“Our true nationality is mankind.”H.G.

“ሕልውናችን የሚረጋገጠው በአሸናፊነት ብቻ ነው” አዴፓ- የኮምንኬሽኑ ም/ሃላፊ አቶ መላኩ አላምረው

ይህ ጽሁፍ ይነበብ!!

የጽሁፉ ባለቤት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲው (አዴፓ) የመንግስት ኮምንኬሽኑ ምክትል ሃላፊ አቶ መላኩ አላምረው ነው።

አማራ እንደ ሕዝብ በኢትዮጵያ ምድር ወዳጅ እንዳይኖረው ሆኖ እንዲቀጥል ብዙ ተሰርቶበታል። ወዳጅ እንዳይኖረው ብቻ ሳይሆን ራሱን እንዳያደራጅና ሁለንተናዊ መብቱን እንዳያስከብር ብዙ ሴራ ተጎንጉኖበታል። አቅመ ቢስ፣ አንገት ደፊና ቆዛሚ እንዲሆን ብዙ ተደክሞበታል። ሁሉም እንደ ጠላት እያየ እንዲያሳድደው የፈጠራ የጨቋኝነት ትርክት እየተፈበረከ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል በጠባብ ብሔርተኞች ተሰብኮበታል። አሁን ላይ የደረስንባት ኢትዮጵያ አማራን በሚጠሉና በሚያገሉ ጽንፈኛ ብሔርተኞች እጅ ወድቃ ግራና ቀኝ የምትጎተት ሆናለች። አማራ ጠሎች በኢትዮጵያዊነት የቆመውንና ኢትዮጵያ እንዳትወድቅ ወጥሮ ያያዛትን ምሶሶና ወጋግራ የሆነ ሕዝብ በአላዋቂነታቸውና በራስ ወዳድነታቸው መጠን ገፍተው ገፍተው በትረ ሥልጣኑን ቢይዙም ይይዙትን አሳጥቷቸው ሀገር እንዲህ እንደምናያት እየሆነች ነው። ጽንፈኛ ብሔርተኞቹ በሴራ ተቀናብሮ የተሰበከላቸውን የፈጠራና የጥላቻ ትርክት ሳያላምጡ እየዋጡ አድገው ኖሮ ሀገራዊ ኃላፊነት ሲሰጣቸው ጎጣዊ ፍላጎት ላይ ብቻ ተቸከሉ። ከራሳቸው አልፎ ሌላውን መመልከት አልችል አሉ። ጭራሽ የግፍ ሁሉ ማወራረጃ ይህን መከረኛ አማራን ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። በዚህ መሐል “ተው ስከኑ” የሚል ሀገራዊ ሽማግሌም ሆነ ፓርቲ የለም። በኢትዮጵያ ስም የተደራጁ ፓርቲዎችም ብቅ የሚሉት “ኢትዮጵያዊነትን ለአማራ ለመስበክ” ብቻ ነው። ኢትዮጵያዊ ሆኖ ሲኖር “አማራ ነህ” እየተባለ ለሚፈናቀልና ለሚሳደድ ሕዝብ መብት ሳይጮሁ አሁንም ማፍዘዣ ስብከት ይጨምሩበታል።

Related stories   የሲኤንኤን ዘጋቢ ኒማ- በተወነችው ተውኔት ውስጥ ዳግም ሞት የተፈረደባቸው ዜጎች

->

ከላይም ከታችም ከመሐልም ከዳርም የሚሰነዘሩ ቃላትም ሆነ የሚተገበሩ ተግባራት የሚያሳዩት አንድ ነገርን ነው። አሁን በተስፋ ዘመንም ሁሉም የየራሱን ጥቅም “በአማራ ጉዳት ላይ” ለማስከበር እየሮጠ መሆኑን። ለዚህም ነው “ፖለቲካችን ማሸነፍን ብቻ የሚፈቅድ ነው” የምንለው። የአማራ ፖለቲካ በጠላትነት ተፈርጆ በሁሉም እየተገፋ ያለ ሕዝብ የሚጫወተው ፖለቲካ ነው። ከማሸነፍ ውጭ ምንም ምርጫ የሌለው ፖለቲካ ነው። ማሸነፍ ደግሞ በምኞትም በስሜትም አይሆንም። በባዶ ወኔም አይመጣም። ከተሴረብን በላይ ሴራ መስራትን ይጠይቃል። ከተደገሰልን በላይ መደገስን ይሻል። ይህን ስናደርግም ሁሉንም እያወጅን አይደለም። የምንናገረው ጥቂቱንና አስፈላጊውን ብቻ ነው። ሁሉም አይነገርም። ለሁሉም ዘመቻ ጦርነት አይታወጅም። ለሁሉም ሰርግ አይዘፈንም። ለሁሉም ሞትም አይለቀስም።

->

ማንም አማራ ነኝ የሚል ይህን ለአፍታም መዘንጋት የለበትም። የአማራ ሕልውና የተመሠረተውም የሚቀጥለውም በራሱ ፖለቲካ ማሸነፍ ላይ ነው። ይህ እንዲሆን የፈለገው አማራ አይደለም። ሳይበድላቸው በደልኸን ብለው ሳይጠላቸው ጠላት አድርገው የሳሉት ሌሎች ከወንድም ሕዝብ የተወለዱ አማራ-ጠሎች ናቸው። ይህን ጠላቻቸውን አማራ ማስቀረትም ማስተውም አይችልም። እንዲወዱት መለማመጥም የለበትም። አማራ ለመወደድም ለመከበርም ጨዋና ሐቀኛ የኢትዮጵያ ጠበቃ ሆኖ ከመኖር በላይ ምን ማድረግ ነበረበት? የሀገር ፍቅርም ሆነ ትርጉም የማይገባቸው ሆን ብለው የከፉበት አካላት እስካሉ ድረስ የአማራ ምንም መሆን ጽንፈኛ ፍላጎታቸውን አያስቆመውም። ስለዚህ ለአማራ ያለው ምርጫ አንድ ብቻ ነው። ማሸነፍ ብቻ። ለአማራ ሕልውና የአማራ ፖለቲካ ያሸንፍ ዘንድ አማራጭ አይደለም። ግድ ነው። በሁለንተናዊ መልኩ ለማሸነፍ ብቻ እንዘጋጅ። አማራ ሲያሸንፍ ሁሉም ነገር በአግባብና በሕግና በሥርዓት ብቻ ይስተካከላል። ማንም ተደራጅቶ አይዘርፍም፤ ማንም ሁሉን የእኔ አይልም።

Related stories   አሜሪካ ለጊዜው ሲባል የከረመ ሃሳብ ያካተተ መግለጫ አወጣች፤ ምርጫውን በተዘዋዋሪ ደግፋለች

->

አሁን እዚህም እዚያም በአማራ ላይ የሚለኮስብን እሳት ዋና አላማው ወቅታዊ ረብሻና ሁከት አይደለም። ዋና ግቡ ፖለቲካችን እንዳይረጋና ወደ አሸናፊነት እንዳይመጣ መረበሽ ነው። አሸናፊነት ተረጋግቶ ከማሰብና ተደራጅቶ ከመዝመት እንደሚመነጭ ጠንቅቆ የሚያውቅ አካል ሆን ብሎ ለሚያደርገው ሁሉ በርግገን አይሆንም። ድንጉጥና ብርጉግ አያሸንፍም። በሆነ ባልሆነው ማማረርና ማለቃቀስም የአሸናፊነት ሥነ-ልቦናን ይሸረሽራል። ቆፍጠን ጀገን እንበል።

—>

ማንንም ለማሸነፍ ጦርነት የግድ አይደለም። ጦርነትን አንፈልግም። ጦርነትን የማንፈልገው ለማሸነፍ ስለማይጠቅም ሳይሆን አሸናፊውም የሚጎዳበት ሁሉን አክሳሪ መንገድ ስለሆነ ነው። እናም “የግድ ካልሆነ በቀር ለማሸነፍም ቢሆን” ጦርነትን ምርጫ አናደርግም። ይህ ማለት ግን ጦር ሰብቆ ለሚመጣ ደረታችንን እንሰጣለን ማለት አይደለም። መመከቻ ጋሻችንን በጠንካራ ክንዳችን ሳንይዝ በጦር አውርዶች ተከበን ዝም ብለን አንቃመጥም። ጦርነትን አንመርጥም ማለት ጦርነትን እንፈራለን ማለትንም አይተካም። ካላበደ በቀር ማንም ለድብድብ ይጋብዘናል ጦርነትም ይጀመራል ብለን ባናምንም በሰላምና በፍቅር ለመሸናነፍ ተፈጥሮውም ዕድገቱም ለማይፈቅድለት የጦር ዛር የሰፈረበት ጥጋበኛ ምሱን ለማቅመስ ግን ተፈጥሯዊ መብታችን እንዘጋጅ ዘንድ ያስገድደናል።

Related stories   የመ/ሰራዊትን መለያ ለብሶ ከሱዳን ወደ ወልቃይት ሊገባ የነበረ የትህነግ የሽብር ሃይል ተደመሰሰ፤

->

እኛ ማሸነፍ የምንፈልገው ሁሉን አቃፊና አካታች በሆነና ሁሉም በሚያሸንፍበት አግባብ ብቻ ነው። ሁሉም የሚያሸንፍበትን አሸናፊነት እንጅ ማንም የሚሸነፍበትን ድል አንፈልግም። ችግሩ ይህ ዓይነት መንገድ ባንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚሆን አይደለም። ሁላችንም ማሸነፍ እየቻልን ወደመሸናነፍ ፖለቲካ ቀድሞ የገባና በዚሁ የጥሎ ማለፍ ሜዳ ላይ ብቻ መጫወትን የሚወድ እስካለ ድረስ ግን ብቸኛው ማለፊያ አማራጭ ማሸነፍ ብቻ ይሆናል።

—>

->

አንድ ነገር ግን ልብ እንበል። የግድ ለመሸናነፍ የሚጋብዝ ተጫዋች ገፋፍቶን ይህን አክሳሪ ጨዋታ ብንገባበት እንኳን “መሸናነፉ ለፖለቲካው” እንጅ ለሕዝቡ አይደለም። የትኛውም ሕዝብ የትኛውንም አያሸንፍም። የትኛውም ሕዝብ ከየትኛውም ጋር ለመሸናነፍ አይጫወትም። ሕዝብ ሁልጊዜም ሁሉም የሚያሸንፍበትን ጨዋታ ነው የሚጫወተው። እርስ በርሱ በፍቅር ይጋባል፤ ይዋለዳል፤ ይዋሓዳል። ከፍቅር በቀር ሌላ መሸናነፊያ መንገድ አልለመደም። ሕዝቡ ያው ሕዝብ ነው። ማንም ለማንም ጠላት አይደለም፤ አይሆንምም። ሕዝቡን ተጠልለው የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ በሕዝቡ ሜዳ ለማስተግበር የሚሮጡም ይዘገይ ካልሆነ ይገለጣሉ፤ ይጋለጣሉም።

።።።።።።።።።።።።።።።።

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0