ቢሮክራሲ የሚለው ጽንሰ ሀሣብ በማህበራዊ ሳይንስ ውስጥ ተሿሚ ያልሆኑ የመንግስት ባለሙያዎችን አሰራር የሚመለከት ጉዳይ ነው:: ነገር ግን ቢሮክራሲው የተጓተተ፣ በአድሎአዊነት የተጠመደ፣ ተገቢውን አገልግሎት በሀገራችን መስጠት ስላልቻለ “ቢሮክራሲ” የሚለው ቃል የተዝረከረከ የመንግስት አሰራርን እንዲወክል ሆኗል:: ቃሉ ስድብ መስሏል::

አቶ በላይነህ አላምረው በዳቦ ፋብሪካ ሙያ ላይ ተሰማርተዋል:: አቶ በላይነህ የድርጅታቸውን ጉዳይ ለማስፈፀም የባህር ዳር አስተዳደር ከንቲባን ለማግኘት ሁለት ወር ተመላልሰዋል:: ከንቲባው አንዳንዴ ቢሮ የሉም:: ሲኖሩም ከፀሐፊዎች አልፎ ከንቲባውን ማናገር ቤተመንግስት የመግባት ያህል ከባድ ነው ይላሉ:: ኃላፊዎች በፀሐፊዎቻቸው እየተደበቁ ደንበኛ ለማግኘት ፈቃደኞች አይደሉም ሲሉም ያክላሉ::

ሌሎች ስማቸው እንዳይገለጽ የሚሹ ወገኖችም በመንግስት ተቋማት ያለ ሙስና መገልገል ቀርቷል ሲሉ ያማርራሉ:: መታወቂያ ለማግኘት እንኳ ወይ ገንዘብ መክፈል በነፃ ከሆነ ግን ከወር በላይ መመላለስ ግድ ነው ይላሉ::

የጤና ተቋማት ሳይቀሩ ህሙማን ለማስተናገድ ቀጠሮ የሚያስይዙ፣ ባለሙያው የለም የሚያስብሉ፣ አጣዳፊ ህመምን በቀጠሮ የሚሸኙባቸው ሆነዋል የሚሉም አሉ::

አስተያየታቸውን ለበኩር የሰጡ የመንግስት ሠራተኞች በበኩላቸው የመንግስት አሰራር ለሀቀኛ ሠራተኞች ቦታ የለውም ሲሉ ይወቅሳሉ:: አቶ አሸናፊ አበራ የተባሉ የስራ አመራር አማካሪ በኢትዮጵያ የመንግስት ተቋማትን አሰራር በተመለከተ የተሰራ ጥናትን ጠቅሰው ለሸገር ራዲዮ እንዳሉት ከሠራተኞች መካከል 70 ከመቶው ኃላፊዎቻቸውን አያምኑም:: 30 ከመቶው ብቻ ኃላፊዎቻቸውን እና የሚሰጧቸውን ስራ አምነው ይሠራሉ::

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

አቶ አሸናፊ እንዳሉት ባለሙያ እና ኃላፊ፣ መሪ እና ተማሪ መተማመን ካልቻሉ ስራውን ሊሰሩት አይችሉም:: የተቋማት መሪዎች የሚፈልጉትን የማይናገሩ፣ የሚናገሩትንም የማይተገብሩ፣ ከሙያው መንፈስ የራቁ መሆናቸው በሠራተኞች ዘንድ እንዳይታመኑ አድርጓቸዋል::

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ እጩ ዶክተር የሆኑት አቶ ቹቹ አለባቸው በበኩላቸው መንግስት እና የፖለቲካ ፓርቲ አንድ እና ያው መሆናቸው ሙያዊ አሰራሩን ቀብሮታል ይሏሉ::

የመንግስት መዋቅሩ በፖለቲካ ተጽዕኖ ስር የወደቀ ስለሆነ ፣ ፖለቲካው በተበላሸ ቁጥር የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥም አብሮ ይደክማል ሲሉም ይገልፃሉ::

ከገዥው ፖለቲካ ድርጅት ሀሳብ ጋር የማይሰማሙ ባለሙያዎች በመንግስት ተቋማት ላይ ተቀጥሮ ለመስራት ይከብዳቸዋል:: ቢሠሩም በማስመሰል የተሞላ ስለሆነ ውጤታማ አይሆኑም ይላሉ::

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስራ አመራር ሳይንስ እጩ ዶክተር የሆኑት አቶ ሙሉቀን ገላው በመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚኖሩ የስራ መፋዘዞችን በሶስት ፈርጅ ይመለከቷቸዋል:: የተቋማት የስራ ባህል ዝቅተኛ መሆን የተቋማትን መፋዘዝ መንስኤ አድርገው ይወስዳሉ:: አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በዘመድ አዝማድ ሰንሰለት የተሳሰሩ መሆኑ፣ በችሎታ ላይ ያልተመሰረተ ሹመት፣ ግልጽ የሆነ የአገልግሎት አሰጣጥ መርህ አለመኖርና ለሠራተኞች ሙያ ስልጠና አለመኖር ከተቋሙ ላይ መጥፎ ድባብ ይፈጥራል:: ይህ መሆኑ የአገልግሎት አሰጣጡን ደካማ እና ልፍስፍስ ያደርገዋል ይላሉ::

በሌላ በኩል ደግሞ ይላሉ አቶ ሙሉቀን ማህበራዊ ጉዳዮችንም እንደ አንድ መንስኤ ይጠቁማሉ:: ለሱስ ተገዥነት መኖሩ ሠራተኛው በተለይ ከሰዓት ወደ ቢሮው እንዳይገባ ያደርጋል:: በአሁኑ ወቅት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከ40 በመቶ በላይ ወጣቶች ለሱስ ተገዥ ሆነዋል:: ጫትን የመሳሰሉት ሱሶች ደግሞ ብዙ መቀመጥን ስለሚሹ ሰራተኛው በቢሮ ተገኝቶ አገልግሎት እንዳይሰጥ ሊያደርጉት ይችላሉ:: በሱስ የተገዛ ባለሙያ ሱስን ችሎ አገልግሎት ቢሰጥ እንኳ፣ መጨቃጨቅ እና ድብርት ስለሚያበዛ ፈጣን አገልግሎት ላይሰጥ ይችላል:: በተለየ ሁኔታም የገንዘብ ጥቅማጥቅምን ከተገልጋዩ ሊጠይቅ ይችላል:: ነፃ አገልግሎትን በገንዘብ መግዛት ደግሞ ለተጨማሪ ቀውስ ይዳርጋል::

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

የመንግስት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ መፋዘዝ ሌላው መንስኤ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሊነሱ ይችላሉ:: የደመወዝ ማነስ፣ ጥቅማጥቅም አለመኖር፣ የመንግስት ሠራተኛው የገበያውን ንረት በደመወዙ መቋቋም አለመቻሉ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ማነቆ ሊሆንበት ይችላል:: ለድብርትም ሊዳርገውም ይችላል::

በዚህ ትይዩ ደግሞ የመንግሰት ተቋማት የገዥው የፖለቱካ ማስፈፀሚያ መሆናቸው ሌላው እንቅፋት ሆኗል:: ለመሸለም፣ ባለሙያን ለማበረታታት ከስራ ይልቅ መስፈርቱ ለፖለቲካ ማደር መሆኑ በተቋማት ዘንድ አስመሳይነት፣ የተጠያቂነት መንፈስ መላላት፣ የተሰፋ ቢስነት ድባቦች ሊንፀባረቁ ይችላሉ:: የፖለቲካ ፓርቲው በደከመ ቁጠር ተቋማትም አብረው ስለሚደክሙ ፖለቲካ እና የመንግስት ስራ አለመለያየቱ አደጋ ሆኗል ይላሉ አቶ ሙሉቀን::

በማይጠቅም አጀንዳ ላይ ስብሰባ ማብዛት፣ ሞራል ነኪ ግምገማዎች፣ በተቋማት አገልግሎት ላይ አወንታዊ ድባብ አለመኖሩ፣… ለሠራተኛውም ለተገልጋዩም ፈተና ሆኗል የሚሉት ደግሞ አቶ ቹቹ ናቸው::

የግምገማ መብዛት ተቋማትን የንትርክ ማዕከል ስላደረገ ሠራተኞች ከእሁድ ምሽት ጀምረው በድብርት ይወድቃሉ:: ሰኞም የቀናት ሁሉ ጥቁር ቀን ተብላ እንድትጠራ የመንግስት ሠራተኛው ሞራል ይፈቅዳል ይላሉ አስተያየት ሠጭዎቹ:: የመንግስት ሰራተኛው በሚሰራው ስራ አለመርካቱ የስራ ቀናት የመርገምት ቀናት ሆነው እንዲሳሉ አድርጓል::

Related stories   Ethiopia’s transition misrepresented. Reply to Obang Metho

መውጫ መንገድ

ተቋማትን ከፖለቲካ ተጽእኖ ነፃ ማድረግ እና ሙያን ለባለሙያ መስጠት አስፈላጊ ነው ይላሉ አቶ ሙሉቀን:: ከዚህ ባሻገርም ሠራተኛውን የሚመጥን ሙያ ያለው መሪ መሾም ተገቢ ነውም ይላሉ::

ሠራተኛውን መሸለም፣ የቢሮክራሲ አሰራርን ማዘመን፣ የተጠያቂነት አሰራር መዝርጋት፣ ግልጽ መርህ ማስቀመጥ፣ ስብሰባን በውጤታማነት መጠቀም፣ የፖለቲካ ህመሙ ወደ መንግስት ተቋማት በቀላሉ እንዳይሻገር ፖለቲካን ከመንግስት ተቋማት አሰራር መነጠል መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው የሚሉት ደግሞ አቶ ቹቹ አለባቸው ናቸው:: በዘመድ አዝማድ፣ በወንዝ ልጅነት የሚፈጸመውን መጠቃቀም በማስቀረት አሰራርን በችሎታ እና በግልጽ መርህ መሠረት ላይ በማድርግ መበጠስ የመንግስት ተቋማትን መፋዘዝ ሊቀንስ እንደሚችልም ተወስቷል::

በመንግስት በኩል በ2010 ዓ.ም 1064/2010 አዲስ የወጣውን የመንግስት ሠራተኞች የተሻሻለ አዋጅ ነባራዊ ሁኔታ በፈቀደው ልክ መጠቀምም በተገቢነት ይቀመጣል::

ይህ አዋጅ የመንግስት ሰራተኛው የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጥ የወጣ ቢሆንም ወደ አሰራር ግን ገና አልተዘረጋም::

በኩር (የሺሀሣብ አበራ) ሚያዚያ 14 ቀን 2011 ዓ.ም ዕትም

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 14/2011ዓ.ም (አብመድ)

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *