በያዝነው ወር መጀመሪያ አካባቢ በሰሜን ሸዋ ዞን በኤፍራታና ግድም ወረዳ በአጣዬ ከተማ አስተዳደር እና አካባቢው ለተከታታይ ሦስት ቀናት በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ ሀብትና ንብረት ወድሟል፤ ነዋሪዎቹም ለስጋትና ለከፋ የሥነ-ልቦና ችግር ተጋልጠዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን በከተማዋ እና አካባቢው በተፈጠረው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ዙሪያ ትናንት ከነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ከርዕሰ መስተዳድሩ ጋር ውይይት ያደረጉት የከተማዋ ነዋሪዎች በተፈጠረው የፀጥታ ችግር አሳሳቢነት፣ ስጋቶችና ዘላቂ መፍትሔዎች ላይ ጥያቄዎችን አንስተዋል፤ አስተያየቶችንም ሰንዝረዋል፡፡ ‹‹ድርጊቱ ለዘማናት አብሮ የኖረውን የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ግንኙነት ለማጠልሸት ታስቦና ታቅዶ የተፈፀመ እኩይ ተግባር ነው›› ያሉት ነዋሪዎቹ የመንግሥትን ለዘብተኛ አቋም፣ የቅድመ መከላከል አቅም ውስንነትና የደኅንነት መዋቅሩን መላላት ተችተዋል፡፡ ‹‹መከላከያ እንደ ተቋም ለሀገር የሚከፍለውን መስዋትነት ባንክድም በውስጡ ግን የተለየ ዓላማ ያላቸውን ኃይሎች ፍላጎት የሚያራምዱ አባላትና አመራሮች አሉት›› ነው ያሉት ነዋሪዎቹ፡፡ ችግሩ እንደተፈጠረ በአካባቢው የመከላከያ ሠራዊት ቢደርስም ‹‹ትዕዛዝ አልደረሰኝም›› በሚል ሰበብ የሰው ሕይወት እየጠፋ፣ ንብረት እየወደመ እና የሕግ የበላይነት እየተጣሰ እያዬ በቸልተኝነት ማለፉ እንዳሳዘናቸው ነዋሪዎቹ በአስተያየታቸው አንስተዋል፡፡

Related stories   ህወሃትና ኦነግ ሸኔ በሽብርተኛ ድርጅትነት እንዲሰየሙ የውሳኔ ሐሳብ ቀረበ

በግጭቱ ሀብትና ንብረታቸውን ያጡ ተጎጅዎችን መልሶ በማቋቋም፣ የደረሰውን የሥነ-ልቦና ስብራት መልሶ በመጠገን፣ ችግሩን በዘላቂነት በመፍታት፣ የአጥፊዎችን ማንነት አጣርቶ ለሕዝብ በመግለፅና ለሕግ በማቅረብ፣ በአካባቢው ዘላቂና አስተማማኝ የፀጥታ ኃይል በመገንባት እና የሕዝብን ደኅንነት በማስጠበቅ በኩል መንግሥት ያለውን አቋም ግልፅ እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል፡፡

ከነዋሪዎቹ ለተነሱት ጥያቄዎች የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን እና የሰሜን ሽዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድማገኝ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹የተፈጠረውን ግጭት በብልጣብልጥ ፖለቲከኞች የሃይማኖት እና የብሔር መልክ ለማስያዝ የተደረገው ሙከራ አስተዋይ በሆነው ሕዝባችን ከሽፏል›› ያሉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የተፈናቀሉትን ለማቋቋም፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ወደ ነበሩበት ሕይወት ለመመለስ፣ አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ እና የአካባቢውን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የችግሩ ባለቤት ከየትኛውም ወገን ይሁን ተጣርቶ ለህግ ይቀርባል›› ያሉት አቶ ተፈራ አመራሩ የችግሩ ባለቤት ሆኖ ከተገኘ ለሕግ የማይቀርብበት ምክንያት አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡

Related stories   ሱዳን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ የሉዓላዊነት ጥያቄ እንደምታነሳ አስጠነቀቀች፤ "ብሄራዊ የጀግንነት ጥሪ ያፈልጋል"

መከላከያ እንደ ተቋም ሀገራዊ እና ብሄራዊ ኃይል መሆኑን ያወሱት ዋና አስተዳዳሪው በተቋሙ ውስጥ ችግር ያላባቸውን አካላት ለይቶ ለሕግ ለማቅረብ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ ተቋምን ከግለሰብ ለይቶ ማየት እና ነገሮችን በብስለት መመልከት በተለይም በዚህ ወቅት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በአካባቢው የደረሰው ጉዳት እና የተፈጠረው የሥነ-ልቦና ስብራት ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

‹‹መንግሥት እንደ መንግሥት እኛም እንደ አመራር ሙሾ አውራጅ ሆኖ ሕዝብን ማስለቀስ ከችግራችን አያሻግረንም›› ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት መፍታት እንዲችል ሕዝቡ ስሜቱን ተቆጣጥሮ በአስተዋይነትና በብልጠት የመንግሥትን አቅጣጫዎችን ብቻ እንዲያስፈፅም ጠይቀዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚሠሩም ርዕሰ መስተዳድሩ ለነዋሪዎቹ አረጋግጠውላቸዋል፡፡ ‹‹ከተሳካልን ከዚህ በኋላ በክልሉ ግጭት እንዳይፈጠር እና የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ እንሠራለን›› ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው ባለፉት ጊዜያት የዘር ልዩነት ከልክ በላይ በመሰበኩና በሰፊው በመሠራቱ በዚህ ወቅት መንግሥታቸው በሁሉም አቅጣጫ ውጥረት እንደበዛበት ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ወሬ ከቦታውና ከድርጊቱ ሲርቅ የቅርፅና ለዛ ለውጥ ያመጣል›› ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ሕዝቡ በየቦታው ከሚነዙ አሉባልታዎች ራሱን አርቆ መንግሥት በሚዲያ ተቋማት ብቻ የሚያወጣቸውን መግለጫዎችና መረጃዎች በንቃት በመከታተል የሰላሙ አጋዥ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Related stories   አፍሪካ ህብረት ቁርጠኛነቱን አሳይቷል፤ አውሮፓ ህብረት ምርጫ አልታዘብም አለ

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 16/2011ዓ.ም (አብመድ)

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከአጣዬ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *