“Our true nationality is mankind.”H.G.

ትናንት ዛሬ አደለም – ( በእውቀቱ ስዩም)

ይገርማል!! ያገራችን ገበሬ የሚያርስበት በሬና ማረሻ ጥንታዊ ሰው ከአራት ሺህ አመት በፊት ይገለገልበት የነበረውን ነው:: ይሁን እንጂ ቢቀናው ክላሺንኮቭ ይታጠቃል:: ደሞ ገበሬውን ዘመናዊ ጠመንጃ እንጂ ዘመናዊ ማረሻ ለማስታጠቅ የሚያልም አክቲቪስት አይተን አናውቅም::
ዘመናይ የብሄር አክትቪስት ጦርነት በናፈቀ ቁጥር ያባቶቹን ጀብድ ይዘክራል:: ባባቶቹና በሱ መካከል በሰፊው የሚያዛጋ የጊዜ ገደል እንደተዘረጋ አይገባውም:: የድሮ ሰዎች ከማረስ ይልቅ መዋጋት ቢወዱ አይገርምም:: ያኔ ጦርነት ወጭው ትንሽ : ትርፉ ብዙ ነበር:: ጥቂት የተደራጀ ጭፍራ ጥቂት ፈረስና ጦር ይዞ በሺ የሚቆጠር የቀንድ ከብት መማርክ ይቻል ነበር:: ዛሬ አንድ መንደር አርሶ የሚያበላ ትራክተር ባስራ አራት ሺህ ዶላር መግዛት ትችላለህ:: አንድ መንደር አፈር የሚያስበላ ታንክ ለመሸመት ከፈልግህ ግን ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር መክፈል ይጠበቅብሃል:: እና በዚህ ዘመን ተዋግቼ አተርፋለሁ ብሎ ጉራውን የሚነፋ አዲስ የተመረተ ዴዴብ መሆን አለበት!!!
ድሮ በሰላምም ሆነ በጦርነት ባጭሩ መቀጨት ያባት የናትህ እዳ ነበር:: በጦርነትም ሆነ በሰላም ጊዜ ከሞት ጋር ያለህ ርቀት ተቀራራቢ ነው:: ይህን የሚያውቁት ቀዳማዊ ሀይለስላሴ በማይጨው ዋዜማ የክተት አዋጃቸው “ቤትህ ቁጭ ብለህ በሳልና በጉንፋን ከመሞት ጠላትን መክተህ ብትሞት ክብር ነው” ብለው ዜጋውን ጀንጅነውታል:: ልክ ነው! በህዳር በሸታ ከመሞት በጦርነት መሞት ስም እና ምርኮ ሊያስገኝ ይችላል::
ዛሬ ሰላም ወጭ ቆጣቢ ነው:: ሰላም ያለው ብዙ ሀብት ብዙ እድል ብዙ ተስፋና ብዙ እድሜ ይኖረዋል:: ታድያ ለሰላም ሲባል ወደረኞቻችንን ብንለማመጣቸው ብናቆላምጣቸው ብንወያያቸው እንዴት ነውር ይሆናል? ዛሬ መደራደር መወያየት የሚያሳፍርበት : ውረድ እንውረድ የሚያስኮራበት ዘመን አይደለም::
ዛሬም እንደ ጥንቱ በርስት ወይም በማንንት ሰበብ የሚደረግ ጦርነት የሚጎዳው ዜጎች እንጂ ጌቶች አይደለም:: ከእምባቦ ከሰገሌ እና ከባድመ ክሽፈት እንዳየነው አገሬው በጦርነት ያልፋል: አገር መሪው ግን ይተርፋል:: በምባቦ ጦርነት ንጉስ ምኒልክና ንጉስ ተክለሃይማኖት ገጥመው በብዙሺህ የሚቆጠር ባላገር ያአሞራ ቀለብ ሆነ:: ሁለቱ ሃያላን ግን ታርቀው ተፋቅረው ረጅም እድሜ ኖሩ:: ሰገሌ ላይ የንጉስ ሚካየል ባላገርና የተፈሪ መኮንን ባላገር ተፈሳፈሰ:: ደሙን ለሁለቱ መሳፍንት የክብር ሲል አፈሰሰ:: ንጉስ ሚካኤልም ሆነ ተፈሪን ግን ከጦርነቱ ማጠናቀቂያ ባንድ ድንኩዋን ውስጥ ተቀምጠው ” አባቴ እንኩዋን አተረፈዎ! ልጄ እንኩዋን አተረፈህ” እየተባባሉ ተቃቀፉ:: በባድመ ጦርነት ያ ሁሉ ወጣት አላማም ሆነ ኢላማም በሌለው ጦርነት ሜዳ ላይ ቀረ:: የጦርነቱ ጠንሳሾች ለሙታን ተገቢውን መታሰቢያ ሳያደርጉ ላደረጉት ይቅርታ ሳይጠይቁ በህይወት ይርመሰመሳሉ :: ነገም ከዚህ የተለየ አይሆንም!!
እና እምቢ በል!!! አሻፍረኝ በል!! በቀረርቶ አትወሰድ! በመፈክር አትሸወድ!!

0Shares
0