“Our true nationality is mankind.”H.G.

የኢህአዴግ ውህደት ተስፋ ወይስ ስጋት?

በቀድሞው የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ኢህዴን/ እና በህወኃት አማካኝነት ግንቦት 1981 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራስያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ከተመሰረተ 30 ዓመት አስቆጥሯል:: ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ከፖለቲካ ፓርቲነት አልፎ መንግስት ሆኖ እየመራ ነው::

የአራት (የአዴፓ፣ የህወሓት፣ የኦዴፓ፣ የደኢህዴን) ግንባር የሆነው ኢህአዴግ ግራ ዘመም /ሶሻሊታዊ/ የፖለቲካ መርህ ላይ አዘንብሎ በአብዮታዊ Image may contain: 1 person, closeupዴሞክራሲያዊ ቅኝት ሲመራ ቆይቷል:: የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዋነኛ መገለጫ የሆነው “ዴሞክራሲያዊ ማእከላዊነት” ደግሞ አራቱን የኢህአዴግ ግንባር ፓርቲዎች እና የታዳጊ ክልል አጋር ፓርቲዎችን ሁሉ ተመሳስለው እንዲያስቡ አድርጎ በኢህአዴግነት ጥላ ስር አቅፏቸው ቆይቷል::

የፖለቲካ ሊሂቃን እንደሚሉት ኢህአዴግ የብሔራዊ ፓርቲዎች ግንባር ሆኖ፣ ኢትዮጵያን በብሔረሰቦች የሚገልጽ፣ የብሔር ጭቆና አለ ብሎ የሚያምን እና ከመደብ ትግል ይልቅ የብሔር ነፃነት ላይ የሚያተኩር የብሔሮች ግንባር ፓርቲ ነው::
የሀገሪቱ አውራ ፓርቲ ሆኖ የከረመው ኢህአዴግ ከግንባርነት ይልቅ ውህድ ፓርቲ እመሰርታለሁ ሲል በሊቀመንበሩ በዶክተር ዐብይ አህመድ በኩል ገልጿል::

የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር ዐብይ አህመድ የሐረሪ፣ የሶማሌ፣ የአፋር፣ ቤንሻጉል እና የጋምቤላን ወኪሎች ሰብስበው ሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል የሚነጋገሩበት፣ የሚወስኑበት፣ ድምጽ የሚሰጡበት፣… ኢህአዴግ አንድ ሀገራዊ ውህድ ፓርቲ ሆኖ ይወጣል ብለዋል::

የኢህአዴግ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳደት ነሻን ኢህአደግ ከግንባርነት ወደ ውህድ ፓርቲነት የመቀየር እሳቤው ያደረ እና የተፈፃሚነት ጉዳዩም የዘገየ ሀሳብ ሆኖ እንጂ ከተመከረበት ቆይቷል ሲሉ ለቢቢሲ ሀሳባቸውን አጋርተዋል::ኢህአዴግ ወደ ውህደት ለመምጣት በ11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤው ዘክሮ ለተግባራዊነቱ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ መገለጹም የሚታወስ ነው::

ዕውን ኢህአዴግ መዋኻድ ይችላል?

የቀድሞው የኢህዴን ታጋይ የነበሩት እና በህግ እጩ ዶክተር የሆኑት አቶ ቹቹ አለባቸው የኢህዴግን የውህደት ሀሳብ በሁለት አንጓዎች ከፍለው ይመለከቱታል:: በመጀመሪያ ይላሉ አቶ ቹቹ የኢህአዴግ የውህደት ሀሳብ ከአሻጥር የፀዳ ከሆነ የተበታተነውን የህዝብ እሳቤ እና የደቀቀውን ሀገራዊ ዓላማ ለመመለስ አይነተኛ መፍትሄ ነው:: በክልል ደረጃ ያሉ ብሔራዊ ፓርቲዎች ከክልላዊ ቅንፋቸው ወጥተው ስለ ዜግነታቸው፣ ስለ ሀገራቸው እንዲያስቡ የኢህአዴግ የመዋኸድ እሳቤ በር ይከፍታል ይላሉ::ውህደቱ በብሄራዊ ክልሎች ስልጣኑን አሳልፎ የሰጠው ማዕከላዊ መንግስት የተሻለ ሃይል ይኖረዋል::

Related stories   የሲኤንኤን ዘጋቢ ኒማ- በተወነችው ተውኔት ውስጥ ዳግም ሞት የተፈረደባቸው ዜጎች

ይሄን ብለው ግን የሃሳቡን ተጨባጭነት ጉዳይ ከምኞት እና ከምናባዊነት የዘለለ ሊሆን እንደማይችል ጥርጣሬያቸውን ይገልፃሉ:: አቶ ቹቹ እንደሚሉት የኢህአዴግ መሰረት እና ማያያዣ የሆነው ዴሞክራሲያዊ ማእከላዊነት ጠፍቶ እህትማማች ወይም የግንባሩ ጥምረት ፓርቲዎች በግላቸው ከኢህአዴግ በላይ ገነዋል:: አዴፓ፣ ኦዴፓ፣ ህወሓት በየራሳቸው ጐልብተው ኢህአዴግ እንደ ግንባር ጉልበቱ ዝሏል የሚሉት አቶ ቹቹ በሀገሪቱ ዋና ከተማ ዙሪያ እንኳን ስምምነት በጠፋበት ሁኔታ ውህደት ይኖራል ብሎ መጠበቅ የማይቻል መሆኑን ያሰምሩበታል::

አቶ ቹቹ በተለይ እንደ አማራ እና አማራውን እንደሚመራው አዴፓ ውህደቱ የመሆን እድሉ ዝቅተኛ ቢሆንም፤ ከሆነ ግን ጉዳት እንዳለውም አልደበቁም::

Image may contain: 1 person, selfie, sunglasses and closeup

የኢህአዴግ ግንባሮች ከ50 ዓመታት በላይ የዘለቀ የዘውግ ብሔርተኝነትን አቀንቅነው የኔ የሚሉትን ህዝብ ችግር ለመፍታት ታግለዋል:: በአንፃሩ የአማራ ብሔርተኝነት ለጋ በመሆኑ የኔ የሚላቸው ጥያቄዎች ገና አልተፈቱም:: መፈታት የሚችሉት ደግሞ በዳበረ ብሔርተኝነት እና የክልሉ መንግስት መጐልበት ሲችል ነው:: ውህደት ከኖረ ግን የአማራ ጥያቄ በውህደቱ ተዳፍኖ ሊቀር ይችላል ይላሉ አቶ ቹቹ::

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የስነ አስተዳደር ትምህርት ቤት ውስጥ የሰላም እና ግጭት አፈታት መምህር የሆኑት አቶ አያና ሞላ በበኩላቸው “ኢህአዴግ ርዕዮተ-ዓለሙን ይመስላል” ይላሉ:: ኢህአዴግ የብሔር ጭቆና ነበር ብሎ የሚያምን ድርጅት ሆኖ 27 ዓመት ቀጥሎ ነበር የሚሉት አቶ አያና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በኦዴፓ በኩል የመደብ ጭቆና ወደ ሚል የዞረ ሲሆን፤ በአዴፓ በኩል ደግሞ አማራ ጨቋኝ መደብ ተደርጐ የታሰበው እሳቤ እንደማይቀበለው አሳውቋል:: በዚህም ኢህአዴግ ከትናንቱ ጋር የተለያየ ሆኗል::

ከርዕዮተ-ዓለሙ ባሻገር አሁን ባለው የኢህአዴግ ለውጥ ላይም ድርጅቶቹ የጋራ አተያይ የላቸውም፤ ህወሓት አሁን ያለውን ሁኔታ ለውጥ ነው ብሎ እንደማይቀበለው አዝማሚያው አመላካች ነው የሚሉት አቶ አያና፣ አዴፓ እና ኦዴፓም በለውጡ ቢያምኑም በለውጡ አካሄድ ላይ ግን በተቃርኖ የቆሙ ናቸው ይላሉ::

Related stories   “ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በአንድነት በመከባበር፤ በመተሳሰብ እና በመረዳዳት ሊያከብር ይገባል”

በሌላ በኩል ህወሓት እና ኦዴፓ በፌዴራሊዝም ስርአቱ አንደራደርም ሲሉ አዴፓ ደግሞ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎቹ እንዲፈቱ የፌዴራሊዝሙ አሰራር እና አተገባበር እንዲሻሻል ይሻል::

በሌላ በኩል በኦዴፓ በኩል የሚነሱት የአዲስ አበባ ጥያቄ እና የአፋን ኦሮሞ የስራ ቋንቋ ይሁንልኝ ጥያቄ የህገመንግስት ማሻሻያ ካልተደረገ በቀር ሊፈታ አይችልም::

በዋና ከተማዋ ህልውና ላይ ሳይቀር ፣ በታሪክ አረዳድ እና በፌዴራሊዝሙ አመሰራረት ሳይቀር በተቃርኖ የተሰለፉ ፓርቲዎች ከግንባርነት ወደ ውህድነት የመቀየር ተስፋ አይኖራቸውም ይላሉ አቶ አያና::

No photo description available.

ወደ ውህደት ለመምጣት ህገመንግስቱ ከብሔሮች ባሻገር ስለ ዜግነት እና ስለሀገር እውቅና እንዲሰጥ መሻሻል ይገባዋል:: መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያም የተቀራረበ ስምምነት እና ፍትሀዊነት መኖር በቅድመ ሁኔታነት አስፈላጊ የመሆኑ ነገር አያጠያይቅም:: ታዲያ ከህገመንግስት እስከ ዋና ከተማ ጉዳይ ያላሰማማቸው ድርጅቶች ይዋኻዳሉ ብሎ መጠበቅ ከእውነታው የራቀ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ::

ህገመንግስቱ ክልሎችን ሉአላዊ ስልጣን ሰጥቷል:: ወደ ውህድ ከመጣ ግን የብሔራዊ ክልሎች ሉአላዊነት ወደ ሀገራዊ ሉአላዊነት ስለሚለወጥ አንድ አማራ ኦሮሚያን፣ ሌላው ኦሮሞም አማራ ክልልን ሊያስተዳድር ይችላል:: ይህ ግን ባለው ህገመንግስት ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ራስን በራስ የማስተዳደር ሙሉ መብት ለብሔራዊ ክልሎች የተሰጠ ነውና ሲሉ ያስረዳሉ:: ከዚህም በላይ ሀገሪቱ አሁን ከገባችበት የብሄር ፖለቲካ ንረት አንጻር ሲታይ ሁኔታውን ቀላል የሚያደርገው አይመስልም::

 

የኢህአዴግን ውህደት ከመስራች ድርጅቶቹ ባህሪ አንጻር ተንተርሶ መመልከቱም ጠቃሚ ይሆናል፤ ኢህአዴግ አንድ የተዋሃደ ፓርቲ ሲሆን መሰራች ፓርቲዎቹ የሚኖራቸው ህልውና ምን ሊሆን እንደሚችል እንመልከት፤ በኦዴፓ እንጀምር::

ውህደቱ ለኦዴፓ

 

የኦሮሞን የዘውግ ፖለቲካ እና ብሄርተኝነት የፈጠረው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የትግል አድማሱ ኦሮሞ እና ኦሮሞ ብቻ የሚል ነበር የሚሉት አቶ ቹቹ፣ የአሁኑ የኦዴፓ ፖለቲካ ደግሞ ኦነግ ከተከተለው መንገድ በተቃርኖ የቆመ ነው:: ኦዴፓ ኢትዮጵያዊነትን ከኦነግ በተሻለ በማቀንቀን የመጠቅለል እና የወከለውን ህዝብ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ የተሻለ ለመጥቀም የሚፈልግ ይመስላል:: ኦዴፓ ውህደቱ ከተሳካ የመጠቅለል ሚና ሊኖረው ይችላል ይላሉ አቶ ቹቹ:: ይሁን እንጂ የኢህአዴግ ውህደት የብሄር ፌዴራሊዝሙን ቅርጽ እንደማይቀይረው እና ወደ አሃዳዊ አስተዳደር እንደማያመራ ግንባሩ በተለያየ ጊዜ አሳውቋል::

Related stories   እስራኤል አልጃዚራ ቴሊቪዥን፣ አሶሲየትድ ፕሬስና ሌሎች ሚዲያዎች የሚጠቀሙበትን ህንጻ አወደመች

ውህደቱ ከደኢህዴን እና ከህወሓት በኩል

በ56 ብሄሮች እና ህዝቦች የተደራጀው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ደርጅት ውህደቱ ብሄረሰባዊ ዞኖች የክልል ጥያቄ እና ሽኩቻ እንዲቀርለት ደኢህዴን ውህደቱን ሊፈልገው ይችላል:: በሌላ በኩል ህዋሃት ሀገራዊ ፓርቲነቱን ባይጠላውም፤ ቀድሞ ራሱ ባሰመረው ኢህአዴጋዊ ፌዴራሊዚም ያገኛቸውን ጥቅሞች ላለማጣት መሃል ላይ ሊቆም ይችላል ሲሉ አቶ ቹቹ ያስረዳሉ::

ውህደቱ ከአዴፓ አንፃር

ኢህአዴግ በጨቋኝ እና በተጨቋኝነት የፖለቲካ ትርክት መሰረቱን ሲጥል የአማራን ህዝብ በገዥ መደብ ስም አግልሏል:: በማግለሉም የኢኮኖሚ ድቀት (Economic genocide) ደርሶበታል የሚሉት አቶ አያና አማራ በብሔራዊ ማንነቱ ቁሞ የደረሰበትን የሰብዓዊ፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ መገለል ማስታረቅ አለበትም ይላሉ::

አቶ ቹቹም በአቶ አያናው ሀሳብ ተስማምተው አማራ በሀገራዊ ፓርቲ የማይፈቱ አጀንዳዎች ስላሉት ከውህደቱ ይልቅ አቃፊ እና ዓላማ ተኮር ብሔርተኝነት ያስፈልገዋል ይላሉ:: ጎባጣው ከተቃና እና ሀገራዊ ፍትሃዊነቱ ከነገሰ ግን ውህደቱ ለሀገሪቱ ህልውና በጎ ሚናን ይዞ ይመጣል የሚል እምነት አላቸው::

በባለፈው ሳምንት የበኩር ህትመት የአዴፓ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሃንስ ቧያለው ኢህአዴግ በመሰረታዊ አቅጣጫው አንድ ነው ያሉ ሲሆን፤ በግንባሩ ፓርቲዎች መካከል ያለው የሃሳብ ልዩነት የጤነኛ ፖለቲካ መልክ ነው ብለውታል:: ፖለቲካ በሃሳብ ልዩነቶች ዙሪያ የሚደረግ ድርድር እንጂ በሁሉ ነገር መስማማት አይደለምም ሲሉም የወቅታዊውን የኢህአዴግ አሰላለፍ አመላክተዋል::

ለበኩር ጋዜጣ ሃሳባቸውን የሠጡ ሊሂቃን ግን ኢህአዴግ በሰፊ ተቃርኖ ውስጥ የቆመ ግንባር በመሆኑ የውህደቱ ጉዳይ ሊሳካ የማይችል ምኞት አድርገው ይወስዱታል::

በኩር (የሺሀሣብ አበራ) መጋቢት 16 ቀን 2011 ዓ.ም ዕትም

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0