሚል እምነት የለኝም። ፖለቲካውን አያራመድን ነው የሚል መዘባበት ውስጥም ከገቡ፣ ሊሆን የሚችለው የጃንደረባ ፖለቲካ ብቻ  ነው።

By – (አበጋዝ ወንድሙ)

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0