‹‹አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ከተማ እንደሆነች የኢህአዴግ እህት ፓርቲዎች ያምናሉ፡፡ ይህን ባለማመን የኃይል ርምጃን የሚያስተናግድ የፖለቲካ ርዕዮት አይኖርም፡፡›› አዴፓ

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሜቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው በፓርቲው የሁለት ቀናት የውይይት ጭብጦችና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሜቴ በክልሉ ያለውን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ለሁለት ቀናት ገምግሟል። ለውጡን ለማስቀጠል የሚረዱ ተግባራት ጥሩ ቢሆኑም በሂደቱ ግጭቶች እና የሰላም ውስንነቶች መፈጠራቸውንና አመራሩን የማጠናከር ሥራ መሠራቱን የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ዮሐንስ በመግለጫው ላይ አንስተዋል።

በለውጡ መንገድ የተስተዋሉ ቀውሶች ምጣኔ ሀብቱ ላይ ተፅዕኖ ማሳደራውን ፓርቲው መገምገሙን የጠቆሙት አቶ ዮሐንስ በቀጣይ የመኸር ወቅት መቀዛቀዝ እንዳይታይ የመንግሥት ሠራተኞች አርሶ አደሮችን እንዲያግዙ ፓርቲው ጥሪ ማስተላለፉን አስታውቀዋል፡፡

‹‹ምሁራን እና በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ከባለፉት ዓመታት በተለየ መንገድ ከእኛ ጋር አብሮ ለመሥራት ፍላጎት እያሳዩ ነው›› ያሉት የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ወጣቶች በለውጡ የተጋረጡ ችግሮችን በመታገል የአማራን ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት ፓርቲው እንደሚያመሠግን ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመፈቃቃር ላይ የተመሠረተ አንድነት እንዲፈጠር እስካሁን ካደረገው ጥረት በላይ መሥራት እንደሚያስፈልግም አቶ ዩሐንስ አስታውቀዋል፡፡

መላው ሕዝቡ የተጀመረው ለውጥ ፍጥነቱን እንዲቀጥል በማድረግ ጠንካራ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ‹‹ተፎካካሪ ፓሪቲዎች የያዛችሁትን ዓለማ ለማሳካት በሕጋዊ መንገድ ለምታደርጉት እንቅስቃሴ አዴፓ ድጋፍ ያደርጋል›› ብለዋል፡፡

ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍልም የአካባቢውን ሰላም በሚያስከብርበት ወቅት አልፎ አልፎ ችግሮች መታዬታቸውንም በመግለጫው አንስተዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ቀናት በባሕር ዳር እና ደሴ የታዩ ችግሮች ከኅብረተሰቡ የሰላም ፍላጎትና የንቃት ደረጃ የማይመጥኑ ደካማ ድርጊቶች እንደነበሩ ነው የተናገሩት፡፡ ኅብረተሰቡ እና የፀጥታ ኃይሎች ችግሩ ወደ አስከፊ ደረጃ እንዳይሄድና በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መቆጣጠር መቻላቸው የሚደነቅ እንደሆነም ማዕከላዊ ኮሚቴው መገምገሙን በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ በአዴፓ እና ኦዴፓም ሆነ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ተናግረዋልው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታፍኖ የነበረ በመሆኑ የልዩነት ሐሳብ ቅራኔ ይመስላል፤ ግን ጤናማ የአስተሳሰብ ለውጥ ነው፡፡ በድሮ ኢህአዴግ ብዙ የታፈኑ ድምፆች ስለነበሩ ልዩነቶች አይንፀባረቁም፤ ሕዝቡም አልለመደውም፡፡ አሁን እነዚህ የዴሞክራሲ እና የሐሳብ ብዝኃነቶች ሲስተናገዱ ሕዝቡ ሊደናገጥ አይገባም፡፡ በእኛ እና ኦዴፓ መካከል ልዩነት የተፈጠረ መስሏቸው የሚቦርቁም አሉ፤ ለእነዚህ መርዷቸውን ንገሯቸው፡፡ እኛ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕድል ብሩህ ለማድረግ እየሠራን ነው›› ብለዋል፡፡

‹‹ከትግራይ መንግሥት ጋርም ዘራፊዎችን አሳልፎ አለመስጠቱ እንጂ ሌላ ቅሬታ የለንም›› ያሉት አቶ ዮሐንስ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር በሂደት በደም እና በዝምድና የተሳሰረው የአማራና የትግራይ ሕዝብ ዘራፊዎችን አብረው እንደሚታገሉም የፓርቲያቸው እምነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹አዴፓ በስግብግብነት የታሪክ እና የቦታ ሽሚያ ውስጥ አይገባም፡፡ ከሌሎች ሕዝቦች የተለዬ ጥቅም ለአማራ በማምጣት ለሌሎች ስጋት እንዲታይም አይሰራም›› ነው ያሉት፡፡ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ከተማ እንደሆነች የኢህአዴግ እህት ፓርቲዎች እንደሚያምኑ በመግለጽ ይህን ባለማመን የኃይል እርምጃን የሚያስተናግድ የፖለቲካ ርዕዮት አንደማይኖርም ጠቁመዋል፡፡

‹‹አሁን የሚፈጠሩት ችግሮች በጭቆናው ዘመን ታፍነው የነበሩ የተከማቹ ድምፆች ውጤት ናቸው፡፡ የሕዝቡ መከፋት እና መቆጨት ደግሞ ለለውጡ መልካም ጫና መሠረት የጣሉ ናቸው›› ብለዋል አዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ዮሐንስ ቧያለው፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2011ዓ.ም (አብመድ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *