“Our true nationality is mankind.”H.G.

ስለሽመልስ አብዲሳ የዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ምስክርነት

የዛሬ ሦስት ሳምንት ገደማ፣ በአሜሪካ በነበረኝ ቆይታ፣ ሜሪላንድ አካባቢ ወደ አንድ ትልቅ የምግብ ማዕከል(Food Court) አምርቼ ነበር፡፡ “ምን ዓይነት ምግብ ልብላ፤” እያልኩ እያሰብኩ፤ ከአንደኛው ረድፍ ወደ አንደኛው ረድፍ በምዘዋወርበት ጊዜ፤ አንዲት በፍልስፍና የተመረቀች ተማሪዬን በሥራ ገበታዋ ላይ አገኘኋት፡፡ ከባለቤቷ እና ከልጇ ጋር እንደመጡ ነገረችኝ፡፡ እኔም አሜሪካን ሀገር ተጋብዤ እንደመጣሁ፣ በቅርብም ወደ ቦስተን ባለቤቴን እና ልጄን ለመጠየቅ እንደምሔድ ነገርኳት፡፡ በመገናኘታችንም ኹለታችንም በጣም ደስ አለን፡፡

ድንገት “ዶ/ር” አለችኝ፤ “ሽመልስ አብዲሳ (የክፍል ጓደኛዋ ስለነበር) የፕሌቶን ሪፓብሊክ፣ በሚገባ አንብቧል፡፡” አለችኝ፡፡ ይኸንንም ስትል፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያለ፣ የPolitical Philosophy ኮርሱን በሚገባ ተከታትሎ ገቢራዊ እንዳደረገው እየጠቆመችኝ ነበር፡፡

እኔም “እከሊት” አልኳትና፣ ”መች ይህ ብቻ፤ የኢትዮጵያን ታሪክ ጠንቅቆ ለመረዳት በእጅጉ የጣረ ሰው ነው፡፡ በተለይም፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የኦሮሞ ታሪክ ህልው መኾን፣ የፈጠረውን ልዩ የታሪክ አንድምታ የተረዳ ሰው ነው፡፡ ይህም ማለት፤ ሽመልስ የኦሮሞን ሕዝብ ትልቅነት እና አኩሪ ታሪክ የተቀበለ እና የሚያውቅ ምሁር ነው፡፡” አልኳት፡፡

ከልጅቱ ጋር ከተነጋገርነው ቁምነገር በተጨማሪ፣ በInstitute of Human Right የድኅረ ምረቃ ተማሪ በነበረበት ጊዜ፤ የመመረቂያ ጽሑፉን፤ በአማካሪነት እና በመምህርነት አብሬው ለኹለት ዓመታት ቆይቻለሁ፡፡ የጥናቱ ትኩረት “በነጻነት እና ሥርዓታዊነት (Liberty and Order) መካከል ያለውን ግንኙነት እና ቅራኔ” በመፈተሸ፤ ከሔግል እስከ አይዛያ በርሊን የጻፉትን የፍልስፍና ደርሳናት መርምሮ ጥናቱን አቅርቧል፡፡

በዚህ የትምህርት ሒደት እና በጥናትና ምርምሩ ያከማቸው ምሁራዊ ጥሪት፤ አኹን ለደረሰበት ከፍተኛ ኃላፊነት በእጅጉ ይረዳዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በመጨረሻም፤ ሽመልስን፣ ባለቤቱን፣ ወላጅ አባቱን፣ በተለይም የዛሬ 12 ዓመት ጊንጪ በወላጆቹ ቤት ግብዣ ተደርጎልኝ ከመቀመጫቸው ተነስተው “ልጄን ሰጥቼሀለሁ” ላሉኝ እናቱ፣ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ሽመልስም፤ በተሠየመበት የሥራ ገበታ ለሀገሩ ትልቅ አስተዋጽዖ ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንኳን ደስ አለህ፣ እንኳን ደስ አለን፡፡

ተፃፈ በዶክተር ዳኛቸው አሰፋ

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0