“Our true nationality is mankind.”H.G.

አዴፓ – ኢትዮጵያዊነትና አማራነትን የተወናበደበት ድርጅት!!

አዴፓዎች ማንም አይድረስብን ባሉና ኢትዮጵያ በማለታችን ተገፋን፣ ተበደልን፣ ተሰደድን በሚሉ ኃይሎች የተከበበና ኢትዮጵያዊነትና አማራነትን አዋህዶ መምራት የተወናበደበት ድርጅት ነው፡፡ በዚህ ላይ አዴፓ በውስጣዊ የአማራነት፣ አትድረሱብኝ ባይነትና የተበዳይነት፤ በውጭ የወልቃይትና የራያ አጀንዳ እንዲሁም በየጊዜው በሚፈበረክለት የቅማንት፣ የአገው፣ የከሚሴ ኦሮሞ ጥያቄ ተወጥሮ የተያዘና ከሚሊኒክ ቤተመንግስትና ከፌደራል ስልጣን ፈጽሞ የራቀ ድርጅት ሆኗል፡፡
ደኢህዴን፤ ክልል ከመሆን ጥያቄ ውጭ ሌላ አጀንዳ የሌላቸውና ለቀሪው ብሔር ደንታ የማይሰጣቸው የሲዳማ ጌታዎቹ እየተፈራረቁ እንዲያስተዳድሩት የተፈረደበት ደካማ ክልል በመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥዊም ሆነ ውጫዊ ጉዳይ ከቁም ነገር የሚጽፈው የለም፡፡ አገር በማስተዳደር ሂደት ውስጥ የተገፋ ድርጅት ነው፡፡
ሕወኃት አማራጭ በማጣት ኢትዮጵያዊ የሆነ ድርጅት ነው፡፡ ግራ የመጋባቱ ጥግ ደግሞ የነጻ አውጭነት ስሙ ዛሬም ተጣብቆበት መቀጠሉ ነው፡፡ ሕወኃት ሃጢያቱና ግፉ ገደፍ ሞልቶ ከመፍሰሱ የተነሳ ቅዥቱ ከሕዝብ መሃል አላስቀምጥህ ብሎታል፣ በራሱ ጊዜ ተሰዶ በክልሉ ውስጥ መሽጎል፡፡ ክልሉን ነጻ በማውጣትና በኢትዮጵያዊነት መቀጠል መካከል ውዝግብ ውስጥ የወደቀ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ከሕዝብ ሸሽቶ ስለመሸገ አገር ለማስተዳደር የነበረውን የጋራ ሚና በገዛ ፈቃዱ ያጣ ድርጅት ነው፡፡
ቀሪዎቹ የኢህአዴግ አባላትና ተባባሪ ድርጅቶች በውስጣቸውና በዙርያቸው በቀፈቀፉት ወጥንቅጡ የጠፋ የስደት፣ የመፈናቀል፣ የዘረፋ፣ ኢኮኖሚና የፖለቲካ ኪሳራ ምክንያት እንኳን አገር መምራት ይቅርና በክልላቸው ውስጥ በእግራቸው ለመቆም አቅቷቸው፣ እየተውተረተሩ ይገኛሉ፡፡
ኦዴፓ እስካሁን በተናጠል ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ሕዝቦች የትልቁ ብሔር መሪ ድርጅት ስለሆነ ትልቅነቱ የሚጠበቅ መሆኑን መረዳት፣ ማጣጣምና ማመን የቸገረው ድርጅት ነው፡፡ በዚህ ዉሃ ልክ እየመዘነ ኢትዮጵያን ከማስተዳደር ይልቅ፤ እንደ አናሳ ድርጅት ኢትዮጵያዊ ለመሆኑ ልዩ የዜግነትና ልዩ የባለቤትነት ጥቅም በመጠየቅ አልፎ ተርፎም ተገፋሁ፣ ተናቀሁና አትችልም ተባልኩ በሚሉ የዝቅተኝነት ተረኮች የተጠመደ ፓርቲ ነው፡፡
በዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ መሃል ሆነን ኦዴፓ የጋራ ሃገሪችንን መቶ በመቶ ሊባል በሚችል ደረጃ ተቆጣጥሯታል፡፡ ይህም ሆኖ ዋልታ ረገጥ ፍላጎቱንና በእቅድ ያልተደገፈ ጉጉቱን ከግብ ለማድረስ አንዳንድ ጊዜ ከአክቲቪስቶች፣ ከታጠቁና በአመጽ ላይ ካሉ ድርጅቶች ጋር እየተሞዳሞደ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከቄሮ ጋር እየተጣመረ ሲመቸው ደግሞ መለስ ብሎ የመንግስት መዋቅርንና ጉልበትን እየተጠቀመ ሲያሻው ደግሞ ስለ ኢትዮጵያዊነት እየሰበከ በተምታታ የሃሳብ በፈረቃ እየገዛን ይገኛል፡፡
ኦዴፓ ሃገርን አቀናጅቶ ለመምራት ግር ሊለው የሚችለው በአንድ ምክንያት የተነሳ ይመስላል፡፡ በአንድ በኩል የሁላችንም በሆነች ኢትዮጵያ ላይ መሪ ድርጅት ሆኖ “የኔና የብቻዪ” የሚል ልዩ ጥቅም መፈለጉና በሌላ በኩል ደግሞ የሁላችን የሆነችውን ኢትዮጵያን በጋራና በእኩል ተጠቃሚነት ለማስተዳደርና ለመምራት ማሰቡ ሊታረቁ በማይችሉ ፍጥጫዎች ውስጥ እንዲተበተብ በመገደዱ ነው፡፡
ኦዴፓ የመርህ ድርጅት መሆን ሊያዳግተው አይገባም፡፡ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን፤ ሃገር በመምራት ላይ የሚገኝ ፓርቲ መድሕኑ ያለው በአቋምና በመርህ ላይ ተመስርቶ ሕግና የሕግን የበላይነት ማረጋገጥ ሲችል ብቻ ነው፡፡ ይህንን አማራጭ ሁለተኛ አማራጭ አደርጎ ለመውሰድ መሞከሩ ግን ጉዞውን የቁልቁለት ጉዞ አደርጎበታል፡፡ በስሜት ተጠምዶ በየወንዙ መማማልና ከአክቲቪስት ጋር እየተሞዳሞደ፣ በተቃራኒው ደግሞ ከሕዝብ ጋር ትከሻ መፈታተሸን የተሻለ አቋራጭ መንገድ ማድረጉ የዚሁ ዝንባሌው ሌላው መገለጫ ይመስላል፡፡
መፍትሔው ውስብስብ አይደለም፡፡ የተበጣጠሱና የቁልቁለት ጉዞ የጀመሩ የኢህአዴግና አጋር ድርጅቶችን አሰባስቦ ኢ-መደበኛ የሆነውን መንገዱ በመተው፤ ወደ መደበኛው መንገድ በመግባት የመንግስትነት ሚናውን፤ በመንግስት መዋቅር ውስጥ በቅጡ መወጣት መጀመር አለበት፡፡ ስራ በውጤት ይለካል፡፡ ተወደደም ተጠላም ውጤት ደግሞ ያስከብራል፡፡ ልማት፣ እድገትና ዴሞክራሲን ማስፈን ከተቻለ አገር በምርጫ ውጤት ይዳኛል፡፡ የምርጫ ውጤት ሕጋዊ ዳኝነት የሚሰራው ለተቀናቃኝ ብቻ ሳይሆን ለገዢው ፓርቲም ጭምር መሆኑ ግልጽ መደረግ አለበት፡፡
ለአጼ ሃይለስላሴ፣ ለደርግ፣ ለሕወሃት በጸጥታ ተገዝታችሁ ነበር ከሚል የተዛባ ምልክታ በመነሳት ዛሬ ተራው የኔ ስለሆነ ለኔም በጸጥታ ተገዙ፣ አድምጡን እንጂ አትናገሩ፤ አድንቁን እንጂ አትተቹን በጥቅሉ እኛ እናስብላችኋለን በማሰብ አትድከሙ የሚል ተረክ ውስጥ እራስን መቀርቀር መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ ተወደደም ተጠላም የጋራን አገር በጋራ በፈጠርነው ስርዓት ውስጥ ሆነን መምራት መጀመር አለብን፡፡
“እገላለሁ ሲሉ መሞት”
“አጠፋለሁ ሲሉ መጥፋት”
“አፈርሳለሁ ሲሉ መፍረስ”
“ትልቅ ነኝ ሲሉ ትንሽ” መሆን አለ።

Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ
Mushe Semu

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0