‹‹መግለጫው ኦዴፓ በሌሎች ኃይሎች ተፅዕኖ ስር መውደቁን የሚያመላክት ነው፡፡››
‹‹መግለጫው የፖለቲካ ምረጡኝ ቅስቀሳ ይመስላል››
‹‹መግለጫው ሲመዘን ‹ተረኛ ነኝ› የሚል ተራ አስተሳሰብ ይስተዋልበታል፡፡›› ምሁራን
‹‹አዲስ አበባ ሁሉም ነዋሪዎች በእኩልነት የሚጠቀሙባትና የሚበለጽጉባት የጋራ መዲናችን ናት፡፡›› ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

ባለፈው ረቡዕ የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 51 ሺህ 229 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን አስገንብቶ በዕጣ ለተጠቃሚዎች አስተላልፏል፡፡ ከጋራ መኖሪያ ቤቶቹ የዕጣ ማውጣት ሂደት በኋላ ጉዳዩን አስመልክቶ የተነሱ ሐሳቦች ከተማዋን አጀንዳ የሀገሪቱ መነጋሪያ አጀንዳ አድርገዋት ሰንብተዋል፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም የአዲስ አበባ ጉዳይን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ ደግሞ የአጀንዳው መነሻ ነው፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በመግለጫው ‹‹በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ መካከል ያለው የአስተዳደር የወሰን ጉዳይ እልባት እስከሚያገኝ የኦሮሚያ ክልል ጥያቄ እያነሳባቸው ያሉ የክልሉን ወሰን አልፈው የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለተጠቃሚዎች በዕጣ ማስለላለፍ ትክክል እንዳልሆነ ክልሉ ያምናል›› ብሏል፡፡ ውሳኔው ሥራ ላይ እንዳይውል የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጠንካራ አቋም መያዙንም ገልጿል፡፡

በመግለጫው ‹‹በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚከናወኑ ሥራዎች ሁሉ ከክልሉ መንግሥት ዕውቅና ውጭ ለመሥራት መታቀዳቸው አግባብ አይደለም›› ያለው የክልሉ መንግሥት በአዲስ አበባ ጉዳይ ከወሰንና ቤቶች ጉዳይ በዘለለ የኦሮሞ ባለቤትነትን ለማረጋገጥ እንደሚሠራም ነው ያስታወቀው፡፡

መግለጫው አሁን ካለው ሀገራዊ ለውጥ፣ ፖለቲካዊ ሁኔታ እና ከሕግ አንፃር ትርጉሙ ምን ምንድን ነው? ስንል የተለያዩ ምሁራንን አነጋገረን የሚከተለውን ትንታኔ አዘጋጅተናል፡፡

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

‹‹አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ከተማ ናት፡፡ ምንም እንኳን የቁጥር ልዩነቶች ቢኖሩም ነዋሪዎቿ ደግሞ ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ ናቸው›› ያሉን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ አስተዳደር ኮሌጅ የሰብዓዊ መብት እና ፌደራሊዝም ረዳት ፕሮፌሰሩ ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ ናቸው፡፡ መግለጫው የሐሳብ ልዩነቶችና መሠረታዊ ችግሮች እንዳሉበትም ተናግረዋል፡፡

መግለጫው የኦሮሚያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ‹‹በሌሎች ኃይሎች ተፅዕኖ ስር መውደቁን የሚያመላክት ነው›› ያሉት ዶክተር ሲሳይ የአዲስ አበባ ከተማን የባለቤትነት መብት ጥያቄ አድርጎ ማቅረብ ከጊዜያዊ የፖለቲካ ፍጆታነት የዘለለ ፋይዳ እንደማይኖረውም ነው ያብራሩት፡፡

በኢፌደሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 5 ላይ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለው ‹‹የልዩ ተጠቃሚነት›› መብት ‹‹መሠረቱ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምን እና መሰል ጉዳዮችን የሚመለከት እንጅ ባለቤትነትን አመላካች አይደለም›› ሲሉም ዶክተር ሲሳይ ተናግረዋል፡፡ አዲስ አበባ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 2 ‹‹ራሷን በራሷ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን ተሰጥቷታል›› ነው ያሉት፡፡

‹‹አዲስ አበባ የኦሮሞ ከተማ ናት የሚል የሕግ ማዕቀፍ የለም፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችን አብሮ መኖር የሚፈልግ ድርጅትም በኅብረ ብሔራዊ ከተማ ‹ልዩ ጥቅም› አያስፈልገውም›› ያሉት ደግሞ ጠበቃ፣ የሕግ አማካሪ እና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ተከራካሪው አቶ አለልኝ ምሕረቱ ናቸው፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶች የተሰሩባቸው ቦታዎች የአዲስ አበባ ከተማ የገጠር ቀበሌዎች መሆናቸውን የገለጹት አቶ አለልኝ ‹‹የጋራ መኖሪያ ቤቱ የተሰራባቸው ቦታዎችም እንዲሁ ከአርሶ አደሮች በነፃ የተነጠቁ አይደሉም፤ ካሳ ተክፍሎባቸው እንጂ›› ብለዋል፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር መነጋገር ካለበት በካሳው በቂ መሆን አለመሆን እና በአርሶ አደሮቹ ዘላቂ ሕይወት ላይ የመፍትሔ ሐሳብ ማመንጨት ላይ ቢያተኩር እንደሚሻለው ነው ሐሳብ የሰጡት፡፡

Related stories   Ethiopia’s transition misrepresented. Reply to Obang Metho

አዲስ አበባን በታሪክም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከተማ እንጂ የአንድ ብሔር እና የአንድ ክልል ከተማ አለመሆኗንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወጥ ሀገራዊ ፓርቲ ለመመሥረት በሚንቀሳቀስ ሀገራዊ ድርጅት ውስጥ የብቻ ከተማ ለመፍጠር መሞከር አያስኬድም፡፡ መግለጫው ሲመዘንም ‹ተረኛ ነኝ› የሚል ተራ አስተሳሰብ ይስተዋልበታል›› ነው ያሉት አቶ አለልኝ፡፡

ሀገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር እና ‹የለውጥ አራማጅ ነኝ› ከሚል የፖለቲካ ፓርቲ የሚጠበቅ መግለጫ አይደለም ያሉት ደግሞ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አቶ ታደሰ አክሎግ ናቸው፤ ‹‹መግለጫው የፖለቲካ ምረጡኝ ቅስቀሳ ይመስላል›› ነው ያሉት ምሁሩ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ‹‹በነባሩ የኢህአዴግ አገዛዝ ሥርዓት ለግጭት ምንጭነት የተጠመደች ቦንብ ናት›› ያሉት የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ አቶ ታደሰ ‹‹ኦዴፓ ቦንቡን በመርገጥ ቀዳሚ እየሆነ ይመስላል›› ብለዋል፡፡ የፅንፈኞች አስተሳሰብ የጠመዘዘው ኦዴፓ አሁንም የብሔርተኞች ጥቅምን የሚያስቀድም እንደሚመስልም አብራርተዋል፡፡

በአንድ ቤት ውስጥ ‹ልዩ ጥቅም› ያለው የቤተሰብ አባል አይኖርም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አንድ ሀገራዊ ፓርቲ እንመሠርታለን ከሚል ድርጅት ውስጥ ‹ልዩ ጥቅም› የሚያስፈልገው ብሔር አይኖርም ነው ያሉት አቶ ታደሰ፡፡

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሌሎች የመፍትሔ ሐሳቦችን መጠቀም እንደሚገባም ምሁራኑ አሳስበዋል፡፡ ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ የፌደራል መንግሥቱ መቀመጫ ከተማ ከአንድ በላይ መሆን እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ ሀገራት የመንግሥት መቀመጫ ከተሞች ከአንድ በላይ ናቸው፤ በመሆኑም የሕግ አስፈፃሚው አዲስ አበባ ላይ ከሆነ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አውጭ አካላት በተለያዩ ከተሞች ላይ ቢሆኑ ፍትሐዊ የሆነ የከተሞች ዕድገት እንዲኖርና እና የአዲስ አበባ ከተማ ጫናን ለመቀነስ አማራጭ እንዲሆን ይመክራሉ፡፡

ትናንት በነበረው የአማራ ክልል አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር በዓለ ሲመት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢፌደሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮነን የአዲስ አበባን ጉዳይ አስመልክተው ‹‹አዲስ አበባ ሁሉም ነዋሪዎች በእኩልነት የሚጠቀሙባትና የሚበለጽጉባት የጋራ መዲናችን ናት፡፡ የከተማዋ ዕድገት ማንንም ሳይጋፋና ማንንም ሳይጎዳ ሁሉንም ሊጠቅም በሚችል መልኩ ተፈፃሚ መሆን ይገባዋል›› ብለዋል፡፡

‹‹በከተማዋ ማደግና መስፋፋት ምክንያት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎችን በዝርዝር አጥንቶ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ማድረግ የሁሉም አካላት ኃላፊነትና ግዴታ ነው›› ያሉት አቶ ደመቀ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮች ሕዝቡን ባሳተፈ ሁኔታ ሕግን መሠረት አድርጎ በቀጣይ በውይይት መፈታት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው –  (አብመድ)

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *