የህዝቡን አንድነት በማጠናከር በልማት የበለፀገች ኦሮሚያን ለመገንባት ያለ እረፍት ሌት ተቀን እንደሚሰራ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ገለፀ። የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የክልሉን መንግስት አቋም የሚያንፀባርቅ መግለጫ አውጥቷል።
ቢሮው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ የኦሮሚያ ክልል መንግስት በሁሉም አቅጣጫ በሚሰሩ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ከህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን በቅደም ተከተል ለመመለስ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን እና ውጤቶችንም እያስመዘገበ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በሚሰሩ ስራዎች ውስጥም ህዝቡ የሚሰጠው ድጋፍ፣ አስተያየትና ሞራል እንዲሁም ጥፋቶች ሲኖሩ እንዲስተካከሉ አቅጣጫ በመጠቆም በማንኛውም ችግር ወቅት ከጎኑ በመሆኑ የክልሉ መንግስት ለህዝቡ ከፍተኛ ክብር እንዳለው ገልጿል።
 
የክልሉ መንግስት ከዚህ በመነሳት በቀጣይ የትግል ምእራፍ በሚሰሩ ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን በማስቀደም በትኩረት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።
 
አሁን መታየት የጀመረውን የነፃነት ብርሃን ማምጣት የተቻለው ከሁሉም በላይ የክልሉ ህዝብ አንድ በመሆኑ ነው ያለው የክልሉ መንግስት፥ የተገኘውን ድል በመጠበቅ የህዝቡን ነገ ለማሳር ሁልጊዜም በከፍተኛ ተነሳሽነት እንደሚሰራ አስታውቋል።
 
ለአፋን ኦሮ እድገት እንዲሁም በኦሮሞ ህዝብ ባህል፣ እሴትና ማንነት ላይ በሁሉም መስክ እንደሚሰራም ነው የክልሉ መንግስት በመግለጫው ያስታወቀው።
 
የኦሮሚያ ክልልን ለማልማት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍና የአገልግሎት አሰጣጦች ማሻሻል የሚቻለው ሰላምና የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ነው ያለ ሲሆን፥ ለዚህም ለኦሮሚያ እና ለኦሮሞ ህዝብ ዋስትና የሚሆን ጠንካራ የፀጥታ ሀይል እንደሚያደራጅና ድጋፍ እንደሚያደርግለትም አትቷል።
 
ጠንካራ ኦሮሚያን መገንባት ከተቻለ ኢትዮጵያ ትጠነክራለች ያለው የክልሉ መንግስት፥ ስለዚህ ሁሉም የክልሉ ህብረተሰብ ማለትም አርሶ እና አርብቶ አደሩ፣ ተማሪው፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ምሁራን እንዲሁም የክልሉ ወጣቶች ስራቸውን በሚሰሩበት ወቅት ኦሮሚያን መገንባትን በልባቸው አድርገው በእልህ መስራት አለባቸው ብሏል።
 
የክልሉን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርጉ እድሎችን መለየት፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ቴክኖሎጂን መጠቀም፣ የማዳበሪያ አቅርቦትና የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ማዳበር እንዲሁም የልማት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም እንዲፋጠን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አስታውቋል።
 
አሁን ያለንበት የትግል ምእራፍ የመጣው ወጣቶች በከፈሉት መሰዋእትነት ነው ያለው የክልሉ መንግስት፥ ስለዚህ መንግስት በሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች ውስጥ ወጣቶቸን ማሳተፍና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑና በክልሉ በሚካሄዱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ለወጣቱ የስራ እድል መፍጠር በሚቻልበት መልኩ እንደሚከናወን አንስቷል።
 
የክልሉን የኢኮኖሚ ልማት ለማፋጠንም በክልሉ የተጀመረውን የኢኮኖሚ አብዮት የበለጠ በማስፋፋት ህዝቡ ያለውን ገንዘብ፣ የተፈጥሮ ሀብትና እውቀት አቀናጅቶ በመደራጀት በጋራ ሰርቶ ከድህነት አንዲወጣ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቋል።
 
የክልሉ ወጣቶች ስራ ለማግኘት የሚያቀርቡት ጥያቄ መፍትሄ እንዲያገኝም በቅርቡ ትልቅ በጀት ተመድቦ ወደ ስራ እንደሚገባም የክልሉ መንግስት ገልጿል።
 
ከተለያዩ አካባቢዎች በጠላት በሸረበው ሴራ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ስራም የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶት የሚሰራ መሆኑንም ገልጿል።
 
“በእጃችን ያለው ኃላፊነት የኦሮሚያና የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነው” ያለው የክልሉ መንግስት፥ በጋራ ለመልማት እና ለማደግ ህዝቡ የሰጠውን አደራ ከዳር ለማድረስ እሰራለሁ ብሏል።
 
ህዝቡ የሚሰጠው ድጋፍ ሞራል እንደሚሆነው እና ከህዝቡ የሚቀርቡ አስተያየትና ትችቶች ደግሞ ሀይል እንደሚሆነው የገለፀው የክልሉ መንግስት፤ ህዝቡ ዛሬም እንደ ትናንቱ ጥሩ ስራ ሲሰራ እያበረታታ፤ ችግር ሲፈጠር ደግሞ እያረመ ከጎኑ እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል።
 
በሙለታ መንገሻ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   Ethiopia’s transition misrepresented. Reply to Obang Metho

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *