……ከትላንት በስቲያ ሰኞ ቀኔ ጎዶሎ ነበር። ወደፊት ለሚጀመር አንድ የሬዲዮ ፕሮግራም አንዳንድ ቀረፃዎችን ሳከናውን አምሽቼ ሰአቱ ገፋ ብሎ ነበር። ከአንድ ጓደኛዬ ጋር በላዳ ታክሲ መጣንና የእሱ ቤት ሩቅ ስለነበር ታክሲው መርካቶ አካባቢ ሲደርስ ለእሱ አዝኜ እንዲመለሱ በመንገር በአመዴ ገበያ በኩል ወደላይ በእግሬ ማዝገም ጀመርኩ። አንዳንዴ በደንብ የምታውቁት አካባቢ የሚሰማችሁ የደህንነት ስሜት አለ አይደል? ከታች ከምዕራብ ጀምሮ ያሉ የሱቅ እና የድርጅት ጥበቃዎችን፤ የመንገድ ላይ ሻይ ነጋዴዎችን፤ መኪና የሚጠብቁ ወጣቶችን፤ ሽቀጦችን የሚሸጡ ጀብሎዎች፤ ጎዳና ተዳዳሪዎችን እና አልፎ አልፎም መንገድ ላይ ገበያ የሚጠብቁ ምስኪን ሴተኛ-አዳሪዎችን ሳይቀር ስለምግባባ በሆነ አጋጣሚ ሳመሽ ያን ያህል የፍርሃት ስሜት አይሰማኝም….. የሚሸኙኝም ህፃናት ብዙ ናቸው ። ግን ከላይ የቀን ጎዶሎ ያልኳችሁ በሕይወታችን የሚገጥሙን ነገሮችን በራሳችን ኃይል የመወሰን ብቃቱ የለንም። ትላንት ያላጋጠመን ነገር ዛሬ አያጋጥመንም ማለት አይደለም።
፨…..እናም ሀገር አማን ነው ብዬ ወደ ሰፈሬ የሚወስደኝ የአውቶብስ ተራን ዋና መንገድ ልቀላቀል 20 ሜትር ያህል ሲቀረኝ ከየት እንደመጡ ህልም የመሰሉኝ ወደ አስር ጎረምሶች እየተጯጯሁ በቅፅበት ከበቡኝ። ምንም አይነት ነገር ማሰብ እስከማልችልበት በግራ መጋባት ተዋጥኩኝ። እጄን ወደላይ አንስቼ <የምትፈልጉትን ውሰዱ ብቻ አትጉዱኝ! ስላቸው አንደኛው ቀድሞ በጨበጣ ድንጋይ ጭንቅላቴን ፈነከተኝ።

ትኩስ ደም በአንገቴ ሲወርድ ይሰማኛል፤ ከዚያ ደረቴን: ጀርባዬን፤ ሆዴን…. ያገኙት ቦታ እየቀጠቀጡ ተረባረቡብኝ። የፈለጉትን እንዲወስዱ ፈቅጄላቸው ለምን ይሄን እንደሚያደርጉ አልገባኝም። አንገቴን ጨምቆ ይዞ አንደኛው መሬት ላይ ሲጥለኝ ሌሎቹ መጀመሪያ ኪሴ ስር ገብተው ሁለት ሞባይል፤ በርካታ ኢንተርቪዎች የያዘ ድምፅ መቅረጫ፤ ፍላሾችን፤ ቻርጀር፤ የተወሰነ ገንዘብ እና ኪሴ ስር የነበሩ የወረቀት ዝርያዎችን አንድም ሳያስቀሩ ወስደው ሳያበቁ….ከትከሻዬ ላይ ያንጠለጥልኩት እና ብዙ ፋይሎች እና ጠቃሚ ሰነዶች የያዘውን ተንጠልጣይ ቦርሳዬን ለመውሰድ ሲታገሉ እሱን ለማዳን ተፍጨረጨርኩ። ግን ከወደኩበት በእግራቸው እየጨፈለቁና ከአስባልት ላይ እያጋጩ ጭንቅላቴን አደነዘዙት። ከዚህ በኋላ አልቻልኩም….ቦርሳውን ለቅቄ ተዘረርኩ፤ ልጆቹ ምንም የፈሩት ነገር የለም። ተነስቼ ምንም ነገር ብሞክርና ብከተላቸው አንገቴን እንደሚቀነጥሱት በያዙት ረጅም ሳንጃ አስጠነቀቁኝ።

ጉዳዩ የደፈጣ ዝርፊያ ሳይሆን ገሃድ የሆነ የቡድን ዝርፊያ ነበር። መንገድ ላይ ያገኙትን ሁሉ እየጠራረጉና እየዘረፉ ነበር የመጡት። እንደሌላው መደበኛ ዘራፊ ሳይሆን የተፈቀደ ህጋዊ ስራ የሚሰሩ ይመስሉ ነበር። ከእኔ በኋላም ሌላ መንገደኛ ፍለጋ በፉከራ እያሰሱ በኩራት ወደ መርካቶ ወረዱ። ተነስቼ ደሜን እየጠረኩኝ እና ራሴን አረጋግቼ ቁጭ ባልኩበት ከደቂቃዎች በኋላ የተወሰኑ ፖሊሶች ከሌሎች የተዘረፉ ሰዎች ጋር እየሮጡ መጡ። አንደኛው ቴሌግራም የያዘው ፖሊስ ኃይል እንዲጨመር ንግግር ይዟል። ልጆቹ በተወሰነ ርቀት ላይ ሆነውም ፖሊሶቹን አልፈሯቸውም። ጭራሽ ድንጋይ ይዘው <ልብ ካለህ ተከተለን> እያሉ ለውርወራ ተዘጋጁ። ከፖሊሶቹ አንዱ እየተንቀጠቀጠ ወደ ላይ አይሉት ወደ ታች አንድ ጥይት ተኮሰ። አሁን ልጆቹ ሩጫ ጀመሩ…..

የዚህን ጊዜ ፖሊሶቹ የልብ ልብ ተሰምቷቸው የፍርሃት ጩኽት እየተጯጯሁ <ያዘው! ያዘው!> እያሉ መከተል ያዙ። ፖሊስ ያልያዛቸውን ወንጀለኞች ማን እንደሚይዝላቸው እግዜሩ ይወቀው!!…..እንደምንም ተነስቼ በደመ-ነብስ ከፖሊሶቹ ጋር ተከተልኩኝ። ምናልባት ቦርሳውን እንኳን ቢጥሉት የሚል ተስፋ ነበረኝ። በተነገራቸው የቴሌግራም መልህክት ከየአቅጣጫው የት ተደብቀው እንደቆዩ የማይታወቅ ተረኛ ፖሊሶች እየተቀላቀሉ የልጆቹ የመጨረሻ ማምለጪያ መንገድ የሆነው ተክለሃይማኖት በርበሬ ተራ መግቢያ ዋናው አስባልት ስንደርስ ከየማህዘናቱ የመጡት ፖሊሶች ቁጥር ወደ ሃያ አምስት ይደርስ ነበር። አብዛኞቹ ከሲታ እና ልጅነታቸውን ያልጨረሱ፤ በዚያ ላይ ጭልጥ ካለ እንቅልፍ ነቅተው የሚንቀጠቀጡ ነበሩ።

ፈፅሞ የፖሊስ ተክለ-ቁመና የሌላቸው፤ የመንገዱን መግቢያ መውጪያ የማያውቁና አማርኛ መናገር የሰማይ ያህል የራቃቸው ነበሩ። እኔ የተጎዳሁት እያለው ለእነሱ ከልቤ አዘንኩ። ከስምንት ወንጀለኛ አንዱን መያዝ በልቻለ ፖሊስ ለምትጠበቀው አዲስ አበባ እና ለነዋሪው የወደፊት ደህንነት እያሰብኩ ባዶ ስሜት ታቅፌ ተመለስኩ።

ሰውነቴ በደም ረጥቧል፤ ማዘር እንዲህ ሆኜ ብታየኝ ልቧ በድንጋጤ ቀጥ ይላል። ጓደኛዬ ጋር አድሬ ጠዋት ስገባ ስሜቴ ሁሉ ባዶ ቀፎ ሆኖ ነበር….. በስልኮቼ እና በቦርሳዬ የያዝኳቸው የአመታት ድካሞቼን በምን አይነት ሞራል እመልሳቸው ይሆን? ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ። ነገሩን ለፖሊስ ጣቢያ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ሰጥቼ በዚህ የቀን ጎዶሎ ያልገጠሙኝን የከፋ አደጋዎች በማሰብ ፈጣሪን አመሰገንኩት። በያዙት ሳንጃ ወግተው አካለ ጎዶሎ አድርገውኝ ወይ ወደ ሞት ሸኝተውኝ ቢሆን ኖሮ የሳምንት ዜና ብሆን እንጂ ሌላ ምን እጨምር ነበር? ይሄው እስትንፋሴ በመኖሩ የእናቴን ትኩስ አጃ እየጠጣሁ በተውሶ ስልክ ይሄን መጥፎ የቀን አጋጣሚ አካፈልኳችሁ።
ዕድሜ ወንጀለኛና ህግን ላናናቀው የመደመር ፍልስፍና ይሁንና ገና ፖሊስ እያለ የሌለባት ከተማ ወደፊት የነዋሪዋ ፈታኝ አውድማ ትሆናለች።

እግዚአብሔር ከቀን ጎዶሎ ይጠብቃችሁ….ባላችሁበት ሻሎም።

Habte Tadesse fb

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *