“Our true nationality is mankind.”H.G.

“… አገሪቱን ከውጥረት ለማውጣት የበኩላችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ” የአማራ ክልል አዲሱ መሪ

ፖለቲካውን ከክረት በማላቀቅ ሀገሪቱን ከውጥረት በማውጣት አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት፤ ዜጎቿ በሙሉ ነፃነት የሚንቀሳቀሱባት ለማድረግ የበኩላችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን አሉ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን።

ዛሬ በክልሉ ምክር ቤት ርእሰ መስተዳደር በመሆን የተሾሙት ዶክተር አምባቸው ቃለ መሃላ ከፈፀሙ በኋላ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ንግግር የአማራ ህዝቦችን የማስተዳደር ሀላፊነት ስለ ተሰጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

አዲሱ ርዕሰ መስተዳደር በንግግራቸው በክልሉ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ቀደም ሲል የተከናወኑ ስራዎች እንዳሉ ሆኖ በቀጣይ ግን የማስተካከያ ስራ የሚፈልጉ እንደ መንገድና መብራትን የመሰሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች ክፍተቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።

በክልሉ ርብርብ የሚፈልጉ የህዝብ የመልማት ፍላጎት እንዳለም በማንሳት፥ ያሉትን አወንታዊ እና አሉታዊ ሁኔታዎችን በመገምገም ፈጣን ስምሪት እንደሚከናወን ነው የጠቆሙት።

የክልሉ መንግስት በቀጣይ ትኩረት የሚያደርግባቸውን ጉዳዮችም በዝርዝር ያስቀመጡ ሲሆን፥ ጠንካራ መንግስታዊ መዋቅር በየደረጃው መዘርጋቱን በማረጋገጥ ጠንካራ የለውጥ አመራር መገንባት አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

በመላው የክልሉ አካባቢ ሰላም እንዲሰፍን እና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ነው ያስታወቁት።

የስራ እድል ፈጠራን ማጎልበት እና የማምረቻ ኢንዱስትሪን ማስፋፋት እንዲሁም ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርም ይሰራል ብለዋል።

በዚህም የክልሉን ነዋሪዎች ህይወት በቀጣይነት እንዲሻሻል በህዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎና ድጋፍ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

Related stories   አውሮፓ ህብረት እየተሽኮረመመ ታዛቢ ሊልክ ነው

በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች  በፍጥነት እና በብቃት እንዲጠናቀቁም ይሰራል ነው ያሉት።

በማህበራዊ ዘርፍ የትምህርት እና ጤና አገልግሎትን በማሻሻሉም በተለይም ደረጃቸውን ያልጠበቁ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን እንዲጠብቁ ይደረጋል ብለዋል።

በክልሉ የሚገኙ ህዝቦች ወንድማማችነት መንፈስ እንዲያጎለብቱ የሚያደርግ ስራም እንደሚከናወን በርእሰ መስተዳድሩ ንግግር ተጠቁሟል።

ከትግራይ ህዝብ  ጋር የቆየውን ዘርፈ ብዙ አንድነትና ወንድማማችነት ለማደስ ለጋራ ሰላምና ብልፅግና ተግባብቶ እና ተዋዶ መስራትም የአማራ ህዝብ ፍላጎት ነው ብለዋል።

ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆንም ተደጋግፎ በመስራት መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች  ሰላምን የሚያጣጥሙበት፣ ነፃነትን፣ ፍትህን፣ እኩልነትን እና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚቋደሱባት፤ ዜጎች ከሰቀቀን ተላቀው በነፃነት የሚዘዋወሩበት የሚያደርግ ሀገራዊ የፖለቲካ ስርዓት ለመመስረትም የክልሉ ህዝብ እና መንግስት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከምንም በላይ የምትተጠቀመው ከሰላም ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፥ አሁን ላይ የሚታዩትን ፀብ ጫሪ እና የጥላቻ ድርጊቶች ሀገሪቱንም ሆነ ዓለም የደረሰበትን የማይመጥኑ ኋላቀር እና ጎጂ መሆናቸውን አስረድተዋል።

እነዚህ የሀገሪቱን ህዝቦች ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ በመሆናቸው ተማምነንና ተግባብተን ውድቅ ልናደርጋቸው ይገባል ብለዋል።

በምትካቸውም የሰለጠኑ የቅራኔ አፈታቶችን ስራ ላይ በማዋል ፖለቲካውን ከክረት በማላቀቅ ሀገሪቱን ከውጥረት በማውጣት አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት፤ ዜጎቿ በሙሉ ነፃነት የሚንቀሳቀሱባት ሀገር ለማድረግ የበኩላችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉም በንግግራቸው አረጋግጠዋል።

Related stories   እስራኤል አልጃዚራ ቴሊቪዥን፣ አሶሲየትድ ፕሬስና ሌሎች ሚዲያዎች የሚጠቀሙበትን ህንጻ አወደመች

በተያያዘም የክልሉ የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባደረጉት ንግግር ባለፉት አመታት የክልሉን ህዝብ የልማት፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን አስታውሰዋል።

በዚህም በክልሉ የከተሞች እድገት፣ የመሰረተ ልማት፣ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ እመርታ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈም በመስኖ ልማት ዘርፍ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው፥ በክልሉ የማህበራዊ ልማት ዘርፍን ለማጠናከር የተሰራው ስራ ውጤታማ እንደነበር ገልጸዋል።

ባለፉት 5 አመታት በገጠሩ 200 ያክል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውንና የተማሪዎችን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚያግዙ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

በጤናው ዘርፍም መከላከልን መሰረት ያደረገ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል ያሉት አቶ ገዱ፥ በክልሉ የእናቶችንና ህጻናትን ሞት ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።

የሆስፒታል ተደራሽነትን ለማሳደግ በተሰራው ስራም በክልሉ የሆስፒታሎችን ቁጥር ከ20 ወደ 80 ማድረስ ተችሏልም ነው ያሉት፤ አሁንም በዘርፉ ጥራትን ማረጋገጥ ዋናው ስራ መሆኑን በመጥቀስ።

ድህነት፣ ስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት አሁንም የክልሉ አንገብጋቢ ጉዳዮች መሆናቸውንም በንግግራቸው አንስተዋል።

በሃገሪቱ ባለፉት አመታት ኪራይ ሰብሳቢነት ተንሰራፍቶ መቆየቱን ያነሱት አቶ ገዱ፥ ችግሩ የህዝቦችን አብሮ የመኖርና የጋራ እሴት በማጥፋት ሃገሪቱን ለከፋ ችግር ዳርጓት መቆየቱን አውስተዋል።

Related stories   ወደ ድርደር ? ከታንክ ወደ አህያ የወረደው ትህንግ በማን ሊወከል?

ይህም ምዝበራና አድሏዊ አሰራርን በማንሰራፋት ህዝቦች በጠላትነት እንዲተያዩና አብሮነታቸውን መሸርሸሩን ጠቅሰው፥ ይህን ለመቀልበስ በተደረገ ጥረት በሃገሪቱ ለውጥ መምጣቱን ጠቁመዋል።

አሁን ላይም ሃገራዊ ለውጡን ለመቀልበስና የቀድሞውን መረብ ለመመለስ በሚደረግ ጥረት የዜጎች መፈናቀልና ግጭት መቀስቀሱን ጠቅሰዋል።

የአማራ ክልል ህዝብም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን አድሏዊ አሰራርን እና ፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሄድን ለመቀልበስ ባደረገው ትግል ድል አስመዝግቧልም ነው ያሉት አቶ ገዱ።

በቀጣይም ህዝቡ አድሏዊ አሰራር እንዲሰራፋ ያደረገው ቡድን ለመመለስ እያደረገ ያለውን ጥረት እና አዲስ አድሏዊ አሰራር እንዳይሰፍን እንዲሁም ተጠያቂነት ያለው አሰራር እንዲሰፍን ቀጣይ ትግል ማድረግ እንደሚገባውም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከፖለቲካ ስራ ባሻገርም የህዝብ ለህዝብ ወንድማማችነትን ማጠናከር ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ህዝብም ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የሰፈነባት፣ የዜጎች መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚረጋገጥባት እና ብልፅግና የተረጋገጠባት እንድትሆን ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ለዚህም ውስጣዊ አንድነቱን ማጠናከርና ከአጎራባችና ከመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ሰላማዊ ወንድማማችነት በመመስረትና የትብብር ግንኙነትን በማሳደግ ለጋራ ተጠቃሚነት መስራት እንደሚኖርበት ነው ያነሱት።

ፋና – ምንጭ

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0