የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ ድርሻው የጎላ በመሆኑ መንግስታዊ ማህበረሰብ (poltical community) ሆኗል::ይህን የዳበረ የስነ መንግስት ታሪክ ያለውን ህዝብ የሚመራው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ከሚመራው ህዝብ ታሪክ እና ስነልቦናዊ ስሪት ጋር በተቃርኖ እየተጓዘ ለሃያ ሰባት ዓመታት ያህል ተጉዟል:: ይህም የአማራን ህዝብ ባለው እና በነበረው አቅም ልክ ለሀገሩ የሚያደርገውን በጎ አስተዋጽኦ ገትቶታል ይላሉ የፖለቲካ ምሁራን::

አዴፓ እና ጉዞው

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር እና የማህበረሰባዊ ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ቴዎድሮስ ኃይለማርያም እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ያለችው በቅፅበት ከሰላማዊ ድባብ ወደ ብሔራዊ ምስቅልቅልና ቀውስ ሊለወጥ በሚችልበት ሁኔታ ውስጥ ነው:: ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ መስዋዕትነት ከአንድ ጨቋኝ፣ ዘረኛ፣ ሌባና አረመኔ አገዛዝ ቢገላገሉም ወደ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትህና እኩልነት የሚወስደው ጎዳና የመግባታቸው ነገር ግን እያደር አጠራጣሪ እየሆነ ይመስላል::

በአንድ በኩል አዲሱ አገዛዝ የተለመዱትን የአምባገነንነትና የዘረኝነት ምልክቶች እያሳየ ነው:: በሀገሪቱ ውስጥ ህግና ሥርዓትን የማስከበርና ለዜጎች ደህንነት ዋስትና የመስጠት ብቃቱ ሊሻሻል አልቻለም:: በሌላ በኩል ለውጡ ጥቅማቸውን የነካባቸው በየክልሉ የመሸጉ የቀድሞው ስርዓት አቀንቃኞች ጡንቻቸውን አፈርጥመው ተቀምጠዋል:: ቢቻል የቀድሞ ክብርና ጥቅማቸውን ለመመለስ ፣ ባይሆን ደግሞ በዝርፊያና በሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይጠየቁ በማህበረሰቦች መካከል ጥርጣሬና ጥላቻ እየነዙ ለደም መፋሰስ እንዲሰለፉ ደፋ ቀና ይላሉ::

ይህ ከሆነ ዘንዳ አዴፓ በሀገር አማን እንደሚያደርገው በኢህአዴግ ስም የሚላክ ግልባጭ ተቀባይ መሆን የለበትም:: የወቅቱን አደገኛነት የዋጀ፣ ለማንኛውም ነገር ዝግጁ የሚያደርግ ዕቅድ መንደፍ አለበት:: የአማራን ህዝብና መላ ኢትዮጵያን ከጥፋት የሚታደግ መጪ እጣ ፈንታውንም የሚወስን ሁለገብ ዝግጅት ያስፈልገዋል:: “ድርጅቱ” ይላሉ ፕሮፌሰሩ ‹‹ከመማማልና ከእመነኝ ልመንህ ፖለቲካ በአስቸኳይ መውጣት፤ ከዳተኝነት የሚመጣውን አደጋ በውል ተረድቶ በአጭር ጊዜ፣ በመጠነኛ ዋጋ ትርጉም ያለው ውስጣዊ ማስተካከያ ማድረግ ፤ በዚህ ረገድ ማመንታት ሊያስበላው የሚችል መሆኑን መገንዘብ አለበት›› ይላሉ:: አዴፓ የአባቶቹን አሸናፊነት መንፈስ ካልመለሰ ፤ የበከተ ርዕዮታዊ ፣ መዋቅራዊና ሥነልቦናዊ መሰረቱን በሥርነቀልነት ካልቀየረ አሸናፊ ሊሆን አይችልም ሲሉም ደክተር ቴዎድሮስ ሃሳባቸውን ይደመድማሉ::

አዴፓ እና ድርጅታዊ አቋሙ

ዶክተር ቴዎድሮስ፤ አዴፓ አብዮታዊ ዴሞክራ፣ ልማታዊ መንግሥት፣ ምንትሴ የሚባሉትን ውዥንብሮች ወዲያ ጥሎ፣ ራሱን ከባርነት ነፃ አውጥቶና መቅለስለሱን ትቶ በግልፅ የአማራ ወገንተኝነት ማሳየት ለቀጠሮ የማያቀርበው ጉዳዩ መሆን እንዳለበት ያሰምራሉ:: የአማራውን ህዝባዊ አንድነትና ጥቅም የሚያስጠብቅ፣ መላውን የአማራን ህዝብ ከተጋረጠበት የህልውና አደጋ የሚታደግ፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ ስብራቱን የሚጠግን፣ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ውስጥ በእኩልነት መኖሩን የሚያረጋግጥ ስራ በመሥራት ላለፈ ሃጢአቱ ንስሃ መግባት ይኖርበታል::

በአማራው እንባ የሰከሩ ደም መጣጮችን፣ ቅጥረኞችን ያለማመንታት ከመዋቅሩ ጠራርጎ በማስወገድ፣ በአዳዲስና ለህዝባቸው ቀናኢ በሆኑ አመራሮች መተካትም ያስፈልገዋል:: በድርጅቱ መካከለኛና የበታች አመራር ውስጥ እየተጠናከረ የመጣውን የአማራ ተቆርቋሪነት መንፈስ በማጎልበት ወደላይ ማምጣት አለበት::

አጠቃላይ አማራዊ ኃይሎችን፣ ቡድኖችንና የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም በየደረጃው የአማራውን ህዝብ፣ የአማራን ፖለቲካ ኃይሎች ፣ የአማራን ምሁራንና የአማራን ዲያስፖራ ከጎኑ ለማሰለፍ ግልፅ ፖሊሲዎችንና ስልቶችን ነድፎ መንቀሳቀስ ከአዴፓ ወቅታዊ ቁመና የሚጠበቁ አበይት ጉዳዮች ተርታ ያሥቀምጣሉ::

የአማራው ህዝብ

ትዕግስቱና ሆደ ሰፊነቱ ለመገፋት የዳረገው የአማራ ህዝብ በብሔርተኝነት መንፈስ እንደ ቋያ እሳት እየተንቀለቀለ መሆኑ ዓይን ላለው ሁሉ በግልፅ ይታያል:: በቅርቡ የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን እንዳሉት አዴፓ የአማራን ህዝብ ወርድና ቁመት የሚመጥን ፖለቲካ መጫወት ታሪካዊ ግዴታው ነው:: ዶክተር ቴዎድሮስም አዴፓ ‹‹በክልልም፣ ከክልል ውጭም፣ በባህር ማዶም መላውን አማራና አብረው በአንድ ታዛ ስር የሚኖሩትን የአማራ ቤተሰቦች በእኩል ዓይን በመመልከት ከጎኑ ለማሰለፍ መጣር አለበት››ይላሉ::

Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

ለዚህም የአማራው ህዝብ የተጋረጠበት የዴሞክራሲ ፣ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን በግልፅ አምኖ መቀበል ይኖርበታል:: በተለይም ደግሞ የተከዜና የዓባይ ምላሽ ግዛቶች ፣ የሸዋና የአዲስ አበባ ጉዳይ፣ እንዲሁም ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውጭ የሚኖሩ ብዙ ሚሊዮን አማሮች እጣ ፈንታ የአማራ ብሔርተኝነት አዕማዶች መሆናቸውን ተቀብሎ ያለማመንታት መታገል አለበት:: እነዚህን አንጋፋ ቁምነገሮች እንደ ተራ የህገ መንግሥት ጥያቄ ማየት ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ነው ሲሉ ፕሮፌሰሩ ሀሳባቸውን ያሥቀምጣሉ::

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር መምህር የሆኑት አቶ ጥሩነህ አበበ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማዘዣ ጣቢያው ሸዋ እና አካባቢው አዲስ አበባ በመሆኑ አዴፓ የከተማን ፖለቲካ ሊሸሸው ሳይሆን ሊቀርበው ይገባል ይላሉ:: የፖለቲካ ስብራቱ የሚጠገነው በከተማ ፖለቲካ ነው የሚሉት አቶ ጥሩነህ አዴፓ የአዲስ አበባን ጉዳይ በቸልታ እንዳይመለከተውም ሲሉ ያሳስባሉ::

ዶክተር ቴዎድሮስ ‹‹የአማራን ህዝብ ባለፉት 27 ዓመታት በትጋት የተሰራበት ህልውናውን የማጥፋት ዘመቻ እንዲሁም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነልቦናዊ ቁስሎች በዘላቂነት የሚያድን ስልት መንደፍ አለበት›› ብለው ያምናሉ:: የአማራ ክልል በትምህርት ፣ በጤና ፣ በመሰረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪ በየትኛውም ሰብዓዊ ልማት መለኪያ የአገሪቱ ጭራ ከመሆን ፤ በህፃናት መቀንጨር ፣ በወላድ እናቶች ሞትና በመሳሰሉት ወሳኝ የህልውና መስፈርቶች ደግሞ ከፊት መሪነት የሚድንበትን የልማትና የእድገት መንገድ ቀይሶ መንቀሳቀስ የአዴፓ ፍኖተ ፖለቲካ አድርገውም ይወስዳሉ::

ለዚህም የመላውን አማራ ህዝብ በተለይም የወጣቱን ኃይልና የምሁሩን ክፍል የማያወላውል ድጋፍ ማግኘት የግድ ነው:: ባሁኑ ወቅት የድርጅቱ አዲስ አመራር የተያያዘው ህዝብን የማወያየት ተግባር ከአማራ ህዝብ ጋር ቃሉን ከማደስ አንፃር ተገቢ ነው:: ነገር ግን ይህ ተነሳሽነት እንደወትሮው በክልል ጉሮኖው ከተገደበና በመላው የሀገሪቱና የዓለማችን ክፍሎች የሚኖሩ አማሮችን ካላካተተ ጎደሎ ይሆናል ይላሉ ዶክተሩ::

አቶ ጥሩነህም አዴፓ ከአዳራሽ ስብሰባ ወደ ተቋም እና ስራዓት ግንባታ ሳይረፍድ መግባት አለበትም ይላሉ:: ስብሰባ ማብዛት ከሞቅታ ፖለቲካ ስለማያወጣ አዴፓ ከፖለቲካ አሳቢያን ጋር ሆኖ መዝኖ መስራት ተገቢ ነውም ይላሉ::

የአማራው ምሁር

የአማራው ህዝብ ታላቅ ሀብቱና ጥንካሬው የተማረ የሰው ኃይሉ ነው:: ለብሔሩ ታሪካዊና ወቅታዊ ጠላቶች ቀንደኛ የጥቃት ዒላማም ይህ የህብረተሰብ ክፍል ነው:: ምፀታዊነቱ ግን ይላሉ ዶክተሩ ‹‹ አማራ ቀለም ሞልቶ በፈሰሰበት፣ የቅኔና የፍልስፍና ምድር ቢሆንም አዴፓ የሚታማው ግን በቀለም አጠርነት መሆኑ ነው›› ይላሉ::

የቀድሞው ብአዴን/ኢህአዴግ ከምሁሩ መደብ ጋር በቋጠረው ደመኝነት የተነሳ፣ አገልጋይ ሲያሻው ብቻ እየመለመለ ያሰማራል እንጂ ከአማራ ምሁራን ጋር ከልብ ተመካክሮ ሰርቶ አያውቅም:: እንዲያውም የአማራ ምሁራን የኢህአዴግ መንግሥት ዋነኛ ዒላማዎች ሲሆኑ ፣ በውኃ ቀጠነ ከየስራቸው ሲባረሩ ፣ በኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተመድበው እንዳያገለግሉ ሲገለሉ፣ በእኩልነት ተወዳድረው የሚኖሩበት ፍትህ ሲነፈጋቸው፣ በየስብሰባው ስምና ታርጋ እየተለጠፈላቸው ሲወገዙ፣ በአጠቃላይ ከጨዋታ ውጭ እንዲሆኑና አንገታቸውን እንዲደፉ ሲዘመትባቸው ብአዴን በፊታውራሪነት ተሳትፏል:: ስለዚህም ከዚህ የህብረተሰብ ክፍል ጋር አይተማመንም :: ከናካቴው የሚግባባበት የጋራ ቋንቋ እንኳን የለውም ብለው ያምናሉ::

አዴፓ ምሁር ጠልነት ትልቅ ድክመቱ መሆኑን ተረድቶ በአስቸኳይ መቀየር አለበት:: በምሁራኑ ላይ ያለው አካሄድ የግብር ይውጣ አካሄድ መላቀቅ አለበት፡ በጎጠኞች ተንኮልና የማዳከም ዘመቻ ያኮረፈውን ፣ ሀገርና ህዝብ የማዳን ሚናውን ለመቀበል “የእናቴ መቀነት…” የሚለውን የአማራ ምሁር መደብ የሚያነቃቃበትና የሚያሰልፍበትን መላ መፍጠር አለበት:: ምሁሩን የህብረተሰብ ክፍል በፖለቲካ አመራርነትም በአማካሪነትም በተለያዩ ሙያዊ ጉዳዮች በቅንነት በመሳብና በማሳተፍ የሚታይበትን እውቀት አጠርነት መድፈን ለነገ የማይባል ተግባር ነው ሲሉ ግለ ምልከታቸውን ያቀርባሉ::

የአማራ ፖለቲካ ተፎካካሪዎች

Related stories   አስከሬን እንዲለቀም ታዘዘ - ትህነግ የአጽም ፖለትካ ድራማ ይፋ ሆነ

ዶክተር ቴዎድሮስ ‹‹የአማራ ህዝብ በህልውናው ላይ አደጋ ተጋርጦበታል ካልን ፣ ይህን በአስተማማኝነት ሊቀለብስ የሚችለው በተናጠል ሳይሆን በአንድነት ሲቆም ነው›› ብለው ያስባሉ:: የአማራ ፖለቲካ ተፎካካሪዎች እንደ ፖለቲካዊ እምነታቸውና አመለካከታቸው ለአማራው ህዝብ ጥቅም በጋራ የሚሰሩበት መንገድ መፈለግ ለነገ የማይባል ሃላፊነት ነው::

በተለይ በአሁኑ ወቅት እንደ ቋያ እሳት የተንቀለቀለው የአማራ ብሄርተኝነት ፍቅርና አመኔታ የሰጣቸውን እንደ አብን ያሉ ድርጅቶች አቅፎና ደግፎ መስራት አዴፓን ያስከብረዋል፤ ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳውም:: ሀገራዊው የብሄር ፖለቲካ ሥርዓት በህይወት እስካለ ድረስ ለአማራው ጥቅምና ልዕልና በሥልጣን ላይ ያለውን አገዛዝ የሚፎካከሩና የሚያተጉ ቡድኖች ያስፈልጋሉ:: አማራው ከእንግዲህም ታሪኩን፣ ባህሉን ፣ ቋንቋውንና ማንነቱን እንዳይረሳ አዴፓ እንዳመችነቱ በክልሉ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ኃይሎች ጋር በጋራ ለመስራት በቅንነት በሩን ክፍት ማድረግ አለበት::

የአማራ ዲያስፖራ

ባለንበት ዘመን የዲያስፖራውን እምቅ አቅም ችላ የሚል ፖለቲካ የትም አይደርስም:: በተለይ አዴፓና የአማራው የፖለቲካ ድርጅቶች በዚህ ረገድ ገና ያልተነካ ሥራ ይጠብቃቸዋል:: ለአብነት ባለፈው ሰሞን የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ በአንድ ቀን ለጌድኦ ተፈናቃዮች የሰበሰበውን ከሚሊዮን የሚበልጥ ዶላርና በአንፃሩ ለአማራ ክልል ተፈናቃዮች ተብሎ የተከፈተው የእርዳታ ገንዘብ ማሰባሰቢያ “ጎ ፈንድ ሚ “ ከወራት በኋላ ያስገኘውን ገቢ ማነፃፀር ትልቅ ትምህርት ሊሰጥ ይችላል::

በባህር ማዶ የሚኖረው አማራ በኢትዮጵያዊነቱና በአማራነቱ፣ በአማራነቱና በአውራጃዊነቱ መካከል የተፈጠረበትን ውዥንብር የሚያጠራ ሰፊና ጠንካራ ዘመቻ ያስፈልጋል:: ይህ ማለት ግን በውጭ አገር እንደ አሸን የፈሉት የአማራ ድርጅቶችም የብሔረሰቡ አውራጃዊ የታሪክ ቅርስ ነጸብራቆች በመሆናቸው እንደ ድክመት ሊታይ አይገባም:: በዲያስፓራው ላይ የሚሰራው የቅስቀሳ ስራም እነዚህን ብዝሃነቶች ወደ አንድ ድርጅት ለመጨፍለቅ የታለመ መሆን የለበትም:: በመጀመሪያ ወሳኙ ነገር በጋራ የአማራነት ዓላማ ስር መተማመንና መተባበር የሚፈጠርበትንና የሚጎለብትበትን መንገዶች መፈለግ ነው::

ሀገራዊ ኃይሎች እና አዴፓ

ዶክተሩ ቴዎድርስ ‹‹አዴፓ ከራሱ ድርጅታዊ፣ ክልላዊና ህዝባዊ ምህዳር ውጭ ከሀገራዊው የፖለቲካ ሁኔታና ከሌሎች እህት ድርጅቶችና የፖለቲካ ኃይሎች አንፃር ያለውን ግንኙነትም በሥር ነቀልነት ገምግሞ መለወጥ አለበት ›› ሲሉ በቀዳሚነት ያሥቀምጣሉ::

አዴፓ ፈራ ተባ እያለ እንዳመነው ‹‹አማራው ባልተወከለበት ህገ መንግሥት የመገዛት ግዴታ የለበትም:: ይህ ከሀገራዊና ክልላዊ ኃይሎች ጋር ያለውን ግንኙነት የሚፈትንበት አንዱ ቁልፍ ጉዳይ ነው::›› ሲሉ ዶክተሩ ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ::

አዴፓ በተለይ የመሃል ሀገሩን ፖለቲካ ለጉልበተኛ እየተወ ማፈግፈጉ ያስከፈለውን ዋጋ ተገንዝቦ ማረም አለበት:: ለዚህም የአማራ ብሔርተኝነት ሀገሪቱ የተሰራችበት ስሌት ማዕከል መሆኑንና አዴፓም አማራውን በመምራት ለሌሎች ኢትዮጵያውያን መከታ ሊሆን የሚችልበት ታሪካዊ እድልና ኃላፊነት ተፈጥሮለታል:: አማራውን ማዳከም የአማራው ጉዳት ብቻ ያለመሆኑን እውነታ ለአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የተገለጠበት ዘመን ተከስቷል::

የአማራው ፖለቲካ እና ቀለሙ

የአማራ ብሔርተኝነት ፖለቲካ አማራን መምሰል አለበት:: በአማራው ታሪካዊ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብት ላይ የተማከለ ባህላዊ፣ ሥነልቦናዊና መልከዓ ምድራዊ ብዝሃነቱን ታሳቢ ያደረገ የፖለቲካ ፍልስፍናና መርሃ ግብር ያስፈልገዋል::

በአማራነትና በኢትዮጵያዊነት መካከል ያለውን ተፈጥራዊ ሚዛን የወቅቱን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የሚያስጠብቅ የሀገር አንድነቱን ፣ የግፉአን ጠበቃነቱን የሚያረጋግጥ መሆን አለበት::

ለአማራውም ህዝብ ለኢትዮጵያም ህልውና ሲባል የአማራው ተፈጥሯዊ ባህርይ የሆነውን የደቡቡንና የሰሜኑን አደጋዎችና እድሎች ተንትኖ አማካይ የፖለቲካ መፍትሔ የሚያቀርብ መሆን አለበት::

በአሁኑ ወቅት የአማራው ፖለቲካ በማይመለስ ሁኔታ ወደ ጠንካራ ህዝባዊ ንቅናቄነት መለወጡን በቅጡ የተገነዘበ፤ በዚህ ላይ ተመርኩዞ በየፈርጁ የማደራጀት ፣ የማንቃትና የተፅእኖ ፈጣሪነት ሂደቱን የሚያጠናክር ሰፊና ጥልቅ ውስጣዊ አንድነትና የመናበብ መንፈስ የተላበሰ መሆን አለበት::

የአማራ ህዝብ የተጋረጡበትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍታት የሚችለው በሰላማዊ ትግል በየደረጃው መሆኑን የሚያምን፣ ግን ደግሞ በማናቸውም መንገድ የብሔሩን ጥቅምና ልዕልና ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆን አለበት:: ስለዚህ ይላሉ ዶክተሩ ‹‹አማራው በመጀመሪያ ራሱን እያለ እንደሌለ ከመቆጠርና ከምስለኔ ግዛት አላቅቆ በሁለት እግሩ መቆም አለበት::›› አማራው ለህልውናው ሲል አኩሪ ማንነቱን ማስጨበጥና በራሱ መተማመኑን መመለስ ይደር የማይባል ተግባር ነው:: በፌዴራላዊው ሥርዓት ውስጥ በእኩልነት የመደራደር አቅም መፍጠር አለበት::

Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

የአማራው ብሔርተኝነት ገና በቅጡ ጥርት ብሎ አልተቀመረ ይሆናል:: “ነገር ግን” ይላሉ ዶክተሩ ጥያቄውን ፣ ጠላቱን ፣ ፍላጎቱንና ግቡን በውል ለይቷል:: በማህበረሰቡ ውስጥ የተሰራበትን ትልቅ የመከፋፈል፣ የማዋከብና ተስፋ የማስቆረጥ ገደል ተራምዷል:: ከሁሉም በላይ አንድ ልብና መንፈስ ሆኗል:: በዚህ ላይ አማራው የተደራጀና ሥርዓት ገብ ማህበረሰብ በመሆኑ ርዕዮቱን በወጉ የሚያስጨብጠውና የሚመራው ካገኘ ለመከተል ዝግጁ ነው::

አቶ ጥሩነህ ደግሞ የአማራ ክፍለ ግዛታዊ አሃዶች በአካባቢያዊ ማንነቶች ታጥረው የአማራ ፖለቲካ ስንጥቅ እንዳይገጥመው የአማራ ብሔርተኝነትን ወደ ሳይንሳዊ ትግበራ መቀየር ያሻል ይላሉ:: ይህ ተተግባሪ እንዲሆን ደግሞ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስሪት የሚረዱ የአማራ ሊሂቃን ማቅረብ ተገቢ ነው ይላሉ::

‹‹የአማራ ልሂቃን ይህንን ሰፊ ህዝባዊ መናበብና መነሳሳት በጥበብና በአስተዋይነት ወደ ጠንካራ ንቅናቄ መቀየርና ከዳር ማድረስ ታሪካዊ አደራ አለባቸው›› የሚሉት ዶክተር ቴዎድሮስ ናቸው:: የህዝባቸውን ውስጣዊ ጥንካሬውንና ተግዳሮቱን ውጫዊ የኃይል አሰላለፍን በማጤን መሬት የያዘ የትግል ስልት መንደፍ አለባቸው:: ለዚህ ደግሞ የብሔርተኝነት አንቀሳቃሽና መሪ የሆነው ልሂቃዊ መደብ አይነ ጥላውን ገፍፎ መነሳቱ በተለይ በወጣቱ ምሁር ውስጥ የሚታየው የቁርጠኝነት መንፈስ እጅግ ተስፋ ሰጭ ነው:: መንገዱ አልጋ ባልጋ ነው ማለት ግን አይደለም::

የአማራው ትግል ሊገጥሙት ከሚችሉ ፈተናዎች መካከል ቀንደኛው መንግሥታዊ ሥርዓቱ ነው:: በጣምራ የችግሩ ምንጮች የሆኑት ክልላዊና ፌዴራላዊ አገዛዞች ለአማራው ጥያቄ የሚሰጡት ምላሽ የአማራ ብሄርተኝነትን ባህሪና አቅጣጫ በከፊል ይወስነዋል:: እነዚህ መንግሥታዊ አካላት የህዝቡን ብሶት በቅጡ አዳምጠው በአፋጣኝና በቅንነት የሚመልሱ ከሆነ ፣ ምናልባት የራሳቸውን ህዝብ በሂደት ሊያቀርቡ የሚችሉበት እድል ይኖራል::

ነገር ግን ይላሉ ተመራማሪው በሥልጣን ላይ ካሉት ከአዴፓም ሆነ ከራሱ ከኢህአዴግ ታሪክ ከተነሳን፣ መሰረታዊ ለውጥ መጠበቅ የዋህነት ይመስለኛል:: ገና ከወዲሁ እንደተለመደው ብሔረሰቡን የማዋከብ ፣ የመከፋፈል ፣ ከሌሎች ወንድሞቹ ለመነጠል ግጭትና አመፅን የማራገብ ምልክቶች እያየን ነው:: የፌዴራሉና የክልሉ መንግሥታት በአፋኝነት፣ በብልጣብልጥነትና አግላይነት እንቀጥላለን:: የአማራውን ፅኑና ውስብስብ ችግሮች እንደተለመደው በትዕዛዝ መፍትሔዎች እንመልሳለን ብለው መግደርደራቸው የማይቀር ይመስላል::

በአጭሩ አዴፓም ሆነ ኢህአዴግ ባሉበት አቋማቸው የችግሩ እንጂ የመፍትሔው አካል መሆን አይችሉም:: ስለዚህም የአማራ ብሔርተኝነት ቀበቶውን ሳያላላ የችግሮቹ ዋና ምንጭ የሆነውን ሥርዓት ከሥሩ ማድረቅን የመጨረሻው ግብ ማድረግ አለበት::

በዚህም የአማራው ትግል አንድ ጎዳና ብቻ ሊከተል አይችልም:: ከአማራው ተፈጥሮ ጋር የሚስማማው ብዝሃነትን ጥንካሬ የማድረግ ስልት ይመስለኛል:: አሁን እንደሚታየው በግልፅ የአማራ ፓርቲ በማቋቋም ወይም በብዝሃዊ ድርጅቶች ስር ተሰልፎ መታገል ይችላል:: መንግሥታዊ ባልሆኑ የተፅእኖ ቡድኖች ፣ በባህላዊ የአደረጃጀት ሥርዓቶችና ተቋማት አማካኝነትም ትግሉ መፋፋም አለበት::

የአማራው ተግዳሮቶች እጅግ ሥር ሰደዶች ስለሆኑ ድል በቀላል ዋጋ ሊገኝ አይችልም:: የጊዜ፣ ጉልበት፣ አእምሮ፣ ሀብትና ህይወትንም መስዋእትነቶችን ያስከፍላል:: ለሁሉም በሁሉም ነገር መዘጋጀት ያስፈልጋል:: ካለፉት 27 ዓመታት ተመክሮ መዘንጋት የማይገባው ቁምነገር ያንድ ወገን ፍላጎትና ድል ዘላቂ ሰላም አለማስገኘቱ ነው:: ስለዚህም የአማራው ብሔርተኝነት ለአፍታም ቢሆን ትልቁን ሀገራዊ ስዕል ኢትዮጵያዊነቱን ከማየት ሊዘናጋ አይገባም:: ይህ ደግሞ አማራው በመላ ታሪኩ የኖረለትም የሞተለትም ጉዳይ ስለሆነ አዲስ እንግዳ አይሆንበትም::

በኩር መጋቢት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ዕትም

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *