“Our true nationality is mankind.”H.G.

መንዜው ኦሮሞ ጃዋር ሆይ…

By Abebe Gellaw

የዛሬ አስር አመት በካሊፎርኒያ በሚገኘው ስታንፈርድ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ክህሎቴን ለማዳበር የሚያስችል እድል አግኝቼ ዩኒቨርሲቲውን ተቀላቅዬ ነበር። ዩኒቨርሲውን ከተቀላቀልኩ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ አንድ ከዚያ በፊት ስሙን ሰምቼው የማላውቀው የዩኒቨርሲቲው ተማሪ እንኳን ደስ አለህ ሲመችህ ብንገናኝ ደስ ይለኛል የሚል መልእክት ያዘለ ኢሜይል ላከልኝ።

በወቅቱ ጋዜጠኛም አክቲቪስትም ስለነበርኩ ልምዴንም ሃሳብም ለመለዋወጥ ችግር ስላልነበረኝ ለመልእክቱ አመስግኜ በጥቂት ቀናት ውስጥ መገናኝት እንደምንችል በመግለጽ መልስ ሰጠሁት።

ይህ ተማሪ ጃዋር ሲራጅ መሃመድ (Jawar Mohammed) ይባላል። ቀጠሮ ይዘን የዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ትገኝ በነበረች አንድ ካፌ ተገናኘን። ማንነቱን አስተዋውቆኝ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ አስተያየት መስጠት እንደጀመረ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኝ መሆኑን ለመረዳት ጊዜ አልፈጀብኝም።

በትክክል ካስታውስኩ በእናቱ በኩል #የመንዝ_አማራ በአባትቱ በኩል የአርሲ ሙስሊም ኦሮሞ መሆኑን የነገረኝ ጃዋር ስታንፈርድ የደረሰው በልጅነቱ የገጠመውን በርካታ ማህበራዊ ችግሮችን ተቋቁሞ ነበር። ጃዋር ከራሱ የህይወት ተሞክሮ በመነሳት ቂም መቋጠሩን አልሸሸገም። ከዛም ተነስቶ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ፍትህ እንዲኖር አስተዋጽኦ ለማድረግ መፈለጉ ምንም ችግር አላየሁበትም።

ግንኙነታችን አዳብረን ሌሎች በስታንፈርድ ይሰሩና ይማሩ የነበሩ ጥቂት ኢትዮጵያውያንን በመጨመር ብዙ ክርክርም ምክክርም አድርገናል። እንደውም የኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ቀውስ መንስኤ የመደማመጥ እና የመነጋገር ባህል አለመኖሩ ነው በሚል መግባባት አንድ Stanford Ethiopian Forum የሚባል ትርፋማ ያልሆነ ድርጅት መስርተን ነበር።

ጃዋር ጥሩ አክቲቪስት እንደሚወጣው ጥርጥር አልነበረኝም። ግን በወቅቱ ደጋግሜ እሞግተው የበረው ከዘር ፖለቲካ አዙሪት ወጣ ያለ አመለካከት እንዲኖረው መታገልም ያለበት ዘር ቆጥሮ ሳይሆን ለሁሉም ጭቁን ኢትዮጵያውያን መሆን እንደሚገባው ነበር። በእኔ እምነት የኢትዮጵያውያን የጋራ ችግሮች ሳይፈቱ የየትኛውም ብሄረሰብ ችግር በተናጠል ሊፈታ አይችልም። በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በዘረኝነት የተበከለ በመሆኑ የዘር ፖለቲካ ጡዘት መፍትሄ ሳይሆን ቀውስና ግጭት በማባባስ አገራችንን ወደ እልቂትና መበታተን እንደሚወራት ለሚያስተውል ግልጽ ነው።

ዛሬ ጃዋር በስፋት እንዲታወቅና ተጽኖ ፈጣሪ እንዲሆን #ኢሳትን ጨምሮ ብዙዎች እረድተውታል። ይሁንና ጃዋር ያገኘውን አጋጣሚ የሚጠቀመው ሚድያን ጭምር በመጠቀም የዘር ፖለቲካን ለማጦዝ መሆን አይገባውም። መቼም ከዘር ፖለቲካ ጀርባ ጥላቻና ዘረኝነት መኖሩን መካድ ከባድ ነው። አውቀንም ይሁን ሳናውቅ ጥላቻና ዘረኝነትን ማስፋፋት የታሪክ ተወቃሸ እንደሚያደርገን ጥርጥር የለውም።

በአለም ላይ እጅግ ከባዱና እውቀትና ጥበብ የሚጠይቀው ነገር በህዝቦች መካከል እርቅ፣ ሰላም፣ መግባባት፣ ፍቅር፣ አንድነትና መከባበር መፍጠር ነው። በስሜት ነዶ ስሜት መቆስቆስ ቅላል ነው። በዘር ስሜት ግሎ ግጭትና ቁርሾ ማቀጣጠል እውቀት አይፈልግም።

ጃዋርና ሌሎች የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች ሰከን ማለት ይገባቸዋል። ህዝብ ስጋት ውስጥ እየገባ የተጀመረው ለውጥም ጥራጥሬ ውስጥ እንዲገባ አሉታዊ አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉ የዘር ፖለቲካ ግለሰቦችም ይሁኑ መንግስት አደብ ማስገዛት ካልቻለ ተመልሰን አዘቅት ውስጥ መግባታችን አይቀሬ ነው።

#መንዜው_ኦሮሞ ጃዋር ሆይ! ከስሜታዊነት ወጣ ብለህ አስተውል። #መለስ_ዜናዊ በእናቱ በኩል ኤርትራዊ በአባቱ በኩል የትግራይ ተወላጅ ሆኖ በሁለቱም ህዝቦች በኩል የነበረውን ተሰሚነቱን ተጠቅሞ ማቀራረብና ወደ አንድነት መምራቱን ትቶ ወደ መለያየትና እልቂት መራን። በዚህም ለዘላለም በታሪክ ይወቀሳል።

አንተም ከአማራ እና ከኦሮሞ ህዝብ አብራክ መገኘትህን ባለመዘንጋት ሁለቱን ህዝቦች ከማራራቅና ከማናቆር ይልቅ የበለጠ ለማግባባትና አንድ ለማድረግ ብትተጋ መልካም ስራ ሰርተህ ከታሪክ ተወቃሽነት ትድናለህ።

እውቀትህን፣ ችሎታህን እንዲሁን ተጽእኖ ፈጣሪነትህን ለበጎ ተጠቀምበት። አለማችን ብዙ ቆሻሻ ታሪክ እንዳላት በመገንዘብም ታሪክን ለመማሪያ እንጂ ለቁርሾ መቀስቀሻነትና ህዝብን ለማለያየት ከመጠቀም እንቆጠብ።

ኢትዮጵያ የጭቁኖችና የድሆች አገር ናት። ጭቆናን ለመታገልም ዘር ሳንቆጥር ለተበደሉና ለተጨቆኑ ምስኪን ወገኖቻችን ሁሉ በጋራ እንቁም። አገራችንም ለሁኩም ዜጎቿ ፍትሃዊ እንድትሆን በቅንነት እንታገል። በልሂቃን ፖለቲካ ጦስ ድሃ አይፈናቀል ምስኪን አይገደል፣ የጋራ ቤታችን የሆነች አገራችንን እንዳትፈርስ እንጠንቀቅ።

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0