የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ የወንጀል ችሎት በዛሬው ውሎው በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ከተፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 24 ግለሰቦችን ጉዳይ ተመለከተ።
ችሎቱ በዛሬ ውሎው በ5 የተለያዩ መዝገቦች በተለያዩ የመንግስት ተቋማት የስራ ሀላፊዎች የነበሩ የ24 ግለሰቦችን ጉዳይ ተመልክቶ በአራቱ መዝገቦች ውሳኔ አሳልፏል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራከሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን፣ የመድሀኒት ፈንድ እና አቅርቦት ኤጀንሲ እንዲሁም የንብረት ግዥ እና ማስወገድ አገልግሎት ኤጀንሲ የስራ ሀላፊ የነበሩ ግለሰቦች በዛሬው ችሎት ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውስጥም በአራቱ መዝገቦች የቀረቡት እና ከዚህ ቀደም በመርማሪ ፖሊስ እና በጠበቆች ክርክር ተካሂዶባቸው የነበሩት ጉዳዮች ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል።

ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሸን እነ አትክልት ተካልኝ፣ ከመድሀኒት ፈንድ አና አቅርቦት ኤጀንሲ እነ አቶ ሀይለስላሴ ብርሀን የሚገኙበት ሲሆን በአራቱ መዝገቦች የቀረቡት 24 ተጠርጣሪዎች በየተቋሞቻቸው የስራ ሀላፊዎች ሆነው ሲሰሩ በነበሩበት ወቅት በመንግስት ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል በሚል በቁጥጥር ስር ውለዋል።

መርማሪ ፖሊስ ከኢትዮጵያ ኮንስትራከሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የስራ ሀላፊ የነበሩ 10 ግለሰቦች ጋር በተያያዘ 7 የምርመራ መዘገቦችን ለፍርድ ቤቱ ያቀረበ ሲሆን፥ አምስቱ የምርመራ መዝገቦች ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ተያያዥነት ያላቸው መሆኑን አስረድቷል።

Related stories   “ትህነግ ከጁንታነትም ወርዶ በየጫካው ተሹለክላኪ የእህል ሌባ ሆኗል፣ ከያለበት እየታደነ ነው “ሜ/ጀ መሐመድ ተሰማ

ከዚህ ውስጥም ከከሰም የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ከ2003 እስከ 2006 ዓ.ም ተፈፀመ የተባለ ወንጀል፣ ያለ አግባብ ተገዝተው ለጉዳት የተዳረጉ እቃዎችን ግዥ የተመለከተ እና ከአርማታ ብረት ግዥ ጋር የተያያዙ ወንጀሎች ይገኙበታል።

በእነዚህ የምርመራ መዝገቦችም መርማሪ ፖሊስ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን በመጥቀስ፥ ቀሪ የሚባሉ እና ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የሚያስፈልጋቸው እንደ ፎረንሲክ ምርመራ፣ የውስጥ ኦዲት ውጤት እንዲሁም ተጨማሪ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎስን ለማቅረብ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ በእነ አቶ ሀይለስላሴ ቢሆን መዝገብ የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦችን እና በእነ አቶ ተስፋዬ ብርሀኑ የተጠረጠሩ 7 ግለሰቦችን በሚመለከትም ተጨማሪ የመርመራ ጊዜ እንደሚያስፈልገውም ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው የቀረቡት ምክንያቶች ተጨማሪ ጊዜ የማያስፈልጋቸው እና የተጠርጣሪዎቹንም የዋስትና መብት የማይከለክሉ መሆናቸውን በመጥቀስና ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ቀሪ የተባሉትን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን ሊያሸሹ አይችሉም በማለት ጉዳያቸውን ውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

Related stories   የትህነግ "ውሮ ወሸባዬ" - የመንግስት ሩጫ - የሃላኑ የኢትዮጵያን ቋንጃ የመበጠስ የእባብ አካሄድና ባንዳዎች!

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ የተጠረጠሩበት ጉዳይ እስከ 10 አመት ሊያስቀጣ የሚችል እና ተጠርጣሪዎቹ ቢወጡ በመረጃ ማሰባሰብ ስራው ላይ ችግር ሊፈጥሩ እና ማስረጃ ሊያሸሹ ስለሚችሉ የዋስትና መብታቸው ሊፈቅድ አይገባም ሲል ተቃውሟል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱም በአራት መዝገብ የቀረቡ 21 ተጠርጣሪዎች ላይ መርማሪ ፖሊስ ቀሪ ያላቸውን ማስረጃዎች እንዲመረምር እና እንዲያቀርብ 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

በተያያዘም መርማሪ ፖሊስ በአምስተኛ መዘገብ አቶ ይገዙ ዳባን ጨምሮ ሶስት የቀድሞ የግዥ እና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ የስራ ሀላፊ የነበሩ 3 ተጠርጣሪዎች በመንግስት ላይ ከ48 ሚሊየን ዶላር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ለችሎቱ አስረድቷል።

ተጠርጣሪዎቹ በፍጥነት ገበያን ለማረጋጋት ይውል የነበረ እና ለገበያ መቅረብ የነበረበት 400 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴን ለገበያ ማቅረብ ሲገባቸው ያለ አግባብ ጨረታውን ለአራት ጊዜ በማራዘም እና በመሰረዝ በአራቱም ጨረታዎች ላይ ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል የተባለ ኩባንያ እንዲያልፍ በማድረግ በመንግስት ላይ ከፍተኛ የገንዘብ ጉዳት እንዲሁም ስንዴውም በተባለው ጊዜ ተገዝቶ ለገበያ እንዳይውል ማድረጋቸውን ጠቅሷል።

Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

ተጠርጣሪዎቹ በመጀመሪያው ጨረታ ላይ ከ19 ሚሊየን ዶላር በላይ፣ በሁለተኛው ጨረታ ከ17 ሚሊየን ዶላር በላይ፣ በሶስተኛው ጨረታ ላይ ከ4 ሚሊየን ዶላር በላይ እንዲሁም በአራተኛው ጨረታ ላይ ከ3 ሚሊየን ዶላር በላይ ጉዳት አድርሰዋልም ነው ያለው መርማሪ ፖሊስ።

እንዲሁም ስንዴው ከተጓጓዘበት መርከብ ጋር በተያያዘ ከ5 ሚሊየን ዶላር በላይ ያለአግባብ ወጪ እንዲወጣ በማድረግ በአጠቃላይ በመንግስት ላይ ከ48 ሚሊየን ዶላር በላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውም ተመልክቷል።

ከዚህ ባለፈም አሁን በሀገሪቱ ላይ የሚስተዋለው የስንዴ እና የዱቄት እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል ያለው መርማሪ እስካሁንም ከ100 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የሚሆነው ስንዴ አለመግባቱን የሚያመላክት ማስረጃ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

በዚህ መዝገብም ቀሪ ስራዎችን ለመስራት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው ዋስትና እንዲፈቀድላቸው እና ቀሪ ለተባሉ ስራዎችም የተጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ ብዙ በመሆኑና አጭር ቀን እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠ ሲሆን ብይን ለመስጠት ለነገ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በዙፋን ካሳሁን

ፋና ብሮድካስት

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *