“Our true nationality is mankind.”H.G.

… የጥላቻ ንግግር በህግ ይገድብ ይሆን?

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በማህበረሰቡ ዘንድ መጠራጠርና ፍራቻ ነግሶ የሰው ልጅ በአደባባይ የተሰቀለበት፣ ለምርምር የወጡ የዩኒቨርስቲ ምሁራን ተወግረው የተገደሉበትና እንዲሁም ሌሎች ለመስማት የሚሰቀጥጡ ዜናዎች የተሰሙበትና በአገሪቱም ላይ ጠባሳን ትቶ አልፏል።

በተለያዩ በይነ መረቦችና ማህበራዊ ገፆችም ላይ የተለያዩ ማህበረሰቦችን ለጥቃት የሚያነሳሱ፣ የግድያንና የመፈናቀልን የሚቀሰቅሱ መልዕክቶች በተለያዩ ጊዜያት ይስተዋላሉ።

በዚህ ደግሞ ተራ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ማህበረሰቡን የሚመሩ የመብት አራማጆች ማህበረሰቡን እርስ በርስ በማጋጨት በመወቀስ ላይ ናቸው።

የአንዳንድ የመንግሥት ኅላፊዎችም ንግግር ከአውድ ውጭ እየተወሰደ በተፈጠረው መከፋፈል ላይ ቤንዚን በእሳት ላይ እንደ ማርከፍከፍ ሆኖ ለአንዳንድ ጥላቻዎችና መፈራቀቆች መቀጣጠል ምክንያት ሆኗል።

ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መልሶች በሙሉ ጥላቻንና ጥቃትን ምላሽ ያደረጉና ሃይ ባይ ያጡ መልዕክቶች ለፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት እንዳይሆኑ ያሰጋል።

በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ግድያ፣ ጦርነት፣ ዘር ማጥፋት እንደተለመደ ነገር ተደርጎ መቀስቀሱ ቀጥሏል።

በዚህም ምክንያት ሀገሪቷ ውስጥ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ተፈናቅለዋል፤ በርካቶች ለሞት ሲዳረጉ እንዲሁም ለብዙዎች በስጋት ውስጥ ለመኖር ምክንያት ሆኗል።

የተለያዩ ሰብአዊ መብት ድርጅቶችና እንዲሁም የጠቅላይ አቃቤ ህግ ጥናት እንደሚያሳየው ለዚህ ሁሉ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የጥላቻ ንግግር እንደሆነ ያሳያል።

ይሄንንም በጄ ለማለት ከሰሞኑ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ረቂቅ አዋጅ ወጥቷል።

ረቂቅ ህጉ ምን ይዟል?

ረቂቅ አዋጁ የጥላቻ ንግግር ትርጉም ብሎ የሰጠውም ሆን ብሎ የሌላ ግለሰብን፣ የተወሰነ ቡድንን ወይም ማህበረሰብን ብሄርን፣ ሃይማኖትን፣ ቀለምን፣ ፆታን አካል ጉዳኝነትን ዜግነትን፣ ስደተኝነትን፣ ቋንቋን፣ ውጪያዊ ገፅታን መሰረት በማድረግ ሆነ ብሎ እኩይ አድርጎ የሚስል የሚያንኳስስ፣ የሚያስፈራራ፣ መድልዎ እንዲፈፀም፣ ወይም ጥቃት እንዲፈፀም የሚያነሳሳ ጥላቻ አዘል መልእክቶችን በመናገር፣ ፅሁፍ በመፃፍ፤ በኪነጥበብ እና እደ ጥበብ፣ የድምፅ ቅጂ ወይም ቪዲዮ፣ መልእክቶችን ብሮድካስት ማድረግ ወይም በማህበራዊ ሚዲያ ማሰራጨትን ይመለከታል።

ከዚህም በተጨማሪ ረቂቅ ህጉ የሀሰት መረጃን በተመለከተም የፍሬ ነገር ወይም አንኳር ይዘቱ ውሸት መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው፤ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ግልፅ በሆነ መልኩ ከፍ ያለ መረጃን ሆን ብሎ በማንኛውም መንገድ ማሰራጨትና ለህዝብ እንዲደርስ ማድረግ እንደሚገባ አስቀምጧል ።

እነዚህን ተግባራት የጣሰ ሰው በህጉ በተቀመጠው አግባብ መሰረትም በእስራትና በገንዘብ መዋጮ እንደሚቀጣ አስቀምጧል።

ምንም እንኳን የጥላቻ ንግግር አደገኛነት ሳይታለም የተፈታ ነው ቢባልም መፍትሄው አዲስ ህግ ማውጣት ነው ወይ ለሚለው ብዙዎች የራሳቸውን ጥርጣሬ ያስቀምጣሉ።

Related stories   ‹‹የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠነክራል››

አዲስ ህግ ያስፈልግ ይሆን?

በተለይም ህግ አውጭውና፣ ህግ አስፈፃሚው ወይም የፍትህ ሰጪ መዋቅራት ነፃ ባልሆኑበት መንገድ እንዲህ አይነት አዲስ ህግ ማስተዋወቅ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚበልጥ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነትን የሚመለከተውን አንቀፅ 19ን ከመፈረም በተጨማሪ ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብትን አስመልክቶ አንቀፅ 29 በህገ መንግሥቱ ተካቷል።

እንደ አንቀፅ 29 ከሆነ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በፅሁፍ ወይም በህትመት፤ በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ ሀሳብ የመሰብሰብ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን የሚያካትት ነው።

በዚሁ አንቀፅ ላይ ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ ቅስቀሳዎችን እንዲሁም ሀሳብን የመግለፅ ነፃነትም አንዱን ከአንዱ በማጋጨት ሌሎችንም ሰዎች አደጋ ላይ የሚጥል ሆኖ ከተገኘ በህግ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል በግልፅ አስቀምጧል።

ይሄን ህግ ማስከበር እንዲሁም ማሻሻል እየተቻለ ለምን አዲስ ህግ ማውጣት አስፈለገ? የህግ ባለሙያውና ጋዜጠኛ አቶ አብዱ አሊ ሒጂራ ጥያቄ ነው።

” አንቀፅ 29 የጥላቻ ንግግር ባይለውም ፕሮፓጋንዳን ሰውን ማንኳሰስን፤ ለዘር ማጥፋት የሚያነሳሳን ‘በለው በለኝና ላሳጣው መድረሻ’ የሚልን ነገር አልታገስም ይላል። የህጎቹ መሰረት የተደላደለ ቢኖረንና ያሉትን ህጎች ህይወት የሚሰጥ ፍርድ ቤት ቢኖረን እንኳን ለራሳችን ለሌላ በተረፍን ነበር።” ይላሉ።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዝናቡ ቱኒ በበኩላቸው ይህ ህግ የተረቀቀው በዘፈቀደ ሳይሆን አገሪቷ ያለችበትን ውጥንቅጥ ምክንያት መሰረት በማድረግ ጥልቅ ጥናት ከተደረገ በኋላ ነው የወጣው ይላሉ።

የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ለሀገሪቱ ሰላምና አንድነት ጠንቅ ነው የሚሉት አቶ ዝናቡ “የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን ተከትሎ በርካታ የሃገራችን ዜጎች እየተፈናቀሉ ነው፤ በርካታ ንብረት ወድሟል፤ ህይወትም ጠፍቷል። ይሄ መከላከልም ይጠይቃል። ” ይላሉ

ከዚህም በመነሳት ከዚህ በፊት የነበሩት ህጎች የወንጀል ጉዳይን የሚያመላክት ስላልነበር የዚህን ረቂቅ ህግ አስፈላጊነት አበክረው ይናገራሉ።

አቶ አብዱ በዚህ አይስማሙም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ህግ በቂ ነው ባይ ናቸው።

የጥላቻ ንግግርImage copyrightALAMY

“ካወቅንበት አሁን ያለው ህግ ይበቃናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ችግር አዲስ መፍትሄ ማምጣት አያስፈልገንም።” ይላሉ

የጥላቻ ንግግር ረቂቁ ህጉ ነፃነትን ይገድብ ይሆን?

ምንም እንኳን በሀገሪቷ የሰፈነውን የጥላቻ ንግግር አስፈሪነት አቶ አብዱ ባይክዱትም ይሄንን የሚከላከል ህግ ለማውጣት በምታደርጋቸው ጥረቶች ኢትዮጵያ በዘርፉ የተሳካላት ሆና እንደማታውቅ አጥብቀው ይከራከራሉ።

Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

እንደ ምሳሌነትም የሚያነሱትም ብዙዎችን ለእስር የዳረገውና፤ ብዙ ጋዜጠኞችንም የመናገርም ሆነ የመፃፍ ነፃነታቸውን ሸብቦ ያሸማቀቀውን የፀረ ሽብር ህጉን ነው።

“የፀረ ሽብር ህጉ ቦርቃቃ ነው፤ ለትርጉም የሚመች ነው” የሚሉት አቶ አብዱ የጥላቻ ንግግሩም ለትርጉም ክፍት የሆነና አደገኛም እንደሆነ ነው።

“የፈለገው ፖሊስ ወይም አቃቤ ህግ ጋዜጣ አንስቶ ይሄማ የጥላቻ ንግግር ነው ቢል ፍርድ ቤት ‘እልል’ ብሎ የሚቀበልበት ሁኔታ ነው ያለው” ይላሉ

በተለይም የፀረ ሽብር ህጉ ፕሬሱን የማጥቂያ መንገድ አድርገው የሚወስዱት ባለሙያዎችም የፀረ ሽብር ህግ ከመውጣቱ በፊት አሸባሪነትን የሚከላከል ህግ ቢኖርም አጠቃላይ ሂደቱ ሚዲያን ዝም የማሰኘት ነበር ባይ ናቸው።

“ሽብር ማለት እኔን የጠላ ሁሉ አሸባሪ ነው የሚል ትርጉም ተሰጥቶት፤ አንድ ቦታ ላይ ያለ ሰው ድንገት ሊቆጣ ይችል ይሆናል፤ ሌላው ሰው እንዲህ ይተረጉምብኝ ይሆን እንዴ ብሎ እስከመሸማቀቅ በሚል ነፃነትን የገደበ፤ ፕሬሱንም ያሸማቀቀ ነው” ይላሉ የሕግ ባለሙያው አብዱ።

የጥላቻ ንግግር ህግ ወጣም አልወጣም ማንኛውም የንግግር ነፃነት ገደብ እንዳለው የሚናገሩት አቶ አብዱ ከኢትዮጵያ ልምድ በመነሳትም “ገደብ ይጣልበታል ሲባል ገደቡ ገደብ የሌለው ይመስላቸዋል” ይላሉ

ለአቶ አብዱ ዋነኛው አስጊ ነገር የንግግር ነፃነትን የሚገድብ መሆኑ ነው። የንግግር ነፃነት የተፈጠረው ሰውን ለማወደስ ብቻ ሳይሆን ለማስቀየምም ወይም ለማስደንገጥ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ አብዱ ኢትዮጵያ በጣሊያን በተወረረችበት ጊዜም ሞሶሎኒ ለዘላለም ይኑር፤ ጣልያን ጥሩ ናት የሚሉ ንግግሮች እንደነበሩ አስታውሰው

“ሞሶሎኒ ለዘላለም መኖር የለበትም፤ ሞሶሎኒ ፋሽስት ነው ለማለት ነው የንግግር ነፃነት የሚገባው። የንግግር ነፃነት ሰው ሊያስቀይም ይችላል ይህ ግን አደጋ እንዳያስከትል ይሄንን ከህግ ይልቅ በወግ በባህል ነው ልንገነባው የምንችለው።” ይላሉ

አቶ ዝናቡ በበኩላቸው የተወሰኑ ግለሰቦችንም ሆነ የተወሰነ ህብረተሰብን ክፍል ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ለመገደብ ታስቦ የተዘጋጀ ምንም መነሻ መሰረት የሌለውና ከፀረ ሽብር ህጉ ምንም እንደማይገናኝ ይናገራሉ።

“ይህ ረቂቅ ህግ ዜጎች ሰብአዊ ክብራቸው እንዲጠበቅ የዜጎች አብሮ በመኖር፣ በእኩልነት፣ በአንድነት፣ በሰላማቸው ላይ አደጋ እያመጣ ያለውን ነገር እንዲጠብቅ የሚያስችል አቅም ያለው ነውም” ይላሉ።

አቶ አብዱ ግን በተለይም የህግ አውጭ፣ ተርጓሚውና አስፈፃሚዎች ነፃ ባልሆኑበትና “ለይተው የማያውቁትን ህግ ማስታጠቅ ማለት ትክክል አይደለም፤ ህግ የሚያወጡ አካሎቻችን ሁሉ አንካሶች ናቸው። ህግ የማውጣትም፤ ህግ የማስፈፀምም ህመምተኞች ነን፤ መጀመሪያ ከሱ መፅዳት ያስፈልጋል” ብለዋል።

Related stories   በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን በቁጥጥር ስር ዋለ- ትህነግ “ክብሪት” የተባለ ገዳይ ቡድን ማቋቋሙ ታወቀ፣

የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማወያየት የተለያዩ ግብአቶችን በመሰብሰብ ላይ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ዝናቡ በሰከነ መልኩ በደንብ ግብአት ተወስዶ እንደሚፀድቅ ይናገራሉ።

የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ጠንቅ እንደሆነ በመረዳትም የሌሎች ሃገራትን መነሻ አድርገው ህጉ እንደተረቀቀ አቶ ዝናቡ ይናገራሉ።

ምንም እንኳን የጥላቻ ረቂቅ ህጉ መነሻ የተወሰደው ከተለያዩ ሃገራት ስለሆነ ጥሩ ነው የሚል መከራከሪያ ቢያቀርቡም አቶ አብዱ በበኩላቸው “አፋኝ ተብሎ የሚጠራውም የፀረ ሽብር ህጉ የተወሰደው ከእንግሊዝ ነው” ይላሉ።

መፍትሄ

ለአቶ አብዱ ከህግ በላይ ዋነኛው መፍትሄ ንግግር ነው ይላሉ።

“ጋዜጠኞች፣ የመብት አራማጆች ነፃነቱ የሚጠይቀውን ኃላፊነትና ጨዋነት ሊኖራቸው ይገባል። ዝም ብሎ አፍ አመጣ ተብሎ አፍ ያመጣው ነገር አይነገርም። ስንናገር የምንናገረው ነገር ምን ተጨማሪ እሴት አለው መባል አለበት ይላሉ።

በከፍተኛ ሁኔታ ማህበረሰብ በተፈራቀቀበት ሁኔታ ዋነኛው ነገር ህዝብን ማቀራረብ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ አብዱ መከባበርና መቻቻል ባህል ከሆነ በኋላ ህግ ማውጣት እንደማያስፈልግም አፅንኦት ሰጥተው ይሞግታሉ።

“ጨዋነት የሚፈጠረው ህግ በማውጣት አይደለም። ማክበር፣ መከባበርና መቻቻል ባህል ከሆነ በኋላ ህግ ማውጣት አያስፈልግም። ወደ ህግ የሚኬደው እኮ ሌሎች ማህበራዊ ተቋማት ሲከሽፉ ነው” ብለዋል

አቶ ዝናቡ በበኩላቸው የጥላቻ ንግግርንም ሆነ ሀሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨት በህግ ብቻ የሚገታ ሳይሆን ህዝቡ ያሉትን መልካም የጋራ እሴቶች ማዳበርና ከዚህ ባሻገር ሲሆን የህግ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ ይናገራሉ።

የኦፕራይድ መስራች፤ የቀድሞ የአሜሪካ አልጀዚራ ኤዲተር መሀመድ አዴሞ በበኩሉ ዲሞክራሲ ሂደት እንደመሆኑ መጠን ሁሉ ነገር በአንድ ምሽት እንደማይመጣ ይናገራል። ያለውን የዲሞክራሲ ሂደት ለማስቀጠል የጥላቻ ንግግር ህግ ሊበጅለት እንደሚገባ የሚየያስረዳው አቶ መሀመድ ሁሉን የሚያስማማና ሁሉም የኔ የሚለውና ተቀባይነት ያለው ህግ ማውጣት አስፈላጊ መሆኑን ያሰምርበታል።

“ሁሉንም ነገር ለመንግሥት መተው ግን ተገቢ አይደለም። መንግሥት ሁሉን አካታቶ፣ ረቂቁ ላይም የሲቪል ማህበራቱ፣ ጦማርያን፣ ጋዜጠኞችና የህግ ባለሙያዎች ቢወያዩ መንግሥት እንደ ጨቋኝ መሳሪያ እንዳይጠቀምበት መመልከት ያስፈልጋል” ይላል።

ይህም ሁኔታ ህጉን የመንግሥት ብቻ ነው ብሎ ከመግፋት እንደሚታደገውና የሁላችንም ነው የሚል ስሜት እንዲኖረው እንደሚያደርግ ይናገራል።

Read the original story here – BBC Amharic

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0