የደጀና ኬሚካል ኢንዱስትሪ ግንባታን በሚያዚያ ወር 2012 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ። ኢንዱስትሪው በትግራይ ክልል ከመቐለ ከተማ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እየተገነባ ሲሆን፥ ግንባታው አሁን ላይ 50 ከመቶ መድረሱ ነው የተመለከተው።
የደጀና ኬሚካል ኢንዱስትሪ ግንባታ በዋናነት በቻይናው ሲኢሲ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን(CEC) ነው እየተከናወነ ያለው። በሲቭል ምህንድስናና አማካሪነት ስራም የህንድ ተቋም እየተሳተፈ ሲሆን፥ አጠቃላይ ግንባታው 7 ቢሊየን ብር ወጪ እንደሚደረግበት ተነግሯል።
የኬሚካል ኢንዱስትሪው ግንባታው ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር ላይምስቶን፣ ጨውና ሌሎች ጥሬ ዕቃዎችን በመጠቀም የተለያዩ ኬሚካሎችን ያመርታል።
በዚህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት፣ ተዛማጅ ፋብሪካዎች እንዲቋቋሙ በማድረግና ለ10 ሺህ ሰራተኞች በቀጥታና በተዘዋዋሪ የስራ ዕድል በመፍጠር ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ተነግሯል።
በተጨማሪም ከተለያዩ ሀገራት የገበያ ትስስር በመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማረጋገጥ ያለው ፋይዳም ከፍተኛ ነው ተብሏል።
ከዚህ ባለፈም በኬሚካልና ኬሚካል ኢንጅነሪግ በተለያዩ የሀገሪቱ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ለሚማሩ ተማሪዎች ተግባራዊ የእውቀት ሽግግር በማድረግ አቅማቸው እንዲገነባ እንደሚያግዝ ነው የትእምት ፅህፈት ቤት አስታውቋል።
FBC