“Our true nationality is mankind.”H.G.

የአዲስ አበባን ወቅታዊ ጉዳይና “ኮሚቴውን” በተመለከተ

ሀገር በለውጥ ተስፋና በስጋት መሐል ተወጥራ ባለችበት በዚህ ወሳኝ ወቅት የአዲስ አበባን ጉዳይ በዚህ ሁሉንም በማያግባባ መልኩ አጀንዳ አድርጎ ማንሳት ለምን አስፈለገ? በዚህ ወቅት የኢትዮጵያን ቀጣይነትና በልዩነት ስብከት የከረሙ ሕዝቦቿን አንድነት ለማምጣት ከመጣጣር ይልቅ የበለጠ መለያየትንና መጠፋፋትን የሚያፈጥን ጉዳይን መርጦ ማንሳት ለምን ተፈለገ? ይህን አጀንዳ በዚህ መልኩ ለማራገብ በተለይ የአማራና የትግራይ ክልሎች ውጥረት ውስጥ መግባትን ጠብቆ መነሳት ለምን ተፈለገ?

በመላኩ አላምረው

(የአማራ ክልል ም/ቃል አቀባይ)

የአዲስ አበባን ጉዳይ “የኢህአዴግ” (አዴፓ፣ ኦዴፓ፣ ሕወሓትና ደኢህዴን) ወይም የተወሰኑ ክልሎች ጉዳይ ብቻ ያደረገው ማነው?

የድንበር ጉዳይን ጨምሮ አሁን አለ የሚባለውን ችግር ለመፍታት የተቋቋመውን ኮሚቴ አየሁት። አባላቱ ከክልል ክልል (ከድርጅት ድርጅት) ሲነፃፀር የቁጥር አለመመጣጠኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አመራረጡ የአዲስ አበባ ኗሪዎችን ያገለለና በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ብቻ የተወከለ ነው።

=>

1ኛ. በመሠረቱ ጉዳዩ የአዲስ አበባ ጉዳይ ሆኖ ሳለ የከተማዋ ኗሪዎች አልተወከሉበትም፤ (ከተማዋ መስተዳድር አባላት የሚወክሉት አዲስ አበባን እንደከተማ ሳይሆን የመደቧቸውን የየክልል ድርጅቶች ነው። ለየክልላቸው/ለየድርጅታቸው እንጅ ለአዲስ አበባ ኗሪዎች ውግንና ይኖራቸዋል የሚል እምነት እንዳይኖር ያደርጋል።)

2ኛ. በሌላ በኩል (በመዲናዋ ጉዳይ ክልሎች ሊወከሉ ይገባል ከተባለ) አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማና የብሔር ብሔረሰቦች መናኸሪያ እንደመሆኗ መጠን በኮሚቴው ውስጥ ሁሉም ክልሎች ሊወከሉ ይገባል። የአራት ክልሎችን የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች ብቻ የወከለ አካሄድ ትክልል አይደለም። ይህ ኮሜቴ እንደ ክልል አፋርን፣ ሶማሌን፣ ጋምቤላን፣ ሐረሪን፣ ቤኒሻንጉልን… “በአዲስ አበባ ጉዳይ አይመለከታችሁም” እንደማለት ተደርጎ ሊተረጎምምም ይችላል። ይህም ለሀገራዊ አንድነት ሌላ ሳንካ የመፍጠር አካሄድ ነው።

Related stories   ኤፒ ለቅጥፈቱ ይቅርታ አልጠየቀም – ምርጫ ተራዘመ፤ለምን?

3ኛ. በአዲስ አበባ ጉዳይ መሪው ድርጅት ኢህአዴግ ብቻ የሚፈተፍትበት ምንም አግባብ የለም። በከተማነቷ ኗሪዎቿ በትክክል ይወክለኛል በሚሉት አካል መወከል አለባቸው። በኢትዮጵያ ዋና ከተማነቷ ደግሞ ሁሉንም የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም ሁሉንም ሀገራዊና የየክልል የፖለቲካ ፓርቲዎችን ባካተተ መልኩ ነው ጉዳይዋ መታየት ያለበት። ይህን ወደጎን ብሎ “ኢህአዴግ በግንባር ድርጅቶቹ ተዋጽኦ የወከላቸው የከተማዋ አስተዳድር አባላት ከራሱ ከኢህአዴግ አመራሮች ጋር በመደራደር የአዲስ አበባን ጉዳይ እልባት እሰጣለሁ” የሚለው አካሄድ ቅቡልነት ሊኖረውና መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም። ትክክለኛና ተገቢ አካሄድም አይደለም።

4ኛ. የአዲስ አበባ ጉዳይ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ጉዳይ ነው። ምንአልባትም ኢትዮጵያ እንደሀገር የመቀጠል ያለመቀጠሏ የመጨረሻው ወሳኝ ጉዳይ የአዲስ አበባ ጉዳይ ነው። ከዚህም ባሻገር መዲናዋ የአፍሪካ መዲና እና ለሕብረቱ ጉዞ ማስተሳሰሪያ ማዕከል ናት። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዲፕሎማሲ መናኸሪያ በመሆንም ከዓለም ሦስተኛ ናት። የአዲስ አበባ ጉዳይ በኮሚቴም ሆነ በሌላ አግባብ ሲታይ ይህ ሁሉ ግምት ውስጥ ገብቶ ነው መታየት ያለበት። ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜትን በተሞላና መፍትሔን በሚያመጣ አካሄድ ነው ሊታይ የሚገባው። ችግሮችን በሚያባብስ መልኩ በስሜታዊነትና በእልህ መጓዝ ወደ ገደል ብቻ ነው የሚወስደው። የአዲስ አበባ ጉዳይ የአንድ ከተማ ጉዳይ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ እምነት፣ ታሪክ፣ ማኅበራዊ ትስስር፣ ሕብረ ብሔራዊነት ሁሉ ጉዳይ ነው። ከምንም በላይ ተወልደው ያደጉባት እትብታቸውን የቀበረች የኗሪዎቿ መፈጠሪያም መቀበሪያም ከተማ ናት። ይህን ሁሉ ግምት ውስጥ የማያስገባ የአንድ ወገን እይታ መፍትሔ ሳይሆን ችግር ነው የሚወልደው። ያውም ከተማዋን ከማጥፋትም ባሻገር ሀገር የሚበትን ችግር።

Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?

5ኛ. ምንም አይነት ኮሚቴ ቢቋቋም፤

አንደኛ፦ አዲስ አበባን የኗሪዎቿ ከተማ እና የሁሉም ኢትዮጵያዊ መዲና ማድረግ የማይችል ኮሚቴ ከሆነ ቀድሞ ባይቋቋም ይሻላል። አዲስ አበባ ለኗሪዎቿና ለሁሉም ካልሆነች ለማንም ለብቻው የምትሆንብት ምንም ዕድል የለም፤ ለወደፊቱም አይኖርም።

ሁለተኛ፦ አዲስ አበባ በምትስፋፋበት ተፈጥሯዊ ጉዞዋ የሚገፉና ተገቢው ካሣ የማይከፈላቸው ዜጎች እንዳይኖሩ የሚያደርግ ወይም በዙሪያዋ ያሉ አርሶ አደሮችን የከተማዋ አካል እያደረገ ለማቋቋም የሚያስችል አሠራርን እውን የማያደርግ ኮሚቴ ምንም አይነት ዘላቂ መፍትሔን ሊያመጣ አይችልም። የአዲስ አበባ ባለችበት ቦታ መመስረትም ሆነ መስፋፋት በዙሪያዋ ለሚኖሩ ዜጎች መልካም ዕድል ብቻ ሆኖ መሠራት አለበት። በመዲናዋ ዚሪያ ያሉ ሕዝቦች የከተማዋን መስፋፋት የሚናፍቁት እንጅ የሚያማርሩት መሆን አይገባውም። የአዲስ አበባ ባለችበት ቦታ መኖር ለማንም ዕድልና መልካ አጋጣሚ ብቻ የሚሆንበትን አሠራር እውን ማድረግ ይገባል፤ ይቻላልም።

Related stories   የኢትዮዽያ የቁርጥ ቀን ልጅ "ስለአባይ እውነቱን እንካችሁ" – መካ አደም አሊ

===>

=>

በመጨረሻም የመዲናችንን ሰሞንኛ አጀንዳ መሆን በተመለከተ አንድም ሦስትም ጥያቄ/ዎች ላንሳ፦

ሀገር በለውጥ ተስፋና በስጋት መሐል ተወጥራ ባለችበት በዚህ ወሳኝ ወቅት የአዲስ አበባን ጉዳይ በዚህ ሁሉንም በማያግባባ መልኩ አጀንዳ አድርጎ ማንሳት ለምን አስፈለገ? በዚህ ወቅት የኢትዮጵያን ቀጣይነትና በልዩነት ስብከት የከረሙ ሕዝቦቿን አንድነት ለማምጣት ከመጣጣር ይልቅ የበለጠ መለያየትንና መጠፋፋትን የሚያፈጥን ጉዳይን መርጦ ማንሳት ለምን ተፈለገ? ይህን አጀንዳ በዚህ መልኩ ለማራገብ በተለይ የአማራና የትግራይ ክልሎች ውጥረት ውስጥ መግባትን ጠብቆ መነሳት ለምን ተፈለገ?

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0