“Our true nationality is mankind.”H.G.

ለዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ – ከተገረመ አድማጭ

ይህ ጽሁፍ ህወሃት ተሸንፎ ስልጣን አልለቀቀም ይላል። ቴዎድሮስ ጸጋዬ ከናዚ ፕሮፖጋንዳ ጋር ተያይዞ መነቀፉን ይቃወማል። ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ በሚሌኒየም አዳራሽ ላቀረቡት ጽሁፍ በግርድፍ የተላከ የትችት ብዕር ነው። ሙሉው የሚከተለው ነው።

ዶር. ዮሃንስ አበራ አየለ – አይጋ ፎረም

በጆርጅ ኦርዌል ዝነኛ መፅሃፍ፣ “በአኒማል ፋርም”፣ ውስጥ ቦክሰር የሚባል አንድ ቅን ገፀባህሪይ አለ። ይህ ገፀባህርይ የለውጥ መሪዎቹ ምን ያህል መስመር ቢስቱና ለራሳቸው ፍላጎት መገዛት ቢጀምሩ ከሌሎች ሁሉ ተለይቶ “መሪዎቻችን ሁልጊዜ ልክ ናቸው” እያለ ሲከላከልላቸው የኖረ ነው። ይህ ገፀባህርይ ግን ለመሪዎቹ እንደ ጥሩ ወዳጅ መቆጠር የለበትም፣ ባላንጣ እንጂ። ለምን ቢባል በጎ ያልሆነውን ጎንህን ደብቆ መልካምነትህን ብቻ የሚነግርህ፣ ጥፋትህን ካንተ አንስቶ ሌላው ላይ እያላከከ የሚያዘናጋህ ሰው ይወደኛል ብለህ ማሰብ ጅልነት ነው። ልጆቻችንን የምንገርፋቸው ስለምንጠላቸው አይደለም። መጥፎ መስመር መያዝ ሲጀምሩ ጉዳት እንዳይደርስባቸውና ወላጅንም እንዳያሳዝኑ ነው። ለወላጅ ከልጆቹ በላይ ማን አለው?

ዶር. በድሉ በቋንቋ ሳይንስ ሞያዎ የታወቁና የተደነቁ መሆንዎን አውቃለሁ። እኔም ከአድናቂዎችዎ አንዱ ነኝ። የፓለቲካ አቋም ይዞ መንቀሳቀስ መብቶ ነው፤ የፓለቲካን ውስንስብ ባህርይ እየተገነዘቡ መሆን አለበት እንጂ። “ፓለቲካ የማይተዋወቁ ሰዎችን አንድ አልጋ ላይ ያስተኛል” ይባላል በእንግሊዝኛ ተረት። ይህ ማለት የአስተሳሰብና የአመለካከት ልዩነት በፓለቲካ አለም ባህርያዊ ነው። አፈና የሚመጣው ፓለቲካ ልዩነትን ማስተናገድ አቅቶት ተዳክሞ ሲወድቅ ነው። ፓለቲካ ከሆነ አፈና የለም፣ አፈና ካለ ፓለቲካ አይኖርም። ምክንያቱም የፓለቲካ ትርጉም የሃሳብ ልዩነትን ያለ ኩርፊያ ማስተናገድ ማለት ስለሆነ ነው።

ዶር. በድሉ በአንድ ሳምንት ውስጥ በሁለት ነገር ሲያኮርፉ፣ አኩርፈውም በዛ አስደናቂ የቋንቋ ችሎታዎ የተናገሯቸው ቃላት ለአድማጭ ምቾት የማይሰጡ ናቸው። በፓለቲካ አለም ታማኝነታችን መሆን ያለበት ለሃሳብ እንጂ ለግለሰቦች አይደለም። አፄ ሃይለስላሴ የሚማርክ ገፅታ ነበራቸው። ያያቸው ሰው መቸም እሳቸውን አለመውደድ አይችልም። ስድስት ኪሎ ውስጥ ሆኜ “ንጉሱ ይውረዱ” እያልኩ መፈክር ሳሰማ ኖሬ በቀለ ጢሞ እየመራቸው በማርቸዲስ ጃንሜዳ መንገድ ላይ አይን ለአይን ስንገጣጠም ሰላምታ ተለዋውጠናል። እኔም ደስ እንዳለኝ ትዝ ይለኛል። መንግስቱስ ቢሆን ቆፍጣና፣ አይነ ግስላ ነበር። በሰውነቱ ለምን ይጠላል? የሚያሳምም የፓለቲካ ተቃውሞ ስልት ያገኙ የመሰላቸው አንዳንድ ቀውጢዎች መለስ ዜናዊን አንዴ የእንሰሳ ሌላ ጊዜ የጭራቅ ምስል ጋር እያገናኙ በየሚድያዉ ይለጥፉ ነበር። ይህ ወንዝ የማያሻግር ተራ ነገር ነው። መለስ አጠረ ረዘመ፣ ፋንጋ ሆነ ቆንጆ የፓለቲካ ትርጉም የለውም፤ አስተሳሰብ እንጂ።አሁንም ቢሆን በ”ቲም ለማ” የግል ጥላቻ ያለው ካለ ከፓለቲካ አሁኑኑ ይውጣ። ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን መሆናቸውን የዘነጋ ያለ አልመሰለኝም። ኦቦ ለማ መገርሳና ዶር አብይ አህመድ እኮ አንደበተ ርቱዕ የሆኑና ቁመናቸው ያማረ ሊጠሉ የማይገባቸው ወንድሞቻችን ናቸው። የሚተቻቸው ሁሉ በግል ስለሚጠላቸው አይደለም፤ የበለጠ የሚያስጭንቀው የሃገር ጉዳይ ስላለ እንጂ።

Videos From Around The World

“ቲም ለማ” ከህወሓት በላቀ እኔ ኢትዮጵያን ወደፊት አራምዳታለሁ፣ ሰላሟን በተሻለ መንገድ አስከብራለሁ፣ ካዝናዋንም የማንም እጅ ዘው እንዳይልበት አደርጋለሁ ሲሉ እርሶ ብቻ አይደሉም የህወሓት ጭፍራ ብለው ሊመድቡኝ የሚችሉት እኔ ራሴም ደግፌ ነበር። የምንደግፈው ወይንም የምንነቅፈው፣ ሌላው እንዲደግፍ የምንገፋፋውና የሚቃወመውን የምንኮንነው በግል “ወገኔ ነው” በማለት ብቻ ከሆነ እኔ ከጨዋታው መውጣት እገደዳለሁ። እነ ዶር. አብይ ስልጣን ሲጨብጡ የደገፍኩት የኢትዮጵያ ህዝብ ያለው የላቀ ሰላምና ልማት የማግኘት ጉጉቱ እውን ይሆናል ብየ እንጂ ህወሃት አመራር ላይ ያሉት እኮ የወንዜ ልጆች፣ የክፍል ጓደኞቼ፣ አንዳንዱም የግል ጓደኞቼ የነበሩ ናቸው። አሁንም ፊትም እወዳቸዋለሁ።

ዶር. በድሉ ግን ከ”መስመሮች መካከል” ንግግሮን ሳነብ የተገነዘብኩት በህወሓት አመራሮች ላይ የፓለቲካ ሳይሆን የግል ጥላቻ እንዳለብዎት ነው። ማንም ይሁን ማንም፣ መንግስቱ ሃይለማርያምም ቢሆን፣ ህወሓትን ከአራት ኪሎ “ያባረረለዎትን” አቅፈው ደግፈው ከጥቃት ለመከላከል ቆርጠው እንደተነሱ ተገንዝቤአለሁ። ስለዚህ “ቲም ለማ” ህወሓት ተመልሳ አራት ኪሎ እንዳትገባ ለማድረግ የሚችል ብቸኛው ቡድን ነው ብለው የደመደሙ ይመስለኛል። እያገለገሉ ያሉት ራሶን እንጂ ቲሙን አይደለም። ቲሙን ከልብ ከወደዱት ማድረግ ያለብዎት ህዝብ ፊት ከህወሓት የተሻለ መሆኑን በተግባር እንዲያረጋግጥ መርዳት ነው። ይህም እውን የሚሆነው ምንም ቢመረው ቲሙ ራሱን ለትችት አጋልጦ በመስጠትና ከትችቱ ትምህርት አግኝቶ ራሱን በማሻሻል ነው። እንዲሁ በጣፋጭ ንግግርና ተቺን ዝም በማሰኘት ከሆነማ ከህወሓት የሚወዳደር አለ እንዴ? ህወሓት እኮ የወረደችው ስራ ሳትሰራ ቀርታ አይደለም። አለም በሚያውቀው ብዙ ድንቅ ስራ ሰርታለች። ችግሯ አላስተነፍስ ማለትዋ ነበር፤ የሚተቻችን ሁሉ ሽብርተኛ በማለቷ ነበር። ሽብርተኛ አልነበረም ማለት አይደለም፤ በማናለብኝነት ሽብርተኛውን ከሰላማዊ ተቃዋሚ ጋር ስላደበላለቀችው ነው። ለዚህም ነው “ቲም ለማ” ሁሉንም አንድ ላይ ፈቶ በመልቀቁ መከራውን እያየ ያለው።

እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ህወሓትም መልሳ ወደ ስልጣን የማትመጣበት ምንም ምክንያት የለም። ጀሮዎን ሆን ብለው ስላራቁት ነው እንጂ ህዝቡ እኮ “ህወሓት ከዚህ የከፋ ስራ ሰርታ ነበር እንዴ?” እያለ መጠየቅ ጀምሯል። በአለም ላይ እኮ ክፉ ናቸው ተብለው ከስልጣን የወረዱ መሪዎች አዲስ ከመጣው በኣንፃራዊነት የተሻሉ ሆነው ሲገኙ ወደስልጣን የተመለሱ አሉ።ህዝብ የሚፈልገው ብሄሩን ሳይሆን አስተዳደሩን ነው። ይህ ነገር ባይበዛ ጥሩ ነው። ትግራዮች እኮ ጥንታዊ ኢትዮጵያውያን እንጂ ባእድ አይደሉም። እንኳንና ኢትዮጵያዊ ሆኖ ፔሩ የጃፓን ትውልድ ባለው ፉጂሞሪ፣ ታላቋ አሜሪካም የኬንያ ትውልድ ባለው ኦባማ ተመርተዋል።

እንግዴህ አሁን ያለው ሁኔታና ህወሓት በነበረችበት ጊዜ የነበረው ሁኔታ በራሶ አይን ሳይሆን በህዝብ አይን ቢያዩት ኖሮ ጓደኞችዎን ለመውቀስ የመጀመሪው ይሆኑ ነበር እንጂ ንዴትዎን አንዴ “ራስ ወዳድ፣ ግድ የለሽ፣ ማህበራዊ እሴቱ የተበላሸ” ባሉት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተማሪዎ ስለነበረ አሁንም ሊቆነጥጡት የሚችሉ ሆኖ በተሰማዎ በቴድሮስ ፀጋየ ላይ አይደፉም ነበር። ህዝብ “በቲም ለማ” አመራር እየተጨነቀና አንዳንድ ግለሰቦችም ትችት እየፃፉ ያሉት በህወሓት ዘመን እንደዋዛ የታየው ሰላም በመጥፋቱና ስጋት በመስፈኑ ነው። ስጋቱ የሰፈነውም ለውጡን በማምጣት ግንባር ቀደም ከነበረው የህብረተሰብ ክፍል በመሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሓትን ከስልጣን እንዳስወገደ ተናግረዋል። ይህ እውነት ከሆነ ለምን ይህን ያደረገውን ህዝብ እንደማመስገን የለውጥ በአል ሊያከብሩ ማይክ በጨበጡበት ሚሊኒየም አዳራሽ ውስጥ ሆነው የኢትዮጵያን ህዝብ ሲያብጠለጥሉ የዋሉት። እርሶም እኛም እናውቀዋለን፤ ህወሓት በህዝብ ሃይል ከስልጣን አልወረደችም። ደርግም ቢሆን በህወሓት ጦር ሃይል እንጂ የወደቀው በህዝብ ግፊት አልነበረም። ግብታዊ በሆነ ህዝባዊ አመፅ የወረደ መንግስት ቢኖር የንጉሡ ስርአት ነው። ደርግ ከህዝብ ቀምቶ ስልጣን ያዘ እንጂ ለውጥ አላመጣም። የአሁኑ መሪዎችም ወደ ስልጣን እንዴት እንደወጡ ብዙ ስለተፃፈ አልደጋግመውም።

ቴድሮስ ፀጋይ የናዚ ፕሮፓጋንዳ አስፋፍቶ ከሆነ ተው የሚለው ወይንም እርምጃ የሚወስድበት ፓሊስና አቃቤ ህግ እንጂ እርሶ ሊሆኑ አይገባም። “ቴድሮስ ፕሮፓጋንዳህን አቁም” ያሉበት ቪድዮ ስመለከት ተስፋ ቆረጥኩ። በዚች አገር እንደየአቋማችን ተከራክረን ስንጨርስ አብረን ሻይ የምንጠጣበት እድል አይኖርም ማለት ነው? የተለያየ አመለካከት በሰላማዊ መንገድ ስናራምድ ጠላቶች እንሆንና “ዝም፣ ጭጭ በል” ነው የምንባባለው? እኔን ያሳዘነኝ ከ”ቴዎድሮስ አፍን ያዝ” በተጨማሪ ዶር. በድሉ የቴዎድሮስን ሰብእና አለማክበራቸው ነው። “እናትህ የምትንቅህ ራቁትህን ስላየችህ ነው” የሚባል የትግርኛ ተረት አለ። ሰላሳ አመት በከፍተኛ ትምህርት አስተምሬአለሁ፤ አንድም ቀን ቢሆን ተማሪዎቼ ከኔ እንዲበልጡ እንጂ ከኔ ያነሱ እንዲሆኑ ተመኝቼ አላውቅም። አስተማሪ ከሱ የሚበልጡና በነፃነት ማሰብ የሚችሉ ተማሪዎች አስተምሮ ካላስመረቀ አገር ወደኋላ እንጂ ወደ ፊት መሄድ አትችልም። ቴድሮስ ተማሪ እያለ ከቃልዎ የማይወጣ “ጥሩ” ልጅ ነበረ። ይህ ማለት ከርሶ እንዲያንስ አድርገው ነበር ያስተማሩት፣ ነፃ እንዲወጣ አልረዱትም ማለት ነው። ትክክለኛ ትምህርት ነፃነት ነው! ቴድሮስ ግን በትምህርቶ ሳይሆን ራሱ በራሱ ተፍጨርጭሮ ነፃነት አገኘ። ይህ ስላልተዋጠልዎት ባደባባይ የአስተማሪነት ሃላፊነትዎን እንዳልተወጡ የሚያሳብቅ መልእክት አስተላለፉ። እኔ ቴድሮስ ምን እያለ እንደሆነ አልሰማሁም። መስማትም የለብኝም። ሰውን ግደሉ፣ አቁስሉ፣ ዝረፉ፣ ቤት አቃጥሉ፣ መንገድ ዝጉ፣ ህዝብ አፈናቅሉ፣ እስካላለ ድረስ ሌላው ሁሉ መብቱ ነው ብየ ስለማስብ ነው ይህን ፅሁፍ ያዘጋጀሁት።

ይህ አስተሳሰብን የማገድ ድርጊት የፕሮፌሰር መስፍንንና የአቶ ተስፋየ ሸዋየን ውዝግብ ያስታውሰኛል። የቋንቋ ሰው ሆነው የባህል ሚኒስትር ከነበሩበት የደርግ መንግስት ወደ ስድስት ኪሎ ተመልሰው አስተማሪ ሲሆኑ ደርግ እንዲሁ አልተዋቸውም። የዩኒቨርሲቲው የፓለቲካ ሃላፊ አደረጋቸው። ከእለታት ባንዱ ቀን “ጠይቅ” በተባለው የመምህራን ማህበር መፅሄት አንድ መጣጥፍ ያሳትማሉ፤ “የሃሳብ ቁጥጥር” የሚል። ገና ፅሁፉ ብዙ አንባቢ ሳያገኘው ግቢ ውስጥ የተሰራጨው በስራ ላይ በነበሩት በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የተፃፈ ትችት ነበር። ፕሮፌሰሩ በተፈጥሯቸው ማንም አስተሳሰባቸውን እንዲቆጣጠር የማይፈቅዱ ስለሆኑ የፃፉት ፅሁፍ የከረረ ከመሆኑ የተነሳ አቶ ተስፋየንና የፓለቲካ ስርአቱን የሚያስቆጣ ሆነ። ጡረታ የወጡትም ከዛ በኋላ ነበረና ከፅሁፋቸው ጋር ይገናኝ አይገናኝ የማውቀው ነገር የለም። ዋናው ለማለት የፈለግሁት ቁምነገር የዲሞክራቲክ አስተሳሰብ ምሶሶ የአስተሳሰብ ልዩነትን የሚሸከም ደልዳላ ጀርባ ነው።

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0